March 12, 2017
6 mins read

ጨለማውን ከማውገዝ አንድ ሻማ ማብራት -መስቀሉ አየለ

ሞት በቆሸው ሰፈረ የሚል ዜና በአለም አቀፍ የዜና ማሰራጫዎች ጭምር ይናኛል፤ ወትሮስ በዚያ መንደር ህይወት ያለ ይመስል፤ ሞቶ በማለፍና እየሞቱ በመኖር መካከል ልዩነት በማይታይበት፤ ሞትና ህይወት ድንበር ከመጋራት ባለፈ ተወራራሽ ትርጉም በያዙበት የዚህ ክፉ ስርዓት መገለጫ በሆነ በዚህ መንደር;ድሆች የመኖር ተስፋችን ብለው የተደገፉት ሃብታም በልቶ ያስታወከው- አላምጦ የተፋው ቅርሻት ለነርሱ ግን የዕለት እስታንፋሻቸው ሆኖ እንዳልኖረ ዛሬ ሸክሙ በዝቶበት እርሱም ከስሩ የተኮለኮሉትን እኒህን የምድር ጎስቋሎች እስከ ወዲያኛው ይዞዋቸው ሄደ፤ ወያኔ የእንጨት ለቃሚዎቹን ልጅ በጥይት አረር ሲቆላ አንድ ነገር የማይተነፍሰው ቢቢሲ ሳይቀር ዜናውን የዘገበው “Many people had been scavenging at the site to make a living, and some even resided there permanently” ብሎ ነበር። የጥንብ አንሳ ኑሮ የሚኖሩ ማለቱ ነው። ጥንባንሳ ለማለት ፈልጎ ነው።

አዲስ አበባ እንግዲህ ዛሬም መቀነቷን አጥብቃ እንደተለመደው አስከሬን ስትቆጥር ትውላለች። የትንሽ ቀን ጉምጉምታ ከመሆን የማያልፍ ዜና፤

በአንድ ወቅት እግር ጥሎኝ አዲስ አበባ ጎራ ብየ ነበር፤ ፕላዛ ሆቴል ገባ ብሎ በመናኛ ክፍል ተከራይቶ የሚኖር አብሮ አደጌ ጋር ነበር ያረፍኩት። ወደ መንደሩ የሚያስገባው መንገድ ላይ ውሻ ሞቶ ተጥሎ ኖሮ ሰው ሁሉ አፍንጫውን እያፈነ ያልፋል፤ መኪና ያለው መስኮቱን ዘግቶ ይሄዳል። ይህን ማድረግ የማይችሉ ወይንም የማይገባቸው ህጻናት ግን ከመከራው ይቋደሳሉ። ማዘጋጃ ቤት የሚባል መሬት ከመቸብቸብ ውጭ ሌላ ስራ የሌለው ጋንግሪን ተስፋ በማይደረግበት በዚህ ስርአት አልባ ከተማ የውሻውን ባለቤቶች ጨምሮ ሃላፊነት የሚሰማው ጠፍቶ መንደሩ እንዲህ ሲታመስ መፍትሄ ለመፈለግ ቆም ብሎ ማሰብ የሚችል ሰው እንደሌለ ግልጽ በመሆኑ ምንም እንግዳ ብሆንም የቤቱን አከራይ ባዶ የናፍጣ ጠርሙስ እንዳላቸው ጠየኳቸውና ሰጡኝ። ከዚያም በሰፈሩ ውስጥ ከሚገኝ አንድ ሱቅ ጎራ ብዬ አንድ ሊትር ናፍታ ገዛሁና በውሻው እሬሳ ላይ አፍስሸ ክብሪት ብለኩስበት ጸሃይ አቀርንቶት ኖሮ በጥቂት ደቂቃወች ውስጥ እንደ ችቦ ነደደ፤ በአንድ ሊትር ናፍታ ትንሽዬ አቢዮት ተካሄደ ማለት ነው።

ዛሬ ድፍን አዲስ አበባን የሞላት ይኽ የሞት ዜና የሁልግዜ ውርደታችን ሆኖ በአለማቀፍ ደረጃ አንገታችንን ሲያስደፋን በችግሩ ላይ ከማላዘን የችግሩን ምንጭ ማደረቁ ነበር እንባችንን ለዘላለሙ የሚያብስልን። ይህን ዜና በምሰማበት በዚህ ቅጽበት አጠገቤ ያለው ወዳጀ አንድ የመንግስት ቢሮ ውስጥ ስለሚደረግ ስብሰባ የሚያሳይ ፎቶ እያሳየኝ ነበር። ከሰዎቹ ጀርባ የዞምቢውን ፎቶ ገጭ አድርገውታል፨ ሰውየው ከሞተ ከአራት አመት ቦሃላም ዛሬም በሙት መንፈስ መገዛቱን ስራዬ ብለው የያዙት ከተራ የመዝገብ ቤት ሰራተኛ እስከ ኃይለማርያም ደሳለኝ ቢሮ በየመንግስት ቢሮው ፎቶውን መለጠፍ የስራ ዋስትና ማረጋገጫ ብሎም የዜግነት ፓስፖርት ሆኖ መኖሩን መቀጠሉ ነው። በአንድ ወቅት የኢራቅ ህዝብ ብዛት ስንት ነው ሲባል ሰላሳ አራት ሚሊዮን ነው አስራ ሰባት ሚሊዮኑ ግን የሳዳም ሁሴን ፎቶ ግራፍ ነው ይባል ነበር። ዛሬሳዳምም ፎቶዎቹም ኢራቅ ውስጥ ባላመኖራቸው የህዝብ ብዛቱ በግማሽ ቀንሷል ማለት ነው። የኛም አገር የቆሻሻ ምንጭ የጣእራችን መንስኤ ሰዎቹ ተንደግፈውት የሚኖሩት በየቢሮው የተሰቀለው እነርሱ ራእያችን የሚሉት ለእኛ ግን የተጫነብን መርገምት ነው። የሞት ዜና ከሰለቸን፣ውርደታችንን እንደ ኒሻን አጎንብሶ መቀበሉ ከበቃን ዘቻውና ውግዘቱ ቆሸ ሰፈር ላይ ሳይሆን በየቢሮው ከተሰቀለው እውነተኛው የቆሻሻ መፈልፈያ ማህጸን ላይ መሆን አለበት።እርሱ ከላያችን ሲወገድ ያኔ ክብራችን ይመለሰል። ያኔ በአለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጥንባንሳ (ስካቬንጀር) ከመባል እንድናለን።

Go toTop