ፈረስ ተነስቷል! – በላይነህ አባተ

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

አብቹ በልጅነቱ የተጫወተበት የሰላሌ ሜዳ በሰማዩ ልክ እንደ መንፈስ ተዘርግቷል፡፡ ይህ ሜዳም  ለቆ በሚባለው አዲስ ሳር ተሸፍኗል፡፡ ይህንን ለቆ ለመጋጥም ለማዳ እንሰሳት በየክልላቸው ተዘጭተዋል፡፡ በስተምሥራቅ እድሜ ጠገብ በጎችና ፍየሎች “ምስ …ምስ…” እያደረጉ በወላቃ ጥርሳቸው ቀንበት ቀንበጡን ሳር ይነጫሉ፡፡ ሳሩን ነጭተው የጠገቡ ወጠጤዎችና ቂቦች ደግሞ “እቡቡ..ቡቡ..’ በሚል ቋንቋ አየተግባቡ እንደ መደዴ ፈረንጅ ከአውላላው ሜዳ ፍቅር ይሰራሉ፡፡ በስተደቡብ በሬዎችና ላሞች “ቡርፍ –አምፍ… ቡርፍርፍ….አምፍ… ቡርፍርፍ” እያደረጉ እንግጫና ጎድሩን ይግጣሉ፡፡ ጥጆችም ለማራቶን ይዘጋጁ ይመሰል ከወዲህኛው መስክ እዚያኛው እንደ አበበ በቂላ ሩጫ ይለማመዳሉ፡፡ ኮርማዎች እንደ ራስ ዳሽን የተቆለለውን ሻኛቸውን ከክርስቶስ በቀር ማንንም እንዳልፈራው በላይ ዘለቀ ያጎማልላሉ፡፡ በስተሰሜን ያረጁት አህዮች ምኑንም ምኑንም ይገምጣሉ፤ አለሌዎች እንትናቸውን እንደ ችካል ቀስረው ጥጋብን ያክላላሉ፡፡ በስተምዕራብ ፈረሶች ጥጋብን በሚያክላሉት አለሌዎች በመገረም “አሂ…ሂ…ሂሂሂ…” እያሉ የፌዝ ሳቅ ይስቃሉ፡፡ ከፈረሶች ጎን በቅሎዎች በአህዮችና በፈረሶች መካካል የተዘረጋውን ውጥረት ለማርገብ አንገት ላንገት ተቃቅፈው ይመካከራሉ፡፡

ክልልን አሻፈረኝ ያሉ ፈረሶች ከላሞች፣ ከበጎችና ከአህዮችም ተሰበጣጥረረው ይታያሉ፡፡ ከእነዚህ ፈረሶች አንዱ ከአህዮች ክልል እማይጠፋው ሽማግሌው ጥሪኝ ነው፡፡ ጥርኝ እንደ ጋዜጠኞች “ነውጠኛ” እየተባለ ተደጋግሞ ቢከሰስም “ያያቶቼ ደም የፈሰሰብትን እርስት አለቅም!” እያለ ከአህያዎች ሰፈር አይጠፋም፡፡ ጥሪኝ መልኩ ለውቃቢ እንደሚታረድ ዳንግሌ በግ የቀላ፣ ቁመቱ እንደ ደብረ-ማርቆስ ባህርዛፍ መለል ብሎ የወጣ፣ ሽንጡም እንደ ወሎ ፈረስ የተስለከለከ ግርማ ሞገስን እንደ ብልኮ የለበሰ ፈረስ ነው፡፡

ጥርኝ መንግስትና ሕዝብ ያልፈቀዳቸውን አርበኞች ሳይዘነጋ በተዋበ ኮርቻና ግላስ እያጌጠ ሲያገለግል ኖሯል፡፡ በዚህ ያገልግሎት ዘመኑም ቅድመ አያቶቹ ፈረሶች በአድዋና በአምስቱ ዘመን ያሳዩትን የጀግንነት ታሪክ ተምሯል፡፡ ሥለ አያቶቹ ጀግንነት ያዋሱትና ያገሩን ሰንደቅ የሰቀሉት አርበኞች አልቀው ሰንደቋን እንደ ቡቱቶአቸው በጣሉና የጣሊያንን ባንዲራ ባውለበለቡት ልጆች ሲተኩ ጥሪኝ ከግላስ ለባሽ ፈረስነት ወደ ድብዳብ ተሸካሚ መጋዣነት ተቀይሯል፡፡ አዳሩም እንደ ድሮው ሳር ተነጥፎለት ተጋጥ ሳይሆን በለቅ ከሚባል ጠብደል አህያ እየተጋፋ ተጉረኖ ሆኗል፡፡ በዚህም ምክንያት ጥሪኝ “ቀን ሲያዘነብል ሰማይ ተመሬት ይወድቃል!” እያለ ይተርታል፡፡

በለቅ እድሜው ከጥሪኝ ባያንስም የማይጨነቅና የማያስብ በመሆኑ በቀለም የተነፋ እስቲመስል ስላበጠ የሜዳ አህያ ይመስላል፡፡ የቡላና የነጭ ዥንጉርጉር  መልኩም ያህያንም ሥም መላክ ያዋጣዋል ያሰኛል፡፡ ጥሪኝ እንደማንኛውም ካድሬ ከድንጋይ ማምረቻው “ስቪል ሰርቪስ ኮሌጅ” ስለተመረቀ በአህያዎች ዘንድ እንደ ሊቅ ይቆጠራል፡፡

የእነ ጥርኝ ቅደመ አያቶች በኮርቻ ሲሽቆጠቆጡ የበለቅ ቅድመ አያቶች ጀርባን የሚገሸልጥ ድብዳብ ሲለብሱ ኖረዋል፡፡ በለቅም በዚህ የቅድመ አያቶቹ ታሪክ ሲሸማቀቅ ኖሯል፡፡ ቀን ሲያዘነብልና ሰማይ ተመሬት ሲወድቅ ግን ጥሪኝም ተክብር ማማ ወድቆ ተበለቅ እግር ሥር  ወድቋል፡፡ ጥርኝን የረገጠው በለቅም ሊሸከመው ያልቻለ ትቢት ተቆልሎበታል፡፡ ትቢቱ ከአፍንጫው ሲደርስም ተፈጥሮ ባደለው የግፊያ ስልቱ ጥሪኝን ገፍትሮ ተጉረኖው ያስወጣዋል፡፡

ይህንን የበለቅን ጥጋብ መታገስ የሰለቸው ጥሪኝም “እኔ ለግፊያ አልተፈጠርኩም! ተወኝ በለቅ! እባክህ ተወኝ! ተወኝ ተወኝ..” እያለ ደጋግሞ ሲለምነው በለቅ የተፈራ እየመሰለው እንደ ንክር ባቄላ የባሰ አብጦ አህያ መሆኑንም ይረሳና “ደደብ  አህያ..” ብሎ ጥርኝን እየሰደበ ይገለፍጣል፡፡ ጥሪኝም በዚህ ስድብ እየተገረመ “ሂ..ሂ..” ብሎ የፌዝ ሳቅ ይስቃል፡፡ እንደ ቀኛማች ሰውነቴም “እኔን.. እኔን…” ብሎ ይተክዝና “ድንጋዩም መጎለቱን ስላበዛው ወፍጮው ከካው” ብሎ ይተርታል፡፡ በለቅ የጥሪኝን እማያልቅ ተረት ሲሰማ በስጨት ይልና “የሰለቸኝ የፈረስ ተረትና የመጋዣ ቀለብ ነው!” ይላል፡፡ “የአለሌ ጥጋብሳ” ብሎ ጥሪኝ ሲመልስ በለቅ ሥሩ ይገታተርና ግድግዳውን እንደ አምባ ገነን ጠረጴዛ በኮቴው ይደልዘዋል፡፡

በበለቅ ተንኮል እንቅልፍ አጥቶ እሚያድረው ጥሪኝ ሌሊት ያጣውን እንቅልፍ ለማካካስ ቀን ከመስክ ይተኛል፡፡ ሰኔ አስራ ሁለት ቀን ሁለት ሺ ስምንት ዓ.ም ጥርኝ እንደተለመደው እንቅልፉን ሲለጥጥ እንደ ሳውዲ አረቢያ በጋሱ እሚተማመነው በለቅ የጋዝ ቦንቡን እንደ መብረቅ አንባረቆ ጥሪኝን ቀሰቀሰው፡፡ “የሺዎች ግምት” ብሎ ጥሪኝ እንደ ሶማ ጀግና ፎክሮ ሲነሳ በለቅ በፍንጪቱ የፌዝ ሳቅ ሲስቅ አየው፡፡

“ምነው በለቅ? ምነው የላም አሸናፊ ሆንክሳ! ተጉረኖም ተሜዳም ተጀርባዬ አልወርድ አልክ!  ሌት አታስተኛ! ቀን አታስተኛ! ጥጋብህ የእግዜርን ዓይን ጠነቆለ! እንደ ፋና ሬዲዮ ጥንብ እሚነፋውን ፍንጢጣህን እስተምነቃ ብትዘጋው ትሞታለህ?” አለ ጥሪኝ ዳንግሌው ፊቱ የባሰ ቀላና፡፡

“ቦንቡን ያፈነዱት ፀረ-ሰላምና ፀረ-ልማት ኃይሎች ናቸው!” አለ በለቅ ያንን እንደ ዳልጋ የተንዘላዘለ ከንፈሩን በአሽሙር አሞዳሙዶ!

“ድሮ ታህያ የዋለች ጊደር ምን ተምራ ትገባለች ይባል ነበር፡፡ ዛሬ ተፋና የዋለ ካድሬ ውሸት ተምሮ ይገባል እንደሚባለው ማለት ነው” አለ ጥሪኝ ብስጭት በጎረሰ ሐዘን

“የለም! ተፈረስ የዋለ ተረት-ተረት ተምሮ ይገባል!” እንደሚባለው ነው!” አለ በለቅ የቀኝ አይኑን ጠንገር አርጎ በሾርኒ ጥሪኝን እየተመለከተ፡፡

“የፈረስ ተረት እኮ ተውነት፣ ተታሪኩ፣ ተጀግነንቱ፣ ተጦር ውሎው፣ ተዓመት በዐል ግልቢያው ተሰርግ ጭፈራው …ተሞክሮ በመነሳት ነው! የራሱን ታሪክ እሚጠላ ሹምባሽ አባ ታጠቅ፣ አባ ዳኘው፣ አባ ኮስትር ስለሚባሉ ፈረሶች ተጋድሎ ሳይሆን ስለፈረንጅ ፈረሶች ስለሆነ የእንግሊዙን የእንሰሳት አብዮት አንብበሃል ብዬ እገምታለሁ፡፡ በዚህ የእንሰሳት አብዮት አህያን ጨምሮ እንሰሳትን ተባርነት ያላቀቀው ፈረስ ነው” አለ ጥሪኝ  ጆርጅ ኦርዌል የጣፈውን የእንሰሳት አብዮት አስታውሶ፡፡

“በእንሰሳት አብዮት ፈረስ ተዋጋ አሳማ በላ” አለ በለቅ ሂ..ሂ..ሂ.. እሚል የለበጣ ሳቅ ሳቀና

” ዘፋኙስ የሞተለሽ ቀርቶ የገደለሽ በላን የዘፈነው ለዚሁ አደለም?” አለ ጥሪኝ በሐዘን ተውጦ!

“ስለዚህ ፈረስ ዘልዛላ ወይስ ጀግና!” አለ በለቅ ጥርኝን በክርከር የረታሁ መስሎት የንቀት ሳቅ ስቆ፡፡

“ፈረስ ጀግና ነው! ዘልዛላ ያሰኘው ደግነቱ ነው! ጀግንነትና ደግነት አይነጣጠሉም! ጡርቂነትና ጭካኔም እንደዚሁ! ሌሎችን እንሰሳት ማመን ዘልዛላነት አይደለም፡፡ ዘልዛላና ይሉኝታ ቢስ ነፃ ያወጣውን ጀግና እሚክድ ነው! ዘልዛላ ጀርባው እሲቲገሸለጥ ቅርቀብ  ሲጭኑት፣ በዘነዘና ሲደልዙት፣ መሳለቂያ ሲያደርጉት ለክብሩ እማይነሳ ፍጡር ነው” አለ ጥሪኝ ጦረኛ አያቶችቹ ዘልዛላ በመባላቸው ተቆጭቶ፡፡

“በደብተራ ቅኔ ይኸንን በሾርኒ መሳደብህ አቁም፡፡ ደብተራ አከርካሪውን ተመቷል፡፡ ወደድክም ጠላህም እንሰሳና እንሰሶች እኩል የሆኑበት፣ የእንሰሳና እንሰሶች ቋንቋና ባህል የተከበረበት ሥርዓት ተመስርቷል፡፡ ያ የጦረኛው ልጅ! ያ ያርበኛው ልጅ እየተባልክ የምትከበርበት ዘመን ላይመለስ እንጦሮጦስ ገብቷል! ያንተ ጀርባ የጌጥ ኮርቻ የእኛ ጀርባ የጭነት ድብዳብ የሚለብስበት ሥርዓት ድምጥማጡ ጠፍቷል! እድሜ ለእነ ተገዳላይ ደሳለኝ!” አለ በለቅ በአህዮች ታሪክ ሥሙ የገነነውን ደሳለኝን ጠቅሶ፡፡

“ይህንን ተሱዳንና ተምራብ ጅቦች ተሻርኮ መቀመጫችሁን ያስገመጠውን ከንቱ አህያ ነው በጀግንነት የምታነሳው” አለ ጥሪኝ ተገዳላይ ደሳለኝን በስሙ መጥራት ተጠይፎ፡፡

“ተስፋ የቆረጠ ትምክተኛ ፈረስ የማይነዛው የሥም ማጥፋት ዘመቻ የለም”

“ሥም ማጥፋት ዘመቻ!”

“በትክክል! የሥም ማጥፋት ዘመቻ! ተገዳላይ ደሳለኝ እናንተን በግላስ እያስጌጠ እኛን ዳዉላ ይጭን የነበረውን ፈረሰኛ ሥርዓት ገርስሶታል! የቀረውንም ርዝራዥ እንደ አረም እየነቀለ ይጥለዋል!” አለ በለቅ ጥርሱን ነክሶ፡፡

“የኔ ቅድመ አያቶች በግላስ ያጌጡት ጠላትን ባራቱም አቅጣጫ ይፋለሙ ስለነበር ነው! የኔ ቅደመ አያቶች ደም ያልፈሰሰበት የኢትዮጵያ አፈር የለም! ይመስክር መቅደላ! አድዋ! ይመስክር ምጥዋ! ይመስክር ማይጨው፣ ይመስክር ወልወል! ይመስክር ተከዜ! ይመስክር ዓባይ! ይመስክር ጎሬ! ይመስክር ቀብሪ ድሃር …ይመስክር ፊላው! ይመስክር ዱሩ …ይመስክር ሸንተረሩ! ምን ሩቅ አስኬደኝ! ይመስክር ያበሻው ጀብዱ አብቹ! ይመስክር የበጋው መብረቅ ጃጋማ!” አለ ጥሪኝ አካኬ ዘራፍ ብሎ እንደ እሚፎክር ትክሻውን ከቀኝ ወደ ግራ ገፈተረና፡፡

“ይህ የአድዋ፣ ያምስቱ ዘመን ቅብጥሶ ቅብጥሶ… ድል እያላችሁ የምትወሸክቱት ትምክህተኛ ተረት አንገታችን ደርሶ እያስታወከን ነው” አለ በለቅ እንደሚያስታውክ ፊቱን አጨማዶና ያንገቱን ሥር እንደ ገመድ ወድሮ፡፡

“ያስታውክህ እንጅ ታሪክ አይፋቅ! ተይሉኝታ ጋር ብትፈጠር በድሎቹ ፈረስን ታመስግን ነበር!” ብሎ ጥርኝ ሳይጨርስ  “ሂ….ሂ…ሂሂሂ” ብሎ በለቅ ሳቀ በበለዘ ጥርሱ፡፡ ሳቁ ሲበርድም  “ሰው ወዶ አይስቅ! እኛ በእነዚህ ቅብጥሶ ቅብጥሶ እያላችሁ እምትለፍፏቸው ድሎች ተጪነት ተላቀናል? ጥሊያንና እንግሊዝ መንገዱን ቢሰሩትና ካሚዮኑን እንደ ሮምና ለንደን ቢያርመሰምሱበት እስተዛሬ ቅርቀብ እንጫን ኖሯል? እናንተስ ኮርቻና ጋሪ ስትጎትቱ ሶስት ሺ ዘመን ይሞላችሁ ኖሯል? ምን አይነት ቂልነት ነው? ዛሬ አሜካኖች ከወርልድ ባንክ፤ አውሮጳውያን ከአይ ኤም ኤፍ፣ ቻይናውያን  ከኪሳቸው ገንዘብ ባይሰጡ ይህ የምታየው አስፋልት ይሰራ ኖሯል? ባስፋልት መንቀባረር ወይስ ድል፣ ክብር፣ ቅብጥሶ ቅብጥሶ እያልክ በድህነት ስትንፏቀቅ መኖር ይሻልሃል?” ሲል ጠየቀ በለቅ የጥርኝን ብልት አገኘሁት በሚል መንፈስ፡፡

“የሰው ወርቅ አያደምቅ! አንተ እምታወራው ሥለ-አካል ነፃነት ነው! እኔ እማወራው ሥለ-መንፈስ ነፃነት ነው! ከአካልና ከመንፈስ ነፃነት የትኛው ይሻላል?” ብሎ ጥርኝ በለቀን ሲጠይቀው በለቅ ጥያቄው ጠጠር አለበትና “ሥልቻ ቀልቀሎ! ቀልቀሎ ሥልቻ” ብሎ አለፈው፡፡

ጥርኝ “ሥለ ሥልቻና ቀልቀሎ በርግጥም አንተ ታውቃለህ” ሲል በለቅ የጪነት ከብት ብሎ እንደሰደበው ቆጠረና “አንተም የጋማ ከብት ነህ! ጊዮርጊስ ስለተቀመጠብህ ሥልቻና ቀልቀሎ የማታውቅ ቅዱስ የቀንድ ከብት የሆንክ መሰለህ?” አለ፡፡

“ቅዱስ ነን አላልኩም! ተቅዱሳንና ተጀግኖች መዋላችንን ግን  ቅዱሳን በቅዱሳን መጻሕፍት፤ ታሪክ ጠሐፊዎችም በታሪክ መጻሕፍት አውለውናል!” አለ ጥርኝ  በታሪኩ ተኩራርቶ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዕንቆቅልህ ምን ዐውቅልህ! - ነፃነት ዘለቀ

“ትምክተኛ! እናንተ ጊዮርጊስን ተሸከምን ብላችሁ ስትመኩ እኛ ክርስቶስን ተሸከመን ሆሳእና ያስጨፈርኖች ምን እንበላ?” ብሎ በለቅ ጥሪኝን ሲወጥር

ጥሪኝ “ሂ…ሂሂሂ ..ኡሁ …ሂሂሂ ..ሂሂ…ፈነዳሁ” እያለ አንገቱን አንዴ ወደ ሰማይ ሌላ ጊዜ ወደ ምድር እየቆለመመ ተንተክትኮ ሳቀና “ምንትስ ምንትስ..” ብሎ በፊት የእነ እማሆይ ገላነሽ በኋላ  የእነ እየንታ አንዳርጌ ተማሪዎች እነ ቀሲስ አስተርአየ ደብረ ሊባኖስ ሳሉ በሰላሌ ሜዳ በዘሩት ቅኔ ተቀኘ፡፡

“ስትወጠር ማንም አያውቅብኝም ብለህ እንደነ አባ ገብርኤል ግዕዝ እንደ ሽሮ ቋንጣ ጣል- ጣል ታደርጋለህ! እስቲ ባማርኛ መልሰው” አለ በለቅ፡፡

በእማሆይ ገላነሽ ቅኔ “ላይና ታችን እማትለይ ሲያወርዷት ያወጧት ይመስላታል” ማለት ነው አለ ጥርኝ

“ይኸ አባባል እንነጋገር ተነበረው ተጊዮርጊስና ተክርስቶስ ምን ግንኙነት አለው?” አለ ነገርን ማያያዝ ችግር ያለበት በለቅ፡፡

“ክርስቶስ ታህያ ጀርባ የወጣው ተላይ ሳይሆን ተታች መሆናችሁን ለማሳየት ነው!”

“እንዴት? ትምክህታችሁ ክርስቶስንም እያስደፈራችሁ ነው!”

“እውነትን መናገር ክርስቶስን መዳፈር አይደለም! ክርስቶስ እውነትን ነው፤ እውነትንም ይወዳል!  ክርስቶስ ታህያ ጀርባ የወጣው ተተናቀው ፍጡር ውሎ ትህትናን ለማስተማር ነው” አለ ጥሪኝ አለመዳፈሩን ለማሳየት ሶስቴ አማትቦ፡፡

በለቅ የተናቀ የሚለው ቃል አበሳጨውና “ማነው የተናቀ አንተ” አለና የጋዝ ቦንቡን እንደ መርካቶ አጋዚ እንደተለመደው “ብው!” አደረገው፡፡

“ቦንብህን ቆጥብና ለጭንቅ ቀን አውለው!” አለ ጥርኝ  የአፍንጫውን ቀዳዳዎች ለመዝጋት እየሞከረ፡፡

“ተክልሌ መጥተህ የመተንፈስ መብቴን ልትከለክል ነው?” አለ በለቅ ጦርነት መፍጠር አማረውና፡፡

” በአፍንጫ እንጅ በእሬብ አይተነፈስም!” አለ ጥሪኝ በጆሮው አፍንጫውን እየጠቆመ፡፡

“ቅሌታም ሽማግሌ!” አለ በለቅ ንዴቱ እንደ እንፋሎት ቡል አለበትና!

“ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል!! ጊዜ ሰጠህና እንዳሻህ ትናገራለህ” አለ ጥሪኝ በሐዘን፡፡

“ግዜ የሰጠን ነገር የለም! ገደል አንቀጥቅጠን ለዚህ በቅተናል! የደሳለኝን ታሪክ አንብብ” አለ በለቅ፡፡

“እንኳን የተንቀጠቀጠ ገደል የተወዛወዘ ሰንበሌጥም አልነበረም፡፡ ተወንበር የወጣችሁት በሱዳን፣ በእንግሊዝና ባሜሪካ ጉንጉን እንደ ጉድጓድ ውሀ ተስባችሁ ነው፡፡ በዚህ ጉንጉን እየተሳባችሁ በምድር ቤተመንግስቱን፣ ቤተክህነቱን፣ ቤተ መስጊዱን፤ በሰማይም ሲኦልን መሙላታችሁና እኔ ተሞትኩ ሰርዶ አይብቀል እሚለው መፈክራችሁ መሳካቱ እሙን ነው” አለ ጥሪኝ፡፡

“ለሽንፈትህ ሰበብ መደርደሩን ተውና የደሳለኝን ተጋድሎ አንብብ….” አለ በለቅ የንቀት ሳቅ እየሳቀ፡፡

“በእውር ቤት አንድ ዓይና ብርቅ ነው! ደሳለኝ እንዲያውም አንድም ዓይን የለው! እውር ነው! እውሩ ደሳለኝ ተሸጦ ሱዳን ገባ፡፡ እንደገባም ሰርዶ መንቀሉን ተወና የሱዳንና ያረብን ፉል መዛቅ ጀመረ፡፡ ቆየት ሲልም ተምራብ አገሮች የሚላክለትን ፉርሽካ መጎርመዱን ተያያዘው፡፡ ተዛቀው ፉልና ተጎረመደው ፉርሽካ የጋዝ ቦንብ እያፈነዳ፤ በእንግሊዝና አሜሪካ አሳማዎች ካሜራ እየተመራ አዲሳባ ገባ! ይህ የሚያሳየው የረቀቀውን የሃያኛው ክፍለ ዘመን ቅኝ አገዛዝና ባንዳነት ነው!” አለ ጥርኝ በለቅ ላይ አይኑን አፍጦ፡፡

“ይህም የፈረሰኛ ሥርዓት ናፋቂ ፈረሶች ተረት ተረት ነው! እውነታው ግን የነ ደሳለኝ ትግል የእንሰሳትንና እንሰሶችን መብትና ድምፅ ያስከበረ መሆኑ ነው” አለ በለቅ በኩራት፡፡

“ጆሮ አይሰማው የለው! መብትና ድምፅ ያስከበረ? እንኳን የሌላው ያንተስ መብት መቼ ተከበረ!”

“ምን ጎደለብኝ? የመኪናው መንገድ ተስፋፍቶ አቆማዳና ኬሻው በተሰሳቢ መኪና እየተጫነ የኔ ገጣባ ድኗል” አለ በለቅ ከአዲስ አበባ ጎሐጽዮን የተዘረጋውን መንገድ በቀኝ ጆሮው እየጠቆመ፡፡

“ይሉሽን በሰማሽ ገበያ ባልወጣሽ?” አለ ጥሪኝ

“ትምክህተኛ ተረቱን እየተረተ ሶስት ሺህ ዘመናት ተኝቶ ዛሬም አልነቃ! ምን ያሉኝን ነው ያልሰማሁት?” ሲል በለቅ የፌዝ ጥያቄ ጠየቀ፡፡

“ይኸንን መንገድ አንደ ድሪቶ በመጣፊያ የሚጥፉት ቻይኖች ተጅብ የተረፈውን ቂጣችሁን እየከተፉ እየበሉት መሆኑን አልተገነዘብክም? ሉካንዳ ከፍተው ፍሪንባችሁን እየጠበሱ ሊበሉት መዘጋጀታቸውን አልሰማህም?” ብሎ ሲጠይቀው

“ነውጠኞች በመካከላችን ችግር ለመፍጠር የሚያናፍሱት መሰረተ-ቢስ ወሬ ነው!” አለ በለቅ እውነት መሆኑን ቢረዳም እጅ ላለመስጠት፡፡

“ጅብም የሚሞተርፋችሁ በራሳችሁ ቀርቶ በጠባቂ ጌቶቻችሁ እየተማመናችሁ ስለምትኖሩ ነው! በጌታው እሚተማመን እድሉ የመንፍስ ነፃነቱን መገፈፍ ከዚያም በአካሉም ሳያዝዝ መኖር ነው! ያህያ ታሪክ ይኸው ነው! ቻይናዎች መንገድ ሰርተን አህዮችን ከጭነት ነፃ እናወጣለን ብለው ገቡ! ሥር ሲሰዱም አውቀው በመኪና እየገጩ ይበሏችሁ ጀመር! ግንድና ቅርንጫፍ ሲያውጡ ሉካንዳ እየሰቀሉ ሐምበርገርና ጎረድ ጎረድ እየሰሩ ሊውጧችሁ ተደሳለኝ ተስማሙባችሁ! የእንሰሳትና የእንሰሶች መብት መከበር እስከ ሉካንዳ ቤት መሆኑ ነው፡፡ አህያነት ለሉካንዳ እስቲቀርቡ በሆድ መገዛት ነው፡፡ አህያነት አስረስ የኔሰውና አድማሱ ጀንበሬ “ወጣት ተጠንቀቅ እንዳትሳሳት” እያሉ ስለውጪ ኃይሎች መሰሪነት ያስተማሩትን አለመቀበል ነው፡፡ አህያነት በራስ አለመተማመን፣ አለማስተዋል፣ አለመመማርና እንደ ደሳላኝ የራስን ወገን አሳልፎ መስጠት ነው፡፡ አህያነት በሆድ የማምለክ የድንቁርና በሽታ ነው!” ብሎ ጥሪኝ ሐሳቡን ሳይቋጭ በለቅ ተናዶ “ዛሬም እንደ ትናንቱ ደደብ አህያ፤ ደንቆሮ አህያ እያልከን ነው” ሲል

“ወዶ ብለህ ጣፍ! ብለዋል አለቃ ሞገስ” አለ ጥሪኝ

“ወዶ ብለህ ጣፍ? ወድጄ ደደብ ነኝ ብያለሁ! እኔ ደደብ ነኝ?” አለ አሁንም በለቅ ዶማ እራስ የሆነው ሁሉ ደደብ አህያ እየተባለ እሚሰደብ መሆኑን አስታውሶ ይበልጥ ተበሳጨና!

“አዎ ደደብ ነህ! ግም!” አለ ጥሪኝ ጠምቶት፣ እርቦትና መታገሱም ሰልችቶት ስለነበር

በለቅ ደደብና ግም የሚሉትን ቃላት ከጥሪኝ አፍ ሲሰማ ሰማዩም ምድሩም ተገለባበጠበት፡፡ የደም ሥሩ እንደ ዋርካ ሥር ተወጣጥሮና ልምጭምጭ ዓይኑም አለወትሮው እንደ ልቅ ተንጎልጉሎ እንደ ጦጣ እመር አለና የጥሪኝን ማጅራት ባፉ ሞልቶ በመንጋጋው ነግንጎ ያዘው”

ጥርኝ ባልሞት ባይ ተጋዳይነት እየታገለ “ደደብነትህን በእንክሻህ አረጋገጥክ” ሲል በለቀ ብስጪቱ ጋዝ እንደተጨመረበት እሳት እንደገና ቦግ አለና ጥርሱን አስተካክሎ እንደ ጅብ ነከሰው፡፡ ጥሪኝ “የጅብ ዲቃላ መሆንህን አላወኩም ነበር!” ብሎ ሳይጨርስ በለቅ በላይና በታችኛው አቀንጣጤው የማጅራቱን ሥጋ አጣብቆ ሲይዘው “ሂው…..ሂው ሂው ሂውውውውውው…” ብሎ ጮኸ፡፡  የጥርኝን የጣር ድምፆ የሰሙ ፈረሶች እንደ ኮማንዶ ፈጥነው ደረሱ፡፡

አንድ ጎረምሳ ፈረስ የበለቅን ምንግጪል የድንጋይ መዶሻ በሚያህል ኮቴው ቢያፈነዳውም በለቅ ከጥሪኝ ማጅራት አልላቀቅ አለ፡፡ በለቅም በልቡ “እንኳን የጃጀ ፈረስ ኮርማውን ጅብም በእንክሻ ሰውተናል” አለ፡፡ በለቅን ፈረሶች ሲረባረቡበት ያዩ አለሌዎችም ጋልበው ደረሱ፡፡ ፈረሶች ሰማይ ደርሰው እንደ አየር ወለድ እየወረዱ አለሌዎችን በኮቴ ቦቅስ ሲወግሩ አህዮቹ የኋሊት እየተራገጡ የቦንብ እሩምታ አወረዱ፡፡ ፈረሶች በካራቴ ሲፋለሙ፤ አህዮች በእርግጫና በቦንብ ሲታገሉ አስራ አምስት ደቂቃዎች አለፉ፡፡ ብዙ ፈረሶች ተላላጡ፤ አያሌ አህዮችም ጥርሶቻቸውን አጡ፡፡ አንድ ጥርሱ የወለቀ አለሌ ሰርዶ ትዝ አለውና ጥርሳችንን ጨርሰን ሳናጣ የተኩስ አቁም ስምምነት አድርገን በሰላም እንፍታው አለ፡፡ ሌላኛው አለሌ ለፈረስ ተምንበረከክ እንኳን ጥርሳችን አጥንታችንም ይምሸክ አለ፡፡ የሁለተኛው አለሌ ደጋፊም ውርንጪላ ገብረን ተጅብ እርዳታ ጠይቀንም ቢሆን እንፋለማለን እንጅ ለድርድር አንቀርብም አለ፡፡ ግማሹ አህያ የመጀመርያውን የተቀረው ሁለተኛውን ሐሳብ ስለደገፈ በአህዮች መካከል ክፍፍል ተፈጠረ፡፡

ያህዮችን ክፍፍል ያስተዋለች አንድ ባዝራ “እሰይ! አህዮች ተከፋፈሉ! እርስ በርሳቸው ጥርስ ሊሳበሩ ነው” ብላ ሳትጨርስ ያህያን ታሪክ ያጠኑ አንድ ምሁር “ፈረሶች ሆይ! አህያ ይከፋፈላል  እያላችሁ የበሬ እንትን ይወድቅልኛል ብላ ስትከተል እንደዋለችው ቀበሮ አትንዘላዘሉ! አህያ ቢራገጥ ጥርስ አይሳበርም” አለ፡፡ ሌላው ይህን ሐሳብ ደጋፊ  ቀለብ አደረገና “ትክክል! አህያ ጥርስ ይሳበራል ብሎ መጠበቅ የበሬ ቆለጥ ይወድቅልኛል ብላ ስትከተል እንደዋለችው ቀበሮ መንዘላዘል ነው” ብሎ ምሁሩ ለጨዋነት እንትን ያላትን ፍሬ ስትፈጠር በወጣላት ሥም “ቆለጥ” ብሎ ጠራት፡፡  ሴቶቹ ፈረሶች ይህችን ቃል ሲሰሙ ቀበሮ ጆሮዋን እንደ ቁንጮ ቀስራ ጫት እንደ ጎረሱ ጉንጮች ያበጡትን የበሬ ፍሬዎች አፍጥጣ ስትመለከት ታየቻቸውና “ሂ..ሂ…ሂ” ብለው እየተሽኮረመሙ በሳቅ ተንፈራፈሩ፡፡

ጦርነቱ ግሎ ሌላ አስራ አምስት ደቂቃዎች እንዳለፉ ለሽምግልና የተላኩት በቅሎዎች ጋማቸውን ሹርባ ተሰርተውና ጭራቸውን እንደ ኤፍሬም ይስሃቅ እየነሰነሱ መጡ፡፡ “እነዚህ የኤፍሬም ይስሃቅ፣ የሀይሌ ገብረስላሴና የዳንኤል ገብረየሱስ ሆዳም በቅሎዎች እንዳይሆኑ!” አለ አንድ ፈረስ ወደ ጓደኛው ጆሮ ጠጋ ብሎ፡፡ “አይመስሉኝም! ግን ያልጠረጠ ተመነጠረ!  እስቲ እሚሉትን እንሰማለን” አለ ጓደኛው፡፡

ሽምግልናውን እንድትመራው የተመረጠችው ማርዳ የተባለች በቅሎ ተፈጥሮ ያደላትን ውበቷን ለሽምግልናው መጠቀም ፈልጋ ግራና ቀኝ የወደቀውን ጋማዋን ነቅንቃ፣ ለግላጋ ሽንጧን እንደ እንዝርት ሶስቴ ሰብቃና ዳሌዋን አስመርቃ “”አዳምጡኝ ዘመዶቼ!  አዳምጡኝ! አንዴ እድሉን ስጡኝ! አንዴ አዳምጡኝ!! ከዚህ በፊት ለነበሩት፣ አሁን ላሉት፣ ወደፊትም ለሚኖሩት የጋማ ከብቶች ስትሉ የእርስ በርሱን ግጪት አሁኑኑ አቁሙ!” ስትል አዳምጧት “በእናቷ  የክቡር አቶ ሀዲስ ዓለማየሁ የአርበኝነት ዘመን በቅሎ ዘር ናት!” አለ አንድ የሚያውቃት ሽማግሌ ፈረስ፡፡ የሀዲስ ዓለማየሁ ስም ሲነሳ ፈረሶች ጆሯቸውን እንደ መስኮት በረገዱና ማዳመጥ ጀመሩ፡፡ አህዮች ግን “አባቷን ስትጠየቅ አጎቷን ከምትናገር ከሀዲ ምን እንጠብቃለን ብለው” እርግጫቸውን ቀጠሉ፡፡

“አባቶቼ አህዮች ሆይ! ከሀዲ እያላችሁ በቅሎውን ሁሉ በአንድ ቀረጢት አትክተቱ፡፡ ሁሉም በቅሎ አባቱን እሚክድ አይደለም! ባብቱ የሚኮራ እንደኔ አይነቱ በቅሎ አለ! እኔ አባቴ አህያ ነው”  ብላ ሳትጨርስ በለቅ ለመጀመርያ ጊዜ አህያን አባቴ የምትል በቅሎ በመስማቱ ተገርሞና ሲቃ ይዞት ከፈረንጅ በተማረው ቅላፄ “ዋው…ዋው…ማይ ጎድ ዋው! ጀሰስ ክራይስት” ብሎ አፉን ሲከፍት ነግንጎ የያዘውን የጥሪኝ ማጅራት ለቀቀው፡፡ የበቅሎዋን ንግግር የሰሙ አለሌዎችም ሐሳባቸውን ሙሉ በሙሉ ቀየሩና መራገጡን አቆሙ፡፡ አንዳንድ አለሌዎች እንዲያውም የሰለጠኑ ለመምሰል ሱሪያቸውን ከጭናቸው ታጥቀው መቀመጫቸውን እያሳዩ እንደሚሄዱ የከተማ መረኖች “ሄይ ገርል! ሀዊ ዱይንግ” እያሉ ማርዳን ሊያሽኮረምሙ ከጀሉ፡፡ ማርዳም በእነዚህ መረኖች አፍራ “ታህያ መወለድ ችግሩ ይኸ ነው!” አለች በልቧ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ… - ነፃነት ዘለቀ

በሌላ በኩል ደግሞ አህዮችን “አባቶቼ” ስትል የሰሙ አንዳድ ፈረሶች “በቅሎ በአባቷ በአህያ መኩራቷ የሚያሳየው እኛን ቀን ምን ያህል እንደጣለን ነው” እያሉ አጉረመረሙ፡፡ ሌሎች ፈረሶች ደግሞ “ሴት መላ መምታት ስለምትችል አህያ አባቷ መሆኑ የተናገረችው ለሥልት ነው! አባቷ አህያ እንደሆነ ባትናገር በለቅ በእንግሊዝ አፍ ይቀባጥር ኖራል? በለቅ በእንግሊዝ አፍ ባይቀባጥር ጥርኝን ይለቀው ኖራል?” ሲሉ ተከራከሩ፡፡

ይኸንን የፈረሶች ክርክር የተገነዘበች ማርዳም “አጎቶቼ ሆይ! በራሷ የማትተማመን የእህት ልጅ አትበጃችሁም፡፡ በራሱ የማይተማመን ለእናቱም እንደማይበጅ ክቡር አቶ ሀዲስ ዓለማየሁ በየእልም እዣት መጣፋቸው አስተምረዋል” አለች፡፡  “ፍቅር እስከ መቃበር ማለትሽ ነው?” ሲሉ ጠየቁ የበዛብህና የሰብለን ታሪክ ሰምተው የማይጠግቡት አለሌዎችና ጎረምሳ ፈረሶች፡፡ ማርዳም የአለሌዎችና የጎረምሳ ፈረሶችን ትኩረት በመሳቧ ተደስታ እየተሽኮረመመች “የወጣት ነገር! እስከ መቃብርም ባይሆን በበዛብህና በሰብለወንጌል ዱካ ያልተራመደ ማን አለ?” ብላ ፈገግ አለች፡፡ በመቀጠልም “እኔ ለዋቢነት የጠቀስኩት ግን የእልም እዣትን ነው፡፡ የእልም እዣት የህልም ሐብት እንደማለት ነው! ይኽ ድንቅ መጽሐፍ ተከስተ እስተውጪ አገር ያስተማረችውን እናቱን ደመቀች ፀሐይን አፍሮባት አላውቅሽም ማለቷን የሚተርክ ነው” ስትል አንድ አርበኛ ፈረስ “እውነቷን ነው ይህ መጽሐፍ በባዶ እግሯ እየሄደች፣ እየራባት እየጠማት ያስተማረቻቸውን ኢትዮጵያን ዛሬ አናውቅሽም ያሏትን ዶፍተሮችና  ቅብጥሶዎች የሚገልጥ ነው” ብለው ሲደግፏት ማርዳ ጉልበት አገኘችና “በትክክል! ሀዲስ ዓለማየሁ ነቢይ ነበሩ! እንደ ነቢዩ ኢሳያስ የተነበዩት ሁሉ ተፈፅሟል፡፡ እኔንም ይህ እንደ ውዳሴ ማርያም እምደግመው መጣፍ ቀይሮኛል፤ በማንነቴ አኩርቶኛል፡፡ በማንነቴ ታልኮራሁ ላባቴም ሆነ ለእናቴ ዘመዶች አልጠቅምም፡፡ የምጠቅመው በእናንተ በአባቶቼና አጎቶቼ ስኮራ ነው” አለች መጀመምርያ ወደ አህዮች ከዚያም ወደ ፈረሶች ዞረችና፡፡ ማርዳ ያህያ ልጅ መሆኗን ደግማ በማረጋገጧ የተደሰተው በለቅ ብድግ አለና ደም በጎረሰ አፉ ” “የትግላችን ፍሬ ነው! ወደ ፊት እንጅ ወደ ኋላ የለም” ሲል ሁለት አለሌዎች “መጀመርያ አፍህን ጥረግ” ብለው ተቆጡት፡፡ እርሱም ታፈርኩ አይመልሰኝ በሚል ስሜት “የጥሪኝን ማጅራት ባልገምጠው በቅሎ ያህያ ልጅ መሆኗን ታምን ነበር? አለ ለፈረሶች ሊሰማ በማይችል ድምፅ፡፡

በማርዳ ቁጅና፣ በሐሳብ አሰካኳ፤ በዋቢ አጠቃቀሷና ባንደበቷ የተማረኩ ወጣት ፈረሶችም “እውነቷን ነው”፡፡ ሲሉ ድጋፋቸውን ገለጡና በተኩስ አቁሙ ጸንተው የጥርኝን ቁስል ጠራርገው ወደ ፈረስ ሰፈር ይዘውት ሄዱ፡፡ አህዮችም ማርዳ አባቷ አህያ መሆኑን መናገሯን እንደ ድል ቆጥረው አፋቸውን እንደ መቃብር ከፍተው እያክላሉና ቂጣቸውን በጅራታቸው እንደ ታምቡር እየጠበጠቡ ጨፈሩ፡፡

“ጥሪኝ ሊሞት ያጣጥራል እነሱ ይጨፍራሉ” ሲል አንድ ቆፍጣና ፈረስ ሌላው “እግዜር ይይላቸው!” አለ የፊት እግሮቹን ወደ ሰማይ ዘርግቶ፡፡ ቆፍጣናው ፈረስ እግሩን ወደ ሰማይ የዘረጋው ፈረስ አናደደውና “እግርን ወደ ሰማይ መዘርጋት መፍትሔ አደለም የኔ ወንድም! እግዚአብሔርም ጡርቂና ሰነፍ አይፈልግም! ጥረህ ግረህ ብላ! እርዱኝ እረዳለሁ እንዳለ አታውቅም? ስለዚህ ግፍ አትፈጥም፤ ግፍ ሲደርስብህ ግን ተቆጣ! ተነስ፣ ታጠቅ፣ ታገል! ያኔ እግርህን ብትዘረጋ ይረዳሃል፡፡ ይልቅስ እግርህን ከሰማዩ አውርድና ሰይጣንን ከመሬት እርገጥበት” አለ ከንፈሩ እየተንቀጠቀጠ፡፡

“እግዜር ታለ ዓለምንም ያጠፋል እንኳን እንደ በለቅ ያለ አህያን” አለ እግሩን ወደ ሰማይ የዘረጋው ፈረስ ቆፍጣናው ፈረስ በእግዚአብሔር አያምንም በሚል ስሜት፡፡ “አይምሮህም እንደ ልብና አሞትህ ፈሷል ልበል! እግዜር ታልረዳሃው አይረዳህም አልኩህ እኮ! እግዜር እጅና እግር የለውም! የሚጠቀመው አንተን፣ እኔን፣ ነፋሱን፣ ውኃውን፣ እሳስቱን ..ነው! ስለዚህ እግዜር እንዲጠቀምብህ ዝግጁ ሁን፡፡ ሰነፍ፣ ሆዳምና ቦቅቧቃ አትሁን! እግርህን ወደ ሰማይ ዘርግተህ የሎሄ ስትል አትዋል! እንደ እያቶችህ ተቆጣ! እምቢ በል! አያቶችህ ወራሪ አሳማ ሲመጣ እምቢ አሉ! ካህናት እምቢ አሉ! ታቦቱም እምቢ አለ፡፡ አቡነ ጴጥሮስን ሰምቶ ወንዙ፣ ሜዳው፣ ተራራውና ሸለቆው እምቢ አለ፡፡ ያኔ እግዚአብሔርም ሰማ! ጠላት ድባቅ ተመታ!” አለ መሬቱን በኮቴው ድባቅ መታና፡፡

“እግዚአብሔር ፈሪና ሰነፍ አለመውደዱ! ታረዱት አለመርዳቱ የመጣፉ ቃል ነው” አለ በሐሳብ የተረታው ፈረስ እግሩን ወደ መሬት አውርዶ፡፡ ቆፍጣናው ፈረስ በሐሳብ በመርታቱ ተደሰተና ለሰስ ባለ ቃል “ቹኒያ አቸቤ እሚባል ጠሐፊ ፈረንጆች የአፍሪካን አይን በመጣፍ ቅዱስ ሸፍነው መሬታቸውን እንደዘረፉት ጥፏል፡፡ አፍሪካኖች ስለሰነፉ! እምቢ ስላላሉና እግዚአብሄርን ስላልረዱ መጀመርያ መንፈሳቸውን ከዚያም መሬታቸውን ተሰርቀው ታህያ የባሱ ባሪያዎች ሆኑ፡፡ ስለዚህ ባርነትን የስንፍና፣ የከርሳምነትና የፍርሃት ውጤት ነው፡፡ የሚያዋጣው እምቢተኝነት ነው፡፡  እምቢ በል ጭፈራን ሙሽራ ስትሸከም አላስተዋልክም? ይህንን በአህያ ዘመን የተከለከለውን እምቢ በል ጭፈራ ዛሬውኑ መጀመር አለብን!” አለና  ጋማውን እንደ ሽመል ቀስሮ እምቢ በል!!” ማለት ሲጀምር ጎረምሳና ጎልማሳ ፈረሶች ተከትለው “እምቢ በል!”ን ለአስረ ደቂቃዎች ጨፈሩ፡፡ ሴቶቹም ተወንዶች ጀርባ ዳንኪራ መቱ፡፡

እምቢ በል ጭፈራ ከተሰማ ዘመናት ተቆጥረው ስለነበር ሙሽራ ሲወጣና ሲገባ ይሰሙት የነበሩ የቀንድ ከብቶችንም ትዝታ ቀሰቀሰባቸውና  ጭፈራውን ሊያዩ በዚያውም በቤተክህነትና በዘመናዊ ትምህት ብቃቱ የሚታወቀውን ጥሪኝን  ሊጠይቁ ወደ ፈረሶች ክልል መጡ፡፡ ላሞች የቁስል ቅቤ ለጥሪኝ ስጦታ አበረከቱ፡፡ በጎችም “ጠባቂው እረኛ ምህረት በጉነቱን ያውርድልህ!” ብለው ጸለዩ፡፡ ፍየሎችም የባጡን የቆጡን ቀባጠሩና ተሰብሳቢውን ፈገግ አሰኙ፡፡ በሬዎች ያህዮችን ጥጋብ አወገዙ፡፡ አንዱ ኮርማ ሻኛውን እንደ ገብርዬ እናት- አልቢን ተግራ ወደ ቀኝ አገላበጠና “እንደምታውቁት እኛ የቀንድ ከብቶች ማንንም አንተናኮልም፡፡ ይህንን ያለመተናኮል ባህላችንንና ደግነታችንን እንደ ፍርሃት የቆጠረ አንድ መረን አለሌ የተፈጥሮን ሕግ ጥሶ ወንድ ዓይታ የማታውቅን ጊደር ሊጠቃ መጣ” ሲል “እግዞ ማህርነ ክርስቶስ!’ አሉ ተመሳሳይ እጣ የገጠማቸው ሴት ፈረሶች ባንድነት፡፡ ኮርማው ቀጠለና “ይህ መረን እንትኑን እንደ ሽጉጥ አንጠልጥሎ ሲስገበገብ ይኸንን የሾለ ቀንዴን በእግሮቹ መካከል አስገብቼ ከሻኛዬ እንደ ልጅ ሰቀልኩና ዥማዥዌ አጫውጬ ከአለት ሳፈርጠው ስይነሳ ቀረ” ብሎ ሳይጨርስ አንድ በለቅ ስልጣኑን ተጠቅሞ የደፈራት ፈረስ “አንተ ኮርማ ፈረስ ብትሆን ኖሮ እኔንም ታድነኝ ነበር!” ብላ ስትጮህ አንድ ጎረምሳ ፈረስ ኮርማውን ፈረስ ብትሆን ኖሮ ስትል እርሱ እንደተናቀ ቆጠረውና “ትልቅ ሽጉጡን ስታይ ስሜትሽ ገንፍሎ የፈቀድሽለትን እንደተደፈረ እኛን ታሳጫለሽ” አለ የሐፍረት ስሜት ከፊቱ እየተነበበ፡፡ በለቅ የደፈራት ሴት በዚህ ጎረምሳ ፈረስ ፈር የለቀቀ ንግግር ይበልጥ ተናደደችና “አንተ ጡርቂ! ማን አሳድጎኝ ታህያ እልከሰከሳለሁ! ሱሪና ቀበቶስ የለህም!  እንካ ቀሚስ ያለ መቀነት ልበሰው! መቀነትማ የነ ጣይቱ ነው!” አለች ከንፈሯ እየተንቀጠቀጠ፡፡

በማግስቱ በአህያ ሴቶቻቸውን እያስደፈሩና እየተረገጡ መኖር ያንገሸገሻቸው ፈረሶች ለውይይት ተገናኙ፡፡ ውይይቱ ከመጀመሩ በፊት አቡነ ጴጥረስ በልጅነታቸው የጋለቡት ፈረስ የልጅ ልጅ “አባታችን ሆይ…” ብሎ ስብሰባውን ከፈተው፡፡  ከዚያም የስብሰባው መሪ “የመጀመሪያው አጣዳፊ ጉዳይ ጥርኝን ማሳከም ነው” ብሎ ሳይጨርስ “ደብረ-ዘይት ከእንሰሳት ሕክምና ኮሌጁ ቢታከም ይሻላል!” አለ አንድ ደብረ ዘይትን እሚያውቅ ፈረስ፡፡ “እነ በለቅና ደሳለኝ እያሉ እንደ ጥርኝ ያለ ፈረስ ህክምና ሊያገኝ አይችልም፡፡ ህክምና ተነፍጓቸው የሞቱት የመጀመርያው ቀዶ ጥገና ሐኪም ብሮፌሰር አስራትን ተረሱ ማለት ነው?” አለ ሌላው ፈረስ፡፡ “እና ምን ይሻላል?” ሲል ጠየቀ ሰብሳቢው፡፡ “እኛው በጨው፣ ባባሎ፣ በጠበሉም፣ በጸሎትም መርዳት” ሲል አንድ ባዝራ ብድግ አለችና “ጠበል ለመርጨት የሚበቃ ካህን የት ይገኛል? አብዛኛው ካህን ተነደስሳለኝ ተሻርኮ የፈረስ ደም ሲጠጣ አለዚያም እንደ በለቅ ባለትዳር ባዝራዎችን ሲደፍር አይደለም እንዴ እሚውለው?” እያለች በነበለቅ ዘመን የደረሰውን የካህናት ዝቅጠት አስረዳች፡፡

ጥሪኝ በእርሱ ህክምና ምክንያት ተሰብሳቢው ጊዜውን በከንቱ ያጠፋ መሰለውና “ለኔ አትጨነቁ፤ የሚያሳዝነው ባንበሳ ሳይሆን ባህያ መነከሴ እንጅ ህክምና የማግኘትና ያለማግኘቴ ጉዳይ አይደለም፡፡  እንኳን ተዚህ  ቀላል ቁስል ተብዙ መከራ ተርፌአለሁ፡፡ አሁን መወያየት ያለባችሁ ስለ ትውልድ ነው! ማሰብ ለነፃነታችን የረገፉትን ሰማእት ፈረሶች ነው! ማሰብ በአህያ እርግጫ በየቦታው የሚሰቃዩትን ፈረሶች ነው፡፡ ማሰብ ነገ ስለሚወለዱት ፈረሶች ነው! ጊዜው በዚህ ከቀጠለ የሚወለዱት ፈረሶች የሚገቡት ጥቅጥቅ ጨለማ ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ የኔን ጉዳይ ተውና ጥቅጥቅ ጨለማ የሚገፈፍበትን ብርሃን ፈልጉ” ሲል  እርጉዝ ፈረሶች የሚወልዷቸውን ውርንጭላዎች ጥቅጥቅ ጨለማ ውስጥ አዩአቸውና “አህህህ….እህህህ…ህህህህ” ብለው አለቀሱና እንባቸውን በሰልካካ ፊታቸው አወረዱ፡፡

እርጉዝ ፈረሶች ስቅስቅ ብለው ሲያለቅሱ የተመለከተ አንድ ወጣት ፈረስ ” እናቶቻችንን እያስለቀስንና አዛውንቶቻችንን እያስነከስን መኖር የቁም ሞት ነው! በቁሜ መሞትን አልፈቅድም፡፡ ለማዳ ሆኘ ከበለቅ ጋር መኖርን እምቢ ብያለሁ!  አውሬ ሆኛለሁ!” ሲል ሌላው ቀበል አደረገና “አውሬ ተሆኖ የትኛው ጫካ ይኖራል? ጫካው ተመንጥሮ አልቋል? ብሎ ሳይጨርስ አወሬ ሆኛለሁ ያለው ወጣት ደሙ ተንፈቅፍቆና አይኑ ተማቶቱ ወጥቶ “ዝም በል ጡርቂ! ጀግና ሲፈጠር መስኩ ጫካ ነው! ጎበዝ ሲወለድ ሜዳው ገደል ነው! ጥራኝ ዱሩ! እምቢ!! እምቢ! እምቢ!! ብሎ ፎከረና” ወደ ዓባይ በርሃ ሲነጉድ “የትም አይደርስም” አለ ጫካው አልቋል የሚል ሰበብ የፈጠረው ፈረስ፡፡ ሰበበኛውን ፈረስ የትም አይደርስ ሲል የሰማው አንድ ጎልማሳ “የፈረስ መዳረሻው የድሮው ኢትዮጵያ ያሁኑ ሕንድ ውቂያኖስ ነው፡፡ አንተ እዚሁ ለሚስትህ ሙግድ ስታቀብል ጠብቀው አለ” ዝቅዝቅ ደፍቶ እያዬ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጥብቅ ማሳሰቢያ በተለይ ለአማራ ልሂቃንና የነፃነት ታጋዮች - ከትንቢቱ ደረሰ (አዲስ አበባ)

ወጣቶቹ በብስጪት ሲሸፍቱ ያዩ አንድ ሽማግሌ ፈረስ “ወጣቶች ሆይ! የወደቅንበት አዘቅት እንዲህ በስሜትና በችኮላ የምንወጣው አይደለም፡፡ ትግል ዝግጅት ያስፈልገዋል፡፡ እነ በለቅ ታሰቃዩአቸው የቀንድ ከብቶችም መተባበር ያስፈልጋል” ብለው ሳይጨርሱ “ሳር እያዬ ገደል ተሚገባ በሬ መተባበር ምን ሊፈይድ!” አለ አንድ ወጣት በስጨት ብሎ፡፡ ሽማግሌው ተስፋ ሳይቆርጥ “ልጆቼ! ባትተባበሩም እንሰሳውን ሁሉ ጠላት ማድረጉ አይጠቅምም፤ ጠላት ማብዛት ጥበብ አይደለም!” ሲል የሽማግሌውን ሐሳብ የምትደግፍ አንድ ባልቴት ፈረስ “ተበቅሎዎች ብንመካከርስ አይጠቅምም?” ስትል ጠየቀች፡፡  “በቅሎ እንደ አሜሪካና እንግሊዝ አሳማዎች የራሷን ጥቅም አሳዳጅ ናት!  መተማመን ያለብን በራሳችን ወርቺ ነው!” አለ ሌላው ጎረምሳ ሙቀጫ የመሰለ ወርቹን አሳይቶ! በዚህ ወጣት ንግግር የረካ ያለምን ሁኔታ ያጤኔ አንድ ጎልማሳ ፈረስ “ልክ ብልሃል! ደካማን  አህያ ቀርቶ ፈጣሪም አይወደው! ስታሸነፍ አህያ ተጎንህ ነው! ስታሸነፍ ያሜሪካና የእንግሊዝ አሳማ ከጎንህ ነው! ስታሸንፍ የከዳህ አይጥና ጉንዳንም ከጎንህ ነው፡፡ ስታሸንፍ ሁሉ በእጅህ ሁሉ በደጅህ ነው! ተግባባን! ብሎ ሐሳቡን ሲቋጭ ፈረሶች ተነሱና በጭብጨባ መግባባታቸውን ገለጡ፡፡

ውይይቱን በጥሞና ሲያዳምጥ የቆየው ጥሪኝ የቆነጠጠውን ሕመም ጥርሱን ነክሶ አሳለፈና “እስታሁን የተግባባችሁበት ሁሉ የመንፈሳዊውና የቁሳዊውን ዓለም ሁኔታ ያገናዘበ ነው፡፡ ግሩም ነው፡፡ እንደተባለውም ደካማና ፈሪን እንኳን ፍጡር ፈጣሪም አይወደው፡፡ መጣፉ ቀኝህን ሲመታህ ግራህን ስጥ ብሏል እያሉ እንዲሰብኩ በነደሳለኝ የሚላኩትን ደፍተሮች አትስሙ፡፡ እድሜ ለደብረ ሊባኖስ መጣፉን አሳውቆኛል! መጣፉ ሰው እንጅ ሰይጣ ቀኝህን ሲመታህ ግራህን ስጥ አላለም፡፡ ሰው ቀኝህን ሲመታህ ግራህን ስጠው ያለበት ምክንያትም ሰው ቀኝህን መቶህ ግራህን ስትሰጠው ህሊናና ይሉኝታ ይገቱታል ብሎ ነው፡፡ ህሊናንና ይሉኝታን የማያውቅ ሰይጣን ሲመታህ ስንት ዘመን ፊትህን ስታስጠፈጥፍ ልትኖር ነው? ለስይጣን እንኳን ፊትን ለጥፊ እግርም ለቅይድ አይሰጥም፡፡” ሲሉ በሚናገሩት ረክቶ ሲቁነጠጠነት የቆየው የቡነ ጴጥሮስ ፈርስ የልጅ ልጅ “ይበል ብለና አባታችን” አለ፡፡

የአቡነ ጴጥሮስ ፈረስ የልጅ ልጅ ጥሪኝን መደገፉ ደስ ያላለው አንድ ፈረስ ተነሳና “ካህንማ እንዲህ አይልም፡፡ ካህን እሚለው ጊዜ ያመጣውን ጊዜ እስቲመልሰው ታገሱ ነው” ብሎ ሳይጨርስ አንድ ጎልማሳ ፈረስ ብድግ አለና “ይህ የዘኬ ዘክዛኪዎች፤ የመሐል ሰፋሪዎች፣ የቦቅቧቆችና የኢአማንያን ስብከት ነው! ሆድህን እየቆዘርህ ጊዜን ስትጠብቅ በለቅ ፋንድያውን ይጥልብሃል! አህያ ፋንድያ እየጣለባቸው ሆዳቸውን የሚሞሉ ፈረሶች በመካከላችን እንዳሉ እናውቃለን” ሲል ፈረሶች እርስ በርሳቸው ሲተያዩ ለአርባ አምስት ሰከንዶች ጸጥታ ሰፈነ፡፡ የሰፈነውን ፀጥታ ለመስበር ጥሪኝ ጉረሮውን “ኡሁ.. ኡሁ…” ብሎ ጠራረገና ” እንደተባለው ክብርን ጊዜ ይመልሰዋልን መተረት ራስን መሸንገል ወይም ሌሎችን ማዘናጋት ነው!  የትኛው ምዕራፍና አንቀጥ ተጎልተህ ስትጠብቅ ጊዜ ክብርህን እንደጎርፍ አክንፎ ያመጣልሃል ይላል? ክብርህን ጊዜም ሆነ ሌላ እንደ ስጦታ አይሰጥህም፡፡ ክብርህን የምታስከብረው አንተው ነህ፡፡ ክብርህ እንደ በለቅ ፋንድያ የምትጥለውም እንደ ሽፈራው በልጅግ እምታነሳውም አንተው ነህ! አለቀ! ደቀቀ! ክብርህን ስታስከብር አያቶቻችን ደማቸውን ያፈሰሱላት አገርህን  ክብርም ታስከብራለህ፡፡ እኔም የተነከስኩት የአባቶቼ ደም የፈሰሰበት እርስት አለቅም ብዬ የክልል አጥር ስለሰበርኩ ነው፡፡ ክልል ኢትዮጵያን እንደ ጣቃ እንደሚቆራርጣት አንድ ባህታዊ ከብዙ አመታት በፊት አስጠንቅቀው ነበር። አገሪቱን  እሚቆራርጡ ፍልፈሎች ግዮን ተማያዋስናቸው ያገሪቱ ክፍሎች እንደሚፈሉ ተንብየው ነበር፡፡ ያ ትንቢት ዛሬ ደርሷል፡፡” አለ፡፡

ጥርኝ ንግግሩን ሲጨረስ አንድ ልጅ እግር ፈረስ ” የምንታገለው ለፈረስ ክብር ወይስ ለአገር ክብር?” ሲል ጠየቀ፡፡ “ጥሩ ጥያቄ! ሁለቱ አይነጣጠሉም” ብሎ ጥሪኝ መልሱን ቀጠለ፡፡ “በመርህ ደረጃ እንደ እኛ እምነት ሁሉም ፍጡር የእግዜር ፍጡር ነው፡፡ እንደ ሌሎች እምነት ሁሉም ፍጡር የአዝጋሚ ለውጥ ዉጤት ነው፡፡ ሁሉም ፍጡር ሰማይን ተጠልሎ በመሬት የመኖር መብት አለው፡፡ ፈረስ ይህንን መርህ በመቀበል ራሱን ጎድቶ ለፍጡራን መብት መከበር አጥንቱን ሲከስክስና ደሙን ሲያፈስ ኖሯል፡፡” እንዳለ አንድ ተኋላ የተቀመጠ ፈረስ “ያ መብቃት አለበት!” አለ ጮክ ብሎ፡፡ “ቆየኝ- ቆየኝ ልጨርስማ የኔ ልጅ!” አለና ጥርኝ ማስተማሩን ቀጠለ፡፡ “እንዳለመታደል መርህና ነባሪዊ ሁኔታ ተገጣጥመው አያውቁም፡፡ እንዲያውም መርህና ነባራዊ ሁኔታ እሳትና ጪድ ሆነው ይኖራሉ፡፡ ሶቅራጥስ ለእውነት ሞተ፤ እውነት ግን ዛሬም የለችም፡፡ ክርስቶስ ለእውነትና ለፍትህ ተሰቀለ፡፡ እውነትና ፍትህ ግን ነባራዊ አልሆኑም፡፡ ነባራዊ የሆኑት ውሸት፣ ኢፍትሐዊነት፣ ዝርፊያ፣ ክህደት፣ ጭካኔ፣ ስግብግብነት፣ ይሉኝታ ቢስነት የመሳሰሉት የሰይጣን ባህሪያት ናቸው፡፡ ፈረስ እንደ ሶቅራጥስ ተመርህ ተጣብቆ ለፍጡራን ሲታገል ሰይጣናዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ተፈታተኑት፡፡ ስለዚህ ፈረስ በቅድሚያ ህልውናውን ማጠንከር አለበት፡፡ ህልውናውን ሲያጠነክር የድሮ ግዛታችን ጅቡቲ  ግመል ሳይቀር የደፈረውን ያገሩን ክብር ያስመልሳል፡፡ ለራሳችንና ላገራችን ህልውና ተጊዮርጊስ ጋር እንዳደረግነው በጦራችን ድራጎንን እንወጋለን፤ ተዳዊት ጋር እንዳደረግነውም በወንጪፋችን ጎልያድ እንጥላለን! አይደለም እንዴ?” ሲል ጥርኝ “ዝግጁ ነን!” አሉ ሮጠው ያልጠገቡ ፈረሶች ብድግ አሉና፡፡

አሁንም አንድ ቅር ያለው ፈረስ ጆሮውን ወደ መሬት ጣለና “እኛ ብቻ ላገር ሁሌ የምንሞትበት ምክንያት አሁንም አልገባኝ” የሚል አስተያየት ሲሰጥ “ስማኝ ልጄ! የምንታገለው አባቶቻችን እንዳደረጉት ለልጆቻችን ነፃና ሰፊ አገር ለማስረከብ ነው! እኛ ለነፃነታቸው የታገልልናቸው የፈረንጅ ባርያዎች ዛሬ በገንዘብ እየገዙን ነው፡፡ እንደምታዬው ለሱዳን ግመሎች ቅኝ ተገዥዎች ሆነን ያባቶቻችንን መቃብር እየፈነቀሉ ማሽላ እየዘሩበት ነው፡፡ የአረቦች፣ የህንዶችና የቻይና መጋዣዎች በአባቶቻችን ደም የከበረውን መሬታችንን በቆሎ እየዘሩት ነው፡፡ የጅቡቲ ግመል የከረዩን ፈረስ ገፍትሮ ውሃ እየጠጣ ነው፡፡ ይህን ሁሉ ውርደት የተከናነብነው በእነ ደሳለኝና በለቅ ጉዳይ አስፈጣሚነት ነው፡፡ በዚህ መልክ የተቦጠቦጠችውን አገር ለልጆቹ ማስተላለፍ የፈረስ ተፈጥሮው፣ ባህሉም ሆነ ታሪኩ አይደለም፡፡ የተቦጠቦጠውን ግዛታችንን አስመልሰን የተከናነብነውን ውርደት አውልቀን ታልጣልን እኔ ተሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ተሚሉት ተነበለቅና ደሳለኝ በምን ተሻልን?” ብሎ ጥርኝ ምክሩን ሳይጨርስ ሌላው ወጣት ተነሳና “ይኸንን ውርደት ያከናነበን ማን ነው? ማነው ተጠያቂው?” ሲል ጠየቀ፡፡  ይህንን ጥያቄ ሲሰማ ጥሪኝ አይኑን ተመሬት ተከለና “አንገት እሚያስደፋ ጥያቄ ጠየከኝ! አገራችን በሱዳን ግመሎች ቀጥተኛ ተገዥ፤ በቻይና  በሕንድናና ባረብ መጋዣዎች የጥቅም ተገዥ፤ በፈረንጅ አሳማዎች  የእጅ አዙር ቅኝ ተገዥ የሆነችው  በኔና በእኔ እድሜ ባሉ ፈረሶች ድክመት ነው! እንደ ደሳለኝና በለቅ ያሉ አህዮችን ሳይጠነጥኑ ለመቀየድ ሰንፈን ነው፡፡ ቢመረንም ይኸንን ሐቅ መቀበል አለብን! እኛ የናንተ አባቶች የአባቶቻችን አደራ አልተወጣንም!”  ሲል ከልቡ ንስሃ ገባና ያባቶቹን አደራ ልጆቹና የልጅልጆቹ መገዘባቸውን ለማረጋገጥ

“ፈረሱ አባ ታጠቅ ምን አለ?” ብሎ ሲጠይቅ ወጣቶቹ

“አንድ ኢትዮጵያ”

“አባ ዳኘውስ”

“ታልከተትክ አልምርህም!”

“አባ ነጋ?”

“ውኃ እምጠጣው ቀይ ባህር ነው!”

“አባ ኮስትር?

“የኢትዮጵያ ደም መላሽ!”

“አባ ጃካማ”

የበጋው መብረቅ” ሲሉ መለሱ

“እኛ የእናንተ አባቶች ያልተወጣነው ይህንን አደራ ነው! እናንተን ልጅና የልጅ ልጆቼን የምማጠነውም ይህንን እኛ ገደል የጣልነውን ያያቶቻችሁን ክብር ተወደቀበት አንስታችሁ ከተራራ እንድትሰቅሉት ነው፡፡ እኛ አደራ በላ የሆነው የፈረስን የባህልና የርዕዮት ትጥቅ ፈተን የባዕድ አሳማ ባህልና ርዕዮተ ስለታጠቅን ነው፡፡ የአሳማ ባህልና ርዕዮት ታጥቆ የፈረስን ክብር ማስጠበቅ አይቻልም፡የአያቶቻችሁን አደራ መልሳችሁ ከተራራ ለመስቀል የአያቶቻችሁን ባህልና ርዕዮት መታጠቅ አለባችሁ፡፡ ተባእዳን አሳሞች  ያእምሮ ማሾቂያ ሃይማኖት፣ ዘፈን፣ ፊልምና ፍርፋሪ አትረጠቡ፡፡ መበደር እኛ ስናበድር የኖርነውን ጥበብ ብቻ ነው፡፡ ተባእዳን አሳሞች መበደር ጥቅምን የማስጠበቅን ስልት ነው፡፡ ተባእዳን እባቦች መበደር አዳዲስ ግኝቶችንና የመናደፍ ዘዴዎችን  ነው፡፡ ተባዕዳን ቀበሮ መበደር የሥለላ ስልትን ነው፡፡ ተባዕዳን መጋዣዎች መማር ትዕግስት ነው፡፡ ተባዕድ ሃይማኖትና ባህል መበደር ለኢትዮጵያ ፈረስ የቁም ሞት ነው፡፡ ባህላችሁንና ሃይማኖታችሁን እንደ ጓሮ አትክልት ተንከባከቡ፡፡ እንደ አባ ገብረመድህን በቦየንሲ ዳንስና ዳሌ ተመፍዘዝ በአስናቀች ወርቁ ክራርና ትዝታ ስመጡ፡፡ እንደ ፌንጣ በማይክል ጃክሰን ዳንስ ተመወራጨት እንደ ሰው ልጅ እስክስታ ውረዱ፡፡ ሲከፋችሁ ጥራኝ ዱሩ እያላችሁ አቅራሩ፡፡ ሲነሽጣችሁ እምቢ ብላችሁ ፎክሩ! ሲጠነቁሏችሁ እንደ ቀፎ ነብ በአንድነት ተናደፉ፡፡” እያለ መከረና ጥርኝ በመጨረሻም “ፈረስ  እንደ ንብ ተነስቷል! ፈረስ እምቢ ብሏል! ፈረስ ሊቆስል ይችላል፤ ቁስሉን ግን ያድናል! ፈረስ ሊደናቀፍ ይችላል፤ ግን ፈጥኖ ይነሳል” ብሎ ፈጥኖ ተነሳ፡፡ ጥሪኝ ፈጥኖ ሲነሳ ፈረሶች በነቂስ ብድግ አሉና “የምስራች ፈረስ ተነስቷል! ወደ ክብሩ አርጓል!  ፈረስ ተነስቷል!  ፈረስ ተነስቷል! ፈረስ ተነስቷል!” እያሉ ዘመሩ፡፡

 

ሰኔ ሁለት ሺህ ዘጠኝ ዓ.ም.

 

 

Share