“ይህ ዋዛና ፈዛዛ ያናፈዘው ትውልድ ደግሞ ከንቱ ነገሮችን ሁሉ ሳይመረምር ይቀበላል፡፡ ብዙዎች የዚህ ትውልድ አባል በመሆናቸው ደስተኛ አይደሉም፡፡ ህሊናውን በሜዞ የሚሸጥ፣በኩርማን እንጀራ የሚሸነግል በፍርፋሪ የሚደልል ትውልድ ተፈጥሯል፡፡ ይህን ትውልድ ያለ ግብሩ ግብር ያለ ጠባዩ ጠባይ ሰጥተው የፈጠሩት ፖለቲከኞችና አንዳንድ አድርባዮች እንደፈለጉት እየነዱት ይገኛሉ፡፡ፍጡሩም ፈጣሪውን መስሏል፡፡” (ራማቶሓራ ገጽ 80)
……………//……………..
የሰው ልጅ ለመሰሉ ሎሌ ሆኖ የሚያድርበት የተለያዩ ምክንያቶች አሉ ፣የሎሌነት ሁኔታውም እንደ ምክንያቱ ይለያያል፡፡ባለሥልጣን ሆኖ ለባለሥልጣን ሎሌ የሚሆን ነበረ አለ ወደፊትም ይኖራል፤አሁንማ ነገር ብሶ ውርደት ተባባብሶ ጠቅላይ ምኒስትርም ተኩኖ በሎሌነት መኖርን እያየን ነው፡፡ አማራጭ አጥቶ፣ ልኑር ብሎ ተቸግሮ በሎሌነት የሚያድረው እሱ ቀን ሲወጣለት ሁኔታዎች ሲመቻቹለት ወደ እራሱ የሚመለስ በመሆኑ ጌታው ሲያስነጥሰው መሀረብ ለማቅረብ አይዳዳውም፣ከሎሌዎቹ በላይ ሎሌ ለመሆን እዩኝ እዩኝ አይልም፣ማደሪያ ስራውን ያውቃል ያንን ተጠንቅቆ ይሰራል፡፡
በተቃራኒው በራሱ መኖር እየቻለ ወይ ተፈጥሮ ሆኖበት ወይንም በሎሌነት አገኘዋለሁ ብሎ የሚያስበው ጥቅም ልቆ ታይቶት በሎሌነት ያደረ ግን ከሎሌዎቹ በላይ ልቆ በመታየት የጌታውን ጎሽታ ለማግኘት፣ እንዲያም ሲል በግብርዎም በወንበርዎም አይርሱኝ ለማለት የማይሆነው ነገር የማይፈጽመው ድርጊት አይኖርም፡፡
ታዲያ እንዲህ አይነቱ ክብረ ቢስ ተፈጥሮ የበደለችው ሰው ሲያጋጥመው የሀገሬ ሰው “ እሱም አይደል ልቡ ነው እውሩ፣ ጥንድ በሬ እያለው ለጌታ ማደሩ” ይለዋል ይልለታል፡፡ ልብ ከታወረ ሊሆን የሚችለውን አስቡት፡፡ በወያኔም ሆነ በተቀዋሚው ሰፈር የዚህ አይነት ብዙ ሰዎችን እናያለን እንሰማለን፡፡ አንዳንዶች “እኔው በገዛ እጄ እያልኩ ወረደ ወረድ እመቤቱን ልቤን አደረኩት ገረድ” እንዳለችው ሴትዮ ከውርደቱ ሰፈር፣ ከሎሌነት አደሩ ምግባር በመገኘታቸው ልባቸው ምነው አለ ቦታየ ብሎ ሲጠይቃቸው፣ ህሊናቸው ሲጸየፋቸው ውርደቱ ተስምቶአቸው በግዜ ከሎሌነት ራሳቸውን በማላቀቅ የቻሉት በንስሀ ታጥበው፣ በይቅርታ ከህዝብ ታርቀው በአደባባይ በኩራት ሲሄዱ እያየናቸው ሲናገሩ እየሰማናቸው ነው፡፡ ለንሰሀውም ሆነ ለይቅርታው ያልበቁት ወይንም ለዚህ ወኔ ያጡት ደግሞ አንገታቸውን ደፍተው ድምጻቸውን አጥፍተው ይኖራሉ፡፡ በሎሌነት ላደረሱት ጥፋት ንስሀ ባይገቡም፣ በይቅርታ ከህዝብ ባይታረቁም ቢያንስ ከሎሌነት ተገላግለዋልና የተሟላም ባይሆን ግማሽ እፎይታ ይሰማቸዋል፡፡
በተለይ ሥልጣን ፈልገው፣ ሳይወጡ ሳይወርዱ ላብ ሳያፈሱ መከበር ከጅለው፣ወይንም ዘር ቆጥረው ወዘተ ሎሌነት የሚገቡ ወይንም ለሎሌነት ደጅ የሚጠኑ ሰዎች ምግባራቸው ሲታይ ህሊና የሚባለውን ነገር አውልቀው የጣሉ ነው የሚመስለው፡፡ ጌቶቹን ያስደስታቸዋል በዚህም ትንሽ ሥልጣን ወይንም ትንሽ ዳረጎት አገኛለሁ ብለው ካሰቡ ከውሻ ብሰው ለንክሻ ይሰለፋሉ፤ከበቀቀን በልጠው የሰሙትን ሲደግሙ እንደውም አግንነውና አጉልተው ሲናገሩ ይውላሉ፣የጌቶች ጠላቶች ናቸው ያሉዋቸውን ወይንም ጌቶች ክፉ ፊት ሲያሳዩዋቸው ያዩትን ወይንም በጌቶች አፍ በክፉ የሚነሱትን ሰዎች ለመዝለፍ ለመስደብ ስም ለማጥፋት ይሉኝታ፣ ባህል ፣እምነት፣ ፈሪሀ እግዚአብሄር ወዘተ የሚባል ነገር አይገድባቸውም፡፡
በ1985/86 ዓም ነው ወያኔ ሰራተኛውን እየበተነ ሴፍቲኔት በሚባል ከየት መጣሽነቱ በማይታወቅ ሁኔታ እያደራጀ ሳለ የወቅቱ ጠቅላይ ምስትር ታምራት ላይኔ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው ከዚህ የተሻለ አማራጭ በማጣታችን በሁኔተዎች ተገደን የገባንበት ነው በማለት ይመልሳሉ( ከጊዜው ርዝመት አንጻር በትክክል አልጠቅሼ ይሆናል፣ ከዛ ወዲህ አቶ ታምራት አንኳዋን ስንቱን ሆነዋል)
በወቅቱ የትራንስፖርትና መገናኛ ኢንደሰትሪ ፌዴሪሽን የሰራተኛ ማህበር ሊቀመንበር የነበሩት ሰው ( ባልሳሳት መኮንን ኃለስላሴ ይመስለኛል ስማቸው) የአጠቃላዩ የኢሰማአኮ ፕሬዝዳንት ለመሆን በመመኘት ሎሌነታቸውን አሳምረው፣ ከፍላጎታቸው ለመድረስ የጀመሩት ተግባር ዙሪያ ገባውን ማየትም መስማትም ነስቷቸው አቶ ታምራት የተናገሩትን እንኳን ባለማገናዘብ ሴፍቲኔት ሰራተኛው ለአመታት ሲመኘውና በጉጉት ሲጠብቀው የነበረ ነው በማለት ተናገሩ፡፡ የሚያሳዝነው እንደህ ቀለው የተመኙትን አለማግኘታቸው ነው፡፡
አንዳንዴ የፈጣሪ ስራ ይገርማል አግራሞታችን የአንድ ሳምንት፣ አስተውሎታችን ከወየው ጉድ አልፎ ለመማር የሚያበቃን አልሆነም እንጂ፡፡ እንዲያ ከጳጳሱ ቄሱ ይሉ አይት ሆነወ ሰው ምን ይለኛል እንኳን ሳይሉ የቀላመዱ ሰው የተመኙትን ሳያገኙ ለቀላመዱት ንስሀ ሳይገቡ በአጭር ግዜ ወደ ዛኛው ዓለም ሄዱ፣ነብሳቸውን ይማር ይባል ይሆን!
በ1993 ዓ.ም የህውሀት ክፍፍል ወቅት ከሁለቱም ሰፈር በተለይ ሪፖርተር መጽሄትና ጋዜጣ ላይ ብዙ ይጻፍ ነበር፡፡አቶ መዝሙር ፈንቴ ከየትኛው ጎራ ሆነው እንደጻፉት ባልረዳም “ኢህአዴግ አዝማች ብቻ ሳይሆን ዘማችም የሚዘመትበትም ይሁን” የሚል ርዕስ በሰጡት አንድ ጽሁፋቸው ውስጥ በፖለቲካው ሰፈር ያለውን ሎሌነት ቁልጭ እድርገው ነበር ያሳዩት፡፡
አንድ አንቀጽ ልጥቀስ፡፡ “በየስብሰባው ምላሳቸውን አርዘመው አድርባይነታቸውን የሚለፍፉ፣ ንጹሀንን አጥላልተውና አዋርደው ‹የታጋይነት ጥንካሬያቸውን› ሊያስመሰክሩ የሚፈልጉ አፈ ጮሌዎች ታማኝና ጠንካራ ተደረገው ይቆጠራሉ፡፡ አለቆቻቸውን እንደ ጣኦት የሚያመልኩ፣ እንደ ፅላት የሚሳለሙ፣ የግል ጉዳያቸውን በተላላኪነት የሚያስፈጽሙ፣ የፖለቲካ ኩሊዎች ይሾማሉ፤ ይሸለማሉ፡፡ ለቅርብ አለቃ ማደግደግ፣ ወሬ ማቀበል፣ ጆሮ መጥባት፣ እንደ እጅ መንሻነት እየተቆጠረ ያሳድጋል ያስመነድጋል፣”ነበር ያሉት ፡፡ በዚህ መልኩ ያደገ የተመነደገ ሰው ዴሞክራሲን ሲያሰፍን የህግ የበላይነትን አክብሮ ሲያስከብር፣ ለዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ዘብ ሲቆም ለእኩል የሀብት ተጠቃሚነት ሲጥር ይታያችሁ፡፡ በተቀዋሚው ጎራ ከሆነ ደግሞ ለነጻነት በጽናት ሲቆም፣ለለውጥ ከምር ሲታገል፣ ቃል የእምነት እዳ ሲሆንበት ይታያችሁ፡፡
በስልጣን ላይ ያሉ ጌቶችም ሆኑ የፓርቲ ወንበር የሚይዙ ሰዎችም የወዛ አይደሉም፣ከፊት ወጥተውም ይሁን ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው እንዳሻቸው ያውም እንደ ሰው ሳይሆን በርቀት መቆጣጠሪያ መሳሪያ እንደሚታዘዝ ሰው ሰራሽ ሰው የሚታዘዙ ሰዎችን አያጡም፡፡ዙሪያቸውን በሎሌዎች ይከበቡና መሬት ላይ ያለው እውነታ አይታያቸውም፡፡
ሎሌነት በተቀዋሚው መንደር ፣
በ2001 ዓ.ም ሊቀመንበሩን ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን በሁለተኛ ግዜ እስር ያጣው ገና በሁለት እግሩ መቆም ቀርቶ ዳዴ ማለት ያልጀመረው አንድነት መታመስ ሲጀምር አለመስማማቱን በውይይት ችግሩን በፓርቲው ህገ ደንብ ለመፍታት ሲሞከረር ወንበሩን በያዙት ሰዎች ዙሪያ ተኮልኩለው ያስቸገሩትን ሰዎች ፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያም ሎሌዎች በማለታቸው በውስጥም በውጪም ያሉ ነገርን ከስሩ ውሀን ከጥሩ የሚለውን ብሂል የማያውቁ ላይ ላዩና ጋላቢዎች ብዙ ተንጫጭተው ነበር፡፡ ብዙም ውሎ ሳያድር ሎሌ ከተባሉት አንዳንዶቹን በአካል አግኝቼአቸው ስናወጋ ያኔ የሚባለው ሁሉ አይታየንም፣ እውነትም አይመስለንም ነበር፣ለዚህም ነው እነ ፕ/ር መስፍንን እንደ ጠላት እናያቸው የነበረው፣ነገሩ የተገለጠልን ዘግይቶ ነገሮች ከተበላሹ በኋላ ነው ነበር ያሉኝ፡፡ እንደነገሩኝ ነፋስ አይንካቸው ሲሉዋቸው ለነበሩት ሰዎች ተቀዋሚ ሆነው ነው ያገኘኋቸው፡፡ይህን ያነሳሁት ስለ አንድነት ላወራ አይደለም፣ለማሳየነት እንጂ፡፡
ዛሬም እነዚህን መሰሎች የሚነገራቸውን ማገናዘብ፣ የሚያዩትን መረዳት የቸገራቸው ጌቶቻቸው የሚሉትን ብቻ እየተቀበሉ የሚያስተጋቡ አንዳንዴም ከጌቶቻቸው አብልጠው የሚጮሁ በተለያየ ቦታና አጋጣሚ እያየን እየሰማን ነው፡፡ እግዚአብሄር የሰውን ልጅ በአምሳሉ ፈጠረው ሲባል ወርድና ቁመት መልክና ሰውነት አመሳስሎ ማለት አይደለም፡፡ የእግዚአብሄርን ቁመና ማን ያውቅና፡፡ ዋናው ቁም ነገር የሚያስብ አንስሳ አድርጎ ስለ ፈጠረው ይመስለኛል፡፡
ታዲያ የሰው ልጅ ወይ ስልጣን አማሎት ወይ ጥቅም ደልሎት ወይ የዘር ፍቅር አቆራኝቶት ይህን ፈጣሪ በቸርነቱ የለገሰውን የማስተዋል ችሮታ ወደ ጎን ብሎና ለሰው ልጅ በተለየ የተሰጠውን ህሊን አውልቆ ጥሎ ከእውነት ተጣልቶ በዚሁ ተግባሩ ሆዱን ሞልቶ ሲኖር እንደምን አለማዊ ደስታ ሊሰማው እንደሚችል የሚያውቀው የሆነው ብቻ ነው፡፡
በሌነት ያደሩ ሰዎች ለሚናገሩትም ሆነ ለሚጽፉት አይደለም ማስረጃ መረጃ ለማቅረብ እንኳን አይጨነቁም፡፣ከድርጊታቸው መረዳት እንደሚቻለው ዓላማቸውም ሆነ ግባቸው ጌቶቻቸውን ማስደሰትና የሚገኘውን ማግኘት የሚመኙትን መጠበቅ በመሆኑ ጌቶቻቸውን የሚያሞግሱ የሚያወድሱበትን ጠላት የሚሉትን የሚሰድቡ የሚዘልፉበትን ቃላት ከየት እንዲሚያመጡት ፈጣሪ ይወቀው፡፡ በሬ ወለደ ብለው ቢዋሹ ቅንጣት እፍረትም ሀፍረትም አይሰማቸውም፡፡በዚህ ደረጃ የተባሉ የተጻፉ ነገሮችን በማሳያነት ማቅርብ የእነርሱኑ ባህርይ መጋራት ይሆናልና ደግሞም ማህበራዊ መገናኛዎችን የሚከታተል ሁሉ የሚያውቀው ነውና አልሞክራም፡፡
እነዚህ ሰዎች በሎሌነት ያሳደራቸው ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን ለጌቶቻውም ምን አልባት የድርጅት አባል ወይም ደጋፊም ከሆኑ ለድርጅቱም አይበጁም፡፡ ሰው መሻሻል የሚችለው ስህተቱን ሲረዳ ድክመቱን ሲያውቅ ነው፡፡ ድርጅትም እንደዚሁ፡፡ ሎሌዎች ግን ጌቶቻቸውን ማሞገስ የተለየ ሀሳብ የሚያነሳውን መዝለፍ መፈረጅ መወንጀል ስለሆነ ስራቸው ግለሰቡም ሆነ ድርጅቱ የሌለውን አለኝ፣ ያልሆነውን ነኝ እያለ ከእነ ስህተቱ አይደለም ከእነ ግዙፍ ድክመቱ ወደ ውድቀት እንዲጓዝ ነው የሚረዱት፡፡ሎሌነት አመላቸው ነውና የወደቀውን ሸኚተው የሞተውን በወጉም ባይሆን ቀብረው ሌላ ጌታ ማፈላለጉን ያውቁበታል፡፡ ለባለቤቱም በዙሪያው ላሉም ሳይታወቅ ለሚጠናወተወና መፍትሄ ለሌለው የአንባገነንበት በሽታ እየተዳረጉ ለብዙ ሲታሰቡ በአጭር የተቀጩ ብዙዎች ለዚህ የበቁት ለምን እንዴት መቼና ወዴት ብለው በማይጠይቁ ሎሌዎች በመከበባቸው ነው፡፡
የሚበጀው፡
በተለይ የድርጅት አባላት (የፖለቲካም የሌላውም) አባል እንጂ ተከታይ አትሁኑ፡፡ድርጅታችሁ ቆሜለታለሁ የሚለውን ዓላማ አጢኑ እንጂ የመሪዎች ምርኮኛ አትሁኑ፡፡ ጣታችሁን ወደ ሌላ ከመቀሰራችሁ በፊት ራሳችሁን እዩ፣ ድርጅታችሁን መርምሩ፣ መሪዎቻችሁን እወቁ፡፡ ከአንድ ወገን ብቻ ሰምታችሁ አይታችሁ ወይንም አንብባችሁ ለጩኸት አትቸኩሉ፣አንገት የተሰራው አዙሮ ለማየት ነው ይባላልና ዙሪያችሁን ቃኙ፣ተቃራኒ አስተሳሰቦችን መዝኑ፣ እውነትን ፈልጉ፡፤እንጂማ እንደገደል ማሚቶ ወይ እንደ ድምጽ መቅጃ መሳሪያ የተነገራችሁን ብቻ የምትደግሙ አትሁኑ፡፡ ሙግት ክርክራችሁ ለመሸናነፍ ሳይሆን ለጋራ አሸናፊነት ይሁን፣ በመረጃ ማስረዳትን በማስረጃ መሞገትን ባህል አድርጉት፡፡ይህን ማድረግ የሚቻለው ግን ከሎሌነት ተላቆ በራስ በመቆም ህሊናን ማሰራት ሲቻል ነው፡፡
ሌሎቹም ፣ እዩኝ እዩኝ ባዮችን ጠብቋቸው ተጠንቀቋቸው፤እነርሱ ለሀገራዊ ጠቀሜታ ብለው ሳይሆን ለመታየት የሚያደርጉትን መወራጨት ባለመረዳት አድናቂም አድማቂም ሆናችሁ በመሰለፍ ሳታውቁት የሎሌዎች ሎሌ ላለመሆን ንቁ፣ሎሌ አደሩንና ሰርቶ አደሩን፣ ነጋዴውንና ታጋዩን ለዩ፣ ይህን በማድረግ እነርሱንም መታደግ ይቻል ይሆናል፣ከሎሌነት ነጻ ማውጣት፡፡ ችግር የሆነው ለምን አንዴት መቼ ማን የት ወዘተ ብሎ የሚጠይቀው ቁጥሩ አንሶ የሰማውን እንዳለ ተቀብሎ የሚያናፍሰው መብለጡ ነው፡፡የወሬ ገበያ መድራት የአሉባልታ መስፋፋት ወዘተ ደግሞ ለሎሌዎች ምቹ ነው፡፡ በአንጻሩ አብዛኛው ሰው እውነትን ፍለጋ ላይ ቢሰማራ ለራሱም በእውነት መሰረት ላይ መቆም ቢችል ሎሌውም አሉባልተኛውም አውርቶ አደሩም ወዘተ ባልተስፋፋ ነበር፡፡ወሬ ለኢትዮጵያ ምንም አልጠቀማት የሚል ዘፈን ነበር የሚያስታውስ ካለ ጀባ ይበለን!