ሁሉም በነጻ ሜዲያ ስም የሚታወቁት የሬዲዮ: የቴሌቭዥን እና የህትመት ሜዲያወች ሊያወሩባቸው የሚፈልጓቸው እና እንዲነኩባቸው የማይፈልጓቸው ጉዳዮች እንዳሉ ለመረዳት ችያለሁ:: ተቃዋሚ መነካት የለበትም በሚል ምልከታ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶችን በተናጠል ወይም በጅምላ ለመተቸት የሚነሳ ግለሰብ ወይም ድርጅት ላይ የህዝብን ትግል ለመግደል እንደተነሳ የወያኔ ተላላኪ አድርገው የሚወነጅሉና የጥቃት ኢላማ እንዲሆን የሚቀሰቅሱ ሀላፊነት የጎደላቸው ሜዲያወች መኖራቸው ሀቅ ነው:: አንዳንዶች የፈለገው የወረደ ጽሁፍ ቢቀርብም የቀረበው ጽሁፍ መንግስትን የሚቃወም እስከሆነ ድረስ ለመቀበል የማያመነቱ ናቸው:: ግንቦት 7 ን የሚቃወም ጽሁፍ የሚወዱ ወይም የማይወዱ: ኢሕአፓ እንዲነቀፍ የሚፈልጉ ወይም የማይፈልጉ: ኦነግ በጥሩነቱ ብቻ እንዲነሳ የሚፈልጉ ወይም በመጥፎነቱ ብቻ እንዲነገርለት የሚፈልጉ – – – እንዳሉ ተረድቻለሁ:: ከሁለት ቀናት በፊት አቶ ይገርማል የሚባሉ ሰው ከመቶ አመት የቤት ስራወቻችን አንዱ የሆነው ኦነግ በሚል ያቀረቡት ጽሁፍ ቁምነገር ያለው መሆኑን ተረድቸ ወደ ፌስቡኬ ሸር ላደርግ ስል ከድረገጹ ላይ ላገኘው አልቻልሁም: ሰርዘውታል:: የመንግስት መገናኛ ብዙሀንን በአፋኝነት የሚከሱት ነጻ የሚባሉት ሜዲያወች የአቶ ይገርማልን ጽሁፍ ካወጡ በኋላ መልሰው መሰረዛቸው የተለያዩ ሀሳቦች እንዳይንሸራሸሩ እንቅፋት የሚፈጥሩ ማለትም ራሳቸውም አፋኝ መሆናቸውን ያሳያል::
ያም ሆነ ይህ ነፍጠኛ ማለት ከስድብ አልፎ የሚያሳፍር: የሚያስጠይቅ እና ለጥቃት የሚያጋልጥ መጠሪያ ተደርጎ ይታሰብበት በነበረበት ወቅት “ይድረስ ለነፍጠኞች” ብየ በፌስቡክ ላይ በማስነበቤ አሁን ላለው በነፍጠኛ አባት እናቶቻችን ታሪክ ለመኩራት እና ብሎም “አዎ ነፍጠኛ ነኝ” ብሎ ለመውጣቱ የራሴ የሆነ እገዛ አድርጌ ይሆን? ብየ አስብ እና ለህዝቤ ትንሽም ቢሆን በጎ ነገር አበርክቻለሁ በማለት ጮቤ እረግጣለሁ:: የአሁኑ የአማራ ወጣቶች በድፍረት አደባባይ ወጥተው መፋለም እንዲችሉ አንድ ምክንያት እንደሆንሁ: ብርታት እንደሰጠሁ አድርጌ አስብና በደስታ እሰክራለሁ:: የሞቱትን እናትና አባቶቻችንን ቀስቅሸ “ይድረስ ለነፍጠኞች” የሚል ጥሪ በማድረጌ ሙት መንፈሶቻቸው ሰምተውኝ ህዝቡንና ሀገሩን ከጥቃት ለመከላከል ግንባሩን የማያጥፍ ወጣት ይኸው በአይኔ ለማየት በቃሁ:: ለዚህም ፈጣሪየን ከልብ እያመሰገንሁ የሞቱትን ወገኖቸን “ነፍስ ይማር! በሰላም እረፉ!” እላለሁ:: ኦነግ ለብዙ ኦነጎች የተከፈለ ቢሆንም ሁሉም ንዑስ ኦነጎች ዞረው ዞረው ያው የኦሮሞን ነጻነት ማለት መገንጠልን የሚደግፉ መሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው:: አንዳንዶቹ አሁንም በዚያው በዱሮው የመገንጠል አቋማቸው ጸንተው የኦሮሚያ ሪፓብሊክን ለመመስረት የሚያልሙ ናቸው:: አንዳንዶቹ ደግሞ ኦሮሞው በኢኮኖሚው: በፖለቲካውም ሆነ በስልጣን እንደህዝቡ ብዛት ተመጣጣኝ ድርሻ እንዲሰጠው እና ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ለማስቻል የሚታገሉ እንደሆኑ ሲያስመስሉ ይቆዩና ተመልሰው ያንኑ የመገንጠል ጥያቄያቸውን ሲያራግቡ ይገኛሉ:: እነጃዋር የተናገሩት የሽግግር መንግስት እና የመከላከያ ሀይል ምስረታ አላማ የሚነሳው ከዚህ የመገንጠል ፍላጎት ነው::ጃዋር እና አንድ ፕሮፌሰር BBN ከተባለ ሬዲዮ ጣቢያ ጋር ያደረጉትን ቃለመጠይቅ ተከታትያለሁ:: በዚህ ቃለመጠይቅ ላይ የተገነዘብሁት ነገር ቢኖር “ምንም ልታመጡ አትችሉም” የሚል ድብቅ መልእክት ያለው በሽፍንፍን የቀረበ ሊቀር የማይችል የኦሮሚያ ነጻ መንግሥት ምስረታ ፍላጎት መኖሩን ነው:: ማንም ደገፈውም አልደገፈውም ለውጡ አይቀርም ብሎናል ጃዋር:: የሽግግር መንግስት ስለሚል ነገር አልሰማሁም ብለውናል ፕሮፌሰሩ:: ሌላ አንድ ዶ/ ር ደግሞ እናውቅላችኋለን አትበሉን ብለውናል:: የሚያደርጉት ነገር ከሌሎች ወገኖች ጋር በሚናበብ መልኩ ሳይሆን እነርሱ በሚፈቅዱት መንገድ እንደሚሆን ነው እየነገሩን ያሉት:: በጋራ ግዴታ መታሰር እንደማይፈቅዱ ነው ሊያስገነዝቡን የፈለጉት::የአማራ ልጆች ምን ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ አላውቅም:: አቅራሪ “እዚያ ማዶ ሆኖ ክፉ ሰው ተጣራ እዚህ ማዶ ሆኖ ክፉ ሰው ወይ አለው ጎበዝ ተጠንቀቁ ይህ ነገር ለኛ ነው” ያለው ካለ ነገር አይደለም:: ኦነጎች የኦሮሞ ካርታ
አላቸው:: እኔም የአማራን ካርታ አውጥቸ በልቤ ይዣለሁ:: ሞረሽ: ቤተአማራ: ዳግማዊ መዐህድ: የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሀይልና ሌሎችም ሳያስቡበት አይቀርም ብየ አስባለሁ:: ለነገሩ ኦነግን ያተበተው ተቃዋሚ የአንድነት ሀይል የሚባለው ነው:: የኦሮሞ ህዝብ አሁንም ቢሆን ከአማራው ወንድሙ ጎን ተሰልፎ እንደዱሮው ሁሉ ኢትዮጵያን ለመከላከል ወደኋላ የሚል አይደለም:: ለኢትዮጵያ ሲሉ ያላቸውንነገር ሁሉ አሳልፈው የሰጡ ወላጆቻቸውን አርማ አንስተው ለአንድነቷና ለሉአላዊነቷ የሚሰለፉ ኦሮሞወች ከኦነግ ጀሌወች በእጅጉ የበለጡ መሆኑ እየታወቀ የአንድነት ኃይል ነኝ የሚለው ወገን ህዝቡን ማእከል አድርጎ መስራት ሲገባው ኦነግን ወደመለማመጥ በመውረዱ የ 50 አመት ጩጬው ኦነግ ሲገለማምጠን: በትእቢት ሲወራጭብን እያየንእየሰማን ነው:: ኦነግን በሰላ አንደበት እና በበሰለ ጽሁፍ የሚተቹትን አስተዋይ ሰዎች የሚያረክሱ የኦነግ ተከታዮች ሊመጣ የሚችለውን አስከፊ ውጤት አስቀድመው ማየት የተሳናቸው ናቸው:: ኦነግ አደብ ገዝቶ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ተሰልፎ ወያኔን ለማስወገድ እና ከወያኔ ውድቀት በኋላም የጋራ የሽግግር መንግስት እንዲመሰርት የሚመክሩትን ሁሉ እያበሻቀጡ እንደሆነ ከሚቀርቡ አስተያየቶች እየተረዳን ነው:: ስለመጭው የምንጨነቅ እኛ ብቻ ልንሆን እንደማይገባ ሁሉም እንዲገነዘበው ያስፈልጋል:: እስካሁን የጮህነው ጩኸትከፍርሀት የመነጨ ሳይሆን ከማስተዋል የመነጨ እንደሆነ ማንም ሊረዳው ይገባል:: ስለዚህ ድንገት አስቸጋሪ ሁኔታ ቢከሰት መደነጋገር እንዳይፈጠር ሲባል አማራው ተጠንቅቆ መጠበቅና ራሱን መከላከል ይኖርበታል ብለን ስለምናምን የተጠናከረ ወታደራዊ ኃይል ማቋቋም እና የምንሞትለት ካርታ ማውጣት ግድ ይለናል:: ይህን ስል መአት ነገር እንደምባል አይጠፋኝም:: የአማራን እና የኦሮሞን አንድነት ለማደናቀፍ እንደተነሳሁ የሚያስቡ የዋሆች ሊኖሩ ይችላሉ:: የወያኔን ዕድሜ ለማስረዘም ቆርጨ የተነሳሁ አድርገው የሚወነጅሉኝ አይጠፉም:: ማንም ያለውን ይበል መሆን ያለበት ግን ይኸው ነው:: አማሮች ወገኖቸ ስጋቴ ይገባቸዋል:: እንደ እስስት የሚለዋወጡ ቡድኖችን አምኖ እጅና እግርን አጣጥፎ ተዘናግቶ መቀመጥ አግባብ አይሆንም:: ይነስም ይብዛም ኦነግ እና ወያኔ የረጅም ጊዜ ፖለቲካዊና ወታደራዊ እውቀትና አደረጃጀት አላቸው:: ሁለቱንም የሚያስተሳስራቸውና የሚያስማማቸው ደግሞ አማራ ጠላት ነው የሚለው አመለካከታቸው ነው:: እኛ ወታደራዊ ኃይል እናቋቁማለን ስንል ምንም ያላጠፉትን አማራ ያልሆኑ ወገኖቻችንን ለመደብደብ አይደለም:: እንዲህ አይነት ትምህርት ከወላጆቻችን አልተማርንም:: በንጹሀን ላይ ግፍ ለመፈጸም የሚያስችል በክፋት የተበከለ ህሊና ኖሮን አያውቅም: ወደፊትም ሊኖረን አይችልም:: ነገር ግን ጠላቶቻችን ናቸሁ የሚሉን: ሞትና ስደታችንን የሚመኙ ቡድኖች እንዳሉ እናውቃለን:: የኢትዮጵያ አንድነትበአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ የሚመጣ አይደለም:: ሁሉም ቡድኖች ወደስምምነት መጥተው የጋራ ሀገራችንን ዴሞክራሲያዊት ለማድረግ ፍላጎቱ ካለ የመጀመሪያው ምርጫችን ይሆናል:: ካለበለዚያ ግን ራሳችንን ለመከላከል የሚያስችል አቅም ሊኖረን ግድ ነው:: ፈረንጆች might is right የሚሉት አባባል አላቸው:: በአለም ላይ ያለው እውነታም የሚያሳየው ይህንኑ ነው:: ጉልበት ያለው ሰው ማድረግ የሚፈልገውን የማድረግ ያልተጻፈ መብት አለው:: ለምሳሌ አሜሪካ ፓናማን ወርራ የፓናማን ፕሬዚደንት በምርኮ ወስዳ ስታስር ለምን ብሎ የጠየቃት አልነበረም:: የኢራቅን መንግስት የኒዩክሊየር ሀይል በማቋቋምወንጅላ በአመራሯ ስር የተባበሩት መንግስታትን ጦር አሰልፋ ኢራቅን በሀይል ወርራ ፕሬዚደንት ሳዳም ሁሴንን ይዛ በሞት ስትቀጣ ልክ አይደለም ብሎ የሞገታት: ከርምጃዋ እንድትቆጠብ ያደረገ አልነበረም:: ኢራቅ እየገነባች ነው ሲባል የነበረው የኒዩክሊየር ጣቢያ ሀሰት ሆኖ ሲገኝ ደፍሮ የወቀሳት እስካሁን በኢራቅ ውስጥ እየታየ ላለው ሁከትና ለሀገሪቱ ውድመት ምክንያት ነሽ ብሎ የጠየቃት የለም:: ብዙ ሽህ ኪሎሜትር ተጉዛ በቬትናም ሕዝብ ላይ ጦርነት ከፍታ ከአንድ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ስትገድል ማንንም ሳትፈራ ነው:: የአሁኑን እስላማዊ አክራሪ ኃይል መሰረት
የሆነውን ታሊባን የተባለውን የአሸባሪ ድርጅት በአፍጋኒስታን ስትመሰርት አይሆንም ብሎ ያስቆማት አልነበረም:: በሊቢያ: በሶሪያ: በየመን በሶማሊያ – – – ላይ ቦንብ እያዘነበች ሕዝብ ስትጨፈጭፍና ንብረት ስታወድም ትክክል ነበረች:: ሌላው ቀርቶ የኛዋ ኢትዮጵያ እንኳ በአቅሟ አልሸባብ ዝቶብኛል ብላ ጦር ሰብቃ ሶማሊያ የገባችው ጉልበት አለኝ ከሚል እብሪት በመነሳት ነው:: ለዚያም ነው Might is right! የሚባለው:: ጉልበት ካለህ ትፈራለህ: ትከበራለህ:: ድሀ ብትሆንም ምንም ማለት አይደለም:: ያለው ካለው ፈቅዶም ይሁን ፈርቶ ያካፍልሀል:: ራስህ የፈለከውን ያህል ተምነህ ብትወስድም ጠያቂ የለህም:: አቅም የሌለህ ደካማ ከሆንህ ግን እጣ ፈንታህ የሚወሰነው በአንተ አይሆንም::ራስን በወታደራዊ አቅም ብቁ አድርጎ መገኘት ሁልጊዜም አስፈላጊ ነው:: ለሕዝባቸው ከሚያስቡት ነፍስ ያላቸው የብአዴን አባላት ጋር በተጠና መንገድ ግንኙነት መፍጠር ይጠቅማል:: ያ ካልሆነ ግን እንደባለፈው ጊዜ ሁሉ ትንሹም ትልቁም እየተነሳ የሚያሳድደንና የሚገድለን መሆናችን አይቀርም::አማራ መሆን እንደወንጀል ተቆጥሮ በተለያዩ ክልሎች በግፍ የተገደሉት ወገኖቸ ከሞታቸው በላይ ነፍስ ከስጋቸው እስክትለይ ድረስ ያዩትን ስቃይ ማስታውስ አንጀትን እሳት ውስጥ እንደወደቀ ላስቲክ በሀዘን ጭምትርትር ያደርጋል:: እያዩ እየሰሙ በእሳት የተቃጠሉት ወገኖቸን ስቃይ ሳስብ የምሆነውን አጣለሁ:: ሳያውቅ በተዳፈነ እሳት ላይ ለአፍታ እግሩን ያሳረፈ ወይም የፈላ ውሀ ተደፍቶበት በዚያች ትንሿ የአፍታ ቃጠሎ የተንሰፈሰፈ ሰው ከነነፍሱ በእሳት እንዲቃጠል የተደረገ ሰብአዊ ፍጡር ነፍሱ እስክታልፍ ድረስ ሊሰማው የሚችለውን ስቃይ ሊያስብ ይከብደዋል:: እንደእኔ በድህነት በባዶ እግሩ እየሄደ ያደገ ሰው እንቅፋት ሲመታው የተሰማውን ጥዝጣዜ ሲያስታውስ ወገኖቻችን በገጀራ ተገዝግዘው ሲታረዱ ያሳለፉትን ስቃይ ለማሰላሰል አቅሙ አይኖረውም:: የራሳቸው ቤት እና ኑሮ የነበራቸው ቤት ያፈራውን ለተቸገረ ሲመጸውቱ የነበሩት ወገኖቸ የነበራቸውን ተነጥቀው ሲባረሩ የሚሰማቸውን ግራ መጋባትና ተስፋ ማጣት ማሰብ አንጀትን በሀዘን ያላውሳል:: ታያላችሁ አይደል አሁን እየሆነ ያለውን? እየተካሄደ ባለው የህዝብ አመጽ የትግራይ ሰዎች ተጎጅ ሊሆኑ ይችላሉ በሚል ጥርጣሬ እነርሱን ከአመጹ አካባቢ ለማሸሽ እስከ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ የደረሰ ጥንቃቄ ተደርጓል:: የእኛ ወገኖች በየጉራንጉሩ ሲታረዱና ሲሳደዱ ማን ደረሰላቸው? ከእንግዲህ በኋላ ይህ አይነት ሁኔታ እንዲፈጸም መፍቀድ የለብንም:: ራሳችንን መከላከል ከማንችልበት ደረጃ ላይ ከተገኘን በክልሉ የሚኖረውን ሕዝባችንን ሳይቀር አባረው ከኦሮሚያ እየተፈናቀሉ ያሉትን ትግሬወች ሊያሰፍሩበትም ይችላሉ::ህልውናችንን እና መብታችንን ለማረጋገጥ ነው የመከላከያ ኃይል የሚያስፈልገን:: አሁን የምንገኘው በሽግግር ዋዜማ ላይ ነው:: እንዲህ አይነት ጊዜ ደግሞ ፈታኝ ነው:: የቀዳማዊ ኃ/ ሥላሴ ንጉሳዊ የአስተዳደር ስርአት ሲፈርስ በተለያዩ አካባቢወች የሚኖሩ አማሮች ላይ ጥቃት እንደተፈጸመ ከታሪክ እናስታውሳለን:: ሌላው ቀርቶ በወላይታ ሶዶ ይኖሩ የነበሩት አማሮች ላይ ምን እንደደረሰባቸው የሚያውቅ ያውቀዋል:: ደርግ ሲወድቅ የተፈጠረውንስ የማያውቅ ይኖርይሆን?
ለእኛ ያለነው እኛው ነን!