ስለ ቅዱስ ዮሐንስ በዓል – ግጥም

ከዳንኤል ጎበዜ

ቅዱስ ዮሐንስ  የአዲስ ዘመን ንግሥ

የወንዙ ዉሃ ሙላት ሲቀናንስ

ደመናዉ ሁሉ ድርስ ምልስ

የሸቱ ዛላ ጥንቅሽ የጸሃይ ድምቀቱ መንፈስ

የአዲሱ አዋጅ ቀጠሮ ሲደርስ

የናባዬ የነማዬ ነጭ ልብስ አመቱን ሁሉ የሚያካክስ

የጮፌዉ ማማር የግጫዉ ልብስ።

በጧት ለጸሎት ገስግሰዉ

ንስሃ ገብተዉ ስጋ ወደሙን ተቀብለዉ

አስራት ኩራቱን ከፍለዉ

ስዕለታቸዉን አበርክተዉ

ላጡ ድሆች መጽዉተዉ።

 

ቅዱስ ዮሐንስ

የአበባ ቆሎ ሲፈካ

ሰፈር ታድሞ ሲያወካ

ቀይ ደሮ በራፍ ላይ ሲያንካካ

የገቢያ ዋጋ ጣራ ሲነካ።

ያለዉ በግ አርዶ

የሌለዉ ዘመድ ጋ ሂዶ

ደሮ ያጣ ጎመን ቀምሶ  አዲስ አመት ተስተናግዶ

በጤና ላከረመዉ ላምላኩ በጸሎት ሰግዶ

ደሳሳ ጎጆ በንቁጣጣሽ ተሽጎድጉዶ

የአበባ ቆሎ ሲፈነጥቅ ትንሽ ምጣድ ተጥዶ

የቡናዉ ጭስ ነዉዶ ምርቃኑ ተንጎድጉዶ

አዲሱ አመት ተወልዶ።

ቅዱስ ዮሃንስ

የአበባዉ መፍካት ፈጥኖ

የጽሃይ ብርሃን የሰማዩን አድማስ ከይኖ

ያረንጓዴዉ  ዉበት የቀስተ ደመና ጃኖ

በንቁጣጣሽ ተኮፍኖ

የተስፋ ዘመን ደስታ ሆኖ።

ቅዱስ ዮሃንስ

ቤተ ዘመድ ተጠራርቶ

ጎረቤት ሁሉ ተገናኝቶ

አብሮ በልቶ አብሮ ጠቶ

ያለፈዉን አዘክሮ ለመጭዉ ዘመን ተጽናንቶ

ሙሉ ልቡን ለአምላክ ሰቶ

አመቱን ለመስራት ተግቶ

እግዜር ኢትዮጵያዉንን በአሜሪካን ጎብኝቶ

ቅዱስ ኡራኤልን በሚኒሶታ አምቶ

ኪዳነ ምህረትን ሰቶን በበረከቱ ሞልቶ

ምእመናንን አፋቅሮ ከሃናቱን  አበርትቶ

ዘመን ያልሻረዉ ጌታ ሁሌም እኛን ጎብኝቶ

ወስብሃት ለእግዚአብሄር

ከዳንኤል ጎበዜ

ተጨማሪ ያንብቡ:  አርቲስት ግሩም ኤርሚያስ የጥፋት ሐዋርያ ሲሆን
Share