አዲሱ የአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ የባርነት አዋጅ ነው የባርነት አዋጁን አጥብቀን እንቃወማለን !

በስደት ከሚገኙ የሠራተኛ መሪዎች የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ሆይ ! « የጭቁን ሕዝቦችን መብት ለማስከበር ብረት አንስቼ ጫካ ገባሁ » የሚለውን ኣታካች ፕሮፓጋንዳ ከሃያ ስድስት ዓመታት በሁዋላም ማላዘን ያላቆመው የሕወሃት ግፈኛ ኣገዛዝ ላለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት ያለማቋረጥ ያንተን ሁለንተናዊ መብቶች በግፍ እንደረገጠ ዘልቋል። አንተ ከዓፄው ስርዓት ጀምሮ የአንጋፋ መሪዎችህን የነ አበራ ገሙን ሕይወት ጭምር ገብረህ ያስከበርካቸው መሰረታዊ መብቶች በሕወሃት የግፍ ኣገዛዝ ዘመናት ተራ በተራ እየተናዱ ይገኛሉ።

 

ሕወሃታውያን የሃገራችንን አንጡራ ሃብት በጠራራ ፀሃይ ዘርፈው የትላልቅ እርሻዎች ፣ ኢንዱስትሪዎችና የማከፋፈያ ድርጅቶች ባለቤቶች ሲሆኑ ኣንተ ግን ከዓመት ዓመት ወደ ባሰ የድህነት ኣዘቅት ከነ ልጆችህ እየተገፋህ ማለቂያ የሌለው የመከራ ህይወት እንድትገፋ ተገደሃል። አንተና ልጆችህ በረሃብ አለንጋ እየተገረፋችሁ እነሱን ሚሊየነሮች ለማድረግ ብትደክምም በቃኝን የማያውቁት ሕወሃታውያን ግን ላንተ ያዘጋጁልህ ሽልማት አሰሪዎች ባሻቸው ሰዓት ለዓመታት ከደከምክበትና በላብህ ከገነባሃቸው ድርጅቶች እንደ እራፊ አውጥተው እንዲወረውሩህ የሚያስችላቸው ጨካኝ የዱር ሕግ ነው።

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ሆይ ! ችግሩ ባጠቅላይ በሃገራችን የሕግ የበላይነት መጥፋትና የባለ ጊዜዎች ከሕግ በላይ መፍዋለል እንጂ በሠራተኛ ሕጉ ላይ ሊፃፉ የታሰቡት አንቀፆች ከቶውኑ አይደሉም ። ችግሩ ያለው በሠራተኛው ሕግ ላይ ምንም ተፃፈ ምን ባለ ጊዜዎች የፈለጉትን እርምጃ ቢወስዱብህ የሚያስጥልህ ፍርድ ቤት የሚሞግትልህ ነፃ ማህበር ኣለመኖሩ ላይ ነው።

የችግሩ ምንጭ ዛሬ ሃገሪቱን ተቆጣጥሮ ያለው በአገር ክህደቱና የጥፋት ተግባሩ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት የወያኔ ሥርዓት ነው ። የችግሩ ምንጭ ዛሬ ወገኖቻችንን በድህነት ውቅያኖስ አጥሮ፣ በዘረኛና ከአፓርታይድም በባሰ ሁኔታ በጐሳና በሃይማኖት ከፋፍሎ፣ እውነት የተናገሩትን ወህኒ ቤት እየወረወረ፣ ይህ ቀረው የማይባል ሰቆቃ፣ ሥቃይና ግድያ የሚፈጽም ራሱን መንግሥት ብሎ የሚጠራው የወንጀለኛ ቡድን ነው። የችግሩ ምንጭ በኢትዮጵያችን የወጣቱን ተስፋ ገድሎ፣ ሞራሉን በአደንዛዥ ዕፅ አላሽቆ፣ ትምህርትን አዳክሞ፣ በኢኮኖሚ አድቅቆ፣ የኢትዮጵያን ለም መሬት ለባዕዳን እየቸበቸበ፣ ሕዝብን በኑሮ ውድነት በመቅጣት ላይ ያለው ግፈኛ ቡድን ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በአማራ ክልል የደቡብ ወሎ ዞን የደህንነት ቢሮ ሀላፊ አቶ ፍትዊ ግደይ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ተገደሉ፤

መላው ሃገሪቱ በባለ ጊዘዎች ጫማ ስር ሆና ፍትህ የባለ ጊዜዎች መጫወቻ በሆነችበት ሃገር ለሠራተኛው ብቻ የፍትህ ደሴት መመስረት አይቻልም። የሕዝብ አካል እንደመሆንህ ባለ ጊዜዎች ባለፉት ሃይ ስድስት ዓመታት በሕዝባችን ላይ ያደረሱት በደልና ግፍ ያዘነቡት መከራ ባንተና በልጆችህም ላይ ዘንብዋል። በመሆኑም ይህ የግፍ ዝናብ ያባራ ዘንድ መላው የሃገራችን ሕዝብ እያካሄደ ያለውን ሁለንተናዊ የሞት የሽረት ትግል ተቀላቅለህ የዚህን ግፈኛ ሥርዓት ፍጻሜ ለማፋጠን ክንድህን ኣስተባብረህ ተነስ።

ዛሬ በውጭ ኢንቬስተር ስም ከሕወሃት ጋር ተሻርከው ሃገሪቱን የወረሩ የውጭ ባለሃብቶች በገዛ ሃገርህ እንዳሻቸው እንዲጫወቱብህ ተፈቅዶላቸዋል። ሕወሃታውያን ከውጭ ኢንቬስተሮች በሚያገኙት ዶላር እራሳቸውን እና ልጆቻቸውን ለማንደላቀቅ እንዲመቻቸው ያንተን ደሞዝ ይሁነኝ ብለው በማሳነስ እና ጥቅማ ጥቅሞችህን በማስቀረት ከደሃው ዜጋቸው ይልቅ ዶላር ለሚያፈሱላቸው የውጭ ኢንቬስተሮች በማድላት በባርነት እየሸጡህ ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜ የሃገራችንን የብር አቅም በማሳነስ የነሱን ገቢ ወደ ሰማይ እያሻቀቡት ያንተን ገቢ ደግሞ ቁልቁል እየደቆሱት ነው። ትላንት ቀዬህ ድረስ መጥቶልህ ኪሎውን በአንድ ብር ትገዛው የነበረውን ስኩዋር ዛሬ ኪሎውን በሃምሳ ብር ለመግዛት ሃምሳ ኪሎ ሜትር እንድትንከራተት ያደረገህ ይህ በባእዳን እና ሃገር በቀል ዘራፊዎች ትብብር እይተፈፀመብህ ያለው ዘረፋ ነው።

የሃገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እንደመሆንህና ሃገሪቱም የጋራ እንደመሆንዋ አንተና ልጆችህም ከሃገሪቱ ሃብት ተቋዳሽ መሆን የዜግነት መብታችሁ መሆን ሲገባው ሕወሃታውያን ባንተ ላብና ጉልበት በተገኘ ሃብት በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገራት ልጆቻቸውን ሲያሞላቅቁ ያንተ ልጆች በረሃብ እየተገረፉ መኖር በዛባችሁ ተብለው ወደ በረንዳ ኣዳሪነት ሲወረወሩ ዝም ልትል ኣይገባም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለቀናት ታግተው የተለቀቁት የደምቢዶሎ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚደንት ‹‹እኔ ፖለቲካ አይመለከተኝም፣ ያገቱኝ ሰዎችም የተሳሳቱ ይመስለኛል›› አሉ

ሕወሃታውያን ዛሬ ባለ ብዙ ሚሊዮን ንብረት ባለቤቶችና የብዙ ላብ ኣደሮች ቀጣሪዎችና አሰሪዎች ሲሆኑ አንተ ግን ትላንት የነበሩህን መሰረታዊ የሠራተኝነት መብቶች እንኩዋን ይዘህ መኖር አልፈቀዱልህም። ዛሬ በአዲስ የሠራተኛ አዋጅ ሥም

 

ሊጭኑብህ ያዘጋጁት የባርነት አዋጅ ትላንት በዘመነ ደርግ ከነበረው የሠራተኛ መብት ጋር ሲነፃፀር የዛሬ ባለ ጊዜዎችና ሸሪኮቻቸው እነሱ ሰው በላ ከሚሉት ደርግ የከፉ ጭራቆችና የቀን ጅቦች መሆናቸውን ነው የሚያረጋግጠው።

ዛሬ በአዲስ የሠራተኛ አዋጅ ሥም ሊጭኑብህ ያዘጋጁትን የባርነት አዋጅ እምቢ ማለትህና ሕወሃት ይህን የባርነት ዓዋጅ በሃይል ሊጭንብህ ከሞከረም በዓለም አቀፍ ሕግጋት በተደነገገው መሠረት የሥራ ማቆም ዓድማ የማደረግ መብትህን ለመጠቀም እንደምትገደድ ማሳወቅህ ተገቢ እርምጃ ነው። ሆኖም ይህን ውሳኔህን እንድናስፈፅም ከሠራተኛው አደራ ተቀብለናል ባዮቹ የኮንፈዴረሽኑ ሹሞች በምንም መስፈርት የሠራተኛውን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚበቃ ሰብዕናም ሆነ ታሪክ የሌላቸው በሕወሃት የተሾሙ ተላላኪዎች መሆናቸውን ከማንም በላይ አራስህ የምታውቀው በመሆኑ አንተ በሥርዓቱ ላይ እንዳታምፅ ከማባበልና ለሥርዓቱ የመተንፈሻ ጊዜ ለማስገኘት የይስሙላ መግለጫ ከማውጣት አልፈው አሁን በኮንፌዴሬሽኑ አመራር ላይ ያሉት የሕወሃት ተሹዋሚዎች ያንተን መብት ለማስከበር ከፈጣሪያቸው ሕወሃት ጋር በቁርጠኝነት ይታገላሉ ብለህ እራስህን እንዳታታልል አደራችን የጠበቀ ነው።

በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት ሕወሃት ነው ። ታላላቆቹ ባለሃብቶች፣ ቀጣሪዎችና አሰሪዎች ሕወሃታውያን ናቸው። የሠራተኛ ማሕበሩን ከፍተኛ አመራር የተቆጠጠሩት ሕወሃታውያን የሾሙዋቸው ተላላኪዎች እንጂ አንተ በነፃነት የመረጥካቸው መሪዎች አይደሉም። በመሆኑም ሕወሃታውያን እንደ አሰሪ ደምና ላብህን ይመጡሃል። እንደ መንግሥት ኣፋኝ ሕግ እያወጡ መብትሕን በሕግ እንዳታስከብር ያደርጉሃል ። የሠራተኛ ማሕበርህን በሎሌዎቻቸው ቁጥጥር ሥር አስገብተው መከታ ያሳጡሃል። እንዲህ ዙሪያው ገደል በሆነበት ሁኔታ ላንተ ካንተ በቀር ምንም መከታ እንደሌለህ ተረድተህ እንደ ትላንቱ እንደነ አበራ ገሙ ዘመን እርስ በርስህ እየተገናኘህና እየመከርክ ይህን የግፍ አገዛዝ መቋጫ ልታበጅለት የግድ ይላል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በደቡብ ኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ታልታሌ ወረዳ ቡሌደንቢ ቀበሌ ሰዎች በበሬ ፈንታ ቀንበር ሞፈር ላይ አስረው በመጎተት ሲያርሱ - DW

ትላንት በጋራ ቆመህ እንዳትታገላቸው ኃይልህን ለመበታተን በኢንዱስትሪ ዘርፍህ ሳይሆን በብሔርህ ተደራጅ ብለው ሲያስገድዱህ ወጊዱ ብለህ በጋራ እንዳባረርካቸው ዛሬም በብሔር ፣በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፆታ ወዘተ ሳትለያይ በአንድነት ቆመህ የተደገሰልህን የባርነት ድግስ ለማክሸፍ ከመሰለፍ ውጭ ሌላ አማራጭ የለህም።

ሕወሃታውያን በመላ ሃገሪቱ የዘረጉት ለነሱ ድሎትን ያጎናጸፈው የግፍ ሥርዓት በህዝቦች የጋራ ትግል እንዳይመታ ኢትዮጵያውያንን በብሔር በሃይማኖት በቋንቋ ወዘተ ከፋፍለው ሕዝቡን ማቆሚያ ወደሌለው ፍጅት ለማስገባት ቀን ከሌት እየተጉ ነው። አንተም በአንድነት ቆመህ መደባዊ ጥቅምህን ለማስከበር እንዳትታገላቸው በለመዱት የዘር ሃይማኖትና የቁዋንቁዋ መስመር እንዳይከፋፍሉህ በጋራ ለመቆምና አንተንም፣ ልጆችህንም፣ ኢትዮጵያንም ሕወሃታውያን ከደገሱት የደም ድግስ ለመታደግ ታላቅ አደራ አለብህ። ይህን ባንተ ላብ ሰብቶ አንተን ወደ ባሰ ባርነት ለመክተት እየተጣደፈ ያለ ደም መጣጭ ሥርዓት ወደ ግብዓተ መሬቱ ለማጣደፍ ላብ አደራዊ ክንድህን በአንድነት አንሳ። እኛ በስደት የምንገኝ የቀድሞ የሠራተኛ ማሕበራት መሪዎችም እያካሄድክ ላለኸው ሁለንተናዊ ትግል ያለንን አድናቆት እየገለፅን በትግሉ ከጎንህ ቆመን የበኩላችንን አስተዋፅዖ እንደምናደርግ ቃል እንገባለን።

የአገራችሁ ሁኔታ የሚቆረቁራችሁ፣ ሰላም ዴሞክራሲና ማኅበራዊ ፍትሕን የምትናፍቁ ውድ ኢትዮጵያውያን ሆይ ! ለዘመናት በሚያኮራ የወንድማማችነትና የእህትማማችነት መንፈስ ባዳበርነውን አብሮ የመኖር፣ የመከባበርና የመተሳሰር ባህላችንን መሰረት የኢትዮጵያ ሠራተኞች ያነሱትን ፍትሃዊ የመብት ጥይቄ በመደገፍ ከኢትዮጵያ ሠራተኞች ጎን እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

የኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት ለሠራተኛውና ለኢትዮጵያ ሕዝብ መብት መከበር ወሳኝ ነው !

 

ጥቅምት 2010 ዓ/ም 01 November 2017

1 Comment

 1. people are laughing ,

  is there a title called በስደት ከሚገኙ የሠራተኛ መሪዎች ?

  ONES U LEAVE YOUR JOB , YOU CAN NOT BE የሠራተኛ መሪ.

  MOST OF THE ORGANIZATIONS THAT THEY USED TO WORK ARE EITHER PRIVETIZED OR DIVESTED .

  ARE YOU የሠራተኛ መሪ FOR LIFE . LIKE ISSAYAS AFEWORKI , PRESEDENT FOR LIFE
  THE LIVING CONSTITUTION , LAW AND ORDER OF HIS COUNTRY .

Comments are closed.

Share