የሺህ አመት ባሏን በሃያ አመት ውሽማ የለወጠችው ከተማ – ያሬድ ይልማ

ሳህለስላሴ የተባለው በስራ ዘርፋችንም ለልቤም ቢሆን ቅርብ የነበረ ወደጄ፣ የዛሬ ሰባት አመት ገደማ ለትምህርት ከሄደበት አውሮፓ ወደ አገር ቤት ሶስት አመት ሳይሞላው ተመለሰና ፣ እንባ ረጭተን የሸኘነውን ጓደኞቹን አስደነገጠን፡፡ “ምን ሆነህ ነው! ከኤርፖርት እቤት ተመልሰን በወጉ እንባ እና ሲቃችንን ሳናባርድ እንዲ ቀልባችንን የምትገፍፈው? ” ፣ ብለን አምባረቅንበት፡፡ ምክንያቱም የአቶ ሳህለስላሴ ልጅ ፍሬፅዮንን ፣ ሁላችን እጅግ በጣም የምንወደው ልዩ ኢትዮጵያዊ ስለነበር፡ የአሸኛኘቱ ነገር አይረሴ ነበርና ነው፡፡

ያላለቀሰ ፣ ያልተነፋረቀ አልነበረም፡፡ ግን ግን ሶስት አመት ሙሉ የማይደርቅ የሚመስለው፣ ኡመር የተባለው ጓደኛችን ልቅሶ ነበር፡፡ ፍሬፅዮንን ከሸኘንና ኤርፖርት ውስጥ ከገባ ከአራት ሰአት በኋላ ቢራ እየጠጣን ተንሰቅስቆ ሲያለቅስ ያየው፣ ሳምሶን የተባለ ጓደኛችን፣ “ኤጭ በቃ አትነፋረቅብን፣ ምን ቀንተህ ነው እንዴ እንደዚህ እምታላዝነው! በል በቃህ አንደዚህ በማያባራ እንባ አሟርተህበት “ፍሬ” በሄደበት አውሮፕላን ተመልሶ መጥቶ አብራችሁ እንዳታነቡ!” ብሎ አሹፎበት ነበር፡፡ ፍሬን ስናየው የደነገጥነውም ለዚሁ ነበር፡፡

ግን የመጣው እጅግ በጎ ለሆነ ፣ ለዚህ ፅሁፍ መነሻ ለሆነኝና እንደ አስረጂነት የምጠቀምበትን እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ያለውን ማህበራዊ ጥናት ለማካሄድ ነበር፡፡  “ፍሬ” (ቅፅል ስሙ ነው) አውሮፓ ሄዶ ሲያጠናው ለነበረው ትምህርት (International peace, conflict and Justice Management) የመመረቂያ ፅሁፉን መስራት ወስኖ የነበረው “በሃረር ከተማ ልዩ ስሙ “አራተኛ” በተከሰተ ሃይማኖታዊ ምክንያት በነበረው ፀብ ከባድ እልቂትን ሊያመጣ ሲችል ፣ እዛው ከስሞ ስለቀረ ፣ አንድ ልዩ ክስተት” !መነሻ ምክንያቱን እና እንዲሁም – ወዴትም ሳይስፋፋ ድንገት እንዴት ከሰመ? ስለሚለው ዋነኛ ሃቅ ጥናታዊ ድምዳሜ ለመስጠት ነበር፡፡

እንደ ፈረንጅ አቆጣጠር በሁለት ሺህ አራት አመተ ምህረት ገደማ፣ ሃረር አራተኛ በሚባል ሰፈር በጥምቀት በአል ወቅት ፣ በተነሳው በዚሁ ሃይማኖታዊ ምክንያት በነበረው ፀብ ፣ ህይወታቸውን ያጡ የዚያው የሃረር ከተማ ነዋሪ ክርስቲያኖች ነበሩ፡፡ ከነዚያ ከርስቲያኖች ሞት በኋላ በነበሩት ቀናት ውስጥ የሙስሊም “ኢድ” ስለነበር ፣ ከተራ ነዋሪው እስከ መንግስት ድረስ ፣ ተሰራጭቶ የነበረ ፍራቻ ነበር፡፡

ከላይ በተጠቀሰው ክስተት መነሻነት በከፍተኛ  የቂም በቀል ስሜት ፣ ልክ እንዳለፉት የክርስትያኖች እጣፈንታ ፣ በእስልምና እምነት ተከታዮች የከተማዋ ነዋሪዎች ላይ ደግሞ የማይቀር እልቂት ይከሰታል ተብሎ፣ ለሳምንታት ሃረር ከተማ ቀይ መብራት እንደበራባት ከቆየች በኋላ፣ በዚህ ምንያት ነው፣ ይህ ስለተደረገ ነው፣  ተብሎ ለመናገር በማይቻልበት መልኩ፣ ያ ደም ያቃባል የተባል የቂም ደመና የት እንደገባ ሳይታወቅ፣ ድንገት የሽብር እና ስጋት ስሜት የገባበት ጠፍቶ፣ ህይወት ዳግም እንደበፊቷ ቀጠለች፡፡

ይህ ሃይማኖታዊ ፀብ መነሻ ያለው ክስተት፣ በሰሜን ናይጄሪያ አሊያም በኮንጎ ተከስቶ ፣ የሟቾች ቁጥር ምንም ያክል ይሁን ፣ የአንድ ወገን ሃይማኖተኞች በሌሎቹ ወገን ሀይማኖተኞች ተገድለው ቢሆን ኖሮ ?፣ መጨረሻው ምን ይሆን እንደነበር መተንበይ ከባድ የሚሆን አይመስለኝም፡፡ ይህ ፅሁፍም ሆነ የሃረር ከተማ የቅርብ ጊዜ ታሪክ በሌላ አስቀያሚ ቃላት ይፅፍ ነበር፡፡ ግና አገሩ ኢትዮጵያ ሆነና፣ ከተማዋም ሀረር ሆነችና፣ አገር የማጥፋት አቅም ያለውን የእሳት ብልጭታ በእንጭጩ እዛው አዳፍነው፣ ምንም አይነት ሌላ ድራማ ከተማዋ ሳታስተናግድ የሃረር ነዋሪዎች ህይወትን ቀድሞም እንደነበረችው አስቀጠሉ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ትልቁ ችግር ያለው ከውድቀት ከአለመማር እንጅ ከመውደቁ ላይ አይደለም ! - ጠገናው ጎሹ

ይህ በምን ምክንያት ሊሆን ቻለ? ምንድነው የቺ በአራተኛ የተነሳጭውን የእሳት ብልጭታ፣ ወደ ሙሉ እሳትነት፣ ብሎም ከተማ ሊያወድም ወደ ሚችል ነበልባልነት ሳይቀየር እዛው እርጥብ ብርድልብስ ጥሎበት ባጭር የቀጨው? ይህ ነበር የፍሬፅዮን ሳህለሰላሴ ጥናት ዋና ትኩረት! ጥናቱን ሲያጠናቅቅ ታድያ ያገኘው መልስ አስገራሚ ነበር፡፡

በእዚሁ በምስራቅ ኢትዮጵያ ማህበረሰብ ውስጥ ያለ እና በተለይ ሃረር ከተማ ውስጥ አንጋፋነቱ ሺህ የደረሰ፣ በትክክል ለማስቀመጥ፣ የፍሬፅዮንን ጥናት አገላለፅ “ከጠንካራ ጅማት ተሰፍቶ የተሰራ እድሜጠገብ ብርድልብስ” ዋነኛ አስተዋፅኦ እንደተዳፈነ፣ በሃረር ከተማ ሺህ አመት በኖረው በዚህ ውበት ምክንያት ሆኖ አገኘው! በቀላል አማርኛ ለማጠቃለል፡ በሃረር ከተማ ባለው “ልዩ ማህበራዊ እሴት” ምክንያት ነበር፣ ህዝብ ያልተጫረሰው፡፡

ስለዚህ ይህ የፍሬፅዮን የመመረቂያ ፅሁፍ ጥናት ብዙ ሰዎችን፣ ብዙ መዛግብቶችን አሳትፎ የተደረገበት ምክንያት፣ በተሰማራበት የትምህርት ዘርፍ (International peace, conflict and Justice Management) ፣ አለም ከአፍሪካ በተለይ ደግሞ ከኢትዮጵያ ፣ በዚህ ረገድ መማር እንዲችል፣ ይህንን እልቂትን ፣ እንደዋዛ ጭጭ አድርጎ ያስቀረን ጥብቅ ማህበራዊ እሴት፣ ከሃረር ከተማ ጋር እንደ ባሏ ተቆራኝቷት፣ ሃረር ውቧም አቅፋው ተጋብታው ሺህ አመት አብራ የኖረችው፣ ይህ ልዩ የማህበራዊ እሴት ጉልቻ ፣ ምን ላይ ነው የተመሰረተው? የፀኑት እና እንደ ጠንካራ ጅማት እርስ በእርስ ተሳፍተው እንዲኖሩ ያገዙት ብልቶቹ ምን ምን ናቸው? በሚሉ ጥያቄዎች ጠቃሚ ቁምነገሩን መርምሮ ለማወቅ እና ከትቦ መረጃ ለማስቀረት የተደረገ ስለነበር፣ እንደ በረከት የሚያዙትም፣ ወደፊት ይህንን የማህበራዊ እሴት ሁለንተናዊ ህልውና ፀንቶ መቀጠል እንዳይችል ሊያደርጉ የሚችሉ እና የሚያሰጉ ግልፅ በአመክንዮ የተደገፉ ድምዳሜዎች ካሉም እንደ አደጋ ተመድበው፣ የሚያሳይ ሰነድ ለማጠናቀቅ፣ በዚህም አለማቀፋዊ መማሪያ የሚሆን ጭብጥ ማስገኘት፣ ሃረርንም ከውቡ የሺህ አመት ባሏ-“መቻል” ጋር ሌላ ሺህ አመት እንድትኖር አቻ ፋይዳ የሚሰጥ ትልም ይዞ የተፈፀመ ልዩ ፅሁፍ ነበረ፡፡

ይህ ጥናት በውል ያስቀመጣቸው እና ሃረር ለነዋሪዎቿ በሃይማኖታዊ እንዲሁም በማህበራዊ መስተጋብራቸው ውስጥ የፈጠረችላቸውን ልዩ የኑሮ ድባብ በዝርዝር ሲመለከት ካገኛቸው እጅግ ብዙ ፣ እንዲህ አይነት ብጣሽ ፅሁፍ ዳስሶ ሲጨርሳቸው ከማይችላቸው ፣ ሃረር ከተማ ነዋሪዎች መካከል በዘመን ብዛት ከጎለበቱት የማህበራዊ እሴቶች አንዱን ብቻ ነጥለን ብንመለከት የምናገኘው፣ በሃረሪ ቋንቋ “አፎቻ” -(የጓዳ እድር አይነት ህብረት) ወይም “መሪኛች” -(ጓደኛሞች) የሚል ተለዋዋጭ መጠሪያ ያለው እጅግ የሚያስገርም ፣ ከዚያም ከዚህም የተውጣጣን የማህበረሰብ ክፍል ፣ በአንድ ጠንካራ ጅማት አስተሳስሮ የሚያቆራኝ “እሴትን!” ነው፡፡

በአንድ “አፎቻ” ውስጥ የሚጠቃለሉ የህብረተሰብ ክፍል አሊያም ሰፈርተኞች  እራሳቸውን ሲጠሩ ወይ ሰው ሲጠይቁ፣ “እገሌ የነማን አፎቻ ውስጥ ያለ ነው ? ፣ የነማን እድርተኛ ነው ብለው ነው፡፡ እንደ ሃረር ያንዱ ሰፈር ነዋሪ የአንዱ አፎቻ አባል ለመሆን ያለው መስፈርት ሁለት ብቻ ነው፣ እድሜና ፆታ!፡፡ ከዚያ ውጪ ሃይማኖት፣ ብሄር፣ የፖለቲካ አመለካከት፣ የዘፈን ምርጫ እና የሚደግፉትም ሆነ የማይደግፉት የእግርካስ ክለብ አሊያም ሌላ ማህበር ለአፎቻ አባልነት አሉታዊም አዎንታዊም ተፅእኖ የላቸውም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከላይ ሆነን ስናይ (ገለታው ዘለቀ)

በነዚህ የአንድ አፎቻ አባሎች መካከል ባለው የእድሜ ልክ ማህበራዊ አብሮነት፣ ማለትም በሃዘንም በደስታም እያንዳንዳቸውን የህይወታቸውን ምእራፎች፣ ከሁሉ በፊት ቀድመው እየተደራረሱ፣ ሌላውንም አስተባብረው ከአፎቻቸው አባል ባንዱ ቤት ስላለው በረከት ሳቃቸውን አብረው ሲያስካኩና ሲያስተጋቡ፣ ባንፃሩ ደግሞ በአፎቻቸው አባል ባንዱ ቤት ለሚደርሰው ሃዘንም ከልብ ፣ ለልብ ቀድመው እየተደራረሱ፣ ነው ፣ “መሪኛች” ፍሬፅዮን በ“ልዩ ማህበራዊ እሴትነት” ደምድሞ የመደበውን ውቡን የሃረርን የሺህ አመት ፀጋ -“መቻቻልን” የገነቡት፡፡

በዚህም ትስስር ምክንያት እነ ናይጀሪያ ፣ ማይናማር እንዲሁም ኮንጎ ላይ አንድ የአራተኛውን የሚመስል ክስተት በተፈፀመ በቀናት ጊዜ ውስጥ ሲፈፀም አለም ከሰማው በተቃራኒ ፣ ህዝብ እርስ በእርሱ እንዳይጫረስ የምታደርገውን ልዩ ሞራላዊ ስብእና አማርኛ ባንድ ቃል ጠቅልሎ “ይሉኝታ!!!” በሚላት መፍቻ ቃል (Keyword) የሃረር ከተማ ነዋሪዎች እርስ ባንድ ጅማት ታስረዋል፣ ማህበራዊ እሴት ባዳበረው ይሉኝታ፡፡ ስለዚህ እንደተፈራው የአራተኛው የጥምቀት ጣጣ ሌላ የኢድ ቀን መአት ሳያመጣ ባጭሩ፣ ተቀጨ፡፡

ታዲያ በዛው ጥናት ላይ ፍሬፅዮን ፣ ወደፊት ይህ አስገራሚ የማህበራዊ እሴት ጅማት ሳይበጠስ እንዳይቀጥል ሊያደርጉ የሚችሉ፣ አሉታዊ እውነታዎችንም ለማየት ሞክሯል፡፡ እነዚህን የሃረር ከተማ ውስጥ በሚገርም ልዩ ቅመማ የዳበሩና የበለፀጉ ማህበራዊ ትስስሮችን ምን ሊያላላ እና ሊበጥስ የሚችል ግብአት አለ ብሎ ካጠናቸው ነገሮች ውስጥም እንዲሁ በጣት የሚቆጠሩ በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ ተጨባጭ አቅሞችን ጠቅሶ ነው ያለፈው ጥናቱ፡፡ ታዲያ እነዚህ በጣት ከሚቆጠሩቱ የፍሬፅዮን ጥናት ከለያቸውና ፣ ውቡን የሃረርን ማህበራዊ እሴት ሊበጣጥሱ አቅም አላቸው ፣ ብሎ ካረጋገጣቸው ምክንያቶች አንደኛው በተለየ አይን መታየት እንዳለበት መክሮ ያጠቃልላል፡፡ ይህ በተለየ አይን መታየት ያለበት የሃረር ነዋሪ መፃኢ ጠላት፣ “በታሪክ ውስጥ ያለን ቂም በሃረሪ ቋንቋ ውስጥ እንዲካተት የተደረገበት ልማድ እና ለዚህ ልማድ “ከክልልም ሆነ ከፌደራል መንግስት” የተቸረው ፣ “ ታሪካዊ ቂም በቀልን የማበረታታት” ተልእኮ እና ትኩረት ነው!፡፡

ከዘጠኝ አመት በፊት ፣ የሀረር ከተማ ተወላጅ ገጣሚያንና በደራሲያን ማህበር አባሎች አነሳሽነት፣ ከኢትዮጵያ ሚሊኒየም ቀድሞ የጠባውን የሀረር ከተtማን የሺህ አመት በአል በልዩ ሁኔታ ለማክበር ቅን ልቡ እና ፍቅር ሰንቀው ለሄዱ ካዲስ አበባ የተነሱ በጎፈቃደኞች ላይ ከደረሰው አሳፋሪ ከታሪክ የሚነሳ ቂም መርዝ የመጀመሪያ ቡኮ፣ አንደኛ መንገድ፣ መድሃኒያለም ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት እስከ ተተከለው የቂም ሃውልት ድረስ ሀረር፣ ሺህ አመት ተቆራኝታ አቅፋ ያኖረችውን ከልዩነት ይልቅ በፍቅር ላይ የተመሰረተውን መገለጫዋን፣ ልዩነትን በሚያበረታታው፣ አዲስ እና መጤ የሃሳብ ውሽማ ለመቀየር የፈጀባት ጊዜ አጭርነት አስገራሚ ነው፡፡

አንድ ወዳጄ የዛሬ አራ አመት ገደማ፣ በተለያየ ደረጃ የኢትዮጵያ ህዝብ መሪዎችን የሆኑ ሰዎች መሃል ሆኖ ሃረርን ተዘዋውረው ሲመለከቱ ያጀበ ወዳጄ በዚህ ሃረር ከተማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፣ እንደ ኩታ ተሰፍቶላት የለበሰችውን መጤ ቂመኝነት፣ በምሬት ሰነግረኝ እንዲህ ነበር ያለኝ፡፡ ለፍቅር ሲል ታላቋን ሃገሩን ፈረንሳይን ከድቶ ፣ አልፈልግሺም ብሎ የከተመባትን የባለቅኔውን አርተር (ራምባዱ) ራምቦ  መኖሪያ ቤት በአንድ ጎኑ ቀይ ምንጣፍ ተሰቅሎ የቂም ታሪክ የሚነገርበት ስፍራ እስኪሆን ድረስ የሃረር ተጨባጭ ሁኔታ እንዲቀየር ከተማዋ በማይበጅ እና ጠንቅ በሆነ መንገድ ፣ ሆን ተብሎ እየተመራች ነው ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በተለይ ለኦሮሞ ልሂቃን የተላከ ማስታወሻ (ከነፃነት ዘለቀ)

ለዚህ ማሳያ እንዲሆን የነገረኝ ነገረ በተለይ ልብ የሚሰብር ነበር፡፡ የአርተር ራምቦ መኖሪያ ቤትን ሊጎበኝ ከነበረው ትልቅ የመንግስት ሰው ጋር ሆነው በአጀብ እየጎበኙ፣ የሚያስጎበኘው ሰው በአደሬ ባህል፣ “ነደባ” የሚባል ቤት ውስጥ ስለሚነጠፍ፣ “ከሊም” (ቀይ ምንጣፍ) እና ከሱ ጋር ስለሚያያዘው ከሚኒሊክ ጦር ጋር ስለተደረገው የጨለንቆው ጦርነት ይናገር ነበር አስጎብኚው፡፡ “ይህ ቀይ ምንጣፍ ምንም ያክል ደሃ ብትሆን የአደሬ ቤት ሰው በዘካ ገንዘብ ሳይቀር እንድትገዛው አዋጥቶ፣ ይሰጥህና ትገዛለህ ምክንያቱም፣ ፋይዳው ለህዝባችን ወሳኝ ስለሆነ” አለ ጋይዱ፣ ቀጠለና ፣ ይህ ምንጣፍ በጨለንቆው የአሚረ አብዱላሂ ጦር እና በምኒሊክ ጦር መካከል በተደረገ ጊዜ፣ ህይወታቸው ያለፈውን ሰባት መቶ ሙሽሮች ፣ ቀዩን ምንጣፍ እያዩ ልጆች እንዲያድጉ የምናስታውስበት ነው”- እነዛ ሙሽሮች በዛ ጦርነት በማለቃቸው ምክንያት- “ነመ ሰበ ቢጩ” (አናሳ ህዝብ ) ያለው ብሄር ሆነናል፡፡ “አሁንማ ለስራ ጉዳይ የመጣ ቻይና እንኳን በቁጥር ከአደሬ ይበልጠናል!- ለዚህ ተጠያቂው ምኒሊክ ስለሆነ ቀዩ ምንጣፍ ወሳኝ ነው” አለ ጋይዱ ሳቅ ተከተለው የጋይዱን ንግግር አለኝ ወዳጄ!

ይህንን ከቅርብ ግዜ ወዲህ ወደ ሃረር የሚመጣ ጎብኚ ሳይቀር እንዲሰማ የሚነገረውን ታሪክ ሲናገር ጋይዱ ፣ ደጋግሞ “አህ-መራ- አህ-መራ” እያለ ይጠራ ነበር፣ በዚህ ጊዜ ለጉብኝት የመጣው ሰው ምን ማለት ነው “አህ-መራ” ብሎ ሲጠይቅ፣ የሃረሪ ቋንቋ ተናጋሪ የአማራ ብሄር ተወላጆችን ለመጥራት “አማሮችን” የሚጠራበት ስም አጠራር እንደሆነ፣ እና ትርጓሜ እንዳለው ተነገረው፡፡ “አህ-መራ” የሚለው ቀጥተኛ ትርጉምም፣ “ቁጭት ሳይ” የሚል ትርጉም እንዳለው አስጎብኚው ሲናገር፣ ስፍራው በብዙ ሰው ሳቅ የአርተር ራምባዱ ግቢ ተናጋ፡፡

እውነት ይህ የሚያስለቅስ እንጂ የሚያስቅ እውነት ሆኖ ነው! ወዳጄ እንደዛን ቀን ሃረር ላይ እየተዘራ ያለውን ፣ የቂም እና በቀል አስተምህሮት፣ ለአንድም ደቂቃ አስቦት ስለማያውቅ እንዴት እንዳዘነ ያስዳኝ፣ ልብ በሚነካ መልኩ ነበር፡፡ ጎብኚ ሳይቀር እንዲረዳው በኩራት የሚነገር ሰሞኑን ሃረር የገባው አዲስ የቂም ትምህርት ማለተ ይሄ ነው፡፡ መድሃኒአለም ፊት ለፊት ካለው ሃውልት እኩል በክፉ መረጃ ትውልድን መመረዝ ማለት እንዲህ ነው እንግዲህ፡፡ ዩኔስኮ የመቻቻል መዲና ብሎ እውቅና የሰጣት ሃረር፣ ያቺኛዋ ነበረች፡፡ ያቺ ሺ አመት ከጥላቻ እና ልዩነት ይልቅ የፍቅር ቋንቋ ለመላው ኢትየጵያ በተጨባጭ ስታሳይ የኖረችው፣ ሆደ ሰፊዋ ሀረር ነበረች፣ የሺህ አመት ውቢቷ!

ዛሬ ግን ሃረር ያ እውቅናውን ያገኘችበትን ውቡን ማህበራዊ እሴቶቿ በሚያሳዝን ክፋት በሚመሩ ፊት አውራሪዎች እንድትጥል ተገዳ ፣ ከዛ ተምሳሌትነት ከተገባው፣ የከተማ ባህሪዋ ጎድላለች፣ ለብዙዎች ሳይሆን ለጥቂቶች ብቻ እንድትሆን፣ ልዩነትን ረስታ፣ ፍቅርን እያስቀደመች ትሄድበት ከነበረው ስሪቷ በተቃራኒ፣ ቂም እና ክፉ ታሪክን አነፍንፋ የምታፋፋ ፣ የሺህ አመት ባሏን በሃያ አመት ውሽማ የለወጠች ከተማ ሆናለች!

ልብ ያለው ልብ ይበል-ቂም በቀል ክፉ ነውና ሁላችንም ልናወግዘው ይገባል፣ ለኢትዮጵያ አይበጃትምና!!!

ኢትዮጵያዊነት ይለምልም!

ያሬድ ይልማ

 

 

Share