ኢትዮጵያውያንን በዘር ከፋፍለው የሚያፋጁንን ጎሰኞች በአንድነት ተነስተን “በቃችሁ” እንበላቸው!!! ከኢትዮጵያ አገር-አድን የቀውጢ-ጊዜ ግብረ-ኃይል የተሰጠ መግለጫ

ኦክቶበር 25 ቀን፤ 2017 ዓ/ም

አሁን ኢትዮጵያውንን የገጠመን ችግር ድንገተኛ አይደለም። ችግሩ ሰፊ፣ ከባድ፣ ለበርካታ ዓመታት በፀረ-ኢትዮጵያ ባዕዳንና አገር-በቀል የጥፋት መሣሪያዎቻቸው ጥምረት በገፍ እንድንጋተው ከተጠመቀልን መርዝ ገና ገፈቱን ነው እየቀመስን ያለነው። አንዱን ብሔረሰብ በሌላው ማስፈጀት የተጀመረውም ዛሬ አይደለም። ሕወሓት እስከዛሬ በሥልጣን ላይ ለመቆየት የቻለው ኢትዮጵያውያንን በቋንቋ የሚከፋፍል ‘ሕገ-መንግሥት’ አዘጋጅቶ በግድ በሕዝቡ ላይ በመጫን፣ በዕቅድና በስልት፣ ብሔረሰቦችን በሰበብ-አስባቡ እየነጣጠለ፣ እያናቆረ፣ እያጣላ፣ እያጋደለ፣ እንደሆነ ለአንድ አፍታም ልንዘነጋው አይገባንም። ይህንን ዛሬ በስፋት እየታየ ያለውን፣ ከኢትዮጵያውያን ፍፁም የማይጠበቅ፣ በብሔረሰቦች መኻል የእርስ-በርስ መጠፋፋት ለማምጣት ሆን ብሎ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሲነጣጥልና ሲሰነጣጥቅ ነው የኖረው። ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚቻለው ሕዝቡን እርስ- በርሱ ማጋጨትና ማፋጀት ሲቻል ብቻ ነውና፣ ይህን በአዕምሮ-ቢስነት በአግባቡ ተግባራዊ እያደረገ ነው የሚገኘው!!!

 

“ደም-ደም!” የሚያስብል ልክፍት ያለበት ይመስል፣ ሥልጣን ከጨበጠ ጀምሮ ኢትዮጵያውያንን ደም እያራጨ ነው የኖረው። በአማሮች ላይ በአሰቦት፣ በአርባጉጉ በኋላም በወለጋ ውስጥ፣ በኦሮሞዎች ላይ በወተር (ሐረርጌ)፣ በሙስሊም ኢትዮጵያውያን ላይ አንዋር መስኪድ (አዲስ-አበባ)፣ በጉራጌዎችና በስልጤዎች ላይ፣ በጅማ በናዝሬትና በሐረርጌ፣ በአኝዋኮች ላይ ጋምቤላ ውስጥ፣ በኮንሶዎች ደቡብ ውስጥ፣ ሲዳሞ ውስጥ በጊኤዲዖ፣ በቡርጂ፣ በጌሪዎች፣ በደቡብ-ብሔረሰብ አባላት ላይ በተደጋጋሚ፣ ጎንደር ውስጥ አማራና ቅማንት በሚል የፈጠራ ልዩነት አጋድሏል፣ አሁንም አላቆመም። ሕዝቡን ለመነጣጠልና እርስ-በርስ ለማጋጨት፣ ሲያመቸው በእጅ-አዙር፣ አስርጎ በሚያስገባቸው ተቀጣሪዎቹ አማካይነት፣ አለዚያም በቀጥታ በአንዱ ወይንም በሌላው ብሔረሰብ ላይ ጭፍጨፋና ማፈናቀል፣ እንዲሁም እርስ-በርስ ማጋጨትና ማጋደል እንዲካሄድ እያደረገ ነው፣ ሕወሓት በኢሕዴግ ውስጥ ከሰባሰባቸው ተባባሪዎቹ ጋር በመሆን እስከዛሬ ኢትዮጵያውያንን አፍኖና ረግጦ እየገዛ ነው ያለው!!

 

ያለ ሕዝቡ ይሁንታ፣ የተወሰኑ መሰሎቹንና ተባባሪዎችን መልምሎና አዘጋጅቶ፣ ሕገ-መንግሥት ውስጥ አንቀጽ 39ኝን ሰንቅሮ፣ በአንድነት ፈንታ ልዩነቶችን እያጠናከረ፣ በፍቅር ፈንታ ጥላቻን ቋቅ እስከሚለን እየሰበከ፣ ለዚህ ዓይነቱ የእርስ-በርስ መፋጀት እያዘጋጀን ነው የቆየው። ስለሆነም ውድ ወገኖች፣ የዛሬው ችግራችን ምንጭ በዋናነት ራሱን፣ እስከዛሬም “ሕዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ” እያለ የሚጠራው መርዘኛ አጥፊ የሆነ ድርጅትና የተጠናወተው የጠባብ-ብሔረተኛነት/ጎሰኝነት ዕምነቱ ነው። በዚህ እምነቱ ላይ በተመሠረቱ ፖሊሲዎች ነው ሕዝባችን እየታመሰ፣ አገራችንም አሁን ለተከሰተው አስጊና አደገኛ ሁኔታ የተዳረገችው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  «ሕወሓት ከአዲስ አበባ ሌላ ጉዳይ የለውም» ጌታቸው ረዳ

 

ሕወሓት በዓለም ታይቶ የማይታወቅ ቋንቋን መሠረት ባደረገ አሸናሸን አገሪቱን ስላካለልና እያካለለም ስለሆነ ለዘመናት አብሮ ተዋልዶና ተካብዶ የኖረውን ሕዝብ በታሪኩ ሂደት አልፎት የነበረውን ጥቃቅን ልዩነት እየመዘዘ ወደ መናቆር፣ መጋጨት፣ እርስ-በርስ መገዳደል ደረጃ እያደረሰው ይገኛል። ይህ እስከተቻለው ከፋፍሎና እያፋጀ የመግዛት፣ ሲያቅተው ደግሞ አገርን የማጥፋት ዓላማው ያለው ድርጅት በግልጽ ሊታወቅና ሕዝቡ በአንድነት ተነስቶ በቃህ ሊለው ይገባል።

 

ሰሞኑን በኤሊባቦር በቡኖ በደሌ የተከሰተው በጣም አሳዛኝና ሆን ተብሎ ‘የአማራ’ ብሔረሰብ አባላትን ለይቶ የማጥቃትና የማፈናቀል በአይነቱ አጸያፊ የሆነ ወንጀል በዋነኛነት ተጠያቂውና ድርጊቱ የፈጸሙትን የተሰባሰቡ ኃይሎችን በጥላቻ ታሪክና በአይዞህ ባይነት ስልጣን ከተቆናጠጡበት ጊዜ አንስቶ ሲያዘጋጁና ሲያደፋፍሩ የቆዩት በህወሃት መሪነት አማራውን እንደተለየ ፍጡር በወጣቱ አይምሮ ሲቀርጹ የኖሩት ጽንፈኛ ጠባብ ብሔረተኝነት የተጠናወታቸው ቡድኖች ናቸው። ይህ ድርጊታቸው በእሳት እንደ መጫወት ያህል እንደሆነ በቅጡ የተረዱትም አይመስልም፤ ፈሩንም ከለቀቀ እነሱንም ሆነ ሁሉንም ለከፍተኛ አደጋ እንደሚዳርግና ለሚሆነውም ተጠያቂ ከመሆን እንደማያመልጡ ሊገነዘቡት ይገባል።

 

ሁሉም ሰብዓዊ መብቶቹ ተረግጠውበት፣ በዜግነቱ ሊያገኛቸው የሚገቡት ዴሞክራሲያዊ መብቶቹን ሁሉ ተነጥቆ፣ የሕግ-የበላይነት የሚባለው በአገሪቱ ውስጥ ደብዛው ጠፍቶ፣ ኅብረተሰቡን በጎሰኛነት፣ በለየለት አድልዖአዊ አገዛዝና በሙስና በክለው፣ ከስምንት ሚሊዮን በላይ የቆጠሩ ዜጎች ከድርቅ ጋር በተያያዘ ለርሃብና ለጠኔ ተዳርገው፣ መላው ሕዝብ በኑሮ ውድነትና በዋጋ ግሽበት እየተጎሳቆለ መገኘቱ ይታወቃል። በሕወሓት የግፍ አገዛዝ የተማረሩ ወጣት ኢትዮጵያውያን ብሶታቸውን በሠላማዊ ሠልፍ ለመግለጥ መፈክር አንግበው ባዶ እጃቸውን አደባባይ መውጣታቸው እንደ ከባድ ወንጀል ተቆጥሮ የባዕድ ኃይል እንኳን ያደርገዋል ተብሎ በማይታሰብ ደረጃ በአልሞ-ተኳሾች ጥይት በጭካኔ መግደል፣ እንደ እንሰሳ በዱላ መቀጥቀጥ፣ አፍሶ በጅምላ ለወራት በማሰር ኢ-ሰብዓዊ ሰቆቃ መፈጸም፣ ወዘተ… አልፎም “የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ” በማወጅ መሠረታዊ የሚባሉ መብቶችን የጠየቀን ሕዝብ በጥሬ ጉልበት ለማንበርከክ የወሰደው እኩይ እርምጃ የአገዛዙን ለከት-የለሽ አረመኔአዊነት ከማረጋገጥ ውጭ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለፍትኅ፣ ለእኩልነትና ለአንድነት የሚያደርገውን ትግል ፈጽሞ አያመክነውም። አገዛዙ በሰላማዊ ሕዝብ ላይ የወሰዳቸውና እየወሰዳቸው ያሉ የግፍ እርምጃዎች ዓለም-አቀፉን ማኅበረሰብ ለማደናገር የጫነውን ‘ዴሞክራሲያዊ…’ የሚለውን የመሞካሻ ካባውን አውልቆ አምባገነናዊነቱና አማቂነቱ ቁልጭ ብሎ እንዲታይ በማድረጉ፣ ቀደም-ሲል ጭፍን ድጋፍ ይሰጡት በነበሩ ኃይሎች ዘንድ ሳይቀር ማንንቱ ይበልጥ እንዲጋለጥ ሆኗል ማለት ይቻላል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጋዜጠኞች ላይ ያለ ማስረጃ የሚሰነዘሩ ውንጀላዎች ባስቸኳይ እንዲቆሙ እንጠይቃለን!

 

ማንኛውም አምባገነን ዘላለም አንድን ሕዝብ አፍኖ መግዛት አይችልም። ሕወሓትም ይህን ያውቃል። ኢትዮጵያውያኑን በእርስ-በርስ ግጭቶች ውስጥ በመዝፈቅ፣ በመንግሥትና በሥርዓቱ ላይ ያነጣጠረውን የሕዝቡን መነሳሳትና ትግል አቅጣጫ ማሳት ይፈልጋል። ምንም እንኳን “የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ” በሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ቀጥተኛ አመራር ሥር ሲንቀሳቀስ፣ በኢትዮጵያውያን ሶማሌዎች ላይ ከፈተኛ ጭፍጨፋ ሲያደርግ የቆየ “አፋኝና መቺ ኃይል” ሆኖ ቢቆይም፣ ሕወሓት ይህንን “የፏለለ ገዳይ” ቡድን እንዲመሠረትና እንዲጠናከር ያደረገው ታማኝ በሆነው በሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት የሚመራ ስለሆነ ለእንደዚህ ያለ ጊዜ አንዱን ወይም ሌላውን የኅብረተሰባችን ክፍል ነጥሎ ለማጥቃት ታልሞ የተዘጋጀ መሆኑ አጠያያቂ ላይሆን ይችላል። ለምን ሠላማዊ የሆኑት የኦሮሞ ብሔረሰብ ተወላጆች ላይ ይህን ዓይነት ጭፍጨፋ ይደረጋል? ለምን ከቀያቸው እንዲፈናቀሉና እንዲሰደዱ ይደረጋል? በሰላማዊ የሶማሌ ብሔረሰብ አባላት የሆኑት ዜጎቻችን ላይ፣ አገዛዙ ያውም አፋኝ የሆነ የሕወሓት አገዛዝ በሚቆጣጠረው አወዳይ ላይ ለምን ጭፍጨፋና ግድያ ይኖራል? በሁለቱ ብሔረሰቦች መኻል ለምን ደም ማፋሰሱ ተፈለገ?! ግፉ እጅግ በዝቷል። መቼ ነው የሁሉም ኢትዮጵያዊ በሠላም የመኖር መብት የሚከበረው?! ሁላችንም በየተራችን እንድንመታና የእኩይ ገዥዎች ሰለባ እስከምንሆን ተፋዝዘንና ተነጣጥለን እንቁም? ወይንስ ሁላችንም የምንድነው አብረን ስንቆም መሆኑን ተረድተን አንድ ሆነን በበዳዮቻችን ላይ እንነሳ?!

 

ግድያው፣ ግጭቱ፣ መናቆሩና ትርምሱ በዚህ መቀጠል የለበትም። ኢትዮጵያውያን ከቀደምት አባቶቻችን የወረስናቸው በርካታ አኩሪ እሴቶች አሉን። ለክብራችንና ለነፃነታችን መስዋዕት መክፈል የኛነታችን መገለጫ ከሆኑት እሴቶቻችን ዋናው ነው። ቀደምቱ የኢትዮጵያዊ ሕዝብ ኢትዮጵያ የምትባለውን ነፃ አገር ያቆየልን ተከብረን እንድንኖርባት እንጂ እንድንዋረድባት፣ እንድንተላለቅባትም አይደለም። ስለሆነም የሕወሓ.ት/ኢሕአዴግን አገዛዝና ሥርዓት ከነግሳንግሱ ማስወገጃው ወቅት አሁን ነውና በአንድነት ተነስተን የተጀመረውንና በእቅድ ላይ የተያዙልንን እልቂቶችን እናስቁም!!

 

በተለይም የአገርን አንድነትና የሕዝብን ክብር ከባዕዳን ወረራ ለመታደግ በአገር መከላከያ ሠራዊትና በደኅንነት ክፍሎች ውስጥ የምታገለግሉ ወገኖቻችን፣ መኻላ የፈጸማችሁበት ታማኝነትና አገልግሎት ኢትዮጵያ ለምትባል አገርና ከአብራኩ ለወጣችሁበት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ፣ በታሪክ አጋጣሚ በአንድ ወቅት ሥልጣን ላይ ለሚገኝና ዘለቄታዊነት ለማይኖረው፣ ነገም ቢሆን አሁን ትእዛዝ ተቀብላችሁ በሕዝብ ላይ በምትወስዱት ማንኛውም እርምጃ ዋቢ ለማይሆንላችሁና በተናጠል ተጠያቂ ከመሆን ለማያድናችሁ ቡድን፣ ድርጅትም ሆነ ወይም መንግሥት አለመሆኑን ተገንዝባችሁ፣ ግፈኛ ገዥዎችን በሥልጣን ላይ ለማቆየት ውሎ አድሮ በታሪክና በሕግ ተጠያቂ ከሚያደርጋችሁና ከእናንተም አልፎ የልጅ- ልጆቻችሁን አንገት ከሚያስደፋ ተግባር በወገኖቻችሁ ላይ ከመፈጸም እንድትቆጠቡ ጥሪያችንን ስናቀርብ ከከፍተኛ አደራ ጭምር ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሰማያዊ ፓርቲ በመብራት ኃይል አዳራሽና በምኒልክ ት/ቤት ሕዝባዊ ስብሰባ እንዳላደርግ በቢሮክራሲያዊ መንገድ ተከለከልኩ አለ

 

እንዲሁም በጊዚያዊ ጥቅማ-ጥቅሞች በመደለል ወገናችሁን በመሰለልና አሣልፎ በመስጠት፣ ወይም በግንዛቤ ማነስ ምክንያት የልዩነቶች አራጋቢ በመሆን የገዥዎች መሣሪያ የሆናችሁ ሁሉ ከእንደዚህ መሰሉ አሳፋሪ የባንዳነት ተግባር እንድትቆጠቡ እናሳስባለን።

 

በተቀዋሚ ድርጅቶች መልክ የተደራጁትም ሆኑ በሕዝባዊ (ሲቪክ) ማኅበራት መልክ የተደራጁት፣ ነገ ከነገ ወዲያ ሳይባል አገርን እንደ አገር የማቆየት ዓላማን አንግበን በፍጥነት መሰባሰብ፣ መደራጀትና አምርረንም መታገል ያስፈልጋልና ተግባራዊ እርምጃ እራሳችሁን እንድታዘጋጁ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

 

በገዥዎቻችን እኩይ ተግባራት ለተገደሉት ጥልቅ አዘናችንን እንገልጣለን። የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሁሉ እንዲያገግሙና እንዲድኑ እንመኛለን! የተፈናቀሉትና የተሰደዱት በፍጥነት ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ለሟች ቤተሰቦችም አገዛዙ ካሣ እንዲከፍል እንጠይቃለን።

 

ጥሪ ለመላው የኢትዮጵያዝብ

 

  • ሊነጣጥሉንና ሊያፋጁን እንዳይችሉ በቋንቋና በሐይማኖት አንከፋፈልላቸው! ዛሬም እንደወትሮው አንድ ነን እንበላቸው!
  • ሁላችንም እጅ-ለእጅ ተያይዘን “እምቢ! አሻፈረኝ!” እንበላቸው!
  • በጨቋኞች ሥር የሚንቀሳቀሱት የጦርና የፀጥታ ኃይሎች አባላት ልትጠብቁት በሚገባችሁ በወገናችሁ ላይ ሰቆቃና ግድያ አትፈጽሙ!
  • የሁሉም ሐይማኖቶች ተቋሞችና መሪዎች/አባቶች፣ በሕዝቡ ላይ የሚፈጸመውን ግድያ፣ ግፍና በደል በይፋ ተቃወሙ!

ይህንን መግለጫ በአገር አድን የቀውጢ ጊዜ ግብረኃይል ስም በጋራ ያወጡት፣

፦ ዳግማዊ አርበኞች ንቅናቄ

፦ ሞረሽ ወገኔ የአማራ ድርጅት

፦ የኢትዬጵያ ዲሞክራሲያዊ ህብረህዝብ የአንድነት ንቅናቄ

፦ የኢትዬጵያ ሞስሊሞች ሰላማዊ ንቅናቄ ድጋፍ ሕብረት

፦ የኢትዬጵያ ብሔራዊ ሽግግር ምክር ቤት

፦ የኢትዬጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ

፦ ቱሳ የኢትዬጵያ ትንሣኤ ድሞክራሲያዊ ድርጅት

፦ የኢትዬጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ ናቸው፤

 

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

 

 

 

 

 

 

 

4 Comments

  1. You are selfish and a collection of groups with no public bases and vision. You are a bunch of anti-unity. You try to work against the interests of the majority. But it will not work. We are in a new era. We have been making a great history while you try to make undemocratic and  inhuman  campaigns against the vast majority of the Ethiopian people.

    If you want to solve the problems of the Empire state of Ethiopia seriously. First, you have to denounce all the bad deeds of all past and present repressive systems. Second, make sure for yourself that the hegemony of the Habesha will not have place in Oromia henceforth.

    Narrow nationalists are those who are against the democratic rights of the multinationals in Ethiopia. They have been using always derogatory terminologies in order to undermine the demands of the Oromo nation. Those individuals are desperate and hopeless. No more business as a usual.

  2. Gamadaa (aka Hagos).. your comments contradicting each other.. At least, read first, and then understand their concept, and make comments. The word “Unity”; “Ethiopia” and *GYR Flag* always made you very uncomfortable since you are infected with a social & a deadly disease called “Clan federalism”.. it’s fading out and Ethiopian will be for Ethiopians soon and all TPLF’s morons & tugs will be executed and face justice. Remember this.. We are living in the era of 2017/18 NOT 1991

    • You are one of the supporters of this bunch of hallow collection. No wonder for your uncivilized comments. Empty Akaki Serf will not help you. Rather try to think and work rationally.

  3. የአንድነት ሀይል ባለፋት 50 አመታት በመቶ ሺህ የሚቆጠር ኢትዮጵያውያን ህይወት አስበልቶ ፣ 1991 ሀገሬቱን ለብሄር ሀይሎች አስረክቦ ፤ በሽንፈት ነው እጣው ያበቃው። የብሄር ሀይሎች እንዳሸን በፈሉባት ሀገር ፤ አሁንም ያን ያረጀ ፥ ያፈጀ ፥ ተሸናፌ የሆን የአንድነት የማታገይ ስልት እንደመፍቴሄ ማቅረብ ምንማለት ነው?

Comments are closed.

Share