November 4, 2016
36 mins read

ስኬት የሚገኘው ራዕይ ፣ ዕሴትና ተግባር ሲዋሃዱ ብቻ ነው – ማርእሸት መሸሻ

ማስገንዘቢያ የዚህ ፅሑፍ ዋና ዓላማ በኢትዮጵያውያን ዘንድ በተለይም የሰባ ዓመታት የፖለቲካ ጉዞ የዘውዳዊውን፤ የወታደራዊውንናየዘረኛውን ወያኔ ሥርዓቶች ሲቃወሙ በባጁት ወገኖቼ መሃከል ውይይትን ለመቀስቀስ ነው። ይህን ጽሁፍ በእንግሊዝኛቋንቋ “a way forward to a post-woyane demoratic and Just Ethiopia” በሚል ርዕስ አዘጋጅቼ ለንባብ አብቅቼዋለሁ። የቀየርኩት ነገር ቢኖር ርዕሱን ብቻ ነው። የእንግሊዝኛውን ጽሁፍ ለማንበብ : http://www.ethiomedia.com/1016notes/a_way_forward.pdf ይጫኑ። ፅሑፉን በታችኛው የላቲኑ ፊደል ‘a’ የጀመርኩት ሆን ብዬና ለአንባቢዎቼ በዚያ ፅሑፌ ያስቀመጥኩት ትንተናከገባንበት ቅርቃር መውጫ መንገድ የእኔ ብቻ አይደለምና ሌሎች ሊቀርቡ ከሚችሉ አማራጮች እንደ ኣንድ ኣማራጭ እዩልኝ ለማለት ነው። የነቃሁ የበቃሁና የመጠቅሁ ነኝና “የእኔን መንገድ ካልተቀበላችሁ” ለማለት ሳይሆን እንዲያውም በተፃራሪው ያለኝ ዕውቀትና ልምድ በሳይንስና ቴክኖሎጂው መስክ ነውና የፖለቲካ ሳይንቲስት፤ የሥነ-አዕምሮ ጠቢብ ወይም የፍልስፍና አዋቂ አለመሆኔ በግምት ተይዞልኝ፤ እንደማንኛውም አገሩንና ወገኑን እንደሚወድ ዜጋ በጉዳዩ ያገባኛልና ባለኝ አቅም የድርሻዬን ላበረክት ለማለት ነው። የምፅፈው ባለፉት ሁለት አሥርተ ዓመታት በፀረ-ወያኔው ንቅናቄ ካዳበርኩት ልምድ ላይ በመመርኮዝ ነው። በዚህ ልምዴም ከተቃራኒው ወገን የኣሰራርና የኣላማ ጉድለትን አያለሁ። በዚያ ላይ ደግሞ ዴሞክራሲና ፍትህ የሰፈነባት አገርንበመመስረት ራዕይ ዙሪያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች – ሕፃናትና አረጋውያንን ጨምሮ – ከፍተኛ የሆነ መስዋዕት እየከፈሉ ነውና ስለታዘብኳቸው ጉድለቶች መናገር አለብኝ – እየተከፈለ ያለው መስዋዕትም መና ሆኖ እንዳይቀር መናገርአለብኝ! በተጨማሪም ይህ ለዘመናት በተቃዋሚነት ሥነልቦና ብቻ የተተበተበ የሚመስለው ትግላችን ተቀይሮ ውጤት-ተኮር በሆነ ሥነልቦና ተተክቶ ይጓዝ ዘንድ ለማሳሰብም መፃፍ አለብኝ።እንደገና መስቀለኛ መንገድ ላይ ደርሰናልመቼም ቢሆን የኋሊት ማሳያ መስተዋትን ብቻ ተጠቅሞ መንዳት ከግጭት ላይ ማድረሱ አይቀሬ ነገር ነው ይባላል። ያእንዳይሆን ሹፌሩ በሁሉም የማሽከርከር ወቅት ቀልቡን ሁሉ አሰባስቦ የሚጓዝበትን መንገድ ብቻ ሳይሆን አካባቢውን በሰፊ ዕይታና ቅኝት ውስጥ አስገብቶ ወጣ ገባውንና ጠመዝማዛውን ሁሉ እያማተረ ሲያሽከረክር ነው የወደ መድረሻውጉዞ ቀና የሚሆነው። ማንኛውም እይታና ራዕይ ምን ያህል የተወሳሰበ እንኳ ቢሆን – “ግብ” ብለን የተቀበልናቸው እምነቶቻችንላይ ያደርሰን ዘንድ በጥንቃቄ የተሰላ ውጤት-ተኮር ተግባር ማካሄድን ይጠይቃል።የወያኔን አገዛዝ ስቃወም ይኸው ሃያ ዓመታት ሆነኝ። የምወዳትን ሀገሬን ኢትዮጵያን ከለቀቅሁበት ጊዜ ጀምሮ የምወደውን አፈሯን ተመልሼ ሳልረግጥ አብዛኛውን የጉልምስና ሕይወት ያሳለፍኩት አውስትራሊያ ውስጥ ነው። በዚህም ምክንያት እንደ ቅንጅትና ህብረት ያሉ ፖለቲካዊ ቅርርቦችን ሳስተውልና ስከታተል ቆይቻለሁ። የትብብር ምሥረታዎቹም ሆነ የፍርሻዎቹ አካልየነበርኩበት ጊዜ ግን አልነበረም። ዛሬም የወያኔን በጭቆናና በአፈና ላይ የተመሰረተ አገዛዝ ሽረው ዴሞክራሲና ፍትህ የሰፈነባትን ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ እየታገሉ ያሉ ፖለቲካዊና ማኅበረሰባዊ/ሲቪክ ስብስቦች አባል በመሆን የበኩሌን ላበረክት የንቅናቄው አካል ነኝ። ” በወቅቱ ባለው አለመርካት ጥሩ ነው፤ በዚያም ምክንያት መብከንከን ካለ ደግሞ የተሻለ፤ ብሎም አለመረጋጋት ከተከሰተ ደስ የሚል፤ ከዚያ ሃሳቦች ይመንጩ፤ ከባድ ሃሳቦች – ከባድ ሥራዎችም ይፍለቁ፤ በዚህ ሁሉ ውስጥ ራሱን አሳንሶ የሚመለከት ራሱን ከፍ ያድርግ ” ሒዉበርት ሐምፍሬሕዝባችን በጨካኝ ዘረኛ አገዛዝ ሥር ከወደቀ ሩብ ምዕተ አመት ተገባደደ። ለማምጣት ያለምነውን ስኬት ሲታይ ግን የዛሬ ሃያ ዓመት ከነበርንበት ምንም ያህል ፈቀቅ እንኳ አላልንም። ለመሆኑ ግባችን (ያጭሩ ሆነ የረጅሙ) ያልነው ላይ የነጠረ ዕይታ አለን? ግባችን ብለን ወደአቀድናቸው ዐቢይ ጉዳዮች ሊያድርሱን በሚችሉ ተከታታይ ራዕዮቻችን፤ ልንከውን በምንፈልጋቸው ተግባሮችና ልናበረክት በምንችላቸው ድርሻዎች ላይ የጠራ ግንዛቤ አለን? በነዚህ ከልባችንና ከአዕምሮአችን መንጭተው ከወያኔበኋላ የምንመኛትን ኢትዮጵያ ዕውን ለማድረግ መከናወን ስላለባቸው ጉዳዮች የዳበረ ግልፅነት አለን? ራዕዮቻችንን የምናስተነትነው ፍፁም በሆነ ግልፅነት ላይ ተመስርተን ነው? ያንንስ ራዕይ በጸና ዕምነት ላይ አስደግፈን እናጸናዋለን? እያደረግንያለው ሁሉ በጠንካራ የተልዕኮና የስኬታማነት መንፈስ ላይ በፅኑ የተመሰረተ ነው? እነኝህ ሁሉ በጭንቅላቴ ውስጥ የሚመላለሱጥያቄወች ናቸው።ዛሬም ገና በተቃውሞው ምዕራፍ ውስጥ ነው ያለነው። ታዲያ ያለማቋረጥ እያዥጎደጎደን ያለነው መፈክርና እያከናወንን ያለው ከባድ ሥራ ሁሉ ህዝባችንን ወደተስፋይቱ ምድር ወደነፃነት እኩልነትና ፍትህ ሊያደርስ የሚያስችለውን ግልፅነትንና ጥራትን የተጎናፀፈ ነው? ከወያኔ ወዲያ ለምንፈጥራት ኢትዮጵያ ያሉን ራዕዮች ለመሆኑ ምንድን ናቸው? አልፈው አልፈው ብልጭ ድርግም ከሚሉ ቀውጢ ጊዜ ከሚወልዳቸውና በጥቂት ድርጅቶች መሃል ከመነጩ በትብብር የመስራትና የመግባባት መግለጫዎች ባሻገር እስካሁንም የጠራ የጉዞአችን አመላካች ካርታ ያለን አይደለንም። ይህ አጭር ፅሁፍ በርከት ያሉ ጥያቄዎችን በማንሣት ራዕያችን፣ እሴቶቻችንና ተግባራችን ምን ምን መሆን አለባቸው ከሚሉ ነጥቦች ላይ በመንተራስ አማራጭምላሾችን ለማበርከት ይሞክራል። ኣቢይ ኣላማው ግን የወደፊቷ ኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ዜጎች ሁሉ ያሉብንን ድርጅታዊና ግለሰባዊ ድክመቶች አንጥሮ ለማሳየትና እንድንወያይበት ለማበረታታት፤ እንዲሁም ሕብረተሰባችን ተሳስሮ የኖረበትን ማሕበረሰባዊ ድርና ማግ በማይሽር ሁኔታ ለመበጣጠስ ከዲያብሎስ ጋር እንኳን ሊዶልት የማይመለስን ወያኔን እኩይኣላማ ለማክሸፈና፤ ኣዲሲቷን ኢትዮጵያን ለመገንባት የተጠየቀውን መስዋዕትነት ሁሉ ያለስስት ከፍሎ ሊያስወግድ የተዘጋጀ በሃገርም ውስጥ ሆነ በውጭ ኗሪ ኢተዮጵያዊ ትግል የራዕይ፣ የዕሴትና የተግባር ጉድለቶች ያለምንም ፍርሃትና በግልጽነት መጠቆም ኣለባቸው ከሚል ዕምነት የመነጨ ነው።ራዕይ በረጅሙ ታይቶ ታልሞና ታቅዶ ስኬታማ ለሆነ የረጅም ጊዜ ለውጥ የተቀረፀ የተልዕኮ መርሐግብር ስልትና ግብን ስሜት በሚያቃጥል ጽኑዕ ኣላማ ወዳድነት ያካተተ ነው። በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ የፖለቲካና ማህበረሰባዊ/ሲቪክ ድርጅት ወይም ስብስብነን የሚሉ በሙሉ ወያኔ የሚባል የጋራ ጠላት እንዳላቸው ከመግለፅ በተጨማሪ ፍትሓዊና ዴሞክራሲያዊ የሆነ ሥርዓትን መፍጠርንና መገንባትን የሚያስችል የሚል አንድ ወጥ የግብይት ቋንቋ አላቸው ለማለት እቸገራለሁ። ከላይ ከላይ ሲታይ ሁሉምመልካም ይመስላል እንጅ። ሁሉም ዲሞክራሲ ኣስተዳደርን ይፈልጋል። ዕኩልነትና ፍትህንም እንደዚሁ። ታዲያ በዚህ ራዕይ ዙሪያ በጋራ መሰለፍ እንዴት ኣልቻልንም? የፊደል ጋጋታ ድርጅት ስሞቻችንን ከማብዛት ይልቅ። ፍትሓዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትም በህግ የበላይነት ላይ የተመሰረተና ሁሉንም ዜጋ ነፃና እኩል በሆነ መንገድ የሚያስተናግድናለፀረ-ወያኔው ትግል የጋራ መግባቢያ ቢሆንም በራሱ ብሔራዊ/ሀገራዊ ራዕይ ሊሆንም፣ ሊያሳይም አልቻለም። ምክንያቱም ይህ ዓይነቱ ራዕይ ገና የጉዳይ ባለቤት ነንና ያገባናል በሚሉት ፖለቲካዊና ማህበረሰባዊ ድርጅቶች ገና አልተቀረፀምና ነው። ይህ ደግሞ ገና ተገንጥለው የራሳቸው ሥርዓተ-መንግሥት የመፍጠር ምኞታቸው ያልሰከነውን እንኳን ግምት ውስጥ ሳናስገባ የፀረ-ወያኔው ትግል አካል ነን ከሚሉትና በውጭ አገራት እየተደረጉ ካሉ የኦሮሞ የዑጋዴን የሲዳማ ወዘተ ማህበረሰብ አባላት በየጊዜው በሚያደርጓቸው ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ የሚንፀባረቅ ሀቅ ነው። የባንዴራ ትርጉም መጥፋቱ፤ ህጋዊ እውቅና የሌለውና ያገባኛል የሚል ሁሉ ያልተወያየበት፣ ውሳኔም ያልተደረሰበት ኣዕምሯዊ ሃገር ስም ወዘተ ……የመሳሰሉት ራዕየ ቢስነትን ወይም ብዥታን የሚያሳዩ ክስተቶች በሰፊው ሰፍነዋል።ችግራችን የወያኔ መወገድ ብቻ አይደለም። የወያኔን ኣምባ ገነናዊ ስርዓት ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ገጽ መክሰምና መጥፋትማ ልክ የፀሐይን ከበስተምሥራቅ የመውጣቷን ያህል (ያ ደግሞ በቅርቡ እንደሚሆን ተስፋዬ ነው!) እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል። ራዕያችን፣ እሴቶቻችንና ተግባራችን ግን ከወያኔ ባሻገርና ወዲያውኑ የምንፈጥራትን ሀገር – ” ኢትዮጵያችንን ” – በግልፅ ተንትኖ ማስቀመጥ መቻል አለበት።እያንዳንዳችን ምንም የፖለቲካ ኣመለካከቶቻችን ተጻራሪ ቢሆኑ እንኳን እነዚያኑ እምነቶች በግልፅና በመልክ መልኩ አስቀምጠንና ከወዲሁ አርቀን ማቅረብ መቻል አለብን። የፖለቲካ ኣመለካከቶቻችን ድርጅታዊ ፍላጎቶቻችንና ኣላማወቻችንን በተደበቀ ካዝና ውስጥ ታሽገው ለአባላት ብቻ እየተመጠኑ የሚገለፁና ከህዝብ ዕይታ ተሰውረው በሚስጥር የሚያዙ መሆን የለባቸውም። ግልፅነትና ቅንነት ብቻ ነው መንገዳችን አባጣ ጎባጣ እንዳይሆን የሚያደርገው። ስለሆነም “ለመሆኑ ዕምነቶቻችን ምን ምን ናቸው?” የሚለው ጥያቄ መነሳት ያለበት ነው። ለምሳሌ ያህል – ኣለም ኣቀፍ ዳር ድንበሯ የታወቀ፣ የታፈረና የተከበረ፤ሁሉም ዜጋ የታወቀ ክልሏን እያንዳንዷን ካሬ ሴንቲ ሜትር በደሙ ጠብታ ሊከላከል ቁርጠኛ የሚሆንላትን ኢትዮጵያ መፍጠር እንችላለን? ወይንስ የግልም ሆነ የጋራ የረዥም ጊዜ ትግላችን ወራሪው ጣሊያን ያለመውንና ኣገር ኣጥፊው ወያኔ የተገበረውን የዘር ማንዘሬ አፅመ-ርስት የሚለውን የክልል ፍልስፍና ለማስረገጥ ብቻ ነው?የመንግሥት ግንዛቤያችንስ ምንድነው? አሀዳዊ የተማከለ መንግሥት? ወይስ ፌደራላዊ? አሀዳዊና የተማከለ ማለት ሥልጣኑን አማክሎ የያዘው ኅይል ለየክፍለ ሀገራቱ ተሿሚዎቹ በሚያወጣቸው ህጎችና በሚደነግጋቸው አዋጆች እየቆነጠረ ውስን ሥልጣንየሚቸርበት የሥነ-መንግሥት ዓይነት ነው። በንጉሳዊውና በደርግ ዘመን የነበሩት አስራ አራት ክ/ሀገራት የእንደራሴ ሥልጣን ሹም ሽር የአሀዳዊና የተማከለ መንግሥት ምሳሌ ነው። ሌላም ምሳሌ ካስፈለገ የታላቋ ብሪታኒያ የተባበሩ መንግስት United Kingdom ሥርዓተ መንግስትና ሥልጣንን በፈለገው መጠን ቀነጣጥቦ የሚቸራቸው ሰሜን አየርላንድ፤ ስኮትላንድና ዌልስ ተጠቃሽ ናቸው። በአንፃሩ ደግሞ ብዙ ጊዜ በኢትዮጵያውያን ፖለቲካ ኣቀንቃኞች በግርድፍ የሚገለጸው ፊዴራላዊ መንግሥት እንኳን ተግባራዊ በሆነባቸው እንደ ጀርመን፣ ቤልጂየም፣ ካናዳ፣ ኣውስትራሊያ ወዘተ ባሉ በቅልቅል ባህል፣ ፍልስፍናና ፖለቲካ በተመሰረቱ ሃገራት ምን ያህል ችግር ፈጣሪ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። እኛስ በእያንዳንዱ ክ/ሀገር እኩል ሥልጣን ያለበት ፌዴራሊያዊ የመንግሥት ሥርዓት (Symmetric Federal System) ነው የምንሻው? ወይንስ በሥልጣን ክፍፍሉ ጊዜ አንዳንድ ግንዛቤ ውስጥ መግባት ያለባቸው (የህዝብ ብዛት፤ የተፈጥሮ ሀብት ክምችት፤ ምርታማነት ሌላም ሌላም) ጉዳዮች ግምት ውስጥ አስገብቶ ሥልጣንን እንደየአበርክቶው የሚያደላድል (Asymmetric Federal System) ፌዴራሊዝምን? ሁለተኛው ጠቃሚ መነጋገሪያችን መሆን ያለበት ዕሴቶቻችን (የምናምናቸውና የምንታመንባቸው የህይወት መመሪያወቻችን) (Values) ጉዳይ ነው። እነዚህ ዕምነቶች የምንከተለውን የተግባር ክንዋኔና (Action) ውጤት ማስተንተኛ መሳሪያና የዕምነቶቻችን ዝንባሌዎቻችንና ባህሪዮቻችን ቅኝት ማስተካከያም ናቸው። ዕምነት የሞራል (ቅንነት፤ መከባበር፤ ፍትሃዊነት ወዘተ) የፍልስፍና ግንዛቤ (ኃይማኖት፤ ርዕዮተዓለም፤ ፖለቲካ) እንዲሁም ማህበረሰባዊ (የጋራ ብሩህ ተስፋ፤ የጋራ ዕድገት ምኞት፤ አብሮና ተባብሮ መኖር፤ የጋራ ክብርና ሞገስ፤ ከራስ-በላይ-ንፋስ-አለማለትን ወዘተ) የሚያካትት ሲሆን ቅዱስ ነው። “ነፃና ፍትሃዊ የሆነና ግልፅ ምርጫ፤ ኢትዮጵያዊነት፤ የዜጎች እኩልነት ወዘተ” የመሳሰሉት ዕሴቶች የጋራና የተቃውሞ ቋንቋችን ከሆኑ ውለው አድረዋል። ተግባራችንስ በነዚህ ቅዱስ ዕሴቶች የተደገፈ ነው ወይ?”ተስፋ ያለው ወገን ሕልሙ ዕውን ይሆንለት ዘንድ ይመኛል፤ ተስፋ ያጣው ግን ቅዠቱ ዕውን እንዲሆን ይጠብቃል” …. ምንጩ ያልታወቀፈታኝ በሆነ ወቅት የምንሰራው አምነንና የኛ ብለን አንግበን ያቆየናቸው ዕምነቶች ነፀብራቅ ነው። ስለሆነም ለወደቁ ጀግኖቻችንእናነባለን። አንዳርጋቸውን፤ እስክንድርን፤ አንዱዓለምን ስናስብ እናለቅሳለን። በኃዘን የተጎሳቀለች እናትን ስንመለከት ልባችን ይደማል። እምቢ ባይ አትሌት በዓለም ፊት የሕዝብን የተቃውሞ ምልክት ሲያሳይ “እሰይ! እንኳን የኛ ሆነ” ብለን ኩራት ይሰማናል። በኣንጻሩ ደግሞ በመሃላችን የቅቤ-ገበያ-ውሎ ዓይነት ቋንቋን ተጠቅመን ክቡሩን የሰው ልጅ ለማዋረድ፤ ዝቅ አድርገን ለመመልከትና (በነጠላም ሆነ በቡድን) ለማቅለል የምንሞክር ሞልተናል። ዮዲት ወ/ሩፋኤል የተባለችና የአሪዞና ነዋሪ የሆነች ሴት በፌስ ቡክ ላንጎደጎደችው ስድብ የሰተጣት ምላሽ በትግሬና አማራ/ኦሮሞ ዜጎቻችን መሀከል የዘር ፍጅት ጦርነትን ሊጭር የተቃረበ ይመስል ነበር። በርግጥ የዮዲት አባባል የትግራይን ህዝብ ሊወክል ይቅርና እዚህ ግባ የሚባል ግምት ሊሰጠውባልተገባ ነበር። ለኦሮሞና ለኣማራ ጥብቅና የቆሙትም ከትግሬ የተለየ ብልሃት ወይም ጀግንነት፣ ድድብና ወይም ዕውቀት እንደሌላቸው ማወቅ የተሳናቼው መስሎ ነበር። በእንዲህ ያለው ፈታኝ ወቅት በግለሰብ ድርጊት ወይም ርምጃ ተጎትተን ከወደቅንና በሁሉም ማህበራዊና ባህላዊ መስክ መከባበራችን በአንዴ ጥሎን ከነጎደ ታዲያ የቱ ጋ ነው ፍትህ እኩልነትና ዴሞክራሲ የሰፈነባት ኢትዮጵያን የመፈለግ አመክንዮአችን? ኣስተሳሰባችን ሁሉንም ፖለቲካዊና ማህበረሰባዊ ስብስቦችን አካታችና ቀና ኣመለካክትና ፉክክርን healthy competition የሚያበረታታ መሆን አለብን። ኢትዮጵያችን የበርካታዎች እናት፤ የብዙ ብሔር/ብሔረሰቦች አገር፤ የተለያዩ ፖለቲካዊ አመለካከቶች ክምችት ናትና ምንም ወይም ማንም ህብረ ብሄራዊም ሆነ ብሔር/ብሔረሰባዊ ድርጅት በኃይል ሊገዛት የሚገባት አይደለችም – በፍፁም! ሌላው መረዳት ያለብን የማንም ብሔር/ብሔረሰብ ከፖለቲካው ምህዳር መገለል ሰላምንና መረጋጋትን ሳይሆን ቅሬታንና መተረማመስን የሚያስከትል መሆኑን ነው። ስለዚህም ነው ሁሉም የፈረስ-ግብይት በግልፅና ባልተሸፋፈነ መንገድ ተካሂዶ የነገይቱ ኢትዮጵያ የምትገነባበት የመሰረት-ድንጋይ የሚተከልበት ሰነድ በሌጣ ወረቀት ላይ ሁሉም ያገባናል የሚል ወገን በተገኘበት መቀረፅ አለበት የምለው። ይህን ስል የቀደመ ማህበራዊና ባህላዊ የፖለቲካ ታሪካችን በፍፁም መረሳት የለበትም ማለቴ አይደላም። ያንን አለመርሳታችን ነው
እንዲያውም የግድ በአስቸኳይ ማደራጀት የሚያስፈገልንን የሐቅና ዕርቅ ሒደት ሥራችን የሚያቀልልን እላለሁ። ያ ኢትዮጵያና ህዝቧን ለመግዛት ተብሎ በወያኔ የተቀረፀና የተደነገገ ሕገመንግሥት ዕርባና ቢስና መና ነውና ወዳቂ ነው። ስለሆነም የነገዋን ኢትዮጵያ የምንገነባበትን፤ ፖለቲካዊና ማህበራዊ/ሲቪክ አደረጃጀትን የምንከባከብበትን፤ ግለሰባዊ ነፃነትን የማይገስሰውን፤ የሕግ የበላይነትን የሚያረጋገጠውን የመሰረት ሰነድ ለመቅረፅ የመንቀሳቀሻ ጊዜው አሁን መሆኑን ሁላችንም መገንዘብ አለብን። ያን ስናደርግ ነው ያለፈውን ምዕተ ዓመት በሙሉ ስንመለከት ከነበርነው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ታሪክ ቅርቃር ልንወጣ የምንችለው። ይህ የመሰረት ሰነድ የእያንዳንዱን ዜጋ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተሳትፎ ያለምንም ገደብ፤ አድልዎ፤ ማግለል፤ ወይም ማስፈራራት ማስገደድና ማጉላላት ማስከበር መቻል አለበት። ሁላችንም የሕይወትን ክብርነት መቀበልና በማንም ላይ ቢሆን የሚደርስን የአካልና የአዕምሮ ሥቃይን ማስቀረት እንዲሁም በጎሣ፤ በኃይማኖት፤ በፆታም ሆነ በዕድሜ ማግለልን ማስወገድ ዕምነታችን ሊሆን ይገባል። የምንፅፈውም ሰነዳችን ይህን ሁሉ በማያሻማ ቋንቋ መመዝገብ አለበት። ከሁሉም በላይ የሰዎችን የመንቀሳቀስናየመደራጀት መብትን፤ በንግግር፣ በፅሑፍና ኪነጥበብ በነፃነት መብት መግለጽ መቻልንና የነፃ አስተሳሰብ መጎልበትንና የእምነትነፃነትን ማክበር አለብን። ፖለቲካዊ ነፃነት፤ በሕግ ፊት በእኩልነት መታየት፤ የተከሳሽን የመከራከር መብትና ማንም ተከሳሽ በሕግ ፊት በማስረጃ እስኪረጋገጠበት ድረስ ጥፋተኛ ተደርጎ ያለመወስድ መብቱና ጥፋተኛ ሆኖ ካለተገኘም ካሣ የመጠየቅና የማግኘት መብት፤ የዜጎች ኑዛዜ የማድረግ መብት፤ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ፊርማ የማሰባሰብ መብት ወዘተ፤ በአጠቃላይ በዓለም ዐቀፉ ህብረተሰብ ዘንድ ተቀባይነትን አግኝተው የተደነገጉ መብቶች ሁሉ የሚከበሩበት እንዲሆን መትጋት አለብን።በተጨማሪም ራዕዬና ግቤ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መገንባትና ማዳበር ነው ያለ ድርጅት ሁሉ ያንኑ ራዕይና ግብ ከአሁኑ በውስጠ-ድርጅት አሰራሩና አካሄዱ ሁሉ ሳይቀር መተግበር አለበት። በድርጅት ውስጥ የአመራር ክፍተት ሲፈጠር ዴሞክራሲያዊ ከሆነ ሁኔታ ውጭ የኣመራር ለውጥ የሚደረግ ከሆነ ይህን መሰል ድርጅት በምንም ዓይነት ሁኔታ ለማንም አድማጭ ስለዴሞክራሲ መስበክ የለበትም። የምንለውና የምንፈልገው ይሳካልን ዘንድ የምንሰብከውን መተግበር የግድ ይለናል።ፍትህን የምንሻ ሁሉ ፍትሓዊ መሆን ይኖርብናል። እኩልነትን የሚያነበንብ ሁሉ ሰብዓዊነታችን ብቻ ዕኩል እንደሚያደርገን መሆኑን መቀበልና ለዚያም መቆምና መሟገት አለበት። እኛ መሆን የምንፈልገውን ለመሆን መብት የምንጠይቅ ከሆነ የሌሎችንም ለመሆን የሚወዱትን የመሆን ነፃነት ማክበር ይጠበቅብናል። ተግባራችን ዕምነታችንና ራዕያችን ያንጸባርቃል?እኔ ማንም በፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ያለና ለነፃነት ተፋላሚ የሆነ ሁሉ የተሳተፈበት ድርጅት ግልፅና ተጠያቂ መሆኑን ማረጋገጥ እንዲኖርበትና እንዲሰማው እንዲሁም የድርጅቱ ባለቤት አመራር ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ አባል መሆኑን አበክሮ እንዲገነዘብ ብሎም የጎለበተ የድርጅት ውስጥ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፤ ግልፅ የሆነ ህግና ደንብ የተነደፈበትና በተለይም አመራር የተደነገጉ ህጎችን ቀስ በቀስ ሲሽር በተገኘበት ተጠያቂ የመሆን ፖለቲካዊ ባህል እንዲሰፍን ማንሳትና ማሳሰብ እወዳለሁ። መሪወቻችን ወንበር ላይ የሚኮፈሱ ሳይሆን ከአባላት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት proactive relationship ያላቸው፤ ኣባላትን እንደሃሳብ ማፍለቂያ think tank የሚጠቀሙ፤ የብዙሃን ኣባላትን ሃሳብና ውሳኔ የሚያከብሩና የሚያስተገብሩ መሆን ኣለባቸው። ጤናማ ኣዕምሮና ሰውነት ሊኖራቸውም ግድ ነው። ካልሆነ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር፣ ብሩህ ሃሳብ የማፍለቅ፣ ረዥም ሰዓት የመስራት ችሎታቸው ውስን ይሆናል። የጤና ችግር ካለባቸው ልምድና ዕውቀታቸውን በማካፈል እንደኣቅማቸው ድርጅታቸውን መርዳት ይችላሉ። እስከ ዕለተሞት ስልጣን የሚባል ባህል ግን ማስቀረት መቻል ኣለብን። አባላት የድርጅታቸው የተልዕኮ ምሕንድስና ላይ መሳተፍ፤ ራዕያቸው ጥሩ ድምዳሜ ላይ ይደርስ ዘንድ መትጋት፤ አስተዳደራዊ ብቃቱን ማዘመንና ለመጪው ጊዜ ፈተና ማብቃት ይጠበቅባቸዋል። በድርጅት ውስጥ ግማሽ ሰው-ግማሽ አምላክ (ትናንሽ ታቦቶችን) መቅረፅን ማቆም አለብን። ተገቢውን መከባበር ሳይለየን ታማኝነታችን ለራዕዮቻችንና ለአመንባቸው አቋሞች መሆንነው ያለበት። ይህ ፅሁፍ በሁሉም የትግሉ ተሳታፊዎች (መቼም አንዱ ያለ ሌላው አይኖሩምና በአመራር ደረጃ ባሉትም ሆነ የታች አባላት) ዘንድ ውይይት ያስነሳል የሚል ተስፋና እምነት አለኝ። ይህንንም ስል በየድርጅቱ ውስጥ ያሉ የአመራር አባላትና ሊተኳቸው በሚመኙ አባላት ራዕይና አቋም ላይና የመመሪያ ሰነዶቻቸው ላይ በቂ ዕውቀት ይኖረን ዘንድ እወዳለሁ።ዜጎችም የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲወች የሚያቀርቡልንን የድጋፍ ጥያቄም ብዙ ጥያቄወችን መጠየቅ ኣለባቸው። ለመሆኑ ፖለቲካዊና ማህበረሰባዊ ድርጅትና ስብስቦች ስንት አባላት አሏቸው? ካሏቸውስ ምን ያህል? ለመሆኑ ፅ/ቤቶቻቸው የት ነውየሚገኙት? ስላላቸው ካፒታልና ስለምንጩም መጠየቅ መቻል አለብን። እያንዳንዱ ድርጅት የቆመለትን ዓላማ የጉዞ ስትራቴጂውን፤ ድህረ-ወያኔ ኣዲሲቷ ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ያለውን ፖሊሲና ነገ ማንነቱን የምንሰፍርበትን የድርጊት መመሪያመግለጫውን ማየትና ማወቅ አለብን። የመመሪያው፤ የዕምነት፤ የራዕዩና ንድፈ ሃሣባዊ መሰረትና ምንጭ ከየት እንደሆነ ማወቅ አለብን። ራዕያችን ዕሴቶቻችንና ተግባራችን ይገጣጠሙ። ቆም ዕያልን ያሳለፍነውን ጊዜ እንፈትሽ። ውጤት ያላመጣልንን ስልት ችክ ብለን ኣንያዘው። ለመለወጥም ኣንፍራ። ኣስተሳሰባችን ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር እንዲጓዝ እናድርግ። በዚህ መንገድ በጊዜ የቤት ሥራችንን በአግባቡ ሳንሰራ ቀርተን ዘለዓለም ተቃዋሚዎች ሆነን እንዳንቀር። ንጉሳዊ ስርዓቱን የተቃወሙት ራዕያቸው ስኬታማኣልሆነም። ደርግንም የተቃወሙት እንደዚያው። ኣሁን ያለን ” ዕኩልነትና ፍትህ የሰፈነባት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ” ራዕያችንስ ተሳክቶ እናየው ይሆን?የዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ሕልማችን ይጠንክር!ነፃነት እኩልነትና ፍትህ ለኢትዮጵያ ህዝብ!ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!
ጥቅምት ፪፭ ቀን ፪፻፱ / 4 November 2016
mareshetmeshesha@gmail.com

Go toTop