ጥቂት ነጥቦች ለቪዥን ኢትዮጵያ  መድረክ  ስለ ተዘጋጀው  የዶ/ር መረራ  ጽሁፍ  ይገረም አለሙ 

April 16, 2016

ቪዥን ኢትዮጵያና ኢሳት በጋራ ባዘጋጁት የውይይት መድረክ ላይ  ጽሁፍ እንዲያቀርቡ ከሀገር ቤት  የተጋበዙት ብቸኛ ሰው ዶ/ር መረራ ጉዲና በጉባኤው ላይ እንዲገኙ ባልፈለገው ወያኔ  ክልከላ በጉባኤው ለመታደም ባለመቻላቸው ያዘጋጁትን 17 ገጽ ጽሁፍ በድረ-ገጾች አማካኝነት ለአንባቢያን አድርሰዋል፡፡

 

ዶ/ር መረራ በዚህ ጽሁፋቸው ለተቀዋሚ ፓርቲዎች ጠንክሮ መውጣት አለመቻልም ሆነ ለህብረት ውጤታማ አለመሆን የችግሩ ዋንኛ ባለቤት ራሳቸው ስለመሆናቸው ደፈር ብለው ጠንከር አድርገውም ገልጸዋል፡፡ በአፍ የምንለው ሌላ፣ በተግባር የምንሠራው ሌላ በማለት የፖለቲከኞቹን ተግባር የገለጹት ዶ/ር መረራ  ሁሌ የራሳችንን የቤት ሥራ ሳንሠራ፤ የኢሕዴግንም ሆነ የፈረንጆቹን በሮች ማንኳኳቱ የትም የወሰደን ንዳልሆነ ጠያያቂ ጉደይ ይመሰልኝም፤ ፖለቲካ ለሚገባው ሰው ስካሁን ያለው የዓመታት ተሞክሮዎቻችንም ይኸው ነው  ብለዋል፡፡ መሆን አለበት ያሉትንም በገለጹበት ሀሳባቸው  ሁላችንም ከሕልሙ ዓለም ወጥተን በእውኑ ዓለም በውል ካልታገልን ለሕዝባችን የምንመኘው ውጤት የሚመጣ አይመስለኝም በማለት አውነቱን በድፍረት ገልጸዋል፡፡

 

የፖለቲከኞቻችን አንዱና ዋናው በሽታ መታመማቸውን ሀገር ምድሩ እያወቀ እነርሱ አልታመምንም ማለታቸውና በሽታቸውን መደበቃቸው ነውና ጽሁፉ ለመድረኩ በቅቶ ቢሆን ኖሮ  የሚያወያይም መፍትሄ ላማመንጨት የሚረዳም  ይሆን ነበር ብየ አሰባላሁ፡፡

ይሁን እንጂ ዶ/ር መረራ በዚሁ  ከሁለቱ መጽሀፎቻቸው የተወሰደ እንደሆነ በገለጹት 17 ገጽ ጽሁፍ  በዘመነ ኢህአዴግ የተመሰረቱ ህብረቶች ውጤታማ ያልሆኑበትን ምክንያት  የገለጹት በግርድፉ ነው ፤ማለትም ጠለቅ ብለው አላሳዩንም፡፡ ርሳቸው አንደሌሎቹ ፖለቲከኞች የፓርቲ መሪ ብቻ ሳይሆኑ የመስኩ ምሁርም ናቸውና ከአዲስ አበባ አሜሪካ ተጉዘው ሊያቀርቡት በነበረው ጽሁፋቸው ከዚህ በላቀ ሁኔታ  ችግሮችን ከነመፍትሄአቸው  ብሎም የሀገሪቱን መጻኢ እድል ፍንትው አድርገው ሊያሳዩን በቻሉ ነበር፡፡

 

ይህም ቢቀር በሳቸው ደረጃ ተዘጋጅቶ በእንደዛ ያለ ትልቅ መድረክ ላይ የሚቀርብ ጽሁፍ ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ ለማጣቀሻነት የመዋል  እድሉ ሰፊ ነውና  በጽሁፉ ውስጥ የተጠቀሱ ጉዳዮች በበቂ ሁኔታ ሊገለጹ ይገባል፡፡ በወቅቱ ያልነበረ የተደረገ የተነገረውን አይቶም ሆነ ሰምቶ አለያም አንብቦ ያላለፈ ሰው ይህን ጽሁፍ ሲያገኝ  እውነቱ  በጽሁፉ የተገለጸው ብቻ እንደሆነ አድርጎ ያምናል ለሌላም ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡ እኔም በዶ/ር መረራ ጽሁፍ መነሻነት ይህችን ለመጻፍ የተነሳሳሁት ከዚህ አንጻር ነው፡፡ የዘነጉትን ለማስታወስ፤ ሾላ በድፍን በገለጹት ላይ የማስታውሰውን ለማስታወስ፡፡

 

የዘነጉዋቸው ህብረቶች

 

ዶ/ር መረራ ከኢዲኃቅ ተነስተው ኣሁን እስከሚመሩት መድረክ ድረስ  ዘልቀው ስለ ፓርቲዎች ህብረት ሲዘረዝሩ በመዘንጋትም ይሁን ሆን ብለው መጥቀስ ባለመፈለግ የዘለሉዋቸው  ህብረቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ እኔ የማታውሳቸው፤

1—ደቡብ ህብረት

ይህ ህብረት በመንግሥት ለውጥ ማግስት በደቡብ የተመሰረቱና አብዛኛዎቹ የሽግግሩ ምክር ቤት አባል የነበሩ  ከ15 በላይ ፓርቲዎች የመሰረቱት በዶ/ር በየነ ጴጥሮስ ይመራ የነበረ ነው፡፡ደቡብ ህብረት በብዙዎቹ ህብረቶች ውስጥ አባል የነበረም ነው፡፡ አሁን ስሙ ተቀይሯል መሰል እንጂ መድረክ ውስጥም አባል ነበር፡፡ አንድ ህብረት መልሶ የሌላ ህብረት አባል መሆኑ  አንዱ ለፓርቲዎች ህብረት ጠንቅ መሆኑ ቢታወቅም ዶ/ር መረራ  እንደ ችግር አልገለጹትም፡፡

2—የጋራ  ፖለቲካ መድረክ፣

በደቡብ ህብረት፣ በኢትዮጵያ እንቅስቃሴ ቡድን(ኢዳግ) እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ( በጀነራል ጃገማ ኪሎ ይመራ የነበረው) የተመሰረተ ነበር፡፡

3-የምክክር መድረክ፤

በስድስት ፓርቲዎች በ1992 ዓም የተመሰረተውና  ከ1993 የአዲስ አበባ የወረዳና የቀበሌ ምርጫ መጠናቀቅ ጋር አብሮ የከሰመው ይህ መድረክ በኢተፖድህ ድጋፍ ሰጪነት በኦብኮ አስተባባሪነት የተመሰረተ አንደመሆኑ ለዶ/ር መረራ ሊረሳ አይችልም፡፡ ከዚህም በላይ ዶ/ር መረራ ፓርቲዎቹን ለማሰባሰብ የገጠማቸው ውጣ ውረድ፤ መስራች ስብሰባው በእየሩሳሌም ሆቴል ሲካሄድ  የተከሰተው ሁኔታ፤ ከምስረታው በኋላ በመድረኩ ካልተካተቱት ዶ/ር በየነ ጴጥሮስ ጋር ገጥመውት የነበረው አንካ ሰላንትያ (ጦቢያ መጽሄት ሀምሌ 1992 ማየት ይቻላል) የፖለቲከኞቹን የመተባበር ችግር ምንነት በግልጽ ያዩበት ስለነበር  ሊረሱት የሚችሉት አልነበረም፡፡

 

4–ቅንጅት፤

በኢትዮጵያ ተፈጥረው ስለ  ነበሩ ህብረቶች በጽሁፋቸው የዘረዘሩት ዶ/ር መረራ ከኢዴኃህ ወደ መድረክ ነው የተሸጋገሩት፤  በመሀል ተፈጥሮ የነበረው  ቅንጅት መቼም ለዶ/ር መረራ የሚረሳ አይደለም ያልገለጹበት ምክንያት ቢኖራቸው እንጂ፡፡ ስለሆነም ቅንጅትን አንዲህ በፓርቲዎች የህብረት ተርታ ሊጠቅሱ ያልቻሉት ያለ በቂ ምክንያት ሊሆን አይችልምና  ከማለፍ  ችግሮቹ ቢገለጹ ልምድ ሊቀሰምበት ትምህርትም ሊገኝበት በቻለ ነበር፡፡

 

ስለ ህብረቶች መፍረስ የተገለጹት ምክንያቶች

 

1-አማራጭ ኃይሎች፡

ሙሉ መጠሪያው የኢትዮጵያ የሰላምና የዴሞክራሲ አማራጭ ኃይሎች ምክር ቤት የሆነው ይህ ህብረት ከጅምሩ  ለመዳከም የበቃበትን ምክንያት  ዶ/ር መረራ የገለጹት  ከውስጥ እነ መላ አማራ ሕዝብ ድርጅት አፈገፈጉ፡፡ ከውጭ፣ ኢሕአፓና መኢሶን ገሸሽ ማለት ጀመሩ በማለት ነው፡፡

እንደማስታውሰው ይህን ምክር ቤት የመሰረተው የግዮኑ ጉባኤ የተጠራው የሰላምና የእርቅ ጉባኤ ተብሎ ነው፡፡ ዶ/ር መረራ 100 ሺ ሰው በአደባባይ ተገኝቶ ድጋፉን የሰጠው ያሉትም  ለአማራጭ ኃይሎች ሳይሆን ለጉባኤው ነው፡፡ በመስቀል አደባባይ ሲስተጋባ የነበረውም ክፈት በለው በሩን የሰላሙን የሚል ነበር፡፡  በጉባኤው አንዲገኝ የተጋበዘው ኢህአዴግ ግን ማን ከማን ተጣላና ነው የእርቅ ጉባኤ ከማለት አልፎ ለጉባኤ የመጡትን ከቦሌ እያነቀ አሰረ፡፡ ይህን የሰሙ ወደ ጉባኤው እያመሩ የነበሩ  ከመንገድ ተመለሱ፡፡  አቶ ሌንጮ ለታ በአውሮፕላን ገስግሰው አዲስ አበባ ደርሰው የኦነግ ሰዎችን አስፈትተው ይዘው ሲሄዱ አቶ አበራ የማነአብ ለአመታት አስር ተዳረጉ፡፡ ጉባኤው በተገኙት ሰዎች በግዮን ሆቴል ሲካሄድ  ኢህአዴግ ውሎውን በስውር እየቀረጸ በራዲዮ ፋና ያስተላልፍ ነበር፡፡ችግሩ ከዚህ ይጀምራል፡፡

ገባኤው በታሰበው መንገድ ተካሂዶ የታለመለትን ግብ ማሳካት ባለመቻሉ ቅድመ ዝግጅት ባልተደረገበትና ባልተጠና ሁኔታ በሀገር ውስጥም በውጪም የሚኖሩ ፓርቲዎችን  የሙያ ማህበራትንና ተዋቂ ግለሰቦችን  በማጠቃለል  አማራጭ ኃይሎችን መስርቶ ተነሳ፡፡ይህም ሁለተኛው ችግር ሆነ፡፡ ዶ/ር መረራ የገለጹት ማፈግፈግና  ገሸሽ ማለት ደግሞ ሶስተኛው ችግር፡፡ አማራጭ ከነችግሮቹ ሲንገታገት ቆይቶ መጨረሻ የስድስት ፓርቲዎች ህብረት ለመሆን ቢበቃም አንዱ አባል ደቡብ ህብረት አንድም አስራ አምስትም ልሁን ማለቱን ያልተቀበሉት አምስቱ ፓርቲዎች ዶ/ር በየነን ሽረው አቶ ክፍሌ ጥግነህን ሊቀመንበር አደረጉ፤ ምርጫ ቦርድ ደግሞ እኔ የማውቀው ዶ/ር በየነን ነው አለ፣ በዚሁ አማራጭ ሞተ፡፡

 

2–ኢዴኃህ፤

በአብዛኛው በውጪ ሀገር የሚኖሩ ፓርቲዎች አባል የሆኑበትና ከሀገር ቤት መኢአድ፣ኢዴፓ፣ ኦብኮና ዶ/ር በየነ ( በየትኛው ፓርቲ አንደሆነ ዘነጋሁት) በመያዝ በአሜሪካን ሀገር የተመሰረተው የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ኃይሎች ምክር ቤት እንዴት አንደተዳከመ ዶ/ር መረራ ሲገልጹ  ዲሱ ኅብረት ከመሬት ሳይነሳ የገመድ ጉተታው ተጀመረ፡፡ የገመድ ጉተታ ፖለቲካውን ኃይሉ የሚመራው የመላ ትዮጵያ ንድነት ድርጅት ጀመረው፡፡ ውሎ ድሮ የልደቱ ዴፓም ተከተለው፡፡ በሥልጣን ጉዳይ ላይ ሊነሳ የሚችለውን ቅሬታ ለማስቀረት በዙር መራር የመያዝ ቀመራችንም ልሠራ ለን፡ ይላሉ፡፡

ነገሩ በመኢአድ መጀመሩ እውነት ሆኖ ምክንያቱ  አልተገለጸምና  የተሟላ ስእል አይሰጥም፡፡ ጉባኤው ለሀገር ውስጥ አመራር  ዶ/ር በየነና ዶ/ር  መረራን ተፈራራቂ ሊቀመንበር  የኢዴፓውን ዶ/ር አድማሱን ዋና ጸኃፊ አድርጎ ሲመርጥ አንጋፋው መኢአድ  ቦታ ሳያገኝ ቀረ፤ አንዱ ምክንያት ይህ ሲሆን መኢአድ ያቀረበው ጥያቄ የጉባኤው ሰነዶች ይሰጡን የሚል እንደነበረ ይታወሳል፡፡  ወደ ኋላ ተመልሶ ለመኢአድ ሥልጣን መስጠት ባይቻልም ድብቅ ምክንያት ከሌለ በስተቀር የተጠየቁትን ሰነዶች መስጠት ግን የሚቸግር አልነበረም፡፡

 

ኢዴፓ ደግሞ የወጣው በሁለተኛው ጉባኤ ላይ ተገኝቶ ምክንያቶቹን አስረድቶ እንደሆነ በወቅቱ ሲገለጽ ነበር፡፡ለኢዴፓ ዘግይቶ መውጣትም ሆነ ለመኢአድ በአቋሙ ጸንቶ መቀጠል ተጨማሪ ምክንያት የሆነው አመራሩ በሀገር ቤት ይሆናል የሚለው የጉባኤው ውሳኔ ተግባራዊ አለመሆን እንደሆነ በግዜው ከተሰጡ መግለጫዎች ተከታትለናል፡፡ በዚህ ሁኔታ ቀጥሎ በሀገር ቤት ዶ/ር መረራና ዶ/ር በየነ የቀሩት ህብረት ከእነርሱም ጋር  በምርጫ  97 አትወዳደሩ በሚል ተጣላ፤ በኋላም ፓርላማ አትግቡ በሚል ተለያየ፡፡ ዶ/ር በየነ ግን ስሙን ይዘው ቀጥለው መድረክ ሲመሰረት ከስድስቱ ፓርቲዎች አንዱ ኢዴኃህ  ነበር፡፡

3- ትብብር ለዴሞክራሲ በኢትዮጵያ፤

ዶ/ር መረራ ስለዚህ ትብብር ሲገልጹ  ተፓድህ ሞቶ በውል ሳይቀበር፣ ከሀገር ውስጥና ውጭ ተቃዋሚዎችን ለማሰባሰብ ሰፊ ጥረቶች ተጀመሩ፡፡ በሀገር ውስጥ ኃይሉ ዴፓው ልደቱ ላይ ጠንካራ ጥርጣሬ ስለነበራቸው፣ ዴፓን ሳይጨመር ከሳምንታት በላይ ያልቆየ ኅብረት ተፈጠረ፡፡ የዚህ ድርጅት ውልደትም ሆነ ሞት ለብዙ ሰው ይቅርና ለብዙ አባሎቻችንም መታወቁን ጠራጠራለሁ፡፡ ምርጫ ቦርድ የሚባለውም ፋይሉ መድረሱንም  አላሰታውሰም፡፡ ስሙ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ትዮጵያ (Joint Action for Democracy in Ethiopia) ይባል ንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ ብለዋል፡፡

ይህ ጉዳይ በወቅቱ ትብብሩን በመሰረቱት ሶስት ፓርቲዎችና በኢዴፓ መካከል ትልቅ እሰጥ አገባ አስከትሎ ስለነበር የሚረሳ አይደለምና እውነታው አንዲህ እንደተገለጸው አይደለም፡፡የማስታውሰውን በአጭሩ ለመግለጽ ልሞክር፡፡

በ1992 ምርጫ ማግስት በኢተፖድህ ድጋፍ ሰጪነት በኦብኮ አስተባባሪነት በስድስት ፓርቲዎች የትብብር መድረክ የሚባል ተመሰረተ፡፡ አባላቱም መኢአድ፤ኢዴፓ፤ ኦብኮ፤ብዴህ፤ኢዴህ(ኢዲዩ) እና የየም ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ነበሩ፡፡ዶ/ር በየነ ባለመካተታቸው የውግዘት መግለጫ አወጡ፡፡መድረኩ የ1993 የአዲስ አበባን የወረዳና የቀበሌ ምርጫ በጋራ ለመወዳደር አልሞ ቢንቀሳቀስም ሌሎቹ ዕጩ ማቅረብ ባለመቻላቸው የተወዳደሩት መኢአድና (ያኔ መዐህድ ነበር) ኢዴፓ ናቸው፡፡ ሁለቱ ፓርቲዎች በመድረኩ አማካኝነት በፈጠሩት መቀራረብ ተደራድረው የምርጫ ጣቢያዎችን ተከፋፍለው ዕጩ ከማቅረብ አልፈው በአንድ የምርጫ ምልክት ለመወዳደር በቅተው ነበር፡፡ መድረኩን ወደ ህብረት ለማሳደግ ጅምር እንቅስቃሴዎች ቢኖሩም ምርጫው ሲያበቃ እሱም አከተመ፡፡

ከዚህ በኋላ መድረኩ ቢፈርስም አንበታተንም በማለት ይመስላል  በመኢአድ ቢሮ ግንኙነቱ ሲቀጥል ዶ/ር በየነም ተቀላቀሉ፡፡ የአራት ፓርቲዎች ግንኙነት ቀስ በቀስ አድጎ ትብብር ለመፍጠር የሚያስችል ሰነድ እስከ ማዘጋጀት ተደረሰ፡፡ በዚህ መካከል በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የአራቱን ፓርቲዎች ስም የያዘ የጋራ መግለጫ ሲዘጋጅ ኢዴፓ ዶ/ር በየነ በዚህ ትብብር ውስጥ ያሉት  በአማራጭ  ኃይሎች  ነው ወይንስ በደቡብ ህብረት የሚል ጥያቄ አነሳ፡፡ (አምስቱ የአማራጭ አባል ፓርቲዎች ዶ/ር በየነን መሻራቸውን ያስታውሷል) ለጥያቄው የተሰጠውን ምላሽ ባላስታውስም  ጥያቄ ያስነሳው መግለጫ ኢዴፓ ቀርቶ በሶስቱ ፓርቲዎች ስም ወጣ፤ (መዐህድ ኦብኮና አማራጭ)፡ ብዙም ሳይቆይ ትብብር መመስረታቸው ይፋ ሆነ፡፡ከኢዴፓም ጋር ሶስት ለአንድ የቃላት ጦርነቱ ቀጠለ፡፡በዚህ መልኩ የቀጠለው ትብብር እስከ ኢዴኃህ ጉባኤ አደረሳቸውና ዶ/ር መረራና ዶ/ር በየነ የህብረቱ ተፈራራቂ ሊቀመንበር ሆነው ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ በጉባኤው ያልተገኙት ኢ/ር ኃይሉ ምንም ቦታ አጡ፤ትብብሩም እዚህ ጋ ሞተ፡፡

 

ፖለቲካችን ከበሽታው እንዲገላገል ከልብ የምንፈልግ ከሆነ በዝርዝርና በጥልቀት መነጋገር ያሻል፡፡ከዚህ በተጨማሪ በጽሁፍ የተቀመጠ ነገር ውርስ ነውና በተለይ ደግሞ አንደ ዶ/ር መረራ ያሉ ፖለቲካውን በቃልም በተግባርም የሚያካሂዱ ሰዎች የሚጽፉዋቸው ጽሁፎች ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፉ የመሆን እድላቸው ሰፊ ስለሆነ የተሟላ ስእል የሚሰጡ ቢሆኑ መልካም ነው፡ትንሽ ትንሽ እየተሸራረፈ ትንሽ ትንሽ እየተቀየረ ሲጻፍ ኋላ ላይ ሙሉ በሙሉ እውነተኛ መልኩ ይለወጣል፡፡ማን ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ የሚባል የማይገኝበት  ግዜ ሲደረስ ያልነበረው የነበረ ይሆናል፡፡ ለዚህም ነው የጎደለ ለመሙላት ትንሽ ብትረዳ በማለት ይህችን ጽሁፍ ማቅረቤ፡ይህ የፖለቲካ ታሪካችን አንድ አካል ነውና እኔ የሳትኩት ወይንም ያዛነፍኩት ካለ ደግሞ መረጃው በበቂ ያላችሁ አርሙት አቃኑት፡፡ የተሟላ ታሪክ ለማቆየት፡፡

 

 

 

 

 

 

Previous Story

ወያኔና ትግሬ | መስፍን ወልደ ማርያም

Next Story

Hiber Radio: ለጋምቤላው እልቂት ሳሞራ የኑስ እና ጄ/ል አብርሃ ማንጁስ ተጠያቂዎች መሆናቸው ተገለጸ – (ልዩ ዘገባ በጋምቤላና በወቅታዊው የሃገራችን ጉዳይ)

Latest from Blog

አዲስአበባ ተኩስ ተከፈተ “ለመደራደር ዝግጁ ነን” አረጋ ከበደ | አብይ አደገኛውን ካርድ መዘዙ | አዲሱ አዋጅና የቀረበበት ተቃውሞ “የሞተም ሰው ንብረት ይጣራል | ጌታቸው ያጋለጠው ጸብ

አዲስአበባ ተኩስ ተከፈተ “ለመደራደር ዝግጁ ነን” አረጋ ከበደ\  አዲሱ አዋጅና የቀረበበት ተቃውሞ “የሞተም ሰው ንብረት ይጣራል አብይ አደገኛውን ካርድ መዘዙ ጌታቸው ያጋለጠው ጸብ

ከመጠምጠም መማርን እናስቀድም!

;በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com) አብዛኛው አንባቢ ተገንዝቧል ብዬ እንደምገምተው ሕዝብ ለቡና ቲራቲም፣ ለግብዣ፣ ለበዓል፣ ለሰረግ፣ ለሐዘን፣ ለእድር፣ ለእቁብ ለውይይትና ለሌሎችም ማህበረሰባዊ ጉዳዮች ሲገናኝ የሚበዛው አድማጭ ሳይሆን ተናጋሪ  ወይም ደግሞ ለመናገር  መቀመጫውን ከወንበር ወይም
Go toTop