የዛ ሰውዬ ድምጽ … 

ወለላዬ

ፊቱ አሸቦ መስሎ፣ እንደደነገጠ፣
ተጎልጉሎ ወጥቶ፣ ዓይኑ እንደፈጠጠ፣
ባንኮኒው ጋ ሄዶ፣ ቢራውን ጨበጠ።
የሆነውን እንጃ! ሁኔታው ያስፈራል፣
እንባው በጉንጩ ላይ፣ አቋርጦ ይፈሳል
አልቅሶ ሲበቃው፣ ውጪ እየሰለለ፤
ያየውን በውስጡ፣ እያሰላሰለ፣
ገድለው ሲጥሏቸው፣ በዓይኖቼ አየሁ አለ።

ወደ ተናጋሪው፣ አፍጠን እያየን፤
እንደልማዳችን፣ ዝም ተባባልን።
ሰውዬው ቀጠለ፣
ገድለው ሲጥሏቸው፣ በዓይኖቼ አየሁ አለ!
ዘለው ያልጠገቡ፣
እህል የተራቡ፣
አገር የተቀሙ፣
ፍትሕ የተጠሙ፣
አንድ ፍሬ ናቸው!
ገና እንዳገኟቸው፣
ከበው ይዘዋቸው፣
መሣሪያ አስጠግተው፣ ወደ ግንባራቸው፣
ጭንቅላታቸውን … ፈረካከሷቸው።

እያለ ሲናገር፣
ሰውዬው ሲቆጣ፣ ሲያለቅስ ሲያማርር፣
እኔም ልክ እንደሱው፣ በዓይኖቹ ገብቼ፣
አንገቴን አቅፌ፣ በሁለት እጆቼ፣
ጉልበቴ እየራደ፣ ነፍሴ እየበነነች፣
አውጣኝ! ከዚህ ቦታ፣ አድነኝ እያለች፣
ስትለማመጠኝ!
የደም ፍንጣቂ፣ አካሌን ሲያለብሰኝ
እሱ ቦታ ቆሜ፣ እሱን ሆኜ አየሁኝ።

ሰውዬው ቀጠለ፣
ቴሌቭዥን አይቶ፣ እኚህ ናቸው አለ።
ቢራውን ጨለጠ፣
ዓይኑን አፈጠጠ፣
ውሸታሞች ናቸው! ሽብርተኛ አይደሉም፣
ጨርሶ! በጃቸው፣ መሣሪያም አልያዙም፣
አይቻለሁ በዓይኔ፣ ነጻ ልጆች ናቸው፣
ምንም ሳያጠፉ፣ ነው የገደሏቸው!
ኡ! ኡ! አለ ሰውዬው፣ እንደሰማ መርዶ፣
በዜናው እወጃ፣ ክፉኛ ተናዶ
ነገሩ እየቆጨኝ፣ እያንገበገበኝ፣
ጀብረር እንዲያደርገኝ፣
ፍራት እንዲርቀኝ፣
አልኮሌን ደገምኩኝ።

ሰውዬው ተናግሮ አልወጣልህ ቢለው፣
ኡ! ኡ! ብሎ ጮኾ፣ ማልቀስም አማረው!
እሪ! አለ ሰውዬው፣ ንዴቱ ጨመረ፣
ጩኸቱን ለቀቀው፣ ቤቱ ተሸበረ።
ተንጋግቶ ደረሰ፣ ፌደራልም መጣ፣
ይጎትቱት ጀመር፣ እውጪ እንዲወጣ፣
ይሄኔ ተነሳሁ፣ አትነኩትም! አልኩኝ፣
ሰውዬውን ላስጥል፣ ከመሃል ገባሁኝ።
ምን አ’ረገ! አልኳቸው፣
ጥፋቱን ንገሩኝ? ብዬ ጠየኳቸው!
ሽብርተኛ ሲሞት፣ ተንሰቅስቆ አልቅሷል፣
ሕዝብ መሃል ሆኖ፣ ሰላም አደፍርሷል፣
ብለው ሲናገሩ፣ እንደ እብድ አ’ረገኝ፣
ጭራሽ አትወስዱትም! አትነኩትም አልኩኝ።
ያለው ሁሉ እንደኔ፣ በአንድ ላይ አደመ፣
መሃላቸው ገብቶ፣ አሰፍስፎ ቆመ።
ከዛ ቤቱ ሁሉ፣ መተረማመሱ፣
ትንሽ ትዝ ይለኛል፣ ጥይት መተኮሱ
ካለሁበት ቦታ፣ ለሊት ብንን ስል፣
ማንም በሌለበት፣ በጨለማ ክፍል፣
ዘለው ያልጠገቡ፣
እህል የተራቡ፣
አገር የተቀሙ፣
ፍትሕ የተጠሙ፣
አንድ ፍሬ ናቸው!
ገና እንዳገኟቸው፣
ከበው ይዘዋቸው፣
ጭምቅላታቸውን … ፈረካክውሷቸው።
እያለ ይጮሃል፣
የዛ ሰውዬ ድምጽ፣ አሁንም ይስማል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  Sport: የባርሴሎናው ቴክኒሻን ኢኔሽታ ውለታውን እየመለሰ ነው

 

ወለላዬ ከስዊድን

Share