June 14, 2017
9 mins read

ዕንቆቅልህ ምን ዐውቅልህ! – ነፃነት ዘለቀ

“ወዴት እያመራን ነው?” ወይም “ወዴት እየሄድን ነው?” የሚለውን መልስ-አልባ ጥያቄ ራሳችንን እንደጠየቅን ይሄውና በትንሹ ዐርባ ዓመታትን ያህል አሳለፍን፡፡ እኔ ራሴ ለአቅመ ጥያቄ ከደረስኩ ጅምሬ ይህንኑ ጥያቄ ከመጠየቅ ቦዝኜ አላውቅም፡፡ በርግጥም “ወዴት እየሄድን ነው?”

ዲግሪና ዲፕሎማ አልባ አባቶቼ በዐርባ ብርና ሃምሣ ብር ወርኃዊ የዘበኝነት ደሞዝ እኔ ነኝ ያለ ዘናጭ ቤት በሃያ ሁለትና በቦሌ አካባቢዎች ይሠሩ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ እንዲያ ሲያደርጉም ቆጥበው እንጂ በስርቆትና በልመና ወይም በዕርዳታና በሙስና ድጋፍ አልነበረም፡፡ ደግሞም እንዲያ ሲያደርጉ ቤታቸውን በድለውና ተንቆጣቁጠው ሣይሆን በከዚህ ወዲህ ቁረጥልኝ ግምታዊ የሉካንዳ ቤት ሥጋ ቤታቸውን ከወር ወር ሙሉ እያደረጉ፣ የጤፍ እንጀራና  የስንዴ ጥብኛም ከቤታቸው ሳያጡ ነበር፡፡ የያኔው ገንዘብ እንዳሁኑ በራሪ ወፍም ሆነ ተሰፍቶ ያላለቀ ሞሰብ ስላልነበረበት በረከት ነበረው፡፡

ባለዲግሪ ታላቆቼ በአምስት መቶ ብር ወርኃዊ ደሞዝ በ1500 ብር ቅድመ ክፍያ እንደውኃ የምትፈስ አዲስ ቮልስዋገን ከሴፌሪያን እያወጡ በተመረቁ ማግስት ቅንጡ ነዋሪዎች ይሆኑ ነበር፤ ካለሱፍና ክራቫት ቢሄዱ ደግሞ የውርደት ያህል የሚቆጥሩ ሽኬዎች ነበሩ፡፡ የትምህርትንም ዋጋ ያስመሰግኑ ነበር፡፡ “የተማረና የበላ ወድቆ አይወድቅም”ን ያስተረቱ እነዚያ ታላላቆቼ ዛሬ የትም ወድቀው ለማኝ ሆነዋል፡፡ የጡረታ ገንዘባቸው ጡረታ ለመውሰድ የሚፈጀውን የታክሲ ኮንትራት ክፍያ እንኳን የማይሸፍን እየሆነ ነው፡፡ የዚያኔው አንድ ብር አሁን ከመቶና ሁለት መቶ ጀምሮ በሺዎች ይመነዘራል፡፡ የስሙኒን ክትፎ አሁን ሊያውም አንጀትህ ጠብ ለማይለው ከ150 ብር በላይ ስትከፍልበት … አስላና ድረስበት እንግዲህ፡፡

የአባቶቼ ልጅና የታላላቆቼ ታናሽ ወንድም የሆንኩ እኔ በአንድ ሺህ ብር የወር ደሞዝ የዛሬ ሃያ ምናምን ዓመት አካባቢ አንገትን ሰበር አድርጎ ማስገቢያ ዛኒጋባ መሥራት ችያለሁ – ሊያውም በስንት የዘመድ ድጋፍና ብድር፡፡

የኔ ልጆች በአሥር ሺዎች በሚገመት የዘንድሮ ወርኃዊ ደሞዝ ቤት ኪራይ መክፈልና የወር በጀታቸውን መሸፈን እያቃታቸው የጧሪ ተጧሪ በመሆን በየወላጆቻቸው ቤት በጥገኝነት ይገኛሉ፤ መርዳት እየተገባቸው እነሱ ራሳቸው በወላጅ ይደጎማሉ፡፡ ቤት መሥራት ይቅርና በወር አንድ ጊዜ እንኳን በኪሎ ከአምስት መቶ ብር የዘለለውን ጥብስ ወይ ቁርጥ ሥጋ በትልልቅ ሆቴሎች ገብተው መብላት አይችሉም፤ የምን መብላት ኧረ ማየትም አይችሉም፡፡ ሸሚዝና ጫማ ለመግዛት ዕቁብ መግባት እያስፈለጋቸው በሸፋፋ ጫማና በነተበ ሸሚዝ ለመሄድ ተገደዋል፡፡ ዱሮ ሳልቫጅ የድሃ እንዳልተባለ ዛሬ ባለቢሮው ሳልቫጅ ተራን መጎብኘት አይችልም፡፡ በጣም ውድ ነዋ፡፡ ለአንድ አሮጌ ጃኬት ብር 1200 ሲጠሩ ክንዴ ቡቲኮች ቅንጣት ታህል አያፍሩም፡፡ በርግጥም “ወዴት እየሄድን ነው?” መልስም ባይኖረው ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡

ትውልዱ ከትምህርት ይልቅ ለሌብነትና ለዘረፋ ቅድሚያ ሰጥቶ ራሱን ለድንቁርና ያጋለጠው መማር ከአንድ ቀን የዘለለ ደስታ ስለማይሰጥ ነው – የምረቃ ዕለት ብቻ ገዋን ለብሶ ፎቶና ቪዲዮ ለመነሳት፡፡ ከዚያ ውጪ መማር ከሚሰጠው ፋይዳ ይልቅ የሚያከናንበን ውርደት ይበልጣል፤ ያለመታደላችን መክፋት በማስተርስ ዲግሪ ከተመረቅን ከ30 ዓመታት በኋላም በመደበኛ ገቢያችን ወርን ከወር ለመግጠም የምንቸገር እጅግ ብዙዎች ነን – ምድረ ሌባና በሰው ላብ ነዋሪ ግን በየሣምንቱ ሶደሬና ላንጋኖ፣ በየሦስትና አራት ወሩ ደግሞ ዱባይና አውሮፓ ከነቤተሰቡ እየሄደ ይዝናናል – የዕንቆቅልሽ ሀገር፤ የትምህርት ደረጃውን ስታይ ግፋ ቢል መጻፍና ማንበብ ቢችል ነው – የገዛው ዲግሪ ከሌለው በስተቀር፡፡ (አንዱ የዲግሪ ተመራቂ በመመረቂያ መጽሔቱ እፎቶው ሥር “ኮብልስቶን መጣሁልሽ!” የሚል ታሪካዊ ቆንጆ የግርጌ ጽሑፍ አስቀምጧል አሉ፡፡ ጎበዝ አስተዋይ ነው፡፡) ለማንኛውም መማር ዱሮ ቀረ፡፡ የአሁን መማር ለድኅነት ካልሆነ በስተቀር ለድህነት ነው፡፡ ኅሊናህን ሞርደህ የኅሊና ፈውስና የነፍስ ድኅነት ለማግኘት መማር ጥሩ ነው፤ ድህነትን በትምህርት አስወግዳለሁ ብለህ ብትማር ግን የምታተርፈው እከክን ብቻ ነው፡፡ አእምሮ ጠፍቶ ጡንቻ ብቻ በገነነባት ሀገር ውስጥ ዕውቀትና ጥበብ ገደል ይገባሉ እንጂ ምሣና እራት አይሆኑም፡፡ ፈረንጆች ሰማየ ሰማትን ዳስሰው የትና የት ሲደርሱ እኛ ግን በየጊዜው በሚመጡብን መንግሥታት ምክንያት መሠረታዊ ፍላጎታችንን እንኳን ማሟላት አቅቶን በነዚያ ላይ እንረባረባለን፡፡ ከሆድ ባላለፈ አስተሳሰብ ደግሞ የሀገር ልዕልናና የሕዝብ ንቃተ ኅሊና ከእንፉቅቅ ወጥተው ከፍ ወዳለ ደረጃ ሊደርሱ አይችሉም፡፡ ለዚህም ነው የምቀኝነትና መሰል የክፋት መድብሎች ዋሻ ሆነን የቀረነው፡፡ የአኗኗር ዘይቤ አስተሳሰብን በመለወጥ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታልና የተንኮልና የምቀኝነት ወረርሽኝ ተጣብቶን በማይለቅ ደዌ እርስ በርስ የሚያናጅሰን ድህነታችን ነው፡፡ የብዙዎቹ ምናልባትም የሁሉም በሽታዎቻችን መሠረቱ ድህነትና ማጣት ናቸው፡፡ የገንዘብ ድህነትን በማግኘት ይላቀቁታል፤ የአስተሳሰብን ድህነት ግን በምን ይገላገሉታል? ችግር ነው፡፡

ዛሬ ተንደላቅቆ የሚኖረው ዘረኛና ደንቆሮ ወያኔ ብቻ ነው – ወይም እነሱን ተጠግቶ የሀገርንና የሕዝብን ሀብት የሚቦጠቡጥ አጫፋሪ፡፡ አኗኗሪዎች ደግሞ እኛ ነን፡፡ እንዲሁ ትዝ አለኝና በዚህች አጭር ማስታወሻ ወደ ትዝታ ማኅደር ላስገባችሁ ወደድኩ፡፡ ግን ግን ወዴት እየሄድን እንደሆነ አሁንም መጠየቅ እፈልጋለሁ – እናሳ “ወዴት እየሄድን ነው?”

Go toTop