ማረሻ ሲያምጥ፤አገር ይናወጥ፤መንግሥት ይለወጥ!

ከገ/ክርስቶስ ዓባይ                                            ኅዳር 11 ቀን 2010 ዓ/ም

እዚህ ላይ ማረሻ የሚለው ኃይለ ቃል በፈሊጣዊ አነጋገር የገባ አርሶ አደሩን የሚገልጽ ነው። እውነት ነው፤ አርሶ አደሩ የአንድ አገር የጀርባ አጥንት መሆኑ ሳይታለም የተፈታ እንደሆነ ለማንም የተሰወረ አይደለም። ምክንያቱም በጋውን በፀሐይና በአቧራ፤ ክረምቱን በዝናብ እና በጭቃ እየማሰነ መሬቱን አርሦና አለስልሶ፤ እምነቱን በፈጣሪው አንተርሶ፤የሚፈልገውን የእህል ዓይነት ወቅቱን እየጠበቀ በተስፋ ይዘራል። ሥራው ተጀመረ እንጂ መች በዚህ ብቻ ያበቃል? እህሉ ገና መብቀል ሲጀምር አረም የሚባል ምቀኛ ቱግግ ብሎ ይወጣና የቡቃያውን ምግብና ውሀ መሻማት ይጀምራል። አርሦ አደሩም ይህንን መሰል ፈተና ብቻውን መወጣት አይችልም። ብቻውን ልሥራው ቢልም ጊዜ ስለሚወስድ ሰብሉ ከመቀጨጭ አልፎ ሊጠወልግና ብሎም ለደርቅ ይችላል።

ታዲያ የሚያዋጣው ከመሰል ባልደርቦች ጋር በመቀናጀትና ደቦ በመግባት በአጭር ጊዜ ውስጥ አረሙን ማስወገድ ይጠበቅበታል። ቀጥሎም አዝመራው ፍሬ መጥለፍ ሲጀምር ወይም ማሸት ሲጀምር ደግሞ ከአዕዋፍና ከአዕላፍ እንዲሁም እንደ አካባቢው ሁኔታ ከዝንጀሮና ከአሳማ፤ ወይም ደግሞ ከጉማሬ ጋር ትንቅንቅ መፍጠር ያስፈልጋዋል። ይህም ሥራ በጣም አድካሚና አሰልቺ ከመሆኑም በላይ ዕንቅልፍ እስከ ማጣት ያደርሰዋል። አዝመራው ሲበስልና ሲደርስ ደግሞ አጨዳውና ውቂያው ተራ በተራ መከናዎን አለባቸው። በዚህም አያበቃም ከተወቃ በኋላ ደግሞ እህሉን ከገለባው ለመለየት ትዕግሥት አስጨራሽ የሆነውን ‘አግማስ’ መጠበቅ የግድ ይላል። አግማስ ማለት ሚዛናዊ ነፋስ ማለት ነው። ነፋሱ ኃይለኛ ከሆነ እህሉን ከገለባው ጋር በአንድ ላይ ይወስደዋል። ነፋሱ ደካማ ከሆነ ደግሞ ገለባውን ከፍሬው መለየት አይችልም። ከዚያም እንደገና በአቅማዳ ወይም በጆንያ በመክተት በአህያ እየጫነ ወደ ቤት መውሰድ ያስፈልገዋል። አህያ የአርሦ አደሩ ካሚዎን ነበረች። ስለሆነም እሷኑ ለማጥፋት ደግሞ ማረጃ ቄራ ተደራጅቶ በተዘዋዋሪ መንገድ የአርሦ አደሩ አቅም እንዲዳከም እየተደረገ ይገኛል። ያም ሆነ ይህ የግብርና ተግባር የሥራ ሂደት ድፍን ዓመቱን የሚወሰድ ነው።

እንግዲህ አርሦ አደሩ በዚህ ሁኔታ ጥሮና ግሮ ከሚያገኘው ምርት በስተቀር ሌላ ገቢ የለውም። በመሆኑም ለወር ጨው፤ለቡና እንዲሁም የዓመት ልብሱን ለመግዛት እንዲችል ካመረተው እየጫነ ወደ አቅራቢያው ገበያ በመውሰድ ይሸጣል። የሚሸጥበት ገንዘብ ግን እንደልፋቱ መጠን ተመዝኖ ሳይሆን ያለምንም ልፋትና ድካም ከመሬት አንዳፈሰው ተደርጎ በርካሽ ይተመንበታል። አማራጭም ስለሌለው ባወጣው ዋጋ ይሸጥና የሚፈልገውን ዕቃ ደግሞ ተመጣጣኝ ባልሆነ በውድ ዋጋ እንዲሸምት ይገደዳል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መሳሪያ የታጠቀ ማንኛውም አካል እንዲያስመዘግቡ ተጠየቀ

ይህ ሁኔታ ለረጅም ዓመታት ሲወርድ ሲዋረድ የቆየ በመሆኑ አርሶ አደሩ በኋላ ቀር የግብርና ዘዴ፤ ከአፈር ገፊነት ነፃ ወጥቶ አሠራሩን የሚያቃልልበት የዘመናዊ የእርሻ ዘዴ ተጠቃሚ ሊሆን አልቻለም። እንዲያውም የብዝበዛውና የዘረፋው ዘዴ በየጊዜው እየተወሳሰበና እየረቀቀ በመምጣቱ የግፉ ክብደት ጫንቃውን አጉብጦታል። አገር ተጠቃች ሲባል ሞፈር ቀንበሩን ሰቅሎ የሚዘምተው አርሦ አደሩ ነው። ዘመቻ መጣ ልጅህን አዋጣ የሚባለው አርሦ አደሩ ነው። ማዳበሪያ ካልገዛህ እየተባለ መቋሚያ መቀመጫ የሚያጣው አርሦ አደሩ ነው። በመኸር ጊዜ ደግሞ በማንጨነቅ ‘የማዳበሪያ ዋጋ ካልከፈልክ ሡሪ ባንገት’ የሚባለውም አርሦ አደሩ ነው።

ይህን ሁሉ መከራና ግፍ ተሸክሞ እሱ ሳይማር ያስተማራቸው፤ ችግሩን ተመልክተው መፍታት ሲገባቸው የበላይ ሆነው የግፍ ቀንበሩን አክብደውበታል። ከአብራኩ የተገኙትን ልጆቹን አእምሯቸውን በሐሰት ፕሮፓጋንዳ በመስለብና በሥልጣንና በመሃያ በማማለል እንዲያንገላቱት፤ እንዲያስሩትና ያለምንም ፍርድ በጭካኔ እንዲገድሉት ሲደርግ ኖሯል፤አሁንም ቢሆን ፋታ አላገኘም። በተለይ በወያኔው ከፋፋይና ዘራፊ መንግሥት ወቅት አርሶ አደሩ ከምንጊዜውም በላይ በችግር አረንቋ ውስጥ እየዳከረ ይገኛል። ሲታመም ፈውስ የሚያገኝበት ሕክምና የለም፤ ከተገኘም የመድኃኒቱ ዋጋ አይቀመስም። እንዲያውም ለውጭ አገር ምርምር፤ እንደ አይጥ መፈተኛ በመሆን ዘሩን እንዳይተካና ወልዶ እንዳይስም በረቀቀ ዘዴ በክትባት መልክ አምክነውታል።

ስለዚህ አርሶ አደሩ ይህንን በመገንዘብ፤ ሕይወቱ የተንጠለጠለችበት ቀጭን ክር እንዳትበጠስ በንቃትና በጥበብ መንቀሳቀስ ያስፈልገዋል። ለዚህም ያለው ዋነኛ መሣሪያ አንድና አንድ ብቻ ነው።

ይኸውም እነዚህ ጨካኝ ሰዎች በሕይወቱ ላይ እንደቆሙበት እሱም በኅብረት በመሆን ተማምሉ ጉሮሯቸው ላይ መቆም አለበት። እሱን የሚያንገላቱበት ከንዳቸው የሚፈረጥመው ሲበሉ፤ጥጋብ የሚሰማቸው ሲደላቸው ነውና የዚህን ምንጭ መዝጋትና ማቋረጥ ይገባዋል። ለዚህም አቋሙ በሸንጋይ ስብከት ወይም ደግሞ በገንዘብ እንዳይደለል መጠንቀቅ ይኖርበታል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በአማሮች ላይ የሚደረገውን መፈናቀልና መደብደብ በመቃወም በዲሲ ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ ተደረገ

የአርሦ አደሩ ጠላቶች እሱን ለመዝረፍና ለመበዝበዝ፤ እንዲሁም ረግጦ ለመግዛት እራሳቸውን አደራጅተው ያሉ፤ ምድራዊ ሕግ የማይዳኛቸው፤ ፈሪሃ እግዚአብሔር የሌላችው፤ ስግብግብና አረመኔዎች ናቸው። ታዲያ አርሦ አደሩ ለእርሱ ዕድገትና መሻሻል የሚያስብ መንግሥት እንዲመጣና እንዲመሠረት ከፍተኛ የሆነ ሚና መጫወት ይችላል። ይኸውም በመኸር ወቅጥ ፍላጎቱን በመግታት የሚሸጠውን የእህል ምርት በመቀነስ መቆጠብ ይኖርበታል። ነገር ግን እነዚህ ወንበዴዎች በሁለት መንገድ በመዝመት አርሦ አደሩን ሊያስቸግሩ ይችላሉ። አንደኛው ከፍተኛ ዋጋ በማሳየት አርሶ አደሩን ሊያታልሊሉ ይሞክራሉ። ሁለተኛው ዘዴ ደግሞ ያለፈፉበትንና ያልደከሙበትን የእርሻ ሰብል ባላቸው መዋቅር ተጠቅመው በኮታ ደልድለው አስገቡ በማለት ማስገደዳቸው አይቀርም።

“ወዝውዝ የለሽ ንዝንዝ የለሽ

ወንበር ላይ ሆኖ ማዘዝ እንዴት ነሽ::” በማለት  እራሡን ከብዝበዛ ነፃ ለማውጣት ማመጥ (አምቢ ማለት) ያስፈልገዋል።

በዚህ ሁኔታ አርሦ አደሩ ተባብሮ በአንድ አቋም ከጸና፤ አገር ይናወጣል፡ሕዝብ ይበጠበጣል፤ የመንግሥትም ኃይል ቀስ በቀስ እየሟሸሸ ይመጣና ሳይወድ በግድ ይለወጣል።

ቀጥሎም በሚዋቀረው አዲሱ መንግሥት፡ ችግሩን የሚቀርፍለት፤ ብዝበዛውን የሚያቆምለት፤ ፍትህና መልካም አስተዳደር የሚያሰፍንለት መሆኑን አርሦ አደሩ በንቃት በመከታተል እውን እንዲሆን መሳተፍ ይኖርበታል።

ማረሻ ለአንድ መንግሥት መጽናት ዋነኛ መሣሪያ ሲሆን በአንፃሩም የማይፈለግን መንግሥት ለመለወጥ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳለው መረዳት ተገቢ ነው። አሁን የመኸር ወቅት በመሆኑ የወያኔ መንግሥት በወኪሎቹ አማካይነት የአርሦ አደሩን ምርት በየዓይነቱ በሠበር ገበያ በገፍ እየሸመተ በትላልቅ መጋዝን ውስጥ በመከዘን ሕዝቡን ይቆጣጠርበታል። ከዚያም በአገሪቱ በቂ እህል እያለ ሕዝቡ የሚሸምተው ያጣል። ምክንያቱም መንግሥት አስቀድሞ በመግዛት ጥርግርግ አድርጎ ወስዶ ቆልፎበታልና። ለሞት መድኃኒት ቢባል እንኳ የማግኘቱ ነገር ቀላል አይሆንም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሙስናው አስር ምስጢር! (ማረ በላዎቹ ርስ-በርስ ተበላሉ!)

ወያኔ ከአሁን ቀደም በዚህ ዘዴ ያጠራቀመው ቢያንስ የሁለት ዓመት ቀለብ ሳኖረው እንደማይቀር ይገመታል። በተለይ ጤፍ ሳይበላሽ ለረጅም ጊዜ መቆየት የሚችል የእህል ዘር በመሆኑ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ሠፊ ክምችት እንዳለው ይታወቃል። አርሦ አደሩ ለጊዚያዊ ጥቅም ሲል ረብ በሌለው ገንዘብ ያመረተውን እህል አሟጦ ከሸጠ በኋላ የጭቆናና የግፍ ቀንበሩን ከማክበድና ከማጥበቅ ይልቅ፤ ቆም ብሎ በሰከነ ሁኔታ ሊያስብና ሊወያይበት ያስፈልገዋል።

ከአሁን ቀደም ለሃያ ስድስት ዓመታት የተታለለው ይበቃዋል። ለውጥ ዝም ብሎ አይመጣም፤ ትንሽ መስዋዕትነት ግን ለመክፈል ቆራትነት ያስፈልጋል። በኮታ አስገቡ የሚሉትን የይስሙላ ባለሥልጣኖች ጆሮ በመንፈግ አሻፈርኝ ማለት ወቅቱ የሚጠይቀው ዋነኛ ተግባር መሆኑን በመገንዘብ ከአሁኑ ሰዓት ጀምሮ መዘጋጀት ተገቢ ነው።

ዓመት የለፋበትን ምርቱን ለግፈኞች ገዢዎቹ በእንዝህላላነት አስረክቦ በኋላ ከማልቀስ፤ በቁርጥኝነት በመቆም ሥርዓቱን ማርበድበድና ማንቀጥቀጥ አለበት። ይህ ሲባል ግን ጠቅላላውን ምርቱን ታቅፎ ይቀመጥ ማለት አለመሆኑን ማስተዋል ብልህነት ነው። ነገር ግን እህሉን በሚሸጥበት ወቅት በገበያ ዋጋ በቀጥታ ለበላተኛው (ለከተሜው) መሸጥ እንዳለበት ለመጠቆም ጭምር ነው። ምክንያቱም ከተሜው የሚልሰው የሚቀምሰው በማጣት አንጀቱን ጥፍር አድርጎ ከእነልጆቹ በረሃብ እየተገረፈ በመሥቃየት ላይ ስለሆነ የመደብ አጋሩ ለሆነው ከተሜ መሸጡ የሚፈለገው የሥርዓት ለውጥ እንዲፋጠን ያደርጋል።

ስለዚህ ማረሻ እንደ ኒኩሊየር ቦምብ ያለ ኃይል ያለው፤ አንድን መንግሥት ማንቀጥቀጥና ማራድ እንዲሁም ማንኮታኮት የሚችል መሆኑን አውቆ ይህንን አቅሙን በተቀናጀ መልኩ በመተባባር ሊጠቀምበት ይገባል። ጠላትን እየመገቡና እንዲፋፋ እያደረጉ መቀለብ ከየዋህነትም አልፎ ጅልነት ነው። ለዚህ ጉዳይ ተግባራዊነት የግድ አመራር አስፈላጊ አይሆንም። ንቃተ ኅሊና ያለው ማንኛውም ገበሬ ሲያደርገው ቆይቷል፤ አሁንም ለማድረግ ዝግጁ ነው። ግን የተናጥል እንቅስቃሴ የትም አያደርስም። በተባበረ መልኩ ሲከወን ግን ውጤቱ ግቡን ይመታልና፤ አርሦ አደሩ “ከእንግዲህስ ነቅተናል” ማለት መቻል አለበት።

ማረሻ ታላቅ ኃይል ነው! ማረሻ ሲያምጥ፤አገር ይናወጥ፡መንግሥት ይለወጥ ነውና!

Share