ለክርስትና እምነት ዋነኛ መሰረት እና መመሪያ በሆነው መፀሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት አራት የአዲስኪዳን መፀሐፍት ፣ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን የወንጌልን ብርሃን ()ያሰፈሩት አራቱ የክርስቶስ ደቀመዝሙሮች ማቴዎስ ሉቃስ ማርቆስ እና ዮሐንስ፣ ክርስቶስ የክርስትና መሰረት የሆነባቸውን ዋነኛ አስተምህሮቶች እንዲሁም ፣ ህብረቱንና የመስቀል ላይ መከራውን ከዚያም ሞትን ድል ነስቶ መነሳቱነ በተለያየ መንገድ ገልፀዋል፡፡
ከነዚህ የክርስቶስ ደቀመዝሙሮች መሃከል ግን የጊዜ ድርብርብ እና ቆይታ ይበልጥ የቃላቶቹን ዋጋ ከፍ እንድናደርጋቸው የሚያስገድደን ወንጌላዊ ዮሐንስ ነው፡፡ በዮሐንስ ወንጌል መጀመረያ ላይ ያሉ ፣ አይምሮ ሲለጠጥ እና ሲመትር ቢውል ውል ሊያገኝላቸው የማይችላቸውን ፣ የመለኮትን ከጊዜ ቀድሞ የነበረ ህልውና ይህች አለም እስተፈጠረችበት ፣ ከዚያም እስከ ክርስቶስ ወደ ምድረ መምጣት ድረሰ ያለውን ከየትየለሌ ተነስቶ የሚመጣ እውነታ፣ የወንጌላዊው ዮሐንስ መፀሐፍ እጅግ በሚያስገርም የቋንቋ ብቃት እንዲሁም የአረፍተ ነገር ምጣኔ መለኮታዊውን እውነታ፣ ለእንደኔ አይነቱ ተራ አእምሮም ጭምር ቁልጭ እንዲል ያደረገ ታላቅ እና ቅዱስ መንፈሳዊ አባት ነው፡፡ ይህንን የዮሐንስ ወንጌልን የመጀመሪያ ክፍል ስናነብ ከላይ የተገለፀውን የዮሐንስን አገላለፅ በውል መረዳት ይቻላል፡፡ “በመጀመሪያ ቃል ነበረ፣ ቃልም በእግዚያብሄር ዘንድ ነበረ፣ ቃልም እግዚያብሄር ነበረ፣ ከሆነው ሁሉ አንዳችም ያለእርሱ አልሆነም፣……. እያለ ከየትየለሌ የሚነሳን የአምላክን ህልውና እስተ ብርሃን ፍጥረት ፣ እንዲያ እያለ ወንጌልን የገለጠበት ነው፡፡
ኢትዮጵያዊው እና ከዛሬ ዘጠኝ መቶ አመት በፊት የኖረው “ቅዱስ ላሊበላም” የወንጌላዊውን ምሳሌ ተከትሎ እነዚያን አለም በመፀሐፍ ቅዱስ የወንጌል ክፍሎች በቃላት ታትመው ያነበባቸውን ፣ ዋነኛ በአዲስኪዳን የክርስትና አእማድ የሆኑ እውነታዎችን ፣ በአለት ላይ ጠርቦ የፃፈው ሌላኛው ቅዱስ ንጉስ ፣ ሌላ ያይደለ ኢትዮጵያዊ ላሊበላ ነው፡፡ በንደዚህ ያሉ አባቶች ምክንያት ወንጌል በባህር ተወርውሮ፣ በእሳት ተቃጥሎ፣ አሊያም አማኞቹ ተገድለው ላይጠፋ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በቅዱስ ላሊበላ አማካኝነት እዚሁ ከላስታ ተራሮች ባንዷ ፣ በገዛ በራሱ በንጉሱ ስም ተሰይማ ላሊበላ በተባለችው ስፍራ፣ ልክ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ ቃላት መለኮታዊ ሃይልን በሚያሳይ መልኩ ፣ በቅዱስ ላሊበላ የእጅ መጥረቢያ የአዲስ ኪዳን ዋነኛ የወንጌል ክንዋኔዎች በዝርዝር አለት ላይ እንደተፃፉ አሉ፡፡*
ስለላሊበላ ቤተክርስቲያናት አሰራር እና ስለ አጠቃላይ የስነ-ህንፃ ዝርዝር ተረክ የማቅረብ እቅድ የለውም ይኼ አጭር ፅሁፍ፡፡ የዚህ ፅሁፍ ትኩረት በ ላሊበላ በአለት ላይ ከተፃፉት የወንጌል እውነታዎች ውስጥ አንዱን ላይ ብቻ ብርሃን ለማጉላት የሚሞክር ሲሆን፣ ይህም የፅሁፉ ትኩረት የሆነው ቅዱስ ላሊበላ ከዘጠኝ መቶ አመት በፊት ለክርስትና ባለው ከሁሉ የጎላ ዋጋ ምክንያት ፣ በአለት ጠርቦ ስለፃፈው ፣ ልክ እንደ አራቱ ወንጌላት ሁሉ ለኢትዮጵዊው ንጉስም የመጨረሻው የሆነውን የመስቀል ላይ ስራን ፣ የክርስቶስን ቤዛነት “ቤዛ ኩሉ” በሚጮህ በሚጣራ መልኩ የቀረፀበትን አስገራሚ ሃቅ እንዳለ ለማሳየት ነው፡፡
በአራቱም አቅጣጫ ከበዋት በዙሪያዋ ያሉትን እጅግ እጅግ ፣ የሚያስገርሙ የስፍራ ጥጎች ስም እየጠራን ብቻ ስንገረም ልንውል እንችላለን፡፡ ነገር ግን በነዚህ በአራቱም አቅጣጫ አጥረው የሸሸጓት እመሃል እምብርታቸወ ላይ ያለችው ከተማ እንዲሁም በገፀ ሆዷ አጭቃ የያዘቻቸው ፣ ጉልህ የወንጌል እውነታዎች እስከነ አቀማመጧ ድረስ ታትመውባት ያለችው ትንሷ መንደር ቃላት በበቂ ሃይል የማይገልፃት የኢትዮጵያና የአለም እንቁ ናት “ላሊበላ”፡፡
ለቅኝት ያክል፣ በላሊበላ ከተማ ዙሪያ ያሉ ምንም አይነት ቃላት አጋንነው ሊገልጧቸው ከማይችሏቸው መካከል ዋና ዋናዎቹን በወፍበረር እንጥቀስ ብንል መልክአምድር፣ አየርንብረት፣ እና የነዋሪ ልዩ ውበት ተዋህዶ የሚገኝባቸው ለንፅፅር የሚከብዱ ውብ ስፍራዎች የተቸመቸሙበት ነው፡፡ ምትሃተኛ የተራራ ሰንሰለት ላይ ካለችው “አሸተን” ስንነሳ ፣ በተጠጓት ቁጥር ነብስያን እየሰለበ ፀጥ የሚያሰኝ ውበት የተጎናፀፈችውን፣ በተራራ ጫፍ ላይ የከተመችውን ታሪከኛዋን የጥንት አምባ ፣ “አሸተን ማርያምን” ወይስ እታች ወርጄ የታላቁን አባት ናኩቶላብን የእጅስራ አይተው አጀብ ሊሉ ይችላሉ፣ አይ አርዝሜ ልዝለቅ ቢሉ ካሸተን ማርያም ፣ በትይዩ ካለችው “ከልዳት ማርያም” ፣ እና “መኪና መድሃኒአለም” ተቀምጠው አለምን ሊረሱ በአንድዬ ግርማው ሊወረሱ ከበረከቱም ሊቋደሱ ይችላሉ፡፡
ያንኑ መንገድ ለሚከተል “በጠልፈጢት እና ተልባ እርሻ” አሻግረው ከፍ እያሉ የሚሄዱ የእግር እና የበቅሎ መንገዶች ይራዳሉ፣ መድረሻ የሚሆነው ታዲያ ባለዋሻው ንግርት የሆነ ገዳም ፣ በአራት ሺህ አንድ መቶ ሜትር ከፍታ ላይ ከተንጣለለው ከውቡ ካአቡነዮሴፍ (ሪምገደል) አናት ያደርሳል፡፡ ብርቱ ለሆነ እና አይ ዞሬ ልመለስ ቢሉ የምድር የደረት ፀጉሯ በአንድዬ በራሱ ተልጎ የትየለሌ በሚመስል ስፋት ተገልጦ፣ ሲያዩ ዝም የሚያሰኝ ፣ በሶስት ሺህ ሜትር ከፍታ ላይ ለዘመናት የላስታ ኩሩ ህዝብን ያሳደረ ቀዬ በዚህም አለ፣ ሀሙስ እግር ለጣለው ነብስን የሚያረሰረስ ኮረፌ እየተገባበዙ በሚገበያዩበት፣ ሃሙሲት በሚባል የደገኞች መንደር ፣ ካሻዎት በእግሮ አሊያም በፈረስ እና በበቅሎ የሚያስፎንኑ ልዩ የላስታ ውበቶች ያሉት በዚሁ በላሊበላ ዙሪያ ነው፡፡
አዳር “ባአቡነዮሴፍ” የደስታው ብዛት ለአንዷ ነብሴ ያሰጋኛል ቢሉ ፣ መመለሻ የሚሆን መንገድ አለ ፣ ችግሩ ዝምብሎ የሚባል ስፍራ አለመኖሩ ብቻ ነው፣ “ቀንቀኒት ሚካኤልን” አይተው ተገርመው ተደምመው ሳይጨርሱ፣ “ገነተ ማርያምን” ያገኛሉ፣ ተመልሼ ከፍ ልበል ቢሉ፣ የተአምራት መናኻሪያ፣ ገላ ጅማት ስጋ አጥንታቸው ላይበሰብስ ኪዳናቸው የተጠበቀላቸው፣ የቅዱሳን የሺኅ አመት ማረፊያ ከሆነው፣ ልዩ ስፍራ ይደርሳሉ፡፡ ሌላው የአበው ኢትዮጵያዊያንን ክርስትና እምነት እና የመሰጠታቸውንም ጥግ ከሰማያት ደጃፍ አቁሞ በእውነት የሚያሳይ እና እንደ ደጁ ስሙም ያው የሆነ ሌላኛው የነገስተ ላሊበላ- ታላቁ ስራ ፣ “ይምረሓነ ክርስቶስ” ገዳም እንዲሁ ፣ ላሊበላን ከብበው ካሉት አብረቅራቂ ፈርጦች፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና የራስ ጌጦች ዋነኛ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ግን የላሊበላን በአለት ላይ የተጠረበን ህያው ወንጌልን ታላቅነት የሚያጎሉ፣ በመሆናቸው ለማሳየት የአጠቃላይ የላሊበላን እና ብሎም የላስታን ድንቅ የእምነት ማፅኛ ስፍራነት የሚያጎሉ፣ ስራዎች ስለሆኑ እንጂ በዚህ ፅሁፍ ፣ እንዲህ ለኮፍ ለኮፍ ተደርገው ሊዳሰሱ የማይቻሉ እጅግ ግዙፍ ጥልቀት ያለው ታሪካዊ እንዲሁም ሃይማኖታዊ ዳራ ያላቸው ቱባ ቱባ ስፍራዎች ናቸውና ፣ ይችን ፅሁፍ ለላሊበላ ብቻ ገድበናት ሌላ ግዜ በስፋት እንመለስባቸዋልን፡፡
ከሟቹ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት እስከ ዶናልድ ሌቪን እና ኤድዋርድ አለንዶፍ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ዋና መልእክቱን በሸፍጥ ለውሶ ፣ ለላሊበላ አብያተክርስትያናት ውበት ግን እጁን አውርዶ እስከ መሰከረው፣ ግራሃም ሃንኩክ ፣ ሪቨር ጋድ በሚለው መፅሃፉ ድርሰት ውስጥ ሳይቀር ስፍራ ካበጀለት ዊልበር ስሚዝ እስከ ቀደምቱ እና ከአራት መቶ አመት በፊት የላሊበላን ምትሃታዊ ውበት በብእሩ እስካተተው፣ ፖርቱጋላዊ የታሪክ ፀሃፊ ፈራንሲስኮ አልቫሬዝ ድረስ፣ ላሊበላ ሊናገሩለት፣ ስለውበትና ሁለንተናው ሊያወሩለት ሲጀምሩ የሚፈጥረው ስሜት ልክ እንደ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ ቃል፣ “ከዚህ በላይ ብናገር፣ የማወራውን ማንስ ይህ ሁሉ እውነት ነው ብሎ ይቀበለኛል” እንዳለው አይነት ነው!
ግና ግና ከሁሉ በላይ ስለላሊበላ ሲነገር ሆነ ሲፃፍ ጎልቶ፣ ገዝፎ የሚመጣው አንድ ታላቅ ቁምነገር፣ ወንጌል ነው፡፡ በዚህም ውስጥ ሶስት ታላቅ አስተምህሮቶች ከሁሉ ልቀው ይህንን የዚህን ፅሁፍ አርእስት ሲደግፉ ይታያሉ፡፡ ከእነዚህም “አንዱ” -በህንፃዎቹ ላይ በጉልህ የተቀረፁት የምድራዊ እና ሰማያዊ እየሩሳሌም ተምሳሌታዊ የስነ-ህንፃ ጥበቦች ማለትም ፣ በወንጌል ላይ እንዳለው ከክርስቶስ ልደት ፣ ጥምቀት እስከ ስቅላቱ ስፍራ ድረስ የወንጌል አንጓዎች በህያው የተቀረፁበት ሲሆን፣ “ሁለተኛው” -ለሚያምን ኢትዮጵያዊ ሁሉ የዚህን ስፍራ እውነተኛ እየሩሳሌምነት የሚያጎሉት የልደት ወይም “ቤዛ ኩሉ” እና የጊዮርጊስ አመታዊ ክብረ በአላት ሲሆኑ እንዲሁም “ሶስተኛው” እና ታላቁ ቁምነገር ፣ -የቅዱስ ላሊበላ የመጨረሻ ስራ የሆነው ፣ አስር አስገራሚ አብያተ ክርስቲያናትን ይዘው በዮርዳኖስ ወንዝ ለሁለት የተከፈሉትን የላሊበላ ቤተክርስቲያናትን፣ ለብቻው ተነጥሎ ሶስት ማእዘን የሚሰራው እና የአብያተ-ክርስቲያናቱንም ክፍፍል ሶስት አድርጎ ፣ ከስላሴ ቁጥር አንድ የሚያደርጋቸው፣ ቤተ-ጊዮርጊስ ነው!
እነኚህ ከላይ የተገለፁት ሶስቱ የወንጌል መገለጫዎች ፣ ከበጎ እይታ ለተነሱ ፣ ለአንዳንድ የታሪክ ፀሃፊዎች የስራውን ታላቅነት እና ግዝፈት ለመቀበል ስለሚከብዳቸው ላሊበላን የሚገልፁበት መንገድ ፣ ከሰው ስራ ይልቅ ለመለኮታዊ ወይም ለተአምራዊ ሃይል ብቻ በባለቤትነት ሊሰጥ የሚገባው አድርገው ያስቀምጡታል፣ እዚህ ጋር አንዱን ለመጥቀስ ሮዜታ እንዲህ ብላ ትገልፀዋለች፣ “ በመንፈሳዊ ሃይል የምድር ማህፀን የተገላገለው የወንጌል ፣ የብርሃን ልጅ” -ብላ ባጭሩ ታስቀምጠዋለች፡፡
ግልፅ እንዲሆን ትንሽ ለማብራራት ያክል፣ በነባር የኢትዮጵያ መዛግብት ላይ በምድራዊ እና በሰማያዊ እየሩሳሌም ተምሳሌትነት ተፈርጀው፣ በሰሜንና በምእራብ መሃላቸው በተምሳሌታዊው የዮርዳኖስ መንዝ ተከፍለው ያሉትን ቤተክርስቲያኖች ይህች ፀሃፊ፣ “ አንደኛውን (በምድር የተወከለውን) እንደ ምድራዊ ማህፀን በሰማያዊ መንግስት የተወከለውን ደግሞ መንፈሳዊ ፍሬን መስጠት የሚችል ከላይ የሆነ ሰማያዊ (ፋሊስ) ብልት ትለዋለች፣ በነዚህ ፣ “ምድራዊ ማህፀንና”- “መንፈሳዊ ብልት” ‹ መካከል የዛሬ ዘጠኝ መቶ አመት በተፈጸመ መንፈሳዊ ሩካቤ፣ ምክንያትም ቅዱስ ላሊበላ ራእይ አርግዞ፣ ከዚያም አምጦ የወለደው “ተአምር” የጊዮርጊስ መሻት የሆነው ዘር፣ “ቤተ-ጊዎርጊስ” የመንፈስ ልጅ ነው ለማለት ነው፡፡
ግና የላሊበላ ሚስጥር በዚህ ብቻ የሚያበቃ አይደለም ፣ ከአርባ ሺህ የማይልቅ ነዋሪ ያላት ላሊበላ፣ ለልደት ንግስ፣ ከሳምንት እስከ ወር ድረስ በእግር ተጉዘው የሚመጡ አማኝ ፣ የክርስቲያን ምእመናት ከከተማዋ ነዋሪ ከአምስት እጥፍ በላይ በሆነ ቁጥር ፣ አመት አመት ደርሰው “ቤዛ ኩሉ”ን ይታደማሉ፡፡ ቅዱስ ላሊበላ በግሉ ያስቀድስባት እንደነበረባት የሚነገርላትና የመጀመሪያ ስራው በሆነችው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በቤተክርስቲያን የውስጥ ግድግዳና ጣሪያ ላይ ጥበብ እጅግ የሚያስደምም ውበት በለበሰችው “ቤተ-ማርያም” ዙሪያ የሚደረገው የ”ቤዛ ኩሉ” ወረብ እና ሽብሸባ ፣ እንዲህ በሚያስገርም የስነህንፃና የእምነት ስፍራ ላይ ከላስታ ዙሪያ ለመጡ ሰዎች የደስታው ጣሪያ ፣ እላይ ሰማይ ሲደርስ እና የመንፈስ ስካር ሲሸንጥ፣ በእምነት ልቅሶና ደስታ ቅልቅል፣ አንዳንዶች “ሶራ ምት” ሲመቱ ሊታይ ይችላል፡፡
ከሁሉ በላይ ግን ታላቁ የቅዱስ ላሊበላ ስራ እና በአለት ላይ ጠርቦ የፃፈው ስራው ለዘላለም ህያው እንደሆነ የሚታየው ፣ ከላይ ሰማያዊ መንፈስ እና ምድራዊ ማህፀን በፈፀሙት መንፈሳዊ ሩካቤ፣ ስለ እየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በጉልህ ቁጭ ብሎ ያለው፣ ቤተ-ጊዎርጊስ ነው! ስለህንፃው ምንም ሳናወራ ከዘጠኝ መቶ አመት በፊት ተሰርቶ ዛሬም ድረስ ወለል ብሎ ስለሚታየው የቤተክርስቲያኑ ሁለንተናዊ መስቀልነት ትርጓሜ ብቻ ብለን እናብቃ፡፡ ቤተ-ጊዎርጊስን እጅግ ልዩ የወንጌል ማህተም የሚያደርገው አንድ ነገር፣ ክርስትና እና መስቀል ያላቸው ትስስር ነው፡፡ ማንም ሰው ወደ ላሊበላ ተጎዞ እዚያ ደርሶ ከቤተክርስቲያኑ በላይ ለሚቆም፣ ስፍራ ካካባቢው ከፍ ያለ የምድር ከፍ ያለ ስፍራ ስለሆነ የቤተ-ጊዎርጊስ ጣራ ከሆነው መስቀል አጠገብ እራሱን ያገኘዋል፡፡
ነገር ግን ፣ የቅዱስ ላሊበላ መጥረቢያ ፈልፍሎ በሰራት የቤተክርስቲያኑ መድረሻ በሆነችው በጠባቧ መንገድ ተጉዞ እታች ከቤተ-ጊዎርጊስ ቤተክርስቲያን ለሚዘልቅ፣ እንደ ክርስቲያን ከአምላኩ በስፍራው ህብረት ያደርጋል፣ ያኔ ወደ ሰማያት ፊቱን ያዞረው የቤተጊዎርጊስ ጣሪያ ፣ እታች ላለው ሁሉ የምድር ከፍታው ይሆናል፡፡ ይህ ተምሳሌታዊ ፋይዳው አንድ እንዲሆን የተሰራ ድንቅ የክርስትና ምስክርነት ነው! እሱም የምድር ላይ ታላቁ እውቅና በመስቀል ላይ የተሰራው የቤዛነት ስራ ነው የሚል ይሆናል!!!
ለቤዛ ኩሉ ላሊበላ ያገናኘን!!
“ሶራምቱን” እንኳን አዲስ አበባም በሽበሽ ሁኗል!
ኢትዮጵያዊነት ይለምልም!