ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች ሀገራት የተከሰተው ተምች የምግብ እጥረት ሊያስከትል ይችላል ተባለ | በአማራ ክልል በአተት በሽታ የሰዎች ህይወት አለፈ

ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች ሀገራት የተከሰተው ተምች የምግብ እጥረት ሊያስከትል እንደሚችል ተገለጸ፡፡ የዓለም የምግብ ፕሮግራም እንደገለጸው ከሆነ፣ ተምቹ በአሁን ሰዓት በተለይም በኢትዮጵያ፣ በኬንያ እና ሩዋንዳ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል፡፡ ተምቹ በተለይ በበቆሎ ሰብሎች ላይ ከፍተኛ ጥቃት እያደረሰ እንደሚገኝ የገለፀው የዓለም የምግብ ፕሮግራም፣ በተለይ ለድርቅ አደጋ ለተጋለጡ ሀገራት አስጊ መሆኑን አክሎ ገልጿል፡፡

ከአራት ወራት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ዘልቆ የገባው ይኸው ተምች፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ አርሶ አደር ማሳዎችን ሲያጠቃ ቆይቷል፡፡ አሁን ላይም ቢሆን በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተዘሩ ሰብሎችን በማውደም ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ተምቹ ወደ ኢትዮጵያ ዘልቆ ከገባባት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከ500 ሺህ ሔክታር በላይ ላይ የሚገኝ የበቆሎ ሰብልን እምሽክ አድርጎ አውድሟል፡፡ ሁኔታው በዚህ የሚቀጥል ከሆነ፣ እንደ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ገለጻ፣ በኢትዮጵያ የምግብ እጥረት መከሰቱ አይቀሬ ነው፡፡

በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ሀገራትን በማጥቃት ላይ የሚገኘው ተምቹ፣ ከ25 በላይ በሆኑ የአፍሪካ ሀገራት ላይ ተዛምቶ ጉዳት አድርሷል፡፡ ከምስራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ፣ ኬንያ እና ሩዋንዳ በተምች ወረርሺኝ እየተጠቁ ይገኛሉ፡፡ ተምቹ ወደ አፍሪካ ሲገባ በመጀመሪያ ያጠቃው ናይጄሪያን ሲሆን፣ እስካሁን ድረስም ናይጄሪያ ከ700 ሺህ በላይ የበቆሎ ማሳ በተምች ወድሞባታል፡፡ በኢትዮጵያ ከተከሰተው የድርቅ አደጋ ጋር ተያይዞ፣ ተምቹ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል የጠቆሙት መረጃዎች፣ ድርቁ እና የተምች ወረርሺኙ ተጋግዘው ከፍተኛ የምግብ እጥረት ሊያስከትሉ ይችላሉ ተብሏል፡፡

ይህ በ እንዲህ እንዳለ በአማራ ክልል በተከሰተ የአጣዳፊ ተቅማጥና ትከውት በሽታ የሰዎች ህይወት ማለፉ ተገለጸ፡፡ በሽታው በክልሉ መታየት የጀመረው ካለፈው ሚያዝያ ወር አጋማሽ ጀምሮ ሲሆን፣ ከግንቦት እስከ ሐምሌ ባለው ጊዜ ውስጥ ደግሞ የአራት ሰዎች ህይወት መቀጠፉ ተነግሯል፡፡ ሆኖም እንደ መረጃዎች ገለጻ ከሆነ፣ የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ነው፡፡ የክልሉ መንግስት የሟቾች ቁጥር አራት ብቻ ነው ቢልም፣ አመኔታ ማግኘት አልቻለም፡፡
የበሽታው ወረርሺኝ በኃይል የተስፋፋባቸው የክልሉ አካባቢዎች ሰሜን አቸፈር፣ ፍኖተ ሰላም፣ አንዳስ፣ አቡነ ሃራ ገዳም የፀበል ቦታዎች፣ ጎንጅ እና መሰል ቦታዎች እንደሆኑ የክልሉ የጤና ቢሮ አስታውቋል፡፡ የጤና ቢሮው አክሎም፣ ሰሞኑን ደግሞ በደቡብ ጎንደር በሽታው በመዛመት ላይ እንደሚገኝ የገለጸ ሲሆን፣ በዚሁ አካባቢ ስማዳ በተባለ ወረዳ ከ220 በላይ ሰዎች የበሽታው ሰለባ መሆናቸው ተነግሯል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለአፍሪካ ፈላጭ ቆራጭ ገዢዎች ፍትሕ አይቀሬ ናት

የአማራ ክልል የጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አበባው ገበየሁ ከአሜሪካ ድምጽ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ‹‹ቀደም ሲል ከተነገሩት ወረዳዎች በተጨማሪ ባለፈው አንድ ሣምንት ውስጥ በደቡብ ጎንደር ስማዳ ወረዳ ውስጥ 88 ሰው በአተት ተይዞ የሁለት ሰው ሕይወት አልፏል፡፡›› ብለዋል፡፡ ኃላፊው፣ በሽታው ገና ኮሌራ ይሁን አይሁን እየተጣራ ነው ይበሉ እንጂ፣ ከዚህ ቀደም የወጡ መረጃዎች ግን በአማራ ክልል የኮሌራ ወረርሺኝ መከሰቱን የሚያሳዩ ምልክቶች መታየታቸውን ጠቁመው ነበር፡፡

Share