March 2, 2016
6 mins read

ህወሓት “ከቡና ጠጡ” ወደ “መርዝ ጠጡ” ከታደሰ ብሩ

Tadesse Kersmo 2902

የአዲስ አበባ ታክሲ ሾፌሮችና ባለንብረቶች ለሁለት ቀናት ያካሄዱት የሥራ ማቆም አድማ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ትምህርት ሊገኝበት የሚገባ ነው። ስታሊናዊ አፈና በሰፈነባት አዲስ አበባ ውስጥ እንዲህ ዓይነቱ አድማ መሞከሩ ብቻውን የሚያስደንቅ ሳለ ተግባራዊ ሆኖ ከተማዋን ለሁለት ቀናት ማስተኛቱ የታክሲዎችን ጉልበት፤ የሕዝባዊ እምቢተኝነት ውጤታማነት እና የተባበረ እርምጃ ስኬታማነት በተግባር አሳይቷል።
አገዛዙ የአወዛጋቢውን አዋጅ ተፈፃሚነት ለሶስት ወራት ማራዘሙን ተናግሯል። ይህ ማራዘምም ከቅርብ ጊዜዓት ወዲህ ካስተዋልናቸው የማፈግፈግ እርምጃዎች አንዱ ሆኗል። የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን እና የሆሳዕና የትራንስፓርት ህግ ተፈፃሚነት መዘግየት ሌሎቹ ማፈግፈጎች ናቸው።
እዚህ ላይ ሁለት ነጥቦችን ማንሳት ተገቢ ነው።
አንደኛ – ጠላት ማፈግፈግ ሲጀምር ማጥቃት መቀጠል አለበት። የአምባገነን ሥርዓቶች ውድቀት ለማፋጠን ትናንሽ ድሎችን እየሰበሰብን ለበለጡ ድሎች የሚደረገውን ትግል ማጠናከር የዘወርት ሥራችን አካል መሆን ይኖርበታል። ስለሆነም አገዛዙ የተጠየቀውን በአርኪ ሁኔታ መልሶት ቢሆን ኖሮም ሌሎች ጥያቄዎች መነሳታቸው አይቀርም ነበር።
ሁለተኛ – ለአዲስ አበባ ታክሲ ሾፌሮችና ባለንብረቶች ጥያቄ አገዛዙ የሰጠው ምላሽ የማፈግፈግ ምልክት ቢሆንም አርኪ ምላሽ ሊሆን ቀርቶ ግማሽ ምላሽ እንኳን አይደለም። ፓርላማ ያወጣውን አዋጅ አስፈፃሚው በየትኛው ሥልጣኑ ሊያዘገየው እንደቻለ አጠያያቂ ነው። ይህ ህገ አልባነታቸው ለምንም ነገር እንዳይታመኑ ያደርጋቸዋል። አዋጁን በአፋቸው ተራዝሟል እያሉ በተግባር ግን ተፈፃሚ እያደረጉት ስለአለመሆኑ ምንም ዓይነት ማረጋገጫ አለን? ምንም። ስለዚህም የታክሲ ሾፌሮችና ባለንብረቶች ጥያቄዎች እንኳንስ ሙሉ ግማሽም ምላሽ አላገኙም ብለን መደምደም እንችላለን። ይህ ደግሞ በተራው የሥራ ማቆም አድማው ወደፊትም ሊደገም ይችላል የሚለውን መላምት ያጠናክርልናል።
የአዲስ አበባ ታክሲ ሾፌሮችና ባለንብረቶች የሥራ ማቆም አድማ መልሶ መጀመር ስለሚቻልበት ሁኔታ መምከር እና አድማው ወደ ሌሎች የሥራ መስኮችና አካባቢዎችም እንዲዛመት መሥራት የሁላችንም ኃላፊነት ነው።
በዚህ ወቅት ህወሓትስ ምን እያሰበ ነው ብሎ መጠየቅም ብልህነት ነው።
እኔ ባለኝ መረጃ መሠረት የህወሓት ጆሮ ጠቢዎች የአድማው አደራጆችን የመለየት ሥራ ውስጥ ተጠምደው ሰንብተዋል። በተወሰነ መጠን መረጃ ያላቸው ቢሆንም የለመዱትን የጉልበት እርምጃ ለመውሰድ ድፍረት ያጡበት አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል። የኦሮሚያ እና የሙስሊም ወገኖቻችን ንቅናቄ እኚህን እኩያን ጆሮ ጠቢዎች አደብ እንዲገዙ አስገድዷቸዋል። በምትኩም “ለስላሳ መንገድ” ያሉትን መፍትሄ መርጠዋል።
ለስላሳው መንገድ “ቡና እንጠጣ” ብለውታል። እንደ እቅዳቸው በየሰፈሩ ብዙ የቡና እንጠጣ ኢመደበኛ ማኅበራትን ያቋቁማሉ። እያንዳንዱ ካድሬም ጥቂት የሰፈሩን ሰው ቡና እየጋበዘ “ስለ ሰላምና ልማት” እንዲሰብክ ይደረጋል። ልዩ ትኩረት ለባለታክሲዎች፣ ሾፌሮች፣ ተማሪዎችና መምህራን እንዲሰጥ ተወስኗል። “ቡና” የተባለውም እንደ ሁኔታው ወደ ቢራና አልኮል እንዲያድግም በጀት እንዲመደብ ጠይቀዋል።
“ቡና እንጠጣ” ከቀድሞው 1 ለ 5 በመጠኑ ይለያል። 1 ለ 5 ጥርነፋ ሲሆን “ቡና እንጠጣ” ፍርሀት የወለደው ማባበያ ነው። የአሁኑ “ቡና እንጠጣ” በምርጫ 97 ዋዜዋ የነበረው የአርከበ እቁባይ ተለማማጭነትን ያስታውሰኛል። አርከበ በምርጫው በፊት የነበረው “ደግነት” ሁሉ ከምርጫው በኋላ ወደ አውሬነት መቀየሩ አይዘነጋም።
ህወሓቶች የዛሬው “ቡና ማጠጣት” ከተሳካላቸው ነገ ወደ “መርዝ ማጠጣት” እንደሚቀይሩት በበኩሌ እርግጠኛ ነኝ። ስለሆነም “ለቡና እንጠጣ” የምንሰጠው ምላሽ “እንቢ” መሆን ይኖርበታል ብዬ አምናለሁ።

1 Comment

  1. ወሬ ነው የሰለቸኝ።ልብ ካለህ እንደ ጀግናው በቀለ ገርባ መጣሁላችሁ አትልም? ስታርባክ ተደብቀህ ከምታወራ ።ሕዝቡ አስታዋሽ አይፈልግም።በነገራችን ላይ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አምሮበታል ምንድን ነው ሚስጥሩ? እዉነት ይሄ የተባለው ኤርትራ ዉስጥ ሆኖ መዋ ጋት ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ሆኖ እንደመዋጋት ይቆጠራል የተባለው በዚህ እዉነት ሳይሆን አይቀርም።ግን እኮ አንዳርጋቸው ግን አላማረበትም ነበር ምናልባትም ባለ 2ኮከብ ሆቴል አስቀምጠዉት ይሆናል።ግን ከምር ብርሃኑ እንደ ተባለዉ ሊቭ ኦፍ አብስንስ ወስዶ ከሆነ ኤርትራ ሆቴል የገባው ጦር መሪ ሣይሆን ለዪኒቨርስቲዉ ጥናታዊ ፅሁፍ እየሰራ ነዉ እምለዉ።እርግጠኛ ነኝ አንድ ቀን ቤተመንግስት ከኢሣያስ ጋር ችርስ ትባባላላችሁ።የዛን ጌዜ አደራ

Comments are closed.

welkaiyt
Previous Story

መልስ ለኃይሉ የሺወንድም፤ በወልቃይት ፀገዴ ባህልና ማንነት ጥያቄ እኔም ቅሬታ አለኝ!

Next Story

የአድዋ ድል፦ የዘመኑ ኢትዮጵያዊ ትውልድ የማንነት ፈተና – ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop