November 7, 2017
13 mins read

“የህወሓትን ሕዝባዊ ጭፍጨፋና ከፋፋይነት እንኮንናለን፣” – በኮሎኝና አካባቢዋ የኢትዮጵያ ማሕበረሰብ/ኮሚኒቲ ኮሎኝ/ጀርመን

ጥቅምት 28 , 2010 (Oct. 7. 2017)

ህ ወ ሓ ት በየካቲት 1967 ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በዱር በገደል ይንቀሳቀስ በነበረበት ጊዜና ሥልጣን ከጨበጠም ወዲህ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ለ 27 ዓመታት የፍጅት፣ የእሮሮ፣ የእመቃ ዘረኛ ሥርዓት ሳያባራ ተካኺዷል። ዛሬ ላይ ደግሞ ከመቸውም ጊዜ በላይ በከፋና በከረፋ መልኩ ሥርዓቱ ተንኮታኩቶ ወደ ከርሠ መቃብሩ ከመውረዱ በፊት ሕዝባችንን እየፈጀና እያፋጀ ይገኛል።

በኢትዮጵያ ምድር ላይ እሮሮው ከዳር እስከ ዳር በሁሉም ቦታ ተበራክቷል። በአገሪቱ በሁሉም ማእዘናት ሕዝቦች ያነባሉ፣ ሕጻናት፣ በተለይ ወጣቶች፣ ባልቴቶችና ሽማግሌዎች ከባዕድ ጠላት የወረራ ዘመናት በባሰ ሁኔታ የግፍ ርምጃ፣ ውርደትና ኢሰብአዊነት ይካሄድባቸዋል። ወገናችን፣ የአገር ያለህ፣የሰው ያለህ፣ የፍትሕ ያለህ፣ የሕግ ያለህ እያለ በከተማና ገጠር፣ አምባና መንደር ሁሉ ይጮኻል። ሰሚ ግን እስከአሁን አላገኘም። የደም እንባውን የሚያብስለት አጋርና ወገን አላገኘም።

ይህ ሁሉ በደልና ግፍ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ሲወርድ፣ ባዕዳን ሁሉም ተስማምተውብን ጆሮአቸውን ደፍነው ዐይናቸውን ጨፍነው፣ «አሳስቦናል!» በሚል ከአንገት እንጂ ከአንጀት በማይወጣ ቃል ይደልሉናል። «ታሪክ ራሱን ይደግማል» ነውና የኢትዮጵያን ሕዝብ ልቅሶና ዋይታ፣ ሁሉም ባዕዳን ለይምሰልና ለማስመሰል ካልሆነ በስተቀር ግፉንና በደላችንን ለመወጣት በምናደርገው ትግል ሊያግዙን፣ ሊያብሩን ቀርቶ፣ በሕዝባችን ላይ የሚፈጸመውን ፍጅትና ዕልቂት እንኳን መኖሩን ሊረዱ አይሹም። ስለዕልቂታችንና ፍጅታችን ሳይሆን፣ «ስለልማታችንና ብልፅግናችን» እያነሱ ሊያማልሉን ይሻሉ። ከእኛ በላይ ስለእኛ ጉሮሮና ኪስ፣ ዕድገትና ብልጽግና የዳግማዊ ወያኔ/ህ ወ ሓ ት የውሸት ፋብሪካ የሚያደነቁረን ባዶ የቆርቆሮ ጩኸት አንሶ እነርሱ ደግመው የቆርቆሮውን ቀለም ሲቀባቡለትና ሲያሰማምሩለት እንሰማለን፣ እንታዘባለን። ለነገሩ ማን ወያኔን/ህወሓትን በላያችን ላይ ጫነና፣ ለምንስ ዓላማና ተልእኮ?! በመሠረቱ በሰው ልጆች ታሪክ ሁሌም እንደታየው ጌታ ሎሌውን ፣ በቃኽኝ አገልግሎትህን አልሻም ብሎ ያለ፣ ሎሌ አሳዳሪና ገዥ ተሰምቶም ታይቶም አያውቅም። ይህም በመሆኑ፣ ሳይጠሩት አቤት፣ ሳይልኩት ወዴት ባዩን ወያኔን ምን ጎደለብን ብለው አገልጋይ ሎሌአቸውን በቃኽን ብለው ያሰናብታሉ።ስለዚህ ምርጫችንና ዕጣ ፈንታችን በራሳችን ሕዝብና በጽናቱ፣ በቁርጠኝነቱ፣ በነጻነት ወዳድነቱና በአይበገሬነቱ ላይ ተማምነንና ተስፋ አድርገን ስንታገል ብቻ ነው፣ እኛው ስለእኛ የጋራ ዓላማችንና ግባችንን ለመወጣት በያለንበት የዓለም ጫፍ ሁሉ መዋደቁ፣ ብሎም አማራጭ የለሽ ጉዞ ነው ብለን እናምናለን።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በቅርቡ በኦሮምኛና በሶማልኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች መካከል ተፈጥሮ የነበረው ግድያና መፈናቀል፣ በኢሉባቦር ክፍለ ሀገር በአማርኛ ተናጋሪው ማሕበረሰብ ላይ የደረሰው ዕልቂትና ፍጅት፥ እንዲሁም በቤንሻንጉልና ጉምዝ አካባቢ የተፈጸመው ግድያና ሽብርተኝነት ብሎም በቀሪው የኢትዮጵያ ክፍለ ግዛቶች በሚኖሩ ዜጎች ላይ የደረሰው ጸያፍና አሳፋሪ ድርጊቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚከናውነው በህ ወ ሓ ትና ተባባሪዎቹ ዕቅድ መሠረት ነው።
ይህን ነጻ ፍጅትና ግድያ፣ ማፈናቀልና ማዋከብ እንዲሁም ሕዝቦችን ከሕዝቦች፣ ማሕበረሰብን ከማሕበረሰብ ለማጋጨት የተሠራውን ኢሰብአዊ ድርጊትና ውድመት እኛ በኮሎኝ የምንገኝ የኢትዮጵያ ማሕበረሰብ አባላት አጥብቀን እናወግዛለን።

በሌላ በኩል የጋራ አገራችንን ከቀደሙት እንደተረከብናት ለማቆየት የምንሻ ከሆነ፣ ወገናችንና ሕዝባችን ብሎም ሁላችንም እንዳንከፋፈል አጥብቀን የምናምንና ኀላፊነት የሚሰማን ኢትዮጵያውያን ሁሉ፣ መከራው፣ ፍጅቱ፣ እሮሮው፣ ዘረኝነቱና የወያኔ ፋሺስታዊ ድርጊቱ ሁላችንንም ያስመረረና ያሳረረን በመሆኑ፣ ትግሉም ሆነ የኢትየጵያ ትንሣኤ በጋራና በጋራ ብቻ ልንወጣው የሚገባን ተግባርና ተልእኮ መሆን ይገባዋል።

በዚህ የጋራ ጉዞ ላይ ብዥታ ያለው ግለሰብ፣ ቡድን ወይም ድርጅት፣ ከጋራው ዓላማና ትግል፣ እንዲሁም ራእይ ውጭ መጓዙና መታከቱ ጎጂ እንጂ ጠቃሚ እንደማይሆን ለማወቅ ነቢይ መሆንን አይጠይቅም። የኢትዮጵያ ሕዝብ በእምነቶቹ፣ በባህሉና በታሪኩ ኩሩ ካሳኙት ምግባራቱና መለያነቱ፣ መከባበሩና መተሳሰቡ፣ መተሣሠሩ፣ መቻቻሉና በደጉም ሆነ በክፉው ቀን በአብሮነት መቆሙ ነው። ይህ ሕያው ፀጋውና በረከቱ ነው።

ወገኖች ሆይ፣ የወያኔ ጀምበር መጥለቅ ከአድማስ ባሻገር በግልጽ ይታያል። በኢትዮጵያ ሕዝብ አእምሮ ደግሞ የነጻነት ጎሕ እየቀደደ ነውና ሞትና ሽረታችንንም በአንድነት እንወጣዋለን፣ ይህም እውን ይሆናል ብለን አጥብቀን እናምናለን። ይህንን ለ 27 ዓመታት የኢትዮጵያን ሕዝብ ሲያዋክብ የኖረ ጉድ፣ ወቅቱ፣ በጋራ ሆነን እርሱ በረገጠበት የኢትዮጵያ ምድር ሁሉ ማዋከብና ማሳደድ ግዴታችን ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ ተልእኮአችን ሊሆን ይገባዋል። ቀኑ ሳይመሽ፣ ጀምበር ሳይሸሽ ሁሉም የሚጠበቅበትን ድርሻ እንዲወጣ ይመከራል!!!

የህ ወ ሓ ትን የዘረኝነት ወረርሽኝ፣ ፅንፈኝነት እስካሁን በጋራ እንደታገልነው ሁሉ፣ በበሽታው በተለከፉ አንዳንድ በትግራይ ተወላጆች ላይ የሚታየውን ሆነ፣ በሌሎች ቋንቋ ተናጋሪዎችም የፅንፈኝነት ስሜት ማንም ሆነ ማን በዚህ አፍራሽ፣ አግላይ፣ አሳፋሪና ከፋፋይ የአመለካከት ጉዞ ጋር እንዳይሠማራ እናሳስባለን፣ እናስገነዝባለን፣ እንገነዘባለንም። ዘረኝነት ማንም ያንግበው ዘረኝነት ነው፣ ፀያፍ ነው።ይህ በመሆኑም ዘረኝነት/ጽንፈኝነት ለኢትዮጵያውያን እንደ ባህል ነውርና ፀያፍ፣ እንደእምነትም ኩነኔ ነው። ማንኛውንም ዓይነት ፅንፈኝት፣ ዘረኝነት ሕዝብን በሕዝብ ላይ ማነሳሳትንና ማጋጨትን ከማንኛውም አቅጣጫና ምክንያት ይዞ ይነሣ እንቃወመዋለን፣ እናወግዘዋለን።

ከዚህ ጋር አያይዘን፣ የትግራይ ሕዝብና ኀላፊነት የሚሰማቸው የትግራይ ልሂቃን ይህንን ሥርዓት ከቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ወግኖ አብሮነቱን ማሳየት ወቅቱ አሁን ነው። ዛሬ ነው። ያለፈው አለፈ፣ ይህንን ታሪካዊ ወቅት ዝምታውን ሰብሮ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጎን በመቆም ሚናውን መያዝና ድርሻውን መወጣት ለኢትዮጵያም ሆነ ለትግራይ ሕዝብ ወሳኝነት ያለው ጉዳይ ነው።

ወያኔ አንዴ «ኮማንድ ፖስት» ሌላ ጊዜ «ጥልቅ ተሐድሶ» እያለ አምባገነናዊ ሥልጣኑን ለማራዘም ቢሞክርም፣ ሕዝባችንን አምርሮ እንዲታገል ገፋፋው እንጂ አልገታውም። ኢ ህ አ ዴ ግ በሚል የማጭበርበሪያ ስያሜ፣ የኢትዮጵያ ፀር ለሆነው የአገዛዝ ሥርዓት ሽፋን የሆኑት የህ ወ ሓ ት አጋር ድርጅቶች የሚሰኙት ኦህዴድና ብአዴን በባሕርዳር ስብሰባ በማድረግ ስለ አማራና ኦሮሞ ነገዶች/ብሔሮች የቆየና ቀጣይ ስላሉት ትሥሥር ብዙ በጎ ቃላት ቢደረድሩም፣ የአንድ በቁጥር አናሳ የሆነ ብሔር የበላይነት የሚንጸባርቅበትን ጎሠኛና አምባገነናዊ ሥርዓት ለመገርሰስ፣ ዴሞክራሲ ለመገንባትና እኩልነትን ለማሥፈን ካልሠሩ የሚያደርጉት ሁሉ ከንቱ ሽንገላ ብቻ ነው የሚሆነው።

በየአካባቢአቸው/«ክልላቸው» ያለአበሳቸው በየእሥር ቤቱ ታጭቀው ቁም ሥቅል በማየት ላይ ያሉትን በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችንና በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችን ባስቸኳይ እንዲፈቱ ካላበቁ ዲስኩራቸው ሁሉ የሕዝብ ትግል ማዘናጊያና የወያኔ ሥልጣን ማራዘሚያ ከመሆን አያልፍም። ስለሆነም ሕዝባችን ትግሉን በማጠናከር እነዚህን ስለውጥ የሚያወሱትን ቡድኖች ግፊቱን በመቀጠል በተግባር ሊፈትናቸው ይገባል ብለን እናምናለን።

በመጨረሻም፣ በህ ወ ሓ ት አማካኝነት በኢትዮጵያ ምድርና ሕዝቦቿ ላይ የተሠራው አሳፋሪና ፀያፍ፣ በታታኝና ከፋፋይ ሥርዓት በሕዝቦቿ አንድነትና ትግል ለሁሌም ያከትማል። «ድር ቢያብር አንበሳ ያሥር» ነውና እንተባበር!!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘለዓለም ትኑር!!

በኮሎኝና አካባቢዋ የኢትዮጵያ ማሕበረሰብ/ኮሚኒቲ ኮሎኝ/ጀርመን።

1 Comment

  1. የቦርጫሞች ማብቂያ የለለው መግለጫ ፡፡
    ምነው ለስራ እና ለለውጥ እንዲህ እሪ እምቧ ብትሉ ፡፡

    በለው ያዘው ሲሆንማ ላንቃችሁ እስኪበጠስ ማንቧረቅ ነው ፡፡

    መልካም ቅዥት !

Comments are closed.

Previous Story

የማዳኛው ክኒን ኢትዮጵያዊነት ነው

Next Story

ወያኔ ተልካሻ የእርሻ መሳሪያዎች ማስገባቱ ለቅራኔ እንደዳረጉት ታወቀ | ወያኔ የሽብር ድርጊት የሚፈጽሙ አሰልጥኖ ማሰማራቱ ተሰማና ሌሎችም (የፍኖተ ዴሞክራሲ የዛሬ ዜናዎች)

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop