የአቶ ተኮላ ጽሁፍ ትችት ወይንስ ሽሙጥ ከሳᎀኤል ሽፈራው/ዳላስ

ከሳᎀኤል ሽፈራው/ዳላስ

አቶ ተኮላ መኮነን በአቶ ነሲቡ የመጽሀፍ ትችት ላይ ላቀረቡት ሽሙጥ አስተያየት ለመስጠት ነው።ግለሰቡ ለነሲቡ ከመጀመሪያው አረፍተነገር ነበር ትችታቸውን የጀመሩት። እኔ የሳቸውን ሽሙጥ ከመጨረሻ መደምደሚያ አረፍተነገር እጀምራለሁ። አቶ ተኮላ “ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር” ብለው በነሲቡ ላይ የወረወሩትን ሽሙጥ ዘጉ። እኔም ይህ መዝጊያ ቃላቸውን ሳይ በግርምት ይህን አስተያየቴን ለማቅረብ ተገደድሁ።

ለዚህ መጣጥፍ መነሻ የሆነኝ አቶ ነሲቡ ለራሳቸው ለተወረወረባቸው ሽሙጥ መልስ ያጣሉ ብዬ ሳይሆን። በሰሞኑ ተከታታይ በወጡ መጻሕፍት፤ ለፅሀፊወቹ ምስጋና ይግባቸውና በዚህ መንግስት ደጋፊወች ከመጽሀፍቱ በጣም ትንሹን ክፍል አጉልተው ለማሳየት ያደረጓቸው ሙከራወች ሁሉም ሰው ተገንዝቦ መልስ እንደሚገባቸው ስላሳሰበኝ የግል አስተያየቴን ለመስጠት ነው። እናም የአቶ ተኮላ መኮነንን “ትችት” እንደኔ ሽሙጥም የዚሁ የሕወሐት/ኢሕአዴግ ደጋፊወች ሰሞነኛ ተግባር አካል በመሆኑ፤ ቃል በቃል አስተያየት ለመስጠት ሳይሆን ጠቅለል ባለ መልኩ ለማመላከት አሰብሁ። አቶ ተኮላ በተለያዩ የሕወሐት/ኢሓዴግ ስብሰባወች በዳላስ አካባቢ የተደረጉትን በመሪነትና አስተናባሪነት የሚያገለግሉ ሲሆኑ። ይቃወሙናል ያሏቸው ኢትዮጵያውያንን በፖሊስ ከየስብሰባወች እንዳይደርሱ ከሚያደርጉት ሰወች አንዱ ናቸው። የዚህ ዘረኛና ጸረ ዴሞክራሲ አገዛዝ ደጋፊ ከመሆን ባሻገር ስርአቱን የሚቃወሙ ወገኖችን በማክቸልቸል ቅድሚያ ቦታውን ይይዛሉ። በመሆኑ ይህን የሳቸውን ሽሙጥ ሳይ መልስ የሚገባው መሆኑን ስለተገነዘብሁ፤ በሙሉም ባይሆን በከፊሉ እነሆ።

አንባቢ የቃሉን ውበት አይቶ የዞረበት ሊለን ይከጅል ይሆናል። ተገቢ አስተያየት በማለት ይህን ጽሁፌን በትክክል እንዲከተለኝ በትህትና እጠይቃለሁ።

“ኢትዮጵያ ለዛላለም ትኑር” አሜን። ኢትዮጵያ ስንልና ኢትዮጵያ ሲሉ የተለያየ ትርጓሜ እየሰጠ ስለመጣ ችግር መፈጠሩ አልቀረም። ኢትዮጵያ ለዘላለም ኮርታና ተከብራ ትኑር ያሉት የዚያ ትውልድ መሪወችና ታጋዮች ትቂት በተለያየ አጋጣሚ ከተረፉት (እኔንም ይጨምራል) በቀር ይህን መፈክር ከመፈክርነት ባለፈ ለመተግበር በነበራቸው ጽኑ እምነት እስከ የመጨረሻው ዋጋ ሕይወትን አሳልፎ ለትግል በመስጠት ከፍለዋል። ለአብነትም በአንድ የመጋቢት ወር ብቻ መስዋእት የሆኑት ተስፋየ ደበሳይ፤ ዮሐንስ ብርሐኔ፤ጸጋው አየለ እና ሌሎች ነባር ታጋዮን ይህች አገር አጥታለች።

ፈርሳ እንሰራታለን የሚሏትን የኢትዮጵያ የዘመኑ ገዥወች በክብር፣ በሲቃና በፍቅር አይደለም የሚያነሷት። ኢትትዮጵያ ሲሉ “የበሔር/ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች እስርቤት” ማለታቸው ለመሆኑ በተደጋጋሚ ጽሁፎቻቸው፤ በፖለቲካ ፕሮግራማቸው የወጣ በመሆኑ ለትግላቸ ምክንያትም አድርገው ይወስዱታል። ኢትዮጵያን ዘላለማዊት አንድ ጥንታዊ ታሪክ ያላት ሐገር ብለው አስበው አያውቁም። እምነቱም የላቸውም። እንዴውም በአላማ ደረጃ ኢትዮጵያን የመቶ አመት ታሪክ ያላት ቅኝ ገዥ ናት ብለው ያምናሉ። ይህ አበባላቸው ዛሬም በተለያዩ የሕወሐትና የሕወሐት አጋፋሪወች በኩራት ይነገራል። ሕወሐቶችና ደጋፊ አጫፋሪወች ኢትዮጵያ ሲሉ ብሔር/ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በፈቃዳቸው ያገጣጠሟት ኢምፓየር አገር ማለታቸው ነው። ዛሬም ከ22 አመታት በኋላ የትግራይ ነጻ አውጭ፤ የአፋር ነጻ አውጭ ወዘተ. እያሉ ስም ሳይለውጡ መቀጠላቸው ዋነኛ ምክንያት በፈቃዳችን ሲያሻን አብረን የምንኖርባት አለያም የምንለያይባት የስምምነት መንግስት ናት ብለው ስለሚያስቡ ነው።

አቶ ተኮላ ኢትዮጵያ ሲሉ የወያኔ ሰራሽ ማለታቸው ለመሆኑ አልጠራጠርም ምክንያቱም በግልጽ በአደባባይ የዚህን ዘረኛ ስርአት ግንባር ቀደም ደጋፊ በመሆናቸው የተለየ አቋም እንደማያስቡ ወይንም እንደማያስተናግዱ በማመን ነው። በዚህ አባባሌ ካልተስማሙ ከከራረሙበት ጎራ መለየት አምጠዋልና እሰየው ያሰኛል። ወደዋናው ጉዳይ ስመለስ ኢትዮያ ስንል ያች ከንግስተ ሳባ ጀምራ የኖረች ሕዝቧም (ሕዝቦቿ አላለሁም) በአንድ የኖሩ። ክፉን ቀን ደግን ጊዜ የተካፈሉ ናቸው። በኦቶማን ቱርክ አጋዥነት የወረራትን የግራኝ መሀመድ፤ ምጽዋንና የምእራብ ግዛቷን ለመጠቅለል በማሰብ በተደጋጋሚ የዘመተባትን የግብጽ ወረራን። ብሎም የ1884 እ ኤ አ የበርሊንን ስምምነት ከትቢያ የቀላቀለውን 1888 ዓምን የአደዋ ጦርነትን ያስቧል። ኢትዮጵያ ስንል አብዲሳ አጋ በላይ ዘለቀ የተዋደቁላትን  ሁለቱ ወጣቶች አብረሐ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም በአገር ፍቅር ተቃጥለው  ጠላትን በአደባባይ አዋርደው መስዋእትነትን ይተቀበሉባት ማለታችን ነው። ኢትዮጵያ ስንል ዘረያእቆብ የነገሰባት፤ ያሬድ በዜማው የተቀኘባት ጥንታዊት ማለት ነው። ኢትዮጵያ ስንል የነ አምደጽዮን፤ በካፋ አገር ከታላቁ እራስ አሊ እስከ እቴጌ መነን የነገሱባት ማለታችን ነው። እንደነሱ የብሔሮች እስርቤት ማለታችን አይደለም። የዚህ ስርአት ደጋፊወች ብሔሮች/ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ለዘመናት በሰፊ የእስር ሰቆቃ ወደው ሳይሆን ተገደው ኖረውባታል ይሉናል። እናም የሕዝባዊ አርነት ትግራይ ተወልዶ ማደግ ብሎም ለድል መብቃት ግፍ ወልዶ ግፍ ያሳደገው ለማለት ሲሆን። ሰፊው የእስር ሰንሰለት የተፈታም በዚህ ስርአት ነው የሚሉት። አሁንም አቶ ተኮላ በዚ የሕወሐት አባባል ካልተስማሙ አቋም ለውጠዋልና እንኳን ደህና መጡ ያስኛል። ግን ችግሩ በጭምብል የዚህችን አገር ስም ማንሳትና በተግባር እንድትጠፋ ሌት ከቀን ከሚደክሙት ጎራ ቆሞ ትክሻ መስጠት ከእውነተኛው የዚህችን አገር መቀጠል አምነው ስርአቱን የታገሉ፤ ታግለውም ያለፉ፡ ዛሬም በእስር ፍዳን ከሚቀበሉ (እርዮትን፤ እስክንድርን፤አንዷለምንና ሌሎችን ያስቧል) ስሜት፤ እምነት፤ አባባልና እውነተኛ የሐገር ፍቅር ይለያል። ከመነሻየ እንደጠቀስኩት ከታች ከመጨረሻ አባባላቸው ለመጀመር የተገደድሁት ግለሰቡ ለአለፉት 22 አመታት የዚህ ስርአት ተቆርቋሪ ሆነው ስለማውቅና አሁንም በሰሜን አሜሪካ ሕወሐት/በአዴን ባቋቋሙት የቁጩውች  ልማት በሚሉት ማህበር አንቱ የተባሉ ስለሆኑ ነው። በይበልጥም ኢትዮጵያን በተግባር ያፈረሰ፤ የባሕር በር አሳልፎ ሰጥቶ የ90 ሚሊዮኖችን ሐገር ወደብ አልባ እና ለታናናሽ ጎረቤት ለነ ጅቡቲ የጓሮ ጥገት ያደረገን ስርአት ደጋፊ በኢትዮጵያ መሳለቅ አይገባውም ብየ ሰላሰብኩ ነበር።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አልቃሽ እና አወዳሽ  -ህዳር ፳፱  

በኢትዮጵያ ፖለቲካ በኢሕአፓ ያላለፈ ለአሳር እንዲሉ ግን ያነን ድርጅት ገዳይና አስገዳይ የሆነውም ያው አለፍሁበት የሚሉ ግለሰቦች ለመሆኑ ከአለፉት አርባ አመታት ታሪካችን ተምረናል። የከተማ ቀይሽብር በተዋናይነት የተካሔድውና ደናቁርቱን ስለ ድርጅቱ መዋቅርና የስውር አሰራር ሚስጥር አያያዝና ዲስፕሊን አሳልፎ የሰጠውና ለፍጅቱ መጠን ስፋትና ጥልቀት እንዲያገኝ ያደረገው በዚያን ጊዜ በ “ሀ እና ለ” የተነሳው አንጃ ለመሆኑ በዚያ ያለፍን ሁሉ የምናውቀው        ነው። “ነሐሴ 1 ቀን 1969 ዓም በአዲስ አበባ ቀጠና 1 የተሳካ እንቅስቃሴ መድሐኒት፤ ገንዘብና መሳሪያ አግኝቶ፤ ለሚመለከተው የፓርቲ ክፍል ከማስረከቡ በፊት የአሐዱ መሪ የነበረው ተሳታፊ አባላትን የተገኘውን መድሐኒት፤ ገንዘብና መሳሪያ፤ የእነርሱንም ጨምሮ ከተረክቦ የአንጃው አባል እንደሆነ አስታውቆ ለደርግ ተመላሽ እንዲሆን አድርጓል።” ሚያዚያ 29/1969 የአለም ሰራተኞችን ቀን አስመልክቶ ሰልፍ ለመውጣት በኢላማ አስገዳጅነት የተጠራው የድብቅ ሰልፍ ለደርግ ቀድሞ ደርሶት በዚያ ቀን ለተካሄደው ፍጅት ከደርግ በላይ አንጃው እንደነበር ያ ትውልድ ያትታል። ይህንን የአንጃውን እንቅስቃሴ በሰውና በንብረት ላይ ያደረሰውን አደጋ በ ያ ትውልድ ቅጽ 3 ከ187-199 ይመልከቱ።

አንዳንድ መጽሀፍት ሲወጡ ዛሬ ከአርባ አመታት በኋላ ገሚሶቹ ቀይ ሽብር ነጭ ሽብር ባይኖር አይከሰትም ነበር ሊሉን ይከጅላሉ። ሆኖም አቶ ነሲቡ በመልካም የትችት ድርሰቱ አንባቢ በጥሞና ሊያይ እንዲችል በቂ ዋቢ በጊዜው የቀረቡ ጽሁፎችን አያይዟል። አቶ ተኮላ በቀረበው ትችት ለማሽሟጠጥ ከመከጀል በፊት ነሲቡ ያቀረባቸውን ዋቢ መጣጥፍ ቢመለከቱ የቱን ያክል በረዳ ነበር። በእርግጥም አቶ ተኮላ ከማሽሟጠጥ በፊት ዴሞክራሲያን ከ የካቲት 1966 እስከ ጥር 1969 ዓም በአራት ቅጽ የተካተቱ 87 እትሞችን አገላብጠው ማየት በተገባቸው ነበር። ከፍ ብለውም እንዲህ ይላሉ።

“ከዚህ በላይ ባነሱት ነጥብ ላይ ከሳቸው ጋር መለየቴን ስነግራቸው እንደማይቆጡ በማሰብ ነው። የሰላም ትግል ነበር ኢሕአፓ ይመራ የነበረው ሊሉን ከሆነ አንድ ቤት ተቀምጦ የተለያየ ነገር ስላስተዋሉ ተማሪዎች አይነት መሰለኝና ተገረምኩ። ታዲያ ያ ሁሉ ትግልና መስዋእትነት ለመንግሥተሰማያት ሥፍራ ምሪት ነበርን? የከተማ የትጥቅ ትግል ትክክል ነበር ብለው አሁንም የሚያምኑ ከሆነ ደግሞ ለምን አመኑ አልልዎትም። በዚያ ላይ እንደምንለያይ ብቻ ልነግረዎ።”

ተጨማሪ ያንብቡ:  ያማራ ሕዝብ ዐብይ ስሕተት፤ በማንነቱ የሚጠሉትን ለመውደድ መሞከር

አቶ ተኮላ ከዚህ ከላይ ባሳየሁት ሽሙጡ ሁለት ሀሰቦችን አያይዘው ተሳልቀዋል።

1- ኢሕአፓ የሰላም ትግል ያሰበበት ወይንም የተገበረበት ጊዜ አልነበረም

2- የከተማውን የትጥቅ ትግል ጀማሪም ፈጻሚም እሱው ነው በማለት ሊያሳዩ ሞክረዋል

ይህን ሀሳብ ለማደናቆር አቀረቡት እንጅ አቶ ነሲቡ በሚገባ እና በማስረጃ አስደግፎ በመልካም ቋንቋ አስቀምጦታል። ኢሕአፓ የሚባል ድርጅት በይፋም ሳይወጣ እንዴውም ከዴሞክራሲያ እትሞች ንባብ ውጭ ምንም አይነት ሀይልን የተመረኮዘ አመጻ ባልነበረበት ሕዳር 14 ቀን 1967 ዓም ደርግ ጊዚያዊ ወታደራዊ መንግስት ብሎ ስልጣን በጨበጠ ሁለት ወር ከ14 ቀናት በሰላም እጅ ሰጥተው የታሰሩ 61 የቀድሞ መንግስት ባለስልጣናትን በአንድ ሌሊት ጨርሶ ጠዋት የኢትዮጵያን ሕዝብ በማርሽ በታጀበ ፎከራ አርድቷል። ከዚህን ጊዜ ጀምሮ የአገሪቱን መተዳደሪ ሕግ አፍርሶ የነጻ እርምጃ በመውሰድና አገርን በአዋጅ ማስተዳደርን ቀጥሏል። የስልጣን ሽግግሩ በተከናወነበት ቀን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት ማንም ሰው ከዚያች መስከረም ሁለት ቀን ጀምሮ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ብሎም ከሦስት በላይ ሆኖ በአደባባይ ቆሞ መገኘትን ጭምር በህገወጥነት ፈርጆ አዋጁ ማስጠንቀቂያ ሰጧል። ምናልባት አቶ ተኮላ በአካባቢ ላይኖሩ ይችላሉ ከነበሩም ይህን ትልቅ አንባገነናዊ እርምጃ እንዳላስተዋሉ ለአንባቢ ያስገርማል። አሽሟጣጩ ከፍ ሲል [1]በዚያን በትግሉ ዘመን ስለተነሱ ልዩነቶች ማንሳት አልፈለጉም። ለምሳሌ የጊዚያዊ ሕዝባዊ መንግስት አቋምንና፤ የዴሞክራሲ ጥያቄን አስመልክቶ በጊዜው በተነሳው ክርክር “ኢሕአፓ ዴሞክራሲ” ሲልና በደርግ በኩል በተለየም አይዲዮሎጅውን የሰጡት የምሁራን ስብስብ በመኢሶን ግንባር ቀደምትነት የተሰበሰቡት ያነሱት የነበረው የዴሞክራሲ” ጥያቄን አቶ ተኮላ ወደ ጎን ትተው በቃላት ልዩነቶች ላይ እንዲህ ሲል ይሳለቃሉ።

ብዙ ነገር ላይ ልንገባ ነው። በአሁኑ ሰዓት የመታገያ መፈክር አይደለም ብለን በመቀበል ዋናውን እርእዮታዊ መተክሉን እርእዮቱን መተዋችንን እንስማማና ግንዱን ጥሎ እንዴት ቅርንጫፉን እናድን ብሎ መከራከር እንዳይመስልብን እንጠንቀቅ። ይኸ አይደለምእናቸንፋለን እናሸንፋለን፣ ላብ አደር ወዝ አደር። በሚልም የብዙ ወጣት ደም መፍሰሱን አንዘንጋ። በደርግ ፋብሪካ የተቀጠረ ወዛደር ኢሕፓን የተቀበለ ላባደር ማለታችን አልነበረም። እንዴው ስልቻ ቀልቀሎ ቀልቀሎ ስልቻ ነው እንጂ። የተግባባን ይመስለኛል ደርግ የፋሽዝምን መመዘኛ ያሟላ አያሟላ አረመኔ ከፋሽስት የበለጠ ፋሽስታዊ ድርጊት የፈጸመ መንግሥት ነው።

ግለሰቡ ምንም የሚያውቁት እንዳልነበር ከዚህ አባባል ለመረዳት ይቻላል። ለኢሕአፓ መፈጠር ምክንያት የነበሩ ሁኔታወችን Tower in the sky መጸሀፍ ደራሲም በሚገባ ያቀረቡት ሲሆን። የመሬት ላራሹ ጥያቄ አንጋፋውን ቦታ የያዘ እንደነበር በሁሉም የዚያን የቅድመ አብዮትና በአብዮት ወቅት የተጻፉ ወይንም አሁንም በመጻፍ ላይ ያሉትን መመርመር ተገቢ ነው። “Tower in the sky” አንዱ ሲሆን ጸሐፊዋ የፓርቲውም አባል በመሆናቸው በ “በወዛደር” እና “ላባደር” ወይንም “እናቸንፋለን” እና “እናሸንፋለን” በሚል የቃል አጠቃቀም በተነሳ ልዩነት ተነስቶ ደም አልፈሰሰም። የታሪኩ አቅራቢ ሕይወት ተፈራም ቢሆኑ በቃላት ልዩነት ቀይሽብር ተጀመረ አላሉም። አቶ ተኮላ (ትንሽ ሽሮ ይዞ ወደ አሻሮ ጠጋ) እንዲሉ የዚህን የሁለት ፍቅረኞች ታሪክ መታሰቢያ በተጻፈ መጽሀፍ ሰበብ ከባድ ዋጋ የከፈለ ትውልድን መዝለፋቸው በአሁኑ ወዳጆቻቸው የሚያስመሰግን ቢሆንም፤ በታሪክ ፊት ግን ተጠያቂ ማድረጉን ባልዘነጉት ነበር። የቀይ ሽብር ጽልመት በሕዝብ ላይ የወረደው በቃላት ልዩነት በተፈጠረ ግብ ግብ አልነበረም አይደለም። ላለመሆኑም ለዋቢነት ያክል ይህ ከዚህ በታች ያለን የጊዜ ሰሌዳ እንዲመለከቱ እጋብዛለሁ። የደርግና/መኢሶን ካምፕ ኢሕአፓን ለማጋለጥ አስበው ሊሆን ይችላል ከሐምሌ ወር 1967 ዓም እስከ ታሕሳስ 1968 ዓም የዘለቀ የአዲስ ዘመን እለታዊ ጋዜጣ አብዮታዊ መድረክ የሚል አምድ ከፍተው በሁለቱ ጎራወች ማለትም ዴሞን (ኢሕአፓን) የሰፊው ሕዝብ ድምጽን (መኢሶንን) በሚከተሉ መካከል የነበሩ ልዩነቶች ተስተናግደዋል። ልዩነቶችም በዴሞክራሲና፤ በመንግስት ጥያቄ ያላቸውውን የሁለቱ ጎራ እመነት ለማሳየት ሲሆን። በዴሞ ዙሪያ የጊዚያዊ ሕዝባዊ መንግስት አስፈላጊነት በሰፊው ቀርቧል። እንዲሁም ዴሞክራሲ ብሎ በገደብ ማለት አንባገነንነትን መደገፍ መሆኑ ሕዝብ እንዲያውቅ ተከራክረውበታል። በግዜው ወደኢትዮጵያ ገጠሮች የተላከው ተማሪም (እኔንም ይጨምራል) በነዚህ በሁለት አብይ እርእሶች ተወያይቶ ሰፊው ዘማች ወደከተማ ሲመለስ የኢሕአፓን መስመር ለመከተል እረድቶታል። መሰረታዊ ሆኖ የወጣው ልዩነት ደርግ በጊዚያዊነት ይቀጥል ያለው መኢሶንና፡ ጊዜአዊ ሕዝባዊ መንግስት (ጊሕመ) አብዮቱን ይምራ ያለው ኢሕአፓ በሌላ በኩል ሲሆን። ከላይ እንዳሳየሁት በዴሞክራሲ ጥያቄ ላይ በገደብ ያለው መኢሶን/ደርግ ባንድ ጎራና ዴሞክራሲ ብሎ ገደብ የለም ያለው ኢሕአፓ በሌላ ጎራ ቆመው ብዙሀኑ ሕዝብ የኢሕአፓ/ዴሞክራሲያን አቛም በመደገፉና ትግሉን በመቀላቀሉ የደርግ/መኢሶን ካምፕ ቀይ ሽብር ይፋፋም መፈክርን እስከ ትግባሬው አድርሰውታል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ወርሃ ግንቦት ሲታወስ! - (ኢሮብ መብት ተማጓች ማኅበር የበተነው ጽሑፍ)

ለዚህ መጽሀፍ ትችትም ሆነ አስተያየት ለመስጠት ከየተደበቁበት ጎራ አንገታቸውን አቃንተው ያየናቸው የቤኒ ገጽ ታዳሚ ገነነው አሰፋና፤ የአይጋው ድህረ ገጽ ተቀኝ አቶ ተኮላ፤ የመጽሀፉን በጣም ትቂት ክፍል “የጌታቸው ማሩን” ሕልፈት አስመልክተው መንደርደራቸው አስገራሚ ባይሆንም። ከ38 አመታት በኋላ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ የዚያን የፋና ወጊ፤ አገር ወዳድ ብርቅየ ሰማእታትን ስም ጥላሸት ለመቀባት መሞከር ያስገምታል እንጅ ድጋፍ አያስገኝም። ሆኖም እውነታው ግን ሀ ና ለ (አንጃው) ባይነሳ ኖሮ የፍጅቱ መጠንም ምን ያህል በቀነሰ ነበር። አይደለም ያብቻ ዛሬ ለተፈጠረው የአገር ማጥፋት ተግባር አንጃው ጠንካራን ሐይል በማዳከም ሚና አልነበረውም ማለት እንዴት ይቻላል?

ከፍ ብለው አቶ ተኮላ እንዲህ ይላሉ፦

ኢሕአፓ የፖለቲካ ጥያቄ አንስቶ ለስልጣን የታገለ ድርጅት አይደለም የምትለዋ አባባል የምትገርም ነች። ታዲያ ለምን ሲታገል ነበር? የጊዚያዊ ሕዝባዊ መንግስት መፈክር በወቅቱ ሕዝብ ወጣት ያለቀበት መፈክር እንደ ነበር እየተበልኩ መፈክሩ ወቅታዊና ትክክል ነበር ብሎ ዛሬም የሚያምን ካለ እንደ መብት ወሰደንላቸው እንለፍ እንጂ በአባባሉ እምንስማማ አልመሰለኝም። እንዴው አቶ ነሲቡ ካነሱት ዘንድ አንዳንድ ነገር ልጠይቃቸው።

 

ስለ (ጊሕመ) ያወሩንና የአቶ ነሲቡን አባባል ደግሞ ይሳለቁበታል። አቶ ተኮላ ለመጻፍ ሲነሱ ከላይ እንደጠቆምኩት ሌላን ለማስደሰት ጽሁፋቸው (መተያያ) በመሆኑ አልፈርድም። ግን ነገርን ማደባለቅ ደግሞ መልስ ይጠብቀዋል። አብዮታዊ በሆነ ወቅት ስልጣን በአየር ላይ መሆኑን ማንም ሊስተው አይገባም። ቀድሞ የቀለባት ይይዛታልና። በዚያች ቀውጢ ጊዜ የሆነውና ደርግ የሚባል ጉግማንጉግ በአገራችን መፈጠር፤ ሕዝብን ጨርሶና አዳክሞ ለአገር በታኝ ሰጦ ማለፍ ምክንያቱም አብዮት መሆኑ ነበር።

አቶ ተኮላ ያምታቱት ኢሕአፓ ጊዜአዊ ሕዝባዊ መንግስት (ጊሕመ) ብሎ ነበር ይሉናል። ይህን መፈክር ሲተረጉሙት ስልጣን ለፓርቲው ማለት ነው በሚል አባባል ይፈጸማሉ። ልብና ማስተዋሉን ካገኙ ሕዝባዊ መንግስት ይቋቋም አለ። ለዚያም ታገለ አታገለ። ከመሪ እስከ ተራ ታጋይ (ላባደሮች፤ አርሷደሮች፤ ወጣት ተማሪወች እና አገር አፍቃሪ መለዮ ለባሾች) መስዋእትነት ከፈሉበት። ባጭሩ ሕዝባዊ መንግስት ማለት እኔ ስልጣን ልያዝ ማለት አይደለም አልነበረም። ለዚያም ሙሉ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል።

ቸር ይግጠመን

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !!![2]



[1] ክፍሉ ታደሰ ያ ትውልድ ቅጽ 3 ገጽ 187-198

ዴሞክራሲያ የኢሕአፓ አቋሞች ከ 1966 እስከ መጋቢት 1969 ዓ ም

1 Comment

  1. EPRP kkk anyone who criticizes EPRP is woyane kkkk you have pushed so many Ethiopians out of the anti Woyane struggle by labelling them as Woyanes yet you guys are Woyane and your policies had some similarities ie the support of Eritrean independence, and the Support of Somali Invasion etc now u start the same old defamation

Comments are closed.

Share