አዲስ አበባ የውሃ ጥሟ ሊቆርጥላት አልቻለም | ሕዝብ በመብራትም እጦት እየተሰቃየ ነው

በአዲስ አበባ የውሃ እና መብራት ችግር ከቀን ወደ ቀን እየባሰበት እንደመጣ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ አስተያየታቸውን ለቢበኤን የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደገለጹት ከሆነ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመዲናዋ ያለው የመብራት እና ውሃ ችግር መድረሻ እንዳሳጣቸው በምሬት ተናግረዋል፡፡ በተለይ የውሃው ነገር አይነሳ የሚሉት እነዚሁ ነዋሪዎች፣ በፊት በፊት ውሃ ቀን ቀን ቢጠፋ እንኳን አልፎ አልፎ ለሊት ላይ ይመጣ እንደነበርና፣ አሁን ላይ ግን ቀንም ለሊትም ውሃ ማግኘት አዳጋች መሆኑን ነዋሪዎቹ ይገልጻሉ፡፡

አውቶቢስ ተራ፣ ሰባተኛ፣ መርካቶ፣ አለምገና፣ ካራቆሬ፣ ኮተቤ፣ አየር ጤና፣ ቀራንዮ፣ ጦር ኃይሎች፣ ተክለኃይማኖት፣ አሜሪካ ግቢ፣ አዲሱ ገበያ፣ አፍንጮ በር፣ መነን እና በሌሎች ቦታዎች ከፍተኛ የውሃ ችግር መኖሩን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ አሁን አሁን ይላሉ የችግሩ ሰለባ ነዋሪዎች፣ አሁን አሁን ውሃ ሲመጣ እንጂ ሲሄድ መገረም አቁመናል ብለዋል፡፡ በመተሳሳይ ሁኔታም በከተማዋ ከፍተኛ የመብራት ችግር መኖሩንም ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡ መብራት ቶሎ ተሎ ከመሔዱ የተነሳ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን እያቃጠለባቸው እንደሆነ የሚናገሩት የከተማዋ ነዋሪዎች፣ የሁለቱ መሰረታዊ ነገሮች ችግር ከአቅማቸው በላይ እየሆነ መምጣቱን በምሬት ተናግረዋል፡፡

አዲስ አበባ የተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት፣ ኤምባሲዎች፣ ዲፕሎማቶች መቀመጫ ብትሆንም፣ የውሃ እና መብራት ችግር ግን ሊቀረፍላት አልቻለም፡፡ ከተማዋን እያስተዳደርኩ ነው የሚለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ሆነ የፈደራል መንግስት፣ የአዲስ አበባን የመብራት እና ውሃ ችግር መቅረፍ ከተሳናቸው ረዥም ጊዜ ተቆጥሯል፡፡ ችግሩ እየገነነ ከመምጣት ውጭ ምንም የተለወጠ ነገር እንደሌለ የከተማዋ ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡ የአዲስ አበባ ውሃ እና ፍሳሽ ባለስልጣን በከተማዋ ለተፈጠረው የውሃ ችግር፣ መብራት ኃይልን ሲወነጅል የነበረ ሲሆን፣ መብራት ኃይል በበኩሉ ውንጀላውን አንደማይቀበለው በመግለጽ እርስ በእርስ ሲባሉ ነበር፡፡ ውሃ እና ፍሳሽ፣ መብራት ኃይል ለመብራት ዝርጋታ መሬት ሲቆፍር፣ የውሃ ቧንቧዎችን እየሰበረብኝ ነው የሚል ስሞታ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ሆኖም የከተማዋ የውሃ ችግር ግን ውሃ እና ፍሳሽ በሚያቀርበው ሰበብ ብቻ የተገደበ አንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ (ቢቢኤን)

ተጨማሪ ያንብቡ:  ፖሊስ በሐዋሳ ከተማ በቅስቀሳ ላይ የነበሩ የአንድነት አባላትን በሙሉ አሰረ- የታሰሩትንም ደህንነት ማወቅ አልተቻለም
Share