በትምህርት ሥርዓቱና በመምህራ ላይ የተደቀነ አደጋ | ዜና ትንታኔ

በታሪክ አጋጣሚ በሥልጣን ላይ የተቆናጠጡ ገዢ ሃይሎች ሁሉ ሕዝብ የሚያነሳቸውን የመብት ጥያቄዎች በአግባቡ ሲመልሱ አልታዩም። ከሕዝብ ፍላጎትና ጥያቄ ይልቅ የራሳቸውን የፖለቲካ ፍላጎትና ጥቅም በማስቀደም ሕዝቡን ለርሃብ፣ ለድንቁርና፣ ለስደትና ውርደት፣ አገሪቷን ለውድቀት ዳርገዋል።

በተለይ ወያኔ/ኢህአዴግ በመማር ማስተማር ሙያ ላይ የተሰማራውን ሃይል የተለያዩ ስያሜዎችን በመስጠትና በወያኔያዊ ግምገማ በማስመረር ልምድ ያካበቱ መምህራንን ከሥራ ማባረሩና ሙያውን ለቀው እንዲሄዱ ተጽዕኖ ማድረጉ ለትምህርት ውድቀት አመላካች አርምጃ ነው።

በእውቀቱ፣ በክህሎቱና በአስተሳሰቡ የዳበረ ብቁ ዜጋ እንዳይፈጠር የተሸረበው ሴራ ተሳክቶ ዛሬ ለምን ብሎ የሚጠይቅ ትውልድ አለመፈጠሩ የወያኔ/ኢህአዴግ ትውልድ ገዳይ የትምህርት ፖሊሲ ውጤት መሆኑ ሰው ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ሐቅ ሆኗል። በመማር ማስተማር ሙያ ላይ የተሰማሩ መምህራን የወያኔ ሥርዓት እያደረሰባቸው ባለው ግፍ፣ጭቆናና የመብት ጥሰት ስራቸውን እየለቀቁ ወደ ተለያዩ የስራ ዘርፍና ቦታዎች መፍለስ ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል። በዚህ አኳያ በአዲስ አበባ ከተማ በሚያስተምሩ መምህራን ላይ በሚደርስባቸው ዓይን ያወጣ የዘር መድልዎ፣ የፖለቲካ ጫና፣ የደመወዝ ማነስ፣ በመምህራን ውስጥ ከወያኔ ደህንነት መሰሪያ ቤት ተቀጥረው ስለላ በሚያካሄዱ የመምህራንና የወጣት ማህበራት ስላዮች ክትትል፣ የእርካን ጭማሪ መታገድ፣ የትምህርት እድልና እድገት አለመኖር ምክንያት 1500 መምህራን የስራ መልቀቂያ ለአዲስ አበባ ክልል ትምህርት ቢሮ አቅርበው 700 መምህራን የመምህርነት ሙያቸውን እንደለቀቁ ማወቅ ተችሏል። የእድገት፣ የለውጥና የሥልጣኔ መሰረት የሆነው የትምህርት ጥራት መወደቅ፣ ትምህርት ቤቶች ከሕዝብ ቁጥር እድገት ጋር አለመጣጠም፣ የትምህርት ግብአቶች በበቂ ሁኔታ ያለማሟላት፣ ለመማር ማስተማር ሂደት ምቹ ሁኔታዎች አለመፈጠራቸው፣ ለመምህራን ማህበራዊ ከበሬታ ያለመስጠት፣ በየወቅቱ አያደገ ከሚሄደው የኑሮ ውድነት ጋር የሚጣጣም የደመወዝ ጭማሪ ያለመኖር ፣ ባጠቃላይ የመንግስት አያያዝና እንክብካቤ ተስፋ አስቆራጭ ደረጃ ላይ በመድረሱ መምህራን የማስተማር ሥራቸውን እየለቀቁ በብዛት እየፈለሱ ይገኛሉ።

በዚህ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑና ልምድ ያካበቱ መምህራን ፍልሰት የተነሳ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች እስከመዘጋት ደርሰዋል። እንዲሁም ሕጻናትና ወጣቶች ትምህርት እንዲያጡ ተደርገዋል።ለአብነት ያህል በባሕርዳር ከተማ አካባቢ አራት ትምህርት ቤቶች በመምህራን ፍልሰት የተዘጉ ሲሆን የመምህራን እጥረት በተከሰተባቸው አንዳንድ ት/ቤቶችም የአስረኛ ክፍል ትምህርታቸውን አጠናቀው ባገኙት ዝቅተኛ ውጤት ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ማለትም መሰናዶ ትምህርት ቤቶች፣ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችና የተለያዩ የስልጠና ተቋማት ገብተው ለመማር ያልቻሉትን በመልመል የአሰር ቀን የትውውቅ ስልጠና በመስጠት በሰሜን ጎንደር ፣ በሰሜን ወሎ እንዲሁም በሌሎች ዞኖች ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በቋሚ ቅጥር ወደ ማስተማር ሥራ እንዲሰማሩ ተድርጓል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አሰፋ ማሩ – ልክ የዛሬ 18 ዓመት ወደ ቤቱ ሊገባ ሲል በወያኔ ተረሽኖ ሕይወቱ አለፈ

በ2008 ዓ.ም የተከሰተውን የመምህራን እጥረት ለመቅረፍ በሚል ሰበብ በተመሳሳይ መንገድ አስረኛ ክፍል ያጠናቀቁ ተማሪዎች ቅጥር እየተፈጸመ ከመሆኑም በላይ በመምህራን ት/ት ኮሌጆች በዲፕሎማ እንዲሰለጥኑ ለማስተማር ሥራ ልምምድ (Teaching Practice) ከደብረብርሃን፣ ከደሴ–ወዘተ መምህራን ኮሌጆች የወጡት ተማሪዎች የቅጥር ፎርም ሞልተው በዚያው በማስተማር ሥራ እንዲቀጥሉ የተደረገ ሲሆን ያላጠናቀቁትን ትምህርት በክረምት (ሐምሌና ነሐሴ) ተምረው እንዲመረቁ፣ ከአስረኛ ክፍል ስልጠና ሳይወስዱ በቀጥታ የተቀጠሩትም በአራት ተከታተይ ክረምት በመምህራን ትምህርት ኮሌጆች ገብተው እንዲሰለጥኑ ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በተላለፈው መመሪያ መሰረት ከ2007ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።

ይህ በወያኔ አገዛዝ በትምህርት ጥራትና በመምህራን ላይ የሚፈጸመው ዘርፈ ብዙ በደል ደርግ የተባለው የፋሽስቶች ጥርቅም የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር መሪዎችን አስሮ ፣ገድሎ፣ አገር ጥለው እንዲወጡ አድርጎ፣ የማህበሩን ጽ/ቤት ለአራት ዓመታት ዘግቶ በነበረበት ወቅት መምህራን ለራሳቸውና ለሕዝብ መብት በመቆማቸው በአገሪቱ ውስጥ በሁሉም ቦታዎች ብዙ መምህራንን በመግደሉ፣ በማሰሩና እንዲሰደዱ በማደረጉ ትምህርት ቤቶች የመምህራን እጥረት ገጥሟቸው ነበረ። ደርግ የመምህራን እጥረትን ለማቃለል 12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈትነው ወደ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ሊያስገባ የሚችል ነጥብ ያላገኙትን ተማሪዎች በድጎማ መምህርነት ቀጠረ። በትምህርት ጥራት ላይ ችግር ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲፈጠር አደረገ። ለአገርና ለሕዝብ ደንታ የሌላቸው አምባገነኖች በቦታና በጊዜ ቢለያዩም መገለጫቸው ግን አንድ ነው። በሕዝብ ላይ ግፍ መፈጸም። ከራስ ጥቅምና ፍላጎት ውጭ ለአገርና ለሕዝብ የወደፊት እጣ ፋንታ አለማሰብ።

በኦሮሚያ ክልል በተደረገው ሕዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በሰሜን ጎንደር ከማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በተፈጠረው ችግርና አለመረጋጋት የተወሰኑ መምህራን አመፁን አነሳስታችኋል በሚል ሰበብ በመገደላቸውና በመታሰራቸው በበርካታ ት/ቤቶች ለወራት ያህል ትምህርት ተቋርጧል።በአንዳንድ ት/ቤቶችም የመማር ማስተማር ሥራ እስካሁን ድረስ እንዳልተጀመረ ከትምህርት ባለሙያዎች ከተገኘ መረጃ ለማረጋገጥ ተችሏል። ለአብነት ያህል በሰሜን ጎንደር በሚገኙ 154 ት/ቤቶች በ92 ት/ቤቶች በቅርቡ የማስተማር ስራ የተጀመረ ቢሆንም በተቀሩት 62 ት/ቤቶች ትምህርት እንዳልተጀመረ ለመረዳት ተችሏል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የታሰሩት ከፍተኛ የጦር መኮንኖችና የደህንነቶች ቁጥር 126 ደረሰ | ጌታቸው አሰፋ የ እስር ማዘዣ ወጦበታል

በአንድ አገር ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም በዕኩልነት በሚዳረስበት ጊዜ የሰለጠነ የሰው ሃይል ማፍራት ይቻላል፤ የመፍጠር ክህሎት ዳብሮ የአገር እድገትና ብልጽግና ይረጋገጣል። ይህ ሐቅ ግን በዛሬይቱ ኢትዮጵያ አይታይም። የትምህርት እድገትና መስፋፋት ከሕብረተሰቡ ፍላጎትና ከሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገት ጋር መጣጣም ይኖርበታል።በመሆኑም የመምህራን ዋነኛ ተግባር የሰለጠነ ባለሙያ ማፍራት ነው።ለዚህም የመምህራን በብዛትና በጥራት መገኘት በእጅጉ አስፈላጊ ነው። የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት ባለባት ኋላቀር አገራችን በመምህርነት ሙያ የረዥም ጊዜ ልምድ ያካበቱ መምህራንን ማጣት የትምህርቱን ዘርፍ በእጅጉ እየጎዳው ይገኛል።በመሆኑም ብቃት ባላቸው መምህራን መማር የእያንዳንዱ ዜጋ መብት በመሆኑ ባልሰለጠኑ መምህራን የሚሰጠውን ትምህርት እናወግዛለን።የወያኔ አገዛዝም ከዚህ አድራጎቱ እንዲቆጠብ እናሳስባለን።ልምድ ያላቸው መምህራን በስራቸው እንዲቆዩ መብቶቻቸውን በማክበር ችግርን ለመቋቋም ለሚነሱት የደመወዝና ልዩ ልዩ የጥቅማጥቅም ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ አጥብቀን እንጠይቃለን።መምህራን እየደረሰባቸው ያለውን ፖለቲካዊ ጫና ፣ የአካዳሚክ ነፃነት መገፈፍና የመብት ጥሰት ለማስቆም አስፈላጊውን ሰላማዊና ሕጋዊ የትግል እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀት የወቅቱ ጥያቄና ግዳጅ ነው።

በሌላ በኩል ወያኔ በትምህርት ላይ የሚያደርሰውን ሆን ብሎ የታቀደ አደንቁሮ የመግዛት ስልት የመምህርነት ሙያን ክብር በማዋረድ ፣መምህራንን በማጎሳቆል ሲያራምደው የቆየውን የውስጥ ፖሊሲ ሸምጥጦ በመካድ አሁን ለትምህርቱም ፣ ለመምህራን ኑሮም ቅን አሳቢ መስሎ ለመታየትና ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ለመጠቀም እየዳከረ ይገኛል።በዚህ በተካነበትና በለመደበት የቅጥፈት ፕሮፖጋንዳ ለመምህራን የትራንስፖርት ድጎማ ከፍ እንዲል፣ የደመወዝ ጭማሪ እንዲደረግ፣ የቤት መስሪያ መሬት ሊዝ በቅናሽ እንዲያገኙ ፣ኮንዶሚኒየም ቤት ለመምህራን ቅድሚያ እንዲሰጥ —–ወዘተ የሚል በስፋት መራገብ ተጀምሯል። ካሁን ቀደም በ2004ዓ.ም መምህራን ኑሮ እጅግ ስለከበዳቸው ባሳዩት ተቃውሞ ከፍተኛ የደመወዝ ጭማሪ ተደረገ ተብሎ በመገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ ፕሮፖጋንዳ በተለፈፈ ማግሥት ከቤት ኪራይ ጀምሮ በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች የዋጋ ጭማሪ ተደርጎ በሕዝቡ ባጠቃላይና በተለይ በመምህራን ላይ ጫናው እንደወደቀ የምናስታውሰው ነው።ተደርጎ የነበረው ጭማሪም ሰባ ሶስት ብር ብቻ ነበር። ይህ ገንዘብ በወቅቱ ሁለት ኪሎ የሽሮ እህል(አተር ወይም ባቄላ) ሊገዛ የማይችል ማታለያ ሆኖ በመገኘቱ የ2004ዓ.ም የመምህራንን የስራ ማቆም አድማ አስነስቷል።

ያሁኑ የወያኔ የአዛኝ ቅቤ አንጓች ለመምህራን ይደረጋል የሚባል ድጎማ፣የመሬት ሊዝ ቅናሽ፣የኮንዶሚኒየም ቤት ቅድሚያና የደመወዝ ጭማሪ ላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ ዓይነት ባዶ ፕሮፖጋንዳ ከመሆን አይዘልም። ወያኔን በአገር ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት አንፃር ከወሰዳቸው አገር አጥፊ እርምጃዎች አይተን ተቆጭተናል፤ቆዝመናል፤በዘር ፖለቲካው ሸርና ምስቅልቅል ታዝበናል፤በመሬት ነጠቃ፣ በሙስና ፣ በህዳሴ ግንባታ ስም በሚያደርገው የአገር ሀበት ዘረፋና የግለሰቦች ንብረት ቅሚያ፣በሽብርተኝነት ሕግና በራሱ አሸባሪነት ትርኢት ተተራምሰናል። በሊቢያ፣ በሳውዲ አረቢያ፣ …..ዜጎቻችን ሲገደሉና ሲሰቃዩ መንግስት ተብዬው ያሳየውን ግድየለሽነትና ጭካኔ አንረሳውም።በገዛ አገራቸው ዜጎች ሰርተው መኖር እንዳይችሉ በመደረጋቸው ለስደት ተዳርገው በበረሃ አሸዋ ውስጥ አፅማቸው የቀረ፣ የውስጥ አካላቸው ኩላሊታቸውን ጭምር የተቀሙትን ወገኖቻችንን ቤታቸው ይቁጠረው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ፋኖ በሸዋሮቢት ከተማ አደባባይ ተገማሸረ | የጄነራሉ ጠባቂዎች ተገደሉ - ባህርዳር ተናወጠች ፣ አመራሮች እየወጡ ነው |

በቅርቡ በኦሮሚያ ፣በጋምቤላ ( የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው በጋምቤላ በሚገኙ ዜጎቻችን ላይ ግድያ ሲፈጽሙ፣ ከመቶ ሃምሳ በላይ ሕፃናትን አግተው ሲወስዱ፣ በሺዎች የሚገመት የቀንድ ከብት ዘርፈው ስሄዱ የወያኔ አገዛዝ የወሰደው አርምጃ አለመኖር ወያኔ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት እንዳልቆመ በገሃድ አሳይቷል)፣ በቤንሻንጉል( ኑየር፣ ኮንሶ፣ ሐመር፣—) ፣በጎንደር —-ወዘተ ዜጎችን በጅምላ ፈጅቷል።ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የካደ ወያኔ ለመምህራን በጎ ያስባል ማለት ዘበት ነው።

ወያኔ ለመምህራን ሕይወት በተለይ ለአገር እድገትና ብልጽግና ባጠቃላይ ለማሰብ ቢጀምር ( አያደርገውም እንጂ) የመምህራንን በነፃነት የመደራጀት መብትና የአካዳሚክ ነፃነት ማክበር፣የትምህርት ፖሊሲው መምህራንን፣ ወላጆችን፣የትምህርት ባለሙያዎችን፣ ባጠቃላይ ባለድርሸዎችን (Stake holders) ያካተተ ሆኖ እንዲቀረጽ ማገዝ ይጠበቃል። ወደ ሙያው ለሚገቡ የስልጠናውና የምልመላው ሂደትም ከላይ የተመለከቱትን አካቶ ስርዓት ባለው መልክ ማራመድን ይሻል።ትምህርት ቤቶች ሲገነቡም የሰው ኃይል፣ የትምህርት ግብአትና የመሳሳሉት እንዲሟሉ የሚመለከታቸውን አካላት አሳታፊ እንዲሆን ይገባል። እስካሁን እንደታየው በየጫካው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ከፈትኩ በማለት ምርታማ ያልሆኑ ዜጎችን መፈልፈል ሌላ ችግር ማስከተል እንደሚሆን ግንዛቤ ሊደረግበት ያስፈልጋል።

በመጨረሻም መምህራን የትምህርቱ ስርዓት ስኬት እንዲያስገኝ፣ሙያቸውና መብቶቻቸው እንዲከበሩ፣ ባጠቃላይ በትምህርቱና በመምህራን ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመከላከል ቁልፉ ጉዳይ መደራጀት ነው። ስለሆነም የወያኔን የመከፋፈያና የመሸንገያ ዘዴ ለማክሸፍ መፍትሔው መምህራን በአንድነት ቆመውና ቆርጠው እንዲታገሉ፣ ተማሪዎች የተማሪዎች ማህበር ማቋቋም እንዲችሉ፣ በሰለጠኑ መምህራን ትምህርት እንዲያገኙ፣ ለአገር ሕልውናና ለህዝብ መብት እንዲቆሙ፣ ባጠቃላይ ህዝብም በትምህርት ጥራት ላይና በመምህራን ላይ የወያኔ አገዛዝ በመፈጸም ላይ የሚገኘው የትውልድና የአገር ግድያ እርምጃ እንዲቃወሙ የኢትዮጵያ መምህራን በእጂጉ ይጠበቅባቸዋል።

©ነገን ዛሬ እንስራ

1 Comment

  1. Teachers at risk or in danger? Is this news analysis or retelling the same story of a quarter of a century over and over again ? So what? I am sorry to ask kind of frustrating question but I have to . And the question is : Do really teachers know the very power and secret of education or to be educated? It is a powerful weapon to fight against political or man-made catastrophic situations . It is a matter of saving, shaping and reshaping a generation so that it has to live as free and dignified human being . It is a matter of enabling a generation to think independently , to live free, to seek a real sense of justice, to peruse happiness, to be responsible, to be respectful, to be patriotic , to live in a way that one’s life must make sense to others , etc. Do we see these and other characteristics in the majority of teachers? Unless we want to fool ourselves , the answer cannot be surely positive.

    As the higher standard of education heavily depends on the willingness, courage and devotion first and foremost toward creating a generation of knowledge, freedom , justice, dignity, morality, and prosperity ; expecting the prevalence of the higher standard of education without the a strong role to be played by teachers does not make sense.

    It is from this perspective that this “news analysis” seems analysis of clumsy excuse, not analysis of critical thinking .

Comments are closed.

Share