ሰሞኑን የአማራ አክቲቪስቶች በወያኔ መጠለፋቸዉን አንዳንድ ወንድሞች እዚህ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ለጥፈዉ አነበብኩ:: የመረጃዉ አስገራሚነት ደግሞ አንዳንዶቹ ስድስት አክቲቪስቶች ናቸዉ የተጠለፉት ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ ሁለት ናቸዉ ወይም ሶስት ናቸዉ የሚል መረጃ ላይ መከራከራቸዉ ነዉ:: ነገሩን ጠጋ ብሎ ለመረመረዉ ሰዉ ደግሞ አንድም ተጠለፈ ስድስትም ተጠለፈ ለዉጥ የለዉም:: በጣም አስገራሚዉ ነገር ታዲያ እነዚህ ሁለት ወይም አንድ ወይም ስድስት አክቲቪስቶች በሙሉ በማህበራዊ ሚዲያዉ የሚጠቀሙት በብዕር ስም መሆኑ ነዉ:: እዉነተኛ ስማቸዉን አይጠቀሙም::
የሆኖ ሆኖ ነገሩ እንዲህ በይፋ ከወጣ ለህዝብ ማስተማሪያነት እንዲዉል አሁን
በርዕስነት አነሳንዉ እንጅ የዚህ አይነት ታሪኮች ዉስጥ ዉስጡን ይደርሱናል::እናም አንድ የተበላሸ ነገር እና የተቃዋሚዉ ጎራ ሊያርመዉ የሚገባዉ አካሄድ እንዳለ ግልጽ ነዉ::
እንግዲህ ጥያቄዉ እነዚህን በሌላ ስም የሚጠቀሙ አክቲቪስቶች እንዴት እና ማን እየጠቆመ አሲያዛቸዉ የሚለዉ ይሆንንና ይሄንኑ ጉዳይ ለማሳዬት ተያያዥ ጉዳዮችንንም እየመዘዝን እንወያያለን::
ደጋግሜ በአማራ ስም ለተደራጃችሁ የፖለቲካ ድርጅቶች: አክቲቪስቶች እና ጸሃፍት ለማሳሰብ የሞከርኩት ነገር አለ::በአማራ ስም ለቆማችሁት ብቻ አይደልም::በኢትዮጵያዊነት ስም ለተደራጃችሁትም: በኦሮሞነት ለቆማችሁና ለተደራጃችሁም አንድ ነገር ለማብራራት ሞክሬአለሁ::ዛሬም ደግሜ ያንኑ ነገር ማንሳት እፈልጋለሁ:: ዛሬ የማነሳዉ ግን ለዬት ባለ መልኩ ይሆናል::
ጥቂቱ እርሾ ጠቅላላ ሊጡን እንደሚያጠፋዉ እወቁ::የፖለቲካ ትግል ከንክኪ ነጻ እስካልሆነ ድረስ እና እስከሞት ከሚታመኑ ሀይሎች ጋር መቆምህን እስካላረጋገጥህ ድረስ ወያኔ ህልምህንም ሊሰርቅህ እና ህልምህንም ሊያስርብህ እንደሚችል እወቅ::ይሄ ፍርሃት አይደለም::አማራ ነኝ ብሎ እየዘለለ ወደ አንተ ስለመጣ: ኦሮሞ ነኝ ብሎ አካኪ ዘራፍ እያለ ቡድንህን ሊቀላቀል ስለጠዬቀ ወይም ኢትዮጵያዊነትን እወዳለሁ እያለ እዬማለ እና እየተገዘተ ወደ አንተ ፓርቲ ሊቀላቀል ስለጠዬቀ በርህን ወለል አድርገህ የምትቀበል ከሆነ የፖለቲካ ትግል ባትጀምር ይሻልህ ነበር::
አማራ ተበድሏል እያለ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ወያኔን እየረገመ : ከአማራ በላይ አማራ በመሆን የነገስታት ፎቶ ለጥፎ በዉስጥ መስመር የሚስጥር መልዕክት የሰደደልህን ሁሉ ካመንክ ቀድመህ ወደ ፖለቲካ ባትዘልቅ ይሻልሃል::
ዛሬ ወያኔ እና ብአዴን ተጣልተዋል በመሆኑ ዉሻዎቹን ብአዴኖች ልመናቸዉ ብለህ የምትነሳ ልበ አሸዋ ከሆንክ ቀድመህ የፖለቲካ ነገር ሳታነሳ ምነዉ በቀረብህ ነበር? የኢትዮጵያ ቀንደኛ ጠላት የሆነዉ ኢሳያስ አፈወርቂ ገና ለገና ከወያኔ ተጣልቷል እና ኢትዮጵያን ነጻ ለማዉጣት እና አንድነቷን ለመጠበቅ ሊያግዘኝ ይችላል ብለህ ካሰብክ ምነዉ ፖለቲካዉን በጅህ ሳትነካዉ በራቅህዉ ኖሮ? ገና ለገና ኦነግ አማራን የሚጠላዉን ያህል ወያኔ አማራን ይጠላል እና የአማራ ጥላቻ ኦነግ እና ወያኔን ያስተሳስረናል ብለህ ከወያኔ ጋር በአንዳንድ አላማዎች ለመተባበር ወደ ንክኪ የገባህ እንደሆነ ምነዉ ፈጽሞ ወደ ፖለቲካ መስመር ሳትገባ አልጋህ ላይ ተኝተህ በቀረህ ኖሮ?
አሁን ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉ ፖለቲካ የሸፍጥ: የጉልበት: የስለላ: የሚስጥራዊነት እና የጎጠኝነት ብሎም ለአላማቸዉ በቆረጡ እና ለሆዳቸዉ በሚኖሩ ሀይሎች መሃከል ተደበላልቆ ነዉ::እናም እነዚህን ስድስት የአማራ አክቲቪስቶች ያሲያዛቸዉ አማራ ነኝ እያለ ስለ አማራ መበደል እየሰበከ ዉስጥ ዉስጡን ግን ለወያኔ የሚሰራ ሀይል ነዉ::በኢትዮጵያዊነት የተሰለፉ ታጋዮችንም: በኦሮሞነት የተሰለፉ ታጋዮችንም እያስበሏቸዉ ያለዉ የአላማቸዉ ተከታይ እየመሰሉ ነዉ::
አንድ ማስታወሻ ልጨምርበት::ከጥቂት አመታት በፊት ከሰማያዊ ፓርቲ ወደ ሰባት የሚሆኑ ልጆች ሰላማዊ ትግል አያዋጣም ብለዉ ግንቦት ሰባትን ሊቀላቀሉ ወደ ኤርትራ ሊሻገሩ ተነሱ::በሚገርም ፍጥነት ጎንደር ላይ ሲደርሱ በወያኔ ደህንነት ቁጥጥር ስር መግባታቸዉን ሰማን::ከመኢአድ : ከአንድነት እንዲሁም ከጎንደር አርሶ አደር ማህበረሰብ ወደ ግንቦት ሰባት ሊቀላቀሉ የተነሱ ሰዎች በፍጥነት በወያኔ ደህንነቶች እጅ እንደ ገቡ ከዚህ ቀደም ሰምተናል:: ግን ጥያቄዉ ይሄ እንዴት ሊሆን ቻለ የሚለዉ ነዉ:: ይባስ ብሎም ኦነግ 800 ወታደር በደቡብ ሱዳን አድርጎ ወደ ወለጋ ሊያስገባ ሲሞክር አንድም ወታደር ሳይተርፍ በወያኔ ቁጥጥር ስር እንደገቡ ከዛሬ ስንት አመት በፊት የሰማሁት ዜና አሁን ድረስ ይደንቀኛል:: እንዴት?
እንዴት? ለምን? ወያኔ የተለዬ የስለላ አቅም ስላለዉ? ወያኔ መንፈስ ስለሆነ? እኔ እንደሚመስለኝ ወያኔ ተመራምሮ አይደለም ይሄን ሁሉ የስለላ የበላይነት ያገኘዉ::ወያኔ የቴክኖሎጂ ስለላም አድርጎ አይደለም የደረሰባቸዉ:: ወይም የወያኔ ሰዎች የተሻለ አቅም ኖሯቸዉ አይደለም ይሄ ሁሉ የሚስጥር የበላይነት ሊኖራቸዉ የቻለዉ::
ጎቤን የመሰለ ተወርዋሪ ኮከብ ወያኔ እንዴት በራሱ ዘመድ ሊያስገድለዉ ቻለ? በተቃዋሚዎች መሃከል እንዴት አንድ ሚስጢር የሚባል ነገር ጠፋ? ተቃዋሚዎች እርስ በርሳቸዉ መግባባት አቅቷቸዉ ከ1984 እስከ 1997 ዓም ዉስጥ ከመቶ በላይ ሰላማዊ ታጋይ ፓርቲዎች ኢትዮጵያን በምታክል ትንሽ እና ድሃ አገር ዉስጥ እንዴት ሊኖሩ ቻሉ? አሁን በቅርቡ እንኳን በትጥቅ ትግል እናምናለን የሚሉ ከሃያ በላይ ፓርቲዎች እንዴት በዉጭ ሀገራት እንደ አሸን ሊፈሉ ቻሉ? እነዚህ ፓርቲዎችስ እንዴት አንዱ ለሌላዉ በጠላትነት የተሰለፉ ሊሆኑ ቻሉ? ሌላዉ ቀርቶ አንድ ብሄር እንወክላለን እያሉ እንደ አሸን የሚፈሉ ፓርቲዎች በመሰረታዊ የጥላቻ ቀመር እንዴት ሊተበተቡ ቻሉ?
አንድ ቀን ጥናት ለማድረግ ያህል ብለህ ወይም የሀሳብ አንድነት እንዲፈጥሩ አስበህ ከ5 ልዩ ልዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ብትነጋገር አምስቱም ልብህ ዝቅ እስኪል የሚሰብኩህ ከእነሱ ዉጭ ያለዉ ሀይል በሙሉ የወያኔ አሽከር መሆኑን ነዉ::ግን እንዴት ብለህ የጠየቅሃቸዉ እንደሆነ አንዳንዶች ያኮርፋሉ:: አንዳንዶቹም ያልገባህ ነገር አለ ብለዉ አራምባ እና ቆቦ የሚረግጥ ትንታኔ ያቀርቡልሃል::ግን ዋና ማጠንጠኛቸዉ ሌላዉን ተቃዋሚ ጥላቻ ነዉ::ግን ለምን? ይሄ ሁሉ ጥላቻስ እንዴት ሊኖር ቻለ?
እናም ጥያቄዉ ይሄ ሁሉ መዝረጥረጥ በተቃዋሚዉ መሃከል ለምን ተከሰተ? የሚለዉ ነዉ:: በ1997 ዓም ስልሳ የቅንጅት ማዕከላዊ አመራሮች በአንድ ትልቅ አዳራሽ ዉስጥ በጋራ የተሰበሰቡበት የስብሰባ ሚስጥርን ወያኔ ደረሰበት ብሎ አጀብ ሲል የነበረ የኢትዮጵያ ሰዉ አሁን ደግሞ በስማቸዉ የማይታወቁ ስድስት አክቲቪስት ግለሰቦች በወያኔ የስለላ መረብ ተጠለፉ የሚል መረጃ ሲሰማ ኢትዮጵያዊዉ ስለትግል ምን ይሰማዋል? ግንቦት ሰባት እና ዴሜት ተዋሃዱ : የዴሜቱ መሪ ሞላ አስገዶም የዉህደቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነ ተብሎ ዜናዉ እየተነገረ ባለበት ቀን ዉስጥ ሞላ አስገዶም ከዳ የሚል ዜና የሚሰማ የተቃዋሚ ደጋፊ ምን ይሰማዋል? ከዴሜት ወታደሮች ጋር ተደባልቀዉ ትግል ለማድረግ የተዘጋጁ ታጋዮችስ ምን አይነት የትግል ሜዳ ሚስጥራዊ እርግጠኝነት ይሰማቸዋል? የደሜት ደጋፊዎች ከዱ ቢባል ምንም አልነበረም::የደሜት መሪ ከዱ የሚለዉ ግን ከአስደንጋጭም በላይ አስደንጋጭ ነዉ:: እናም ጥያቄዉ መዥጎድጎድ ይጀምራል:: የምትታገለዉ ከማን ጋር ቆመህ ነዉ? ሚስጢር የምትሰራዉ ከማን ጋር ቁጭ ብለህ ነዉ?
ለመሆኑ የየኢትዮጵያን ተቃዉሞን እንዲህ ልል ያደረገዉ ምንድን ነዉ?
ሰሞኑን የአማራን ህዝብ የእርድ ብይን ከህዉሃት ጌቶቻቸዉ ለመቀበል የሄዱትን እነ ገዱን እንደ ጀግና የሚያደንቁ የአማራ ተቃዋሚ አክቲቪስት/ፖለቲከኛ መሰል ሰዎች በአማራ ዲያስፖራ መሃከል ማዬትን የመሰለ ጎምዛዛ እዉነት የለም:: እናም እራስህን መጠዬቅ አለብህ:: የምትቃወመዉ ከማን ጋር ቆመህ ነዉ? ምናልባት አጠገብህ ያለዉ የወያኔ ንክኪ ይሆን? ጥቂቱ እርሾ ብዙዉን ቡኮ ያበላሸዋል እንደተባለዉ ይሄ የወያኔ ንክኪ ህይወትህን እንደኳስ የሚጫወትባት ግለሰብ ቢሆንስ? ደግሞስ ተስፋ ያደረግህዉን ድርጅት ለወያኔ ለማስረከብ በእጁ ዉስጥ ብዙ ሃይል ከወያኔ የተመደበለት ግለሰብ ቢሆንስ?
ለመሆኑ ተቃዋሚዎች በስራቸዉ ስለሚያሰባስቡት ሰዎች ህይወት ይጨነቃሉ? ስለታጋዮቻቸዉ ደህንነት ይጨነቃሉ? ተቃዋሚዎች ተከታዮቻቸዉን እና ካድሬዎቻቸዉን እንዴት ነዉ የሚመለምሉት? ነዉ ወይስ የአንድ ሰሞን ሆያሆዬ ለማግኘት ብቻ ሲባል የመጣዉን ያጋብሳሉ?
የሆነስ ሆነና በድብቅ በብዕር ሥም የሚንቀሳቀሱ አክቲቪስቶች በራሳቸዉ ላይ ህግ አዉጥተዋል? እራሳቸዉን ለማንም መግለጽ እንደሌለባቸዉ የራሳቸዉን መርህ አስምረዋል? ነዉ ወይስ ተቃዋሚ የመሰላቸዉን ሁሉ እያመኑ በዉስጥ መስመር ማንነታቸዉን ይገልጹለታል? ነዉ ወይስ ጥቂት ድጋፍ ብጤ ከዉጭ ሀገር የላከላቸዉን ሰዉ ሁሉ እያመኑ ማንነታቸዉን ያጋልጣሉ? ከሆነስ ሆነ እና በማህበራዊ ሚዲያ ማንነታቸዉ ደብቀዉ የህዝብ ድምጽ ለመሆን ሲወስኑ ስለ ማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም የተወሰነ ግንዛቤን ለመጨበት ጥረት አድርገዋል?
በተቃዋሚ ጎራዉ ወይም በአክቲቪስቶች በኩል ይሄን ሁሉ ለመመለስ ቁርጠኘት ይጠይቃል:: ሆኖም ችግሩ አሁን እኛ ማህበረሰብ ዉስጥ በፍጥነት መታወቅ: ቶሎ መክበር: ቶሎ ማሸነፍ እና በብልጣብልጥ የመከረባበት ህግ አፋጣኝ ድልን መቀዳጀት የሚለዉ የአዬር በአዬር ስነልቦናዊ እሴት ሀገሩን ተቆጣጥሮታል:: እናም መሰረት የያዘ አሰራር ሲነሳ ሁሉም ጆሮዉን ያሳክከዋል::ወይም ቁርጠት እንደያዘዉ ሰዉ ያቁነጠንጠንጠዋል::
ሆኖም ማህበረሰባችን ያለ ተቃዋሚዎች ድጋፍ እና አመራር እንዲሁም ያለ አክቲቪስቶች አነቃቂነት ደግሞ ድልን በራሱ ብቻ ሊቀዳጅ አይችልም:: ስለሆነም ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲሁም አክቲቪስቶች በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት ዉስጥ የተሽሞነሞነ እና በሀሰተኛ ሸፍጥ የተቀባባ ግምገማ ሳይሆን እዉነተኛ ግምገማ ሊያደርጉበት ይገባል::ወደ ትግል እየተሳቡ የሚገቡ ወገኖችንም ብዙ ማስተማር እና ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል:: ተቃዋሚዎች እና አክቲቪስቶች እንዲሁም ትጉሃን የህዝብ ወገን ጸሃፍት በልል መሰረት ላይ የቆመዉን የኢትዮጵያ የተቃዉሞ ፖለቲካ በጥልቀት እና በድፍረት የመመርመር ህዝባዊ ግዴታ አለባችሁ:: ህዝባዊ ግዴታ ብቻ ሳይሆን የህሊና እዳም አለባችሁ::እናንተን አምነዉ ወደ ትግሉ የሚሳቡ ሚሊዮኖችንም የመጠበቅ: ስለ ድህንነታቸዉ የማስተማር: ጥብቅ ሚስጥር ላይ የቆመ ትግል የማድረግ እና የማያወላዉል ህዝባዊ ግብን የታጠቀ አመራር መስጠትም ይጠበቅባችኋል::
የዚህ አለም የድል እና የአሸናፊነት መሰረታዊ መርሆ ትናንትም: ዛሬም: ነገም አንድ ነዉ::መሬት ነክሰህ መሰረቱን ላብህ ጠብ እስኪል ቆፍር::እመሰረቱም ላይ ንጹህ ዘር ዝራ::ዘርህ ከእንክርዳድ ንክኪ የጸዳ እስካልሆነ ድረስ ግን ንጹህ ምርት አታገኝም::ያም ንጹህ ዘር አሸናፊነት እና ድልህ ነዉ:: እናም ሲጠቃለል በአዬር በአዬር መርህ እና በንክኪ መሰረት ላይ ቆመህ በሚከወን አንዳችም አሰራር ዘላቂ ድል የለም:: ዋናዉ የዚህ ጽሁፍ ጭብጥም በአንድ አረፍተ ነገር ሲጨመቅ የሚከተለዉ ነዉ::ተቃዋሚዎች እና አክቲቪስቶች እንዲሁም ትጉሃን የህዝብ ወገን ጸሃፍት በልል መሰረት ላይ የቆመዉን የኢትዮጵያ የተቃዉሞ ፖለቲካ በጥልቀት እና በድፍረት የመመርመር ህዝባዊ ግዴታ አለባችሁ::