በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች አለመጠናቀቃቸው ነዋሪዎችን ክፉኛ አማረረ፡፡ ቤቶቹ ግንባታቸው እና ሌሎች ጣጣዎቻቸው ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል ተብሎ በሚመለከተው አካል ተገልጾ ዕጣ ወጥቶባቸው ነበር፡፡ ዕጣው ከወጣ ረዘም ያለ ጊዜ ቢቆጠርም፣ ቤቶቹ ዕጣው ለወጣላቸው ነዋሪዎች ሊተላለፉ ግን አልቻሉም፡፡ ይህም የሆነው፣ ቤቶቹ ሙሉ በሙሉ ባለመጠናቀቃቸው መሆኑ ታውቋል፡፡ መኖሪያ ቤቶቹ ወደፊትም መቼ ለነዋሪዎች እንደሚተላለፉ የታወቀ ነገር የለም፡፡
ስለ ጉዳዩ አስተያየታቸውን የሰጡ ወገኖች፣ ድርጊቱን ‹‹መንግስታዊ ውንብድና›› ሲሉ ገልጸውታል፡፡ መንግስት አልያም የአዲስ አበባ አስተዳደር ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ፣ ቤቶቹ ገና ሙሉ በሙሉ ሳይጠናቀቁ ከነዋሪዎች ገንዘብ መቀበሉ መንግስታዊ ውንብድና መሆኑን እነዚሁ ወገኖች ይገልጻሉ፡፡ ድርጊቱ ገንዘብ ከፍሎ ቤት የሚጠባበቀውን ነዋሪ ያሳዘነ እና ያስቆጨ እንደሆኑም ከአስተያየት ሰጪዎቹ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ግንባታቸው ተጠናቋል ተብሎ በተለያዩ ሳይቶች ዕጣ የወጣባቸው የኮንዶሚኒዬም ቤቶች፣ ቀለም ያልተቀቡ፣ መብራት እና ውሃ የሌላቸው እንዲሁም ወደ መንደሩ የሚያስገባ በቂ የአስፓልት መንገድ ያልተሰራባቸው ቢሆኑም፣ መንግስት ግን ቤቶቹ ተጠናቀዋል ብሎ ገንዘብ በመቀበል ዕጣ አውጥቶባቸዋል፡፡ በተለይ በ2009 የመጨረሻ ወራት ላይ ዕጣ የወጣባቸው እና ክራውን ሳይት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ ብዙዎችን እያማረሩ ይገኛሉ፡፡ ቤቶቹ የውሃም ሆነ የመብራት አገልግሎት ያልተገጠመላቸው ሆነው ተገኝተዋል፡፡
እንደዚሁም በሌሎች የአዲስ አበባ ክፍሎች የሚገኙ እና ተጠናቅቀዋል ተብሎ በመንግስት ልሳናት ፕሮፓጋንዳ የተረጨባቸው የኮንዶሚኒዬም ቤቶች፣ ገንዘብ ከፍለው በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎችን ክፉኛ አበሳጭተዋል፡፡ ነዋሪዎቹ ወይ ከገንዘባችን ወይ ከቤታችን አልሆንንም ሲሉም እየደረሰባቸው ያለውን የገንዘብ እና የሞራል ኪሳራ ተናግረዋል፡፡ ቤቶቹ ከዚህ በኋላም መቼ ተጠናቅቀው ለነዋሪዎች እንደሚተላለፉ የታወቀ ነገር የለም፡፡ (BBN)