March 24, 2017
17 mins read

እኛ ስናደርገው ትክክል ሌላው ሲያደርገው ወንጀል – ይገረም አለሙ

የፖለቲካ ባህላችን ከጅምሩም ያላማረበት በሂደትም መሻሻል የማይታይበት ሆኖ ዛሬም በትናንቱ መንገድ ከመንጎድ መውጣት ባለመቻላችን ለገዢዎች እንደተመቸን አለን፡፡ብልሹው የፖለቲካ ባህላችን ከሚገለጽባቸው መንገዶች አንዱ ሌላው ሲናገረው ወይንም ሲሰራው ወንጀል ያልነውን አኛ ስንሰራ ስንናገረው እንደ መልካም ነገር ይታይልን መባሉ ነው፡፡

ነጋዴ በገበያ ውስጥ መቆየት የሚችለው እቃውን የሚገዛው እስካገኘ ድረስ ነው፡፡የፖለቲካው ነጋዴዎችም ከገበያው መውጣት ሲገባቸው ብዙ ባያተርፉም ሳይከስሩ መቀጠል መቻላቸው ገዢ በማግኘታቸው ነው፡፡የገዢው አይነት ግን ይለያያል፣አንዳንዱ ጥሎበት በውልደት ይሁን በእድገት ተክኖት የነገሩትን ተቀብሎ ከማስተጋባት ውጪ ለምን አንዴት ማን? ወዘተ ብሎ መጠየቅና ማረጋገጥ አልፈጠረበትምና ጥሩ ሸማች ነው፣ሌላው ከትርፉ ወይንም ከፍርፋሪው ይደርሰዋልና ገዢ ባይሆንም ያሻሽጣል፤አንዳንዱ ደግሞ ሌላውን በመጥላቱ ብቻ  ከዚህኛው ወግኖ ያናግዳል፡፡ ይህ መድሀኒት ያልተገኘለት የፖለቲካ ባህላችን በሽታ ነው አንግዲህ በፖለቲካው ለሚነግዱ ምቹ ሁኔታ የፈጠረላቸውና ያወገዙትን እየፈጸሙ፣ የኮነኑትን እየተናገሩ ባያተርፉም ሳይከስሩ በገበያው ውስጥ እንዲኖሩ ያበቃቸው፡፡ ይህ በሽታ ፈውስ የሚያገኘው በራስ ላይ መዝመት ሲቻል ነው፣ይህን ለማድረግ ወኔው ያላቸው ደግሞ በጣም ጥቂቶች ናቸውና የፖለቲካ ባህላችን ሳይሻሻል ከነበሽታው የመቆየቱ እድል በጣም ሰፊ ነው፡፡ ብዙ ዘበዘብኩ መሰለኝ፣ምን ላድርግ ይህን የወንዝ ውኃ የሚያጮኸው እውስጡ ያለው ድንጋይ ነው ይሉት ሆኖብኝ ነው፡፡

ይህን ሁሉ ለማለት ያበቃኝ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ከነበረው አቶ ይልቃል ጌትነትና የአንድነት ም/ል ሊቀመንበር ከነበረው አቶ ግርማ ሰይፉ ሰፈር የሚሰማው ነገር ነው፡፡ እነርሱ ከገበያው ላለመውጣት የሚያደርጉት ጥረት ነውና ስራቸው ነው እንበል፣ ዙሪያ ከቦ የሚያጨበጭው፣ በርቀት ሆኖ የሚያስተጋባው ግን ይገርማልም ያሳዝናልም፡፡የሰጡትን ተቀብሎ መልሶ የሚናገር በቀቀን፣ የገደል ማሚቱ ወይንም መቅረጸ ምስልና ድምጽ ነው፡፡ ፈጣሪ ለሰው ልጅ አእምሮ የሰጠው እንዲያመዛዝንበት ነበር፣

ይልቃል ሰፈር፡ ወያኔ የድርድር ግብዣ አድርጎ እንዴት እንደምንደራደር  ቀድመን እንነጋገር ባለበት ግዜ የይልቃል ቡድን ጥሪ ደርሶት ፓርላማ ተገኘ፡ ሀሳቡንም ሰጠ፡፡ ልብ በሉ በዚህ ግዜ  ወያኔ መጥራቱም ፣ጥሪውን ተቀብሎ መሄድም ለይልቃል ቡድን ትክክል ነበር፡፡በሻይ ሰአት የሰማያዊ ህጋዊ ወኪሎች እናንተ መስላችሁን ተሳስተናል፣ህጋዊዎቹ ወኪሎች ሌሎች መሆናቸው ስለተነገረን ተብሎ ከአዳራሹ ተሰናበቱና የአቶ የሺዋስ ወገን በውይይቱ እንዲካፈል ተደረገ፡፡ እዚህ ጋር ሲደረስ  የወያኔን ጥሪ መቀበልም ከወያኔ ጋር መደራደርም ወንጀል ሆኖ ከመነገሩ አልፎ እነ የሺዋስን በወያኔነት መፈረጅ ደረጃ ተደረሰ፡፡ በእውነቱ ይህ ማህበረሰቡን መናቅ ነው፡፡ለነገሩ ይገባቸዋል ለምን አይንቁን፣ እንዴት ብሎ መጠየቅ የተሳነን፣ ምነው እናንተ ስትናገሩ ስታደርጉት ወንጀል አልሆነ ብለን መጠየቅ የማይሆንልን  ለምን አንናቅ፡፡

አባቶቻችን አንገት የተሰራው አዞሮ ለማየት ነው ሲሉ ወደ ኋላ ዞሮ መመልከት ማለታቸው አይመስለኝም፣ የዛሬው ድርጊት.ንግግር  ከትናንቱ እንዳይቃረንና ውርደት እንዳያስከትል መምከራቸው እንጂ፡፡ የእነዚህ ደግሞ በአንድ ቀን ጀንበር ነውና የሆነው አንገትም አላስፈለገው፡፡ ጠዋት አነርሱ ሲካፈሉ ትክክል ነበር፣ ከሰአት ሌሎች ሲያደርጉት ወንጀል ሆነ፡፡ አጀኢብ ነው፡፡ ይህን እየተቀባበለ የሚያስተጋባው ደግሞ ጉድ! ያሰኛል፣ ሌላ ምንስ ይባላል ምንስ ይደረጋል፡፡

አቶ ግርማ ሰይፉ ሰፈር፣ እዚህ ሰፈር ደግሞ ስለ አዲስ ፓርቲ ምስረታ እየተወራ፣ ደጋፊዎች አታሞ ለጉመው እየጨፈሩ ባይነግዱም የሚያንግዱት ደግሞ ወሬውን እያሰራጩ ነው፡፡ አዙሮ የሚያይ አንገት ጠፍቶ እንጂ አቶ ግርማ ስለአዲስ ፓርቲ ይሉት የነበረውን ማስታወስ ቢቻል ውካታ ጋጋታው እንዲህ ባልሆነ ነበር፡፡አቶ ግርማ አንድነት ከፈረሰ በኋላ ስለ አዲስ ፓርቲ ምስረታ በፌስ ቡክ ገጻቸውና የርሳቸውን ጽሁፍ በሚያወጡትና በርሳቸው ላይ የሚጻፉ ፅሁፎች ላይ ማእቀብ በሚጥሉ ድረ ገጾች ላይ ከጻፉዋቸው  ጥቂቱን በአስረጅነት ላቅርብ ፡፡

  1. አቶ ተመስገን ዘውዴ፣እኝህ ሰው በምርጫ 97 በቅንጅት ተመርጠው ፓርላማ ውስጥ በተለይ በሙያቸው በኢኮኖሚ ጉዳይ ከአቶ መለስ ጋር ሲከራከሩ ብዙ ሰው ያውቃቸዋል፣ አንድነት ፓርቲ ውስጥ ደግሞ ም/ሊ እና የፋይናንስ ሀላፊ ነበሩ፡ ከዛ በኋላ በምን ኃላፊነት እንደቀጠሉ ባላውቅም አንድነት አቶ ትእግስቱ እጅ ላይ እስከወደቀበት ግዜ ድረስ በአባልነት ዘልቀዋል፡፡ አንድነት እንዳይሆኑ ከሆነ በኋላ ከገዳይ አስገዳዮቹ አንዱ የነበሩት አቶ ግርማ ሰይፉ በየመገናኛ ብዙኃኑ የአዞ አንባ ሲያነቡ አቶ ተመስገን ፓርቲ የመመስረት እንቅስቃሴ የመጀመራቸውን ዜናም ውግዘትም የሰማነው ከአቶ ግርማ ነበር፡፡
  2. አቶ ብሩ ብርመጂ፣ እኚህም ሰው ከአንድነት ምስረታ እስከ እለተ ሞታቸው ከአቶ ግርማ ጋር አንድነት ውስጥ የነበሩና ከአቶ ተመስገን ጋር ፓርቲ ለመመስረት የተንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ነገር ግን ከዚህ ዓለም በሞት በተለዩበት እለት አቶ ግርማ ሞታቸውን በፌስ ቡክ ያረዱን አዲስ ፓርቲ ለመመስረት በእንቅስቃሴ ላይ የነበሩት በሚል የምጸት አገላለጽ ነው፡፣
  3. ኢ/ር ግዛቸው፣የሚታወቁ ስለሆነ ስለሳቸው መግለጽ አያስፈልግም፡፡እዚህ ጋር ያመጣሁቸው አቶ ግርማ ከየት እንዳመጡት ባይታወቅም ፓርቲ ሊመሰርቱ ነው ብለው አንድ ሰሞን ሲወርዱባቸው ስለነበረ ነው፡፡

ይብቃኝ፤ታዲያ ዛሬ የአቶ ግርማ አዲስ ፓርቲ መመስረት ትክክልምተገቢም የሚሆነው በምን አግባብ ነው፤ወይንስ ከላይ የተጠቀሱት ሰዎች የፓርቲ መሪ ለመሆን ብቃት የሌላቸው አቶ ግርማ ግን የበቁ የነቁ ሆነው፤ነገራችን ሁሉ አጀኢብ የሚያሰኝ ነው፡፡ አቶ ግርማ የፓርቲ ሊቀመንበር መሆን ቀርቶ  የአመራር አባልም፣ ይህንንም አይደለም አባል እራሱ ለመሀን  የማይገባው ሰው ነው፡፡ ይህን ደግሞ ዝም ብዬ እንደ እሱ ያለ መረጃና ማስረጃ ሰው ላይ የምለጥፍ ሳይሆን እነሆ መረጃ ማስረጃ፡፡ (ይቅርታ ድርጊቱን ሳስበው አንቱ ለማለት ህሊናየ አምቢ ብሎኝ ነው፡፡) ብዙ ማስረጃዎች ማቅረብ እችላለሁ ግን የማስረጃ ክብደቱ ብዛቱ ሳይሆን እንደ ጉዳዩ ጭብጥ ማስረዳቱ ነውና ጥቂት ይበቃኛል፡፡በቅድሚያ ግን ጭብጥ ላስጨብጥ፣ አይደለም የፓርቲ መሪ፣ የፓርቲ አባል ለዴሞክራሲያዊ መብቶች መረጋገጥ፣ ሀሳብን ለመግለጽ ነጻነት መከበር፣ ለህግ የበላይነት መስፈን ወዘተ የሚታገል መሆን አለበት፣ለመታገል ደግሞ አስቀድሞ ማመን ይጠይቃል፡፡የማቀርባቸው ማስረጃዎች የሚያሳዩት አቶ ግርማ እንዲህ አለመሆናቸውን ወይንም የአቶ ግርማ ሰብእና ከዚህ ተቃራኒ መሆኑን ነው፡፡

ማስረጃ አንድ፣ አቶ ግርማ በአንድነት ምክር ቤት፣ ወቅቱ 2001 ዓም ሀምሌ ወር አጋማሽ ነው፣የአንድነት ም/ቤት ሰብሰባ ተቀምጧል፣አጀንዳው ምክር ቤቱን የጭቅችቅና የንትርክ መድረክ አደረገዋል በተባሉ የምክር ቤት አባላት ላይ የእገዳ ውሳኔ ማሰለፍ የሚል ነው፡፡ እንዳልካቸው የሚባል በዛን ግዜ ወጣት የም/ቤት አባል ይህ ምክር ቤት አስተያየት የሚንሸራሸርበት፣ በልዩነት ሀሳብ ክርክር የሚካሄድበት እንዲሆን አይፈለግም ማለት ነው፣የምትነግሩትን ብቻ የሚቀበል አጨብጫቢ ም/ቤት አንዲሆን ነው የሚፈለገው፣በዚህ አጀንዳ መነጋገር አይደለም ጭራሽ አጀንዳ ሆኖ መቅረብ የለበትም በማለት ይቃወማል፡፡( ቃል በቃል አልገልጬ ይሆናል፡) በዚህ ግዜ ፈጥኖ እጅ ያወጣውና እንዲናገር የተፈቀደለት አቶ ግርማ ሰይፉ ይኼው አልጠሩም ሰንኮፋቸው እዚህ አለ፣ምንም ውይይት አያስፈልግም ድምጽ ይሰጥ አለ፤ ድምጽ ተሰጠ በአንድ ድምጸ ተአቅቦ ተወሰነ፤ እንዳልካቸው መልቀቂያ አቅርቦ  ከም/ቤት ወጣ፤ (ላስጥረው ብዬ ነው)

ማስረጃ ሁለት አቶ ግርማ በሰንደቅ ጋዜጣ፣  ሐምሌ 3/2005 ዕትም አቶ ግርማ ሰይፉ ከጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ዘሪሁን ሙሉጌታ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ያልተገቡ መልሶች እየሰጠ ቆይቶ  በፓርላማ ቆይታው የሚጠበቅበትን ያህል  እንዳልሰራ ለቀረበለት ጥያቄ  የሰጠው መልስ “በሚቀጥለው ምርጫ ተመርጠህ ቦታውን ለምን አንተ አትወስደውም፣  በደንብ አልተናገረክም የሚለኝ ካለ ደግሞ እራሱ በምርጫ ተወዳድሮ ወደ ፓርላማ ገብቶ ሊናገር ይችላል፣አንተ ተመርጠህ ግባና ስራው አንተ ስትገባ ሰርተህ ታሳየናለህ የሚል ነበር”  ስለ አንድነት መድረክ ወቅታዊ ሁኔታ ለተጠየቀውም “ አላወቅም” በማለት ነበር የመለሰው፡፡ ግርማ በዚህ ወቅት የአንድነት ም/ል ሊቀመንበር መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

ማስረጃ ሶስት፣ግርማና ግዛቸው፣ በዚህ በኩል ሊቀርብ የሚችለው ስለ ግርማ ማንነት የሚያሳይ መረጃ ብዙ ነውና ራሱ ከጻፈው ሁለቱን ብቻ ላቅርብ፡፡ የነጻነት ዋጋ ሰንት ነው በሚለው መጽኃፉ ገጽ 91 ላይ “ኢ/ር ግዛቸውን ምርጫው እንዴት ነው የሚል ጥያቄ ጠይቀው …ከክልል በሚሰማው መረጃ ተጨናንቆ በትክክል በደረሰው መረጃ መሰረት ምርጫው ችግር ያለበት መሆኑን ሲገልጽ ይህንኑ እንደማንኛውም ዜና ማቅረብ ሲጠበቅባቸው” በማለት ለኢንጀነር ግዛቸው ጥብቅና የቆመው ግርማ ሰይፉ አንድነት ከፈረሰ ከአመት ግድም በኋላ የዶ/ር መረራ የቡዳ ፖለቲካ በሚል ርዕስ በጻፈው ጽሁፍ አንድነት ከመድረክ ወጥቶም በግዛቸው ሸፈራው መሪነት ቢቀጥል መንግስት ይህን አሳፋሪ እርምጃ አይወስድም ነበር፡፡ ምክንያቱም ባለበት የሚረግጥ ፓርቲ ማንም አይፈራውም፡፡በማለት ኢኒጅነሩን በወያኔነት ይፈርጃል፡፡

ይህ ሰው ነው እንግዲህ የዴሞክራሲ ታጋይ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ፣ ለመናገር ነጻነት ተከራካሪ፣ወዘተ ሆኖ ለመታየት የሚሞክረው ፓርቲ መስርቼ እታገላለሁም የሚለን፤

“ለመደመጥና ለመከበር ብሎም ተከታዮችን ለማፍራት ሐቀኝነት ወሳኝ የተራክቦ መለያ ነው” (መሪነት ገጽ  198 ኮ/ል መርሻ ወዳጆ 2002 )

 

 

 

 

 

Previous Story

አየር ኃይል ውጥረት ውስጥ ገብቷል | 11 አብራሪዎች ታስረዋል

Next Story

ባንዲራው የ ‘ሁላችንም’ ነው!! – ታሪኩ አባዳማ

Latest from Blog

blank

አርበኛ አስረስ ማረ እና ምርኮኞቹ | ስለ ፋኖ የብሔራዊ ባንክ ገዥው ያልተጠበቀ ንግግር |

#ሰበር_ዜና #AmharaFano ➢መሰከረም 29/01/2017 ዓ.ምብዙ ድሎችን አግኝተናል፣➢1️⃣115 ምርኮኛ ➢2️⃣70 እስረኞችን አስለቅቀናል➢3️⃣ 7 ብሬን➢4️⃣2 ድሽቃ➢5️⃣ 4 ስናይፐሮችን➢ለትግል የሚጠቅሙ የነፍስ ወከፍ ክላሾችንተተኳሾችን መኪኖችም ገቢ… pic.twitter.com/GbYaOAtFtr — ትዝብቱ🔔 (@Geteriew1) October 12, 2024 በፋኖ የተማረኩት ኮሎኔል
blank

ትግሉ ይጥራ – ከጥሩነህ ግርማ

የህልውና ትግሉን ወደሚቀጥለው ምዕራፍ ለማሸጋገር የኦይዶሎጂ ብዥታን ማጥራትና በመሬት ላይ ያለውን ተንኮል መጋፈጥና ማፅዳት ያስፈልጋል የህልውና ትግሉ በአማራ ብሄርተኝነት ላይ ያጠነጠነ እንደመሆኑ የመኖር አለዚያም እንደ ህዝብ  የመጥፋት ትግል ነው: ሌላው ኢትዮዽያዊ ወገን
blank

የፋሽስቱ አብይ አህመድ አሊ ኢትዮጵያ ውስጥ በአማራ ላይ እየተካሄደ ስለሚገኘው ጦርነት ከመስከረም 13 እስከ 27/2017 ዓ.ም በተለያዩ ቦታዎች ላይ የደረሰ የጉዳት !!!መረጃ:

ሸዋ በሸዋ ጠቅላይ ግዛት መርሀቤቴ አውራጃ በደራ ወረዳ ልዩ ስሙ ኮሉ በተባለ አካባቢ ላይ በሚገኙ የአማራ ተወላጆች ላይ አሸባሪው የሸኔ ቡድን ከኦሆዴዱ ጥምር ጦር ጋር ቅንጅት በመፈጠር መስከረም 22 ቀን 2017ዒ.ም ከለሊቱ
Go toTop