ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ የተላከ ስኳር ድንበር ላይ እየተበላሸ እንደሚገኝ ተጠቆመ

የህወሓት መንግስት ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ ያጓጓዘው ስኳር ድንበር ላይ ለብልሽት እየተዳረገ መሆኑን መረጃዎች አመለከቱ፡፡ በሀገር ውስጥ በቂ የስኳር ምርት ሳይኖር ለኬንያ ከ50 ሺህ ኩንታል በላይ ስኳር የሸጠው የህወሓቱ መንግስት፣ ስኳሩን ወደ ኬንያ ቢያጓጉዝም ድንበር ላይ ታግቶ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚህም የተነሳ ከ110 በላይ ስኳር ከኢትዮጵያ ጭነው ወደ ኬንያ የተጓጓዙ ተሳቢ መኪኖች ከወር በላይ ሞያሌ ድንበር ላይ ለመቆም ተገድደዋል፡፡

ችግሩ በምን ምክንያት እንደተፈጠረ ለጊዜው የታወቀ ነገር ባይኖርም፣ ከ110 በላይ ስኳር የጫኑ መኪኖች ድንበር ላይ መቆማቸውን ተከትሎ ስሞታ ማሰማት ጀምረዋል፡፡ ስኳሩን ወደ ኬንያ እንዲያጓጉዙ የተመረጠው የመኪኖቹ ባለንብረት ድርጅት ስሞታ ማቅረብ የጀመረው ከወር በፊት ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም ሞያሌ ድንበር ላይ እንዲቆሙ መገደዳቸውን ተከትሎ ለመንግስት ስሞታ ያቀረበው የመኪኖቹ ባለቤት ድርጅት፣ ከኬንያ መንግስት ጋር በተደረገ ስምምነት መኪኖቹ ወደ ኬንያ እንዲገቡ እንደተፈቀደላቸው ተነግሮ ነበር፡፡ ሆኖም ስኳር የጫኑት መኪኖች እስካሁን ድረስ ወደ ኬንያ መግባት አልቻሉም፡፡ በዚህም የተነሳ ስኳሩን የሚረከባቸው አካል አጥተው ከወር በላይ ስኳሩን እንደጫኑ ለመቆም ተገድደዋል፡፡

አንድ ኪሎ ስኳር እስከ 60 ብር ድረስ ከሚሸጥባት አትዮጵያ ከ50 ሺህ ኩንታል በላይ ስኳር ወደ ኬንያ መጓጓዙ ብዙ ሲያነጋግር ነበር፡፡ ስኳር ለኬንያ በተሸጠ በ15 ቀናት ውስጥ በሀገር ውስጥ የስኳር ገበያ ላይ ከፍተኛ መናጋት የተፈጠረ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስም በኢትዮጵያ በቂ የስኳር አቅርቦት አለመኖሩን ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡ በኢትዮጵያ በቂ የስኳር አቅርቦት አለመኖሩን ተከትሎም አንድ ቤተሰብ መንግስት በሚመድብለት ኮታ ወይም መጠን መሰረት ስኳር ለመግዛት ተገድዷል፡፡ የህወሓት መንግስት ለኬንያ የሸጠው ስኳር መጠን 2 ነጥብ 2 ሚሊዬን ዶላር የሚያወጣ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ፊታችሁን ወደምስራቅ አማራ! (ሙሉአለም ገ/መድህን)
Share