ኢትዮጵያን በባርነት በመግዛት ላይ የሚገኘው የወያኔ መንግስት ላለፉት 26 አመታት ኢትዮጵያን ትልቅ ሀገር ከማለት ይልቅ እንደ ትልቅ እስር ቤት፤ ትልቅ የዘር መጥፋት የሚካሄድባት ሀገር ብሎ መጥራት በሚቀልበት ደረጃ አውርዶ እየገዛት ይገኛል፡፡ በእነዚህ 26 አመታት ውስጥ በአንድ ሀገር ዜጋ ላይ መድረስ የማይገባቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፤ ፖለቲካዊ መብት ረገጣዎች፤ መሀበራዊ መብት ጭቆናዎች እና ገድያዎች በኢትዮጵያ ላይ ተፈራርቀውባታል፡፡
በማንኝውም ቦታና ግዜ በየትም አለም የተከሰቱ አምባግነን መሪዎች ከአንድ መሃጸን ውስጥ እንደተፈጠረ ፍጹም መንትዮሸ በድርጊታቸው ይመሳሰላሉ፡፡ አዲስ የተፈጠሩትም አምባገነኖች ታሪክ ሆነው ካለፉት ጨካኞች ብዙ ጭካኔና ግፍን ቀስመውና ልቀው ግፍን ያለገደብ በህዝብ ላይ የፍጽማሉ፡፡ ይህን የግፍና የጭካኔ ዘመን አንጋፋው የፖለቲካ ምሁር ፕ/ር መስፍን ወልደማሪያም ክፉ ቀን ብለው ይጠሩታል፡፡
ፕ/ር መስፍንወልደማሪያም በ 2002 ባሳተሙት አገቱኒ በሚለው መጽሃፋቸው ላይ ክፉ ቀን ብለው በሰየሙት አርእስት ስር ክፉ ቀን ጥሩ ነው የወደቀውን ለድል የጣለውን ለውድቀት ያዘጋጃል፡፡ በመግደል የሚተማመነውን ግዚያዊ ድል ለሞት ይዳርገዋል በሞት ይሸነፋል ተገድሎ የሚያሸንፍ ህዝብ ድሉ የዘላለም ነው፡፡ ክፉ ቀን ጥሩ ነው ክፋት በጎነትን አሸንፎ እንደማይዘልቅ ያሳያል፤ ህግ ቀልቡ ሲገፈፍ ዳኝነት ሚዛን ሲያጣ ጉልበት ሁሉን ደምጦ ሲወጣ የሰውነት ባህሪ ክፉው በጎው ነጥሮ ሲወጣ ያሳያል፡፡ ክፉ ቀን ጥሩ ነው፤ የህዝብን ጥሪ አንድናዳምጥ፤ ከራስ በላይ ንፋስ በሚል እምነት ላይ የቆመውን የግል ኑሮን ማንቆ እንድንበጥስ፤ እንድንተሳሰብ፤ የእድገት ጉዞ እንቅፋቶችን እንድናስወግድ ያሳስብናል፤ ሲሉ የሁሉን ህብረተሰብ ክፍል በሚቆነጥጥ አገላለጽ አስፍረውታል፡፡
ይህንን ክፉ ዘምን ያመጣብንን የህውሀት/ኢህአዴግ ስርአት ከስሩ ነቅሎ ለመጣል የሁላችንም ሃላፊነት ቢሆንም የፖለቲካ ፓርቲዎችና አመራሮቸ አብላጫውን ድርሻ ይውስዳሉ፡፡ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሃገር ሆና ባታቅም ባለፉተ 26 አመታት ውስጥ ህውሃት በታሪክ አይታ ይማታውቀውን ግፍ እና መከራ በህዝቦችዋ ላይ በመፈጸም አምባገነን መንግስት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይህን የግፍ ስርአት ለማስወግድ ሁሉም የኢትዮጵያ ፖለቲካ እየተነጋገሩና እየተደራደሩ ካልሰሩ ብዙ መጉዋዝ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ በሀገራችን ፖለቲካ እንደ እድል ሆኖ ጻድቃን የሚያንሱ ሀጢያተኞች የሚበዙባት ይመስለኛል፡፡
ህውሀት/ኢህአዴግ ሀገሪቱን ከተቆጣጠረ ጀምሮ ሀገሪቱን ወደ እስርና የስቃይ ማእከልነት ቀይሯታል፡፡ ይህ አልበቃ ብሎት፤ ባልፉት ጥቂት አመታት ፍጹም ሰብኣዊ ባህሪ በሌለው መልክ፤ ነጻነት ፍትህና አኩልነት ፈልጎ፤ በመላው ሀገሪቱ ለተቃውሞ በወጡ ሰላማዊ ህዝብ ላይ፤ ፍጹም ርህራሄ በሌለው መልክ በታጠቁ የህውሀት ወታደሮች ሲገድል ሲያሰቃይ እንዲሁም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍል እየለቀመ፤ ወደተለያዩ እስርቤቶችና ወታደራዊካ ምፖች በማጉዋጉዋዝ ለእስርና ለስቃይ ዳርጉዋቸዋል፡፡ ይህም አልበቃ ብሎት ምንም የህሊና እና የህግ ዳኝነት ሳያግደው፤ በመዳፋቸው የወደቀውን ህዝብ ጨፍልቆ ለመያዝ ስጋት በገጠማቸው ግዜ፤ በመክላከያ ኢታማዦር ሹም ጅነራል ሳሞራ ዮኑስ (ይህን ሰው በመከላከያ ዩኒቨርሲቲ ስማርና በመከላከያ ኢንዱስትሪ ውስጥ ስሰራ አውቀዋልው፤ ፍጹም ዘረኛና ከሱ ዘር ውጪ የሆኑትን የመከላከያ አባል በፍጹም የማያምን አና የሚዘልፍ ነው) እና በመከላከያ ሚኒስትሩ ሲራጅ ፈጌሳ የሚመራ የአስቸኩዋይ ግዜ አዋጅ (ኮማንድፖስት) አቁዋቁመው፤ ህዝብን በከፍተኛ ጭንቀት ቀስፎ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ወጣቶችን አዛውንቶችን እስርቤት አጉርዋል፡፡ ይህ የአስቸኩዋይ ግዜ አዋጅ በከፍትኛ የህውሀት ወታደራዊ አመራሮች እየተመራ በኢትዮጵ በተለያዩ ከተሞች በተለይም በአማራና በኦሮሚያ ከተሞችና ገጠሮች፤ የደቡብና የመሀል አዲስአበባን ጨምሮ ህዝብን የማሰር ይመግደልና የማሰቃየት ሀላፊነት የተሰጠው ነው፡፡
በአሁኑ ሰአት መያዣ መጨበጫ ያጣወ የህውሀት/ኢህአዲግ መንግስት በመላ ሀገሪቱ ተቃውሞ ስለተነሳበት የሚያስራቸውና የሚገላቸው ንጹሀን ቁጥር በውል ማወቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ በተቃራኒው ግን ይህ የወያኔ ድርጊት የሚያሳየው ድርጅቱ ተስፋ መቁረጡን ነው ለዚህ ሁሉ ግፍ ከፋይ አለው አስክፋዩ ህዝብም ራሱን እያዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህም ነው ከላይ የፕ/ር መስፍን ወልደማሪያምን ክፉ ቀን ጥሩ ነው ብለው በመጽሀፋቸው ያስቀመጡትን የጠቀስኩት፡፡ እውነት ግን ለምን የዚህ ግፍ ዘመን በኢትዮጵያ ላይ ረዘመ፤ እንደ ፕ/ር መስፍን ሀሳብ ከሆነ ክፉቀን ወይም አሁን የኢትዮጵየ ህዝብ ላይ እየደረስ ያለው ስቃይ ነገ ላይ የሚመጣው ብሩህ ቀን ጠንካራ መሰረት ይጥላል ባይ ብሆንም፤ የስቃይ መብዛቱና መርዘሙ ያሳስበኛል፡፡ የዚህ ግፍ ዘመን ማጠር የሚያስደስተኝም ቢሆንም ለምን እንደረዘም ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ዘወትር ለውጥን እየተመኘ የተቀመጠ ህዝብ ነው፡፡ ታዲያ ለውጥ ያሻ ህዝብ ለምን የፍላጎቱን አላገኘም፤ ለምን የግፍ ዘመን ረዘመበት፤ እንደረዳት ፕ/ር መራራ ጉዲና ሀሳብ በበርካታ ቁርሾዎች የታጨቀውን የሀገራች የተቃዋሚ ፖለቲካ አሁን ካለበት ደረጃ ከፍ አድርጎ ከፈላጊው ህዝብ ጋር ለማገናኘት የመነጋገር የመወያየት ባህል ሊፈጠር እንደሚገባው ያሳስባሉ እኔም የዚህ ሀሳብ ዋንኛ ተጋሪ ነኝ፡፡ የግፍ ዘመኑም መርዘም ቀዳሚ ምክንያት የመነጋገር የመወያየት እና የመደማመጥ እጥረት ነው ብዬም ለመመለስ እደፍራልው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከኔ በላዬ ላሳር የሚለውን አስተሳሰብ ጥሎ ከአንድ ሁለት እንደሚሻል አምኖ በጋራ መስራትና፤ ያንተ ሆድ ስለሞላ ሌላው አልራበውም አለማለት፤ እና የችግሩ መፍትሄ ባትሆን እንኩዋን፤ እንቅፋት አለመሆን የምንመኘውን ነጻነት ሊያጎናጽፈን ይችላል፡፡
ግ. ተ. አበጋዝ፤ መጋቢት፤ 2009፤ ሳስካቱን፤ ካናዳ