(ዘ-ሐበሻ) በሚኒሶታ የቦንድ ሽያጭ ለማከናወን ኢሕ አዴግ የጠራው ስብሰባ ሳይጀመር ብጥብጥ መነሳቱን ዘ-ሐበሻ ከጥቂት ሰዓታት በፊት መዘገቧ ይታወሳል። በስፍራው የሚገኘው የዘ-ሐበሻ ዘጋቢ እንዳለው ፖሊስ ቦንድ የሚሸጥበትን አዳራሽ ዘግቶ ማንም ሰው እንዳይገባ አድርጓል።
አካባቢው በከፍተኛ የፖሊስ ጥበቃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ፖሊስ ማንም ሰው ስብሰባ እንዳያደርግ ከልክሎ አዳራሹን እየጠበቀ ይገኛል። ኢሕ አዴግ በሚኒሶታ ቦንድ እሸጣለሁ በሚል የላኦ ኮምዩኒቲ አዳራሽን ከ2 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት ፒኤም የተከራየው ቢሆንም ከአባይ በፊት በኢትዮጵያ የታሰሩ ሰዎች እንዲፈቱ፤ የሰብአዊ መብት እንዲከበር፣ መንግስት በ እምነቶች ላይ ጣልቃ እንዳይገባ የሚጠይቁ ወገኖች ባደረሱት ተቃውሞ ፖሊስ አዳራሹን ዘግቶታል።
ኢሕ አዴግን ለመቃወም የመጡ ኢትዮጵያውያን አሁን ድረስ በአካባቢው የሚገኙ ሲሆን በኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ገንዘብ የተመደበላቸውና ወጪ ወጥቶባቸው ወደሚኒሶታ የመጡ ተወካዮች ከአካባቢው ተሰውረዋል።
ዘገባውን አሁንም እየተከታተልን እንዘግባለን ይጠብቁን።