መልስ ለኃይሉ የሺወንድም፤ በወልቃይት ፀገዴ ባህልና ማንነት ጥያቄ እኔም ቅሬታ አለኝ!

ከዚህ በታች ያለው ፅሑፍ የአቶ ኃይሉ የሺወንድም የመጀመሪያ 8 ገፅ ፅሑፍ እንደወጣ የተዘጋጀ ነበር። ሆኖም በጊዜ ዕጥረት ምክንያት ትየባውንና የፊደል ለቀማውን ሳልጨርሰው ሁለተኛውን “መልስ ለጀለሶቼ” በሚል 15 ገፅ ፅሁፍ ተከተለ። ታዲያ ፅሁፌን የማቀርበው መጀመሪያ በተዘጋጀው መሠረት ምንም ሳይቀየር አቶ ኃይሉ ካቀረበው 15 ገፅ ፅሑፍ አንድ አራት ነጥቦች ብየ መጀመሪያ ወደተዘጋጀው ፅሑፌ እወስዳችኋለሁ።
በመሠረቱ እውነቱን ምን እንደሆነ እየታወቀ ተከራክሮ አሸናፊ ሆኖ ለመገኘት ብቻ እውነትን እየካዱ እርስ በርስ መወነጃጀሉ ለማንም አይበጅም፤ ምክንያቱም እውነትና ንጋት እያደረ ይጠራልና። እኔ እስከማውቀው እነ አቶ ጎሹ ገብሩ፤ አቶ ቻላቸው አባይ፤ አቶ አባይ መንግሥቱና መሰሎቻቸው ሠፊው የወልቃይት ፀገዴ ህዝብና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያውቃቸው የህዝብ ልጆች መሆናቸውን ነው። ይህን ስል ደግሞ ዝም ብዬ ሳይሆን በሥራቸው ነው። ለምሳሌ “ልሳነ ግፉአን”በሚል የሲቪክ ድርጅት መሥርተው ከዛሬ 4ና 5 ዓመት በፊት በኢሳት ቴሌቪዥንና የአርበኞች ግንቦት 7 ሬዲዮ ቀርበው የወልቃይት ፀገዴ ህዝብ ችግር ሲያጋልጡ ለዓለም ህብረተሰብ ሲያሳውቁ የምናውቃቸው ጀግኖቻችን ናቸው።
አንተ ግን በሥም ማጥፋት ወንጀል ትከሳቸዋለህ። ነገሩ ከአነጋገር ይፈረዳል፤ ከአያያዝ ይቀደዳል ነው። እነሱ አንተ ያልሆንከውንና ያላደርገክውን አልፃፉም። የፈረደ የሺወንድም ወንድም፤ የአዜብ መስፍን ያክስት ልጅ መሆንህንና ወያኔ ያወጣውን የመሬት ቅርምት ፖሊሲ ለመተግበር ከአውሮፓ ወደ ኢትዮጵያ ኢንቨስት ልታደርግ እንደገባህ አንተም አልካድክም። ታዲያ ከዚህ የበለጠ ወያኔን መደገፍ ምን ሊመጣ ነው? እኛ ወያኔዎችን -የወልቃይት ፀገዴ ህዝብ እያሰሩ እየገደሉ መሬታችን ወሰዱ – ብለን ከተቃወምን አንተ የጋምቤላ ወገኖቻችንን አፈናቅለህ መሬት ከተቀበልክ ከወያኔ በምን ተለየህ? የራስህ እንዳይበቃ ደግሞ የወልቃይት ፀገዴ ወጣቶችን የጋምቤላን መሬት እንዲቀራመቱ ታበረታታለህ። አንተ ራስህ ባመንከው መሠረት ማለት ነው።
ሌላው ነገር ከድርጅት ድርጅት ይቀያይራሉ ብለህ እንደምሳሌ ያቀረብከው ከኢሕአፓ ወደ ግንቦት 7 እና ወደ የወቃይት ፀገዴ የአማራ ማንነት ነው። እነዚህ ሁሉም እኮ ህብረብሔር ድርጅቶች ናቸው። ከቤትህ ወደቤትህ እንደመሔድ ነው የሚቆጠረው። ለውጥ የሚባለው ከህብረብሔር ወደጠባብ የዘር ድርጅት ለሚሔድ ነው። በኢሕአፓ ያልታቀፈ ግለሰብ እንዳልነበር ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚያውቀው ነገር ነው። ምን አዲስ ነገር አለው?
በመቀጠልም “ዕውቀት የላቸው፤ ሃብት የላቸው፤ ባዶ ባዶ ናቸው” ብለሃል። መቼም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሰር ወይም ሳይንቲስት ይሁን ካልተባለ በቀር ያላቸው ዕውቀት በቂ ነው። አንተ ሰውን የምትለካው በምንድን ነው? በሀብት ነው እንዴ? በሀብት ከሆነማ፤ ዛሬ ሀብታሞቹ እነ ሳሞራ ዩኑስ፤ ስብሀት ነጋ፤ አባይ ፀሀየ፤ ሼክ አላሙዲን የመሳሰሉ ናቸው። የኢትዮጵያ ህዝብማ ሁሉም ደሃ ነው። እኔ እስከማውቀው እነ አቶ ጎሹ ገብሩ፤ አቶ አባይ መንግሥቱ፤ አቶ ቻላቸው አባይና መሰሎቻቸው በጣም ስኬታማ ሰዎች ናቸው፤ ሁሉም ጥሩ ጥሩ ቤተሰብ መስርተው ልጆቻቸውን በሥነሥርዓት ያሳደጉ፤ የኳሉ፤ የዳሩና ለወግ ለማዕረግ ያበቁ አባወራዎች ናቸው። ለኔ ከዚህ በላይ ሥኬት የለም።
ሌላው በአፄ ፋሲል ዘመን ጎንደር ውስጥ ከትግሬ ይልቅ በብዛት ኦሮሞች ይኖሩ እንደነበር እየገለፅክ፤ በአፄ ምንሊክ ዘመን ደግሞ ኦሮሞዎች እንደባሪያ ሲሸጡ ሲለወጡ እንደነበሩ ትገልፃለህ። የወያኔ ውሸት እንዳይበቃን! ታዲያ በ17ኛው ክፍለዘመን ኦሮሞች ጎንደር ከነበሩ ወረራውን ቀድሞ የጀመረ ማን ነው? ኦሮሞች ወደጎንደር ሲመጡ ዕቅፍ አበባ ይዘው ነበር እንዴ የመጡት? ፈረስ፤ ጋሻና ጦር መስሎኝ! ምነው? ሁሉም ወገኖችህ ናቸው። ለምን ታደላለህ? ፅሁፍህ የመረረ የአማራ ጥላቻ እንዳለህ ያመለክታል። ወያኔዎች እስኪበቃን የነገሩን በቂ ነበርኮ! የመረረ የአማራ ጥላቻ እንዳለህ የሚያመላክት ሦስት ምሳሌዎች ልጥቀስ!
አማራው ገዢ ስለነበር የበታችነት አይሰማውም ብለሃል። እውነቱ ግን የተውጣጡ ገዢ መደቦች ኢትዮጵያን ይገዙ ነበር እንጂ የአማራው ማህበረሰብ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ጭቁን ነበር። ለዚህ ነው የአማራ ወጣቶች ለውጥን ፍለጋ መሥዋዕትነት ሲከፍሉ የነበሩት፤ ያሉትም።
2. በወልቃይት ፀገዴ ውስጥ በወያኔ የደረሰውን በደል ተከድኖ ይብሰል እያልክ፤ ተራ ለሆነው “የአማራ ገዢዎች” አደረሱት የምትለውን በደል በዝርዝር አንድ ሳታስቀር ፅፈሃል።
3. ወያኔዎች “አፄ ምንሊክ ጡት ቆረጡ” እያሉ ነበር የሚከሷቸው። አንተ ደግሞ ጨምረህ “ኦሮሞዎችን ሸጡ፤ ለወጡ” እያልክ በ17ኛው ክፍለ ዘመን ኦርሞዎች ጎንደርን ሲወርሩ ስላደረሱት በደል ግን ያልከው ነገር የለም። እንግዲህ ይህን ካልኩኝ ቀደም ብሎ ወደተዘጋጀው ፅሁፌ ልመልሳችሁ።
በቅርቡ “የወልቃይት ፀገዴ ባህልና የማንነት ጥያቄ” በሚል ርእስ ኢትዮሚዲያ ላይ የወጣውን ፅሑፍ አይቼዋለሁ። የምስማማባቸውና የማልስማማባቸው ነገሮች ቢኖሩም አንተ የወገኔ ጉዳይ ያገባኛል፤ ይመለከተኛል ብለህ መስሎ በታየህ ሃሳብ ላይ ውድ ጊዜህን ሠውተህ የድርሻህን ማበርከት በመቻልህ ከልብ አመሰግናለሁ። ቢሆንም ግን የምስማማባቸው ነገሮች እንዳሉ ሆነው በማልስማማባቸው ጉዳዮች ብቻ አስተየየቴን እሰጣለሁ። ይህ ማለት ግን ያንተ ተቃዋሚ ሆኜ ሳይሆን እንደወንድም ሃሳቤን ላጋራህ ስለፈለኩና በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ከአንተ ዕይታ ውጭ ስለሆኑ ነገሮች ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያህል ነው። እኔ በበኩሌ እንኳን አንተን ቀርቶ ህሊናቸውን በጥቅም ደልለው ጠላት ለሆነው ወያኔ እያገለገሉ ላሉ ወገኖችም ቢሆን ወደህሊናቸው ተመልሰው የበደሉትንና ያደሙትን ወገናቸውን ይቅርታ እንዲጠይቁና እንዲክሱ ከማበረታታት በስተቀር በፍፁም በጠላት ዓይን ተመልክቻቸው አላውቅም። ምክንያቱም በመሃላችን ክፍተት ፈጥረን እሳት በተወራወርን ቁጥር የኛን መኖር የማይፈልጉ እየተወራወርን ባለው እሳት ላይ ቤንዚን ለማርከፍከፍ ተዘጋጅተው የሚጠባበቁ የጋራ ጠላቶች እንዳሉ ስለምገነዘብ ነው። እንግዲህ ለመግቢያ ያህል ይህን ካልኩኝ ወደዋናው ቁምነገር ልመለስ፦
1ኛ. የመጀመሪያው ቅሬታዬ እኛ የወቃይት ፀገዴ ተወላጆች የአካባቢያችንም ሆነ የአገራችንን ጉዳይ በተመለከተ ስንወያይ ሆነ ስንፅፍ ወልቃይት ፀገዴ ብለን እንጂ ወልቃይትና ፀገዴን ለያይተን አንስተን አናውቅም። አንተ ግን 8 ገፅ ሙሉ ፅሑፍ ስታዘጋጅ በስህተት አንድ ጊዜ እንኳ ወልቃይት ፀገዴ ብለህ አልፃፍክም። ወልቃይቴ ሆኖ ከፀገዴ የማይወለድ፤ ፀገዴ ሆኖ ከወልቃይት የማይወለድ ፈፅሞ አይገኝም። አንተ ግን ወልቃይትና ትግራይ የሌለ ትውልድ ፈልገህ እያዛመድክ አንድ የሆነውን የወልቃይት ፀገዴ ህዝብ ግን ለየይተህ ትፅፋለህ። ጭራሽ አርበኛ ክቡር ቢትወደድ አዳነ መኮንንን ወልቃይት ዘምተው በወልቃይት ህዝብ ላይ ወረራ እንደፈፀሙ በመግለፅ አንድ በሆነው ይወልቃይት ፀገዴ ህዝብ መካከል ጥላቻ ትዘራለህ። ይህ ነገር ለማን እንዲመቸው አስበህ ነው? አስተዋዩ የወልቃይት ፀገዴ ህዝብ በወዳጅ ዓይን የሚያይህ ይመስልሃል? ይልቅ አስፍቶና አርቆ በማሰብ እንደእኛ በዘረኛው የትግራይ ወያኔ ስለሚሰቃዩት ስለጠለምት ህዝብ ጭምር መፃፍ ነበረብህ። ካልሆነ ግን ወልቃይት ፀገዴን ባትከፋፍል መልካም ነበር።

2ኛ. የወቃይት ፀገዴ አማራነት ጥያቄ ውስጥ አስገብተኸዋል። የወልቃይት ፀገዴ አማራነት ለመገንዘብ እኮ ብዙ አያዳግትም። ለምሳሌ አንተ በግልህ አማራ ነኝ ብለህ ባታምን እንኳ ጎንደሬ ለመሆንህ ግን እርግጠኛ ነኝ መቶ በመቶ ታምናለህ። ስለዚህ የጎንደር የሆነ ግዑዝ አካል ወይም ሰብአዊ ፍጡር ሊቀርብ የሚችለው ለአማራነት እንጂ ለትግሬነት ወይም ለአፋርነት ሊሆን እንደማይችል ግልፅ ነው – ኢትዮጵያ ዘርን መሰረት ባደረገ አከላለል እስከተካለለች ድረስ። መቼም በአንድ ነገር እንደምንስማማ እርግጠኛ ነኝ። የወልቃይት ፀገዴ ህዝብ አመጣጥ ሊሆን የሚችለው ከአማራው ወይም ከትግሬው አልያም ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ብሔረሰቦች ከአንዱ እንጂ ከሰማይ ዱብ እንደማይል ግልፅ ነው። እኛ የወልቃይት ፀገዴ ተወላጆች ከአሁን በፊት በአገራችን ኢትዮጵያ ዘርን መሰረት ያደረገ ክልላዊ መስተዳድር ስላልነበረ ዘራችን ከየት ነው የሚለውጉዳይ አሳስቦን አያውቅም ነበር። አሁን ግን ሳንፈልገው ኢትዮጵያን በዘርና ቋንቋ ከፋፍለው የወልቃይት ፀገዴ ህዝብ በጉልበት የትግራይ አካል ነው ብለው ህልውናችን የሚፈታተኑ ኃይሎች ስለመጡ “እኛ ማን ነን? አመጣጣችንስ ከየት ነው?” ብለን እንድንመረምር ተገደናል። ሆኖም ከዚህ አንፃር ማንነታችንን ለማወቅ ብዙ ሩቅ መሔድ አያስፈልገንም።
የወልቃይት ፀገዴ ሕዝብ በኢትዮጵያ የ3 ሺህ ዘመን ታሪክ አንድ ቀን እንኳ ከትግራይ ጋር ተዳድሮ አያውቅም። በመቀጠልም ለረጅም ጊዜ ወልቃይት ፀገዴ ቤጌምድር እየተባለ ሲጠራ ቆይቶ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ በደርግ ዘመን ጎንደር ተባለና ከተማውም ክ/ሀገሩም ጎንደር ተባለ። አሁን ደግሞ የዘር ልክፍት የያዘው መንግሥት መጣና ጎንደር የነበረው አማራ ክልል ሲባል እንደጂኦግራፊአዊ አቀማመጣችን አማራ የማንባልበት ምክንያት የለም? እኛ ብቻ ሳንሆን ወሎዬ ወሎዬነቱ እየከሰመ አማራ፤ ጎጃሜ ጎጃሜነቱ እየከሰመ አማራ፤ ሸዋ ሸዋነቱ እየከሰመ አማራ ሲባል እኛ ደግሞ እንድወንድሞቻችን ጎንደሬነታችን እየከሰመ አማራ ልንባል ይገባል ነው። በሰበብ አስባቡ የወልቃይት ፀገዴ ሕዝብ ስሙ ይቀያየር እንጂ ለ3 ሺህ ዘመን የነበረበት ማንነቱ ማንም ሊቀይረው አይችልም። እንደዛሬ ተከዜን የምንሻገርበት ድልድይ ሳይሠራ የወልቃይት ፀገዴ ህዝብና የትግራይ ህዝብ በዓመት 6 ወር ብቻ ሲገናኝ – ተከዜ ከግንቦት ወር እስከ ጥቅምት ስለሚሞላ ማለት ነው – የወልቃይት ፀገዴና የአማራው ማህበረሰብ ግን ዓመቱን ሙሉ ከመገናኘት የሚያግደው ነገር የለም። ስለዚህ የኢትዮጵያ የ3 ሺህ ዘመን ታሪክ ሲሰላ የወልቃይት ፀገዴና የትግራይ ህዝብ ለ1500 ዓመታት ብቻ ሲገናኝ የወልቃይት ፀገዴና የአማራው ማህበረሰብ ግን ለ3 ሺህ ዘመናት አብረው ኑረዋል፤ ተዋልደዋል፤ ተዛምደዋል። ይህን ስል ግን ከትግራይና ከኤርትራ ጋር አልተዋለዱም ለማለት አይደለም። ግን ከመቶ አሥራ አምስት እጅ (15%) አይበልጥም። ከአማራው ማህበረሰብ ግን ቢያንስ ከመቶ ሰማንያ አምስት እጅ (85%) ያህል ተዋልደናል። ለዚህ ማስረጃ ካስፈለገ ደግሞ አብዛኛው የወልቃይት ፀገዴ የዘር ሐረግ ሲቆጠር የአማርኛ ስሞች እንጂ የትግርኛ ስሞች እጅግ ጥቂቶች ናቸው። ለምሳሌ ያንተ የራስህን እንኳ ብንወስድ ኃይሉ የሺወንድም – የሺወንድም ናደው – ናደው ብሬ – ብሬ ማሩ -እያለ ይቀጥላል። በእናትህ ወገን ስናይ ኃይሉ እንጉዳይ – እንጉዳይ ጎላ – ጎላ ጎሹ እያለ ይቀጥላል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ግራጫ አተያይ - ዶ/ር መኮንን ብሩ

ለምሳሌ አንድ ሰው ስሙ መሃመድ፤ የአባቱ ስም አብደላ፤ የአያቱ ስም ኦስማን እያለ ከቀጠለ እስላምነቱ አያጠራጥርም፤ ወይም ስሙ ወ/ሚካኤል፤ ያባቱ ስም ፍቅረየሱስ፤ ያያቱ ስም ሣህለስላሤ ከሆነ ክርስቲያንነቱ አያጠራጥርም። ለምሳሌ ወደደቡብ ኢትዮጵያ ስንሄድ ስሙ በቀለ፤ ያባቱ ስም ተስፋየ ያያቱ ጌታቸው ይልና ቅድመአያቱ ፈይሳ ወይም አብዲሳ ይሆናል እና የዘር ሐረጉ ለማወቅ ከባድ አይሆንም። የአፄ ኃ/ሥላሴ እንኳ ብንወስድ ተፈሪ መኮንን – መኮንን ወ/ሚካኤል ብሎ ወ/ሚካኤል ጉዲሳ ይሆናል። ስለዚህ በከፊል የአፄ ኃ/ሥላሴን የዘር ሓረግ ለማወቅ አይከብድም። ስለዚህ ከሰማይ ዱብ እንደማንል ከተማመንን ቤጌምድር ተባልን ጎንደሬ፤ አማርኛ ዘፍነን ትግርኛ ተናገርን የዘር ሐረጋችን እንድሚያመለክተን ወደድንም ጠላንም አማሮች ነን።

ሌላው የትግራይ አካል ላለመሆናችን ማስረጃ ደግሞ በትግራይ ወያኔ እየተወሰደብን ያለው የጭካኔ እርምጃ ነው። ወገኖቻችን ናቸው ብለው ቢያምኑ ኖሮ እንደዚህ ባልጨከኑብን ነበር። እንዳውም ጭካኔያቸው የንጉስ ሰለሞንን ፍርድ ያስታውሰኛል። “ሁለት እናቶች አንድን ህፃን የኔ ነው የኔ ነው ተባብለው ተጣሉና ለፍርድ ይቀርባሉ። ህፃኑ ለሁለት ተቆርጦ ግማሽ ግማሽ እንዲከፋፈሉ በተወሰነ ጊዜ ያልወለደችዋ ህፃኑ ለሁለት እንዲቆረጥ ስትስማማ፤ የማትጨክነዋ ወላጅ እናት ግን እያለቀሰች ‘ለሁለት ከሚቆረጥ በቃ እሷው ትውሰደው’አለች። ታዲያ ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን ግን የጨካኟን ሴት ቅጥፈትና ጭካኔ ተረድቶ ህፃኑን ለእውነተኛዋ እናት እንደሰጣት” ይነገራል። መቼም ምን ለማለት እንደፈለኩ ግልፅ ይመስለኛል።
3ኛ. የወልቃይት ፀገዴ ትክክለኛ ማንነት በህዝበ ውሳኔ ሊፈታ ይገባዋል፤ አማራ ለመሆን ወይም ከትግራይ ጋር ለመጠቃለል አልያም እንደወልቃይት ፀገዴነቱ ለብቻው ቢፈልግ ትላለህ። ይህ በጣም ትልቅ ስህተት ነው። አንተ ስለ አንድ የህብረተሰብ ክፍል ስትፅፍ እኮ ቢያንስ በመጠኑም ቢሆን የአካባቢውን ሠዎች እንዲሁም የአካባቢው የዕድሜ ባለፀጎች ልታማክር ይገባል። ዝም ብለህ አንተ በመሰለህ ልትፅፍ አይገባም። የወልቃይት ፀገዴ ህዝብ ከጎንደሬነት ወይም ከአማራነት ሌላ ምርጫ ሊቀርብለት አይገባም። ይህ ማለት እኮ ከትግራይ አውራጃዎች አድዋን ወይም አክሱምን ወስዶ “የጎንደር ነው ወይስ የትግራይ ነው?” ብሎ ህዝበ ውሳኔ እንደማድረግ ነው። ምክንያቱም የትግራይ መሆኑ ግልፅ ሆኖ እያለ የወልቃይት ፀገዴ ጉዳይም ከዚሁ ፈፅሞ የተለየ አይደለም። እርግጥ ነው ከኤርትራና ትግራይ ወጥተው ወልቃይት ፀገዴ የተወለዱ የሉም ማለቴ አይደለም። ቢሆንም ግን እነሱ የወልቃይት ፀገዴ ተወላጆች ይሆናሉ እንጂ ወልቃይት ፀገዴን ትግራይ ማድረግ አይችሉም። የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች አብዛኛዎቹ የአማራ ዝርያ ያላቸው ናቸው። ነገር ግን መቀሌ በመወለዳቸው መቀሌዎች ይሆናል እንጂ መቀሌን ጎጃም ወይም ጎንደር ማድረግ ግን አይችሉም። የአድዋ ሰዎችም በብዛት ከኤርትራ ጋር የተዋለዱ ናቸው። ለዚህ ነው አንዳንድ የአድዋ ተወላጆች የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ከኢትዮጵያ ይልቅ ለኤርትራ የሚቆረቆሩት። ቢሆንም ግን አድዋ ስለተወለዱ አድዋ ይሆናሉ እንጂ አድዋን ኤርትራ ማድረግ አይችሉም። የወልቃይት ፀገዴ ህዝብም ከዚህ የተለየ ዕጣ ፈንታ ሊገጥመው አይገባም።

ሌላው ወልቃይት ፀገዴ ለብቻው የሚለውን ቅዠት ነው። ይህች ይህች እንኳ የወያኔ ቡራኬ የዘመኑ በሽታ ትመስላለች። ለመሆኑ ከየት አመጣኸው? ከአባትህ? ከአያትህ ወይንስ ከቅድመ አያትህ? በየትኛው ዘመን ነው ወልቃይት ፀገዴ ለብቻችን ሆነን የምናውቀው? ይህ ለኔ በጣም እንግዳ ነገር ነው የሆነብኝ። ወያኔዎችን የምንቃወመው በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሆኖ የማያውቀውን – ወልቃይት የትግራይ አካል ነው – ስላሉን እኮ ነው። አዲስ ነገር ስላመጡብን ነው። አንተ ደግሞ በታሪካችን ያልነበረ የሌለ አዲስ ነገር ስታመጣብን ከነሱ በምን ተለየህ። ለመሆኑ ለብቻ መሆን ጥቅሙ ምንድነው? የወልቃይት ፀገዴ ህዝብን አጋር ማሳጣት? ወገን አልባ ማስቀረት? በሁለት በኩል እንደጠላት እንዲታይ ለማድረግ? “መሃል ሰፋሪ በሁለት ጥይት ይመታል” ሲባል እንደነበር በሁለት እሳት መካከል ልትጠብሰን?
ደግሞ አማራና የወልቃይት ፀገዴ ህዝብ አጎራባች ብሔረሰብ ታደጋቸዋለህ። በርግጥ ትግሬና ኤርትራ የወልቃይት ፀገዴ አጎራባች ብሔረሰብ እንደሆኑ ግልፅ ነው። ጎንደሬ ወይም የአማራው ማህበረሰብ ግን እንዴት ሆኖ ጎረቤት ይሆናል? የአማራው ወይም የጎንደሬው አካል እንጂ? ምናልባት አንዳንድ ሰዎች አማራ ነን ባይሉም ጎንደሬነታቸው መቶ በመቶ ያምኑበታል። ታዲያ ጎንደሬና አማራ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ማለት ናቸው። ስለዚህ የወልቃይት ፀገዴና የአማራው ማህበረሰብ ሲወርድ ሲዋረድ በደም በሥጋና በአጥንት የተሳሰረ አንድ አካል እንጂ ጎረቤት ሊሆን አይችልም። በአንድ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሥጋ ዘመዶች ቤተሰብ እንጂ ጎረቤት ሊባሉ አይችሉም። አንተ ለወልቃይት ፀገዴ ህዝብ ከልብ ብታስብ ኖሮ እንኳን ለጎንደሬነታችን ለአማራነታችን ብዙ ማስረጃ እያለን ከኤኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንፃር እንኳ ሲታይ ከአማራ ጋር ብንሆን አማራው ለራሱ ቀርቶ ለሌላ የሚተርፍ ሰፊና ለም መሬት አለው። ከኛ ምንም ነገር አይፈልግም። ያውም የዋህነቱ፤ ቅን አመለካከቱ፤ አርቆ አስተዋይነቱና ርህራሔው ሳይጨመርበት ማለት ነው። ከትግራይ ጋር ብንሆን ግን እነሱ ከኛ የሚያገኙት ጥቅም እንጂ እኛ ከነሱ የምናገኘው ጥቅም ፈፅሞ የለም። ለዚህም ነው 800 000 ያህል ህዝብና ሰራዊት እላያችን ላይ አምጥተው ያፈሰሱብን። ያውም የወልቃይት ፀገዴ ህዝብ እያጠፉና ባዶ ስድስት ከሚባል ከመሬት በታች እስር ቤት እያጎሩ። ይህን ስል ግን ወያኔና የወያኔ ደጋፊዎችን እንጂ ድፍን የትግራይ ህዝብ ለማለት እንዳልሆነ እያሳሰብኩ ማለት ነው።
4ኛ. “የአማራ ገዢዎች ወልቃይት ፀገዴን ሲያስተዳድሩ ከፖለቲካ ባሻገር ባህል የመለወጥ ይሁን ኤኮኖሚያዊ አጀንዳ ስላልነበራቸው በሰላም ተስማምተው ኑረዋል። ባህል አስመልክቶ ግን የወልቃይት ፀገዴ ተወላጆች ትግርኛ ተናጋሪዎች በመሆናቸው ቋንቋቸው በቀላሉ ሊቀይሩት አልቻሉም፤ ትግሬዎች ግን በቋንቋ ስለሚመሳሰሉ በቀላሉ ሊቀይሩት ይችላሉ” ትላለህ። ለመሆኑ ጥናት አድርገህ ነው ወይስ በግምት ነው የምትናገረው? እኔ ደግሞ አማርኛ ተናጋሪ ገዢዎች ወልቃይት ፀገዴን ያልቀየሩ ባህሉ በጣም ስለተመሳሰለባቸው እንጂ ቋንቋው ስለጠጠረባቸው ነው የሚል እምነት የለኝም። ምክንያቱም አማርኛ ተናጋሪ ገዢዎች ወደ ወልቃይት ፀገዴ ሲመጡ እንደሌላው አካባቢ እንደትግራይ፤ እንደ ኤርትራ ወይም እንደደቡብ ኢትዮጵያ አስተርጓሚ አያስፈልጋቸውም። ህዝቡ አሳምሮ አማርኛ መስማትና መናገር ይችላል። ገዢዎቹ ወደ የወልቃይት ፀገዴ ስብሰባ ሲመጡ ስብሰባው የሚካሔደው በአማርኛ ነው። ወደ ሠርግ ቢኬድ የሚዘፈነው አማርኛ እስክስታውም አማርኛ ነው። ሀዘን ሊያሰተዛዝኑ ሲሄዱ አስለቃሽ ምሾ የሚያወርደው በአማርኛ ነው። ቤተክርስቲያን ሲሄዱ የሚሰበከው በአማርኛ ነው። ጠላት ያርበደበደ ወይ አንበሳ የገደለ የወልቃይት ፀገዴ ጀግና ገዢዎች ፊት ቀርቦ ቢፎክር በአማርኛ ነው። ሥነ ፅሑፍ ፅፎ ቢያቀርብ በአማርኛ ነው። ታዲያ ምኑን ነው የሚቀይሩት? ያልቀየሩት የሚቀየር ነገር ስላጡ እንጂ ቋንቋው ጠጥሮባቸው አይደለም። እንዳውም ባይተዋር የሚሆኑት ከትግራይ የሚመጥ ሰዎች ናቸው። አንዳንዴ “እንዳው ይች ትግርኛ በየት በኩል ሾልካ ገባች” የምልበት አጋጣሚ አለ። የመሃል አገር ገዢዎች የምትላቸው እንኳን በጣም የሚቀራረብ አማርኛና ትግርኛ ቋንቋ ቀርቶ ከአማርኛ ቋንቋ ጋር ፈፅሞ የማይመሳሰሉ በደቡብ ኢትዮጵያ ቋንቋዎች ላይ ተፅዕኖ አሳድሮ ከ50 ብሔረሰቦች በላይ አማርኛን እንደ ሁለተኛ ቋንቋ እንዲያውቁት አስችለዋል። ደግሞ ታውቃለህ በወልቃይት ፀገዴ ባህል አማርኛ ቋንቋ አውቆ መገኘት የትልቅነት ምልክት መመዘኛ ነው። ህዝቡ አማርኛ የሚለምደው በፍላጎት እንጂ በግዴታ አይደለም። በማህበረሰቡ ዘንድ አማርኛ የማያውቅ ክርስቲያን ሆኖ ዳዊት ያልደገመና (እስላም ሆኖ ቁራን ያልቀራ) እንደሙሉ ሰው አይቆጠርም። ጠቅለል ባለ መልኩ የወልቃይት ፀገዴ ህዝብ አማርኛ ቋንቋ ለክት ትግርኛ ለዘወትር ነው የሚጠቀምበት ለማለት ይቻላል። በአገራችን ባህል ምርጥ ልብስና ነጫጭ ሸማ የክት ሆኖ ለሰርግ ለስብሰባ ለቤተክርስቲያን ለመስጊድ እንዲሁም ለመሥሪያ ቤት ለሩቅ ዘመድ ጥየቃ ተጠቅሞ ለቤት ሥራ ሲሆን የዘወትር ልብስ እንደሚለበስ ማለት ነው።
ወልቃይት ፀገዴም ለሰርግ፤ ለስብሰባ፤ ለቤተክርስቲያን፤ ለፍከራ ለጀግንነት መግለጫና ለመስሪያ ቤት አማርኛን ተጠቅሞ ለዘወትር ሲሆን ትግርኛ ይጠቀማል። ይህ ለማጋነን ሳይሆን ትክክለኛ የህዝቡን ባህል ነው የምገልፅልህ። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ህዝብ አዲስ ነገር አይደለም። ለምሳሌ በፊት ለሁሉም ነገር የግዕዝ ቋንቋ እንጠቀም ነበር፤ ከጊዜ በኋላ ግን ቀደምት አባቶች በግዕዝ ቋንቋ ቃለ እግዚአብሔር እያስተማርን፤ እየቀደስን፤ ቅኔ እየዘረፍን፤ ማህሌት እየወረድን አምላካችንን በምናመሰግንበት ቋንቋ ተመልሰን ክፉ ቃል ልንናገርበት አይገባምና ግዕዝ ለቤተክርስቲያን ብቻ ትተን ለዓላማዊ ነገር ሌላ ቋንቋ ሊኖረን ይገባል ብለው አማርኛም ትግርኛም እንደፈጠሩ ይነገራል። ስለዚህ ግዕዝ የቤተክርስቲያን ቋንቋ ሆኖ ስለቀረ የኢትዮጵያ ቋንቋ አይደለም እንደማይባል ሁሉ የወልቃይት ፀገዴ ህዝብም አማርኛ ቋንቋን ለዘወትር ተግባራት ባለመጠቀሙ አማርኛ ተናጋሪ አይደለም ማለት ፈፅሞ የተሳሳተ አመለካከት ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ወያኔ ጠላቴ ነዉ ያለዉ አማራን እንጅ ኢትዮጵያን አይደለም::አንተ ከዬት አምጥተህ ነዉ ወያኔ የኢትዮጵያም ጠላት ነዉ እያልክ የምትጽፈዉ?  - ሸንቁጥ አየለ

5ኛ. “የትግራይና የወልቃይት ፀገዴ ህዝብ አንድ ዓይነት ቋንቋ በመናገራቸው አብረው በሰላም የመኖር ዕድላቸው ከፍ ያደርገዋል። ከባላባት እስከ ተራ ሰዎች ለዘመናት በጋብቻ ተሳስረውና ተዛምደው ኖረዋል ” ትላለህ። ይህ አንተ ነህ የምትለው፤ እነሱ ግን ተዋልደናል ተዘምደናል አይሉም – መሬታችንንና ንብረታችንን ከመዝረፍ በስተቀር። ደግሞ አንድ ህዝብ በሰላም የሚኖረው ወስጣዊ የአንድነት እምነትና ነባራዊ የሥነልቦና ትስስር ሲኖረው እንጂ አንድ ዓይነት ቋንቋ ስለተናገረ አይደለም። አንድ ዓይነት ቋንቋ መናገር በሰላም የማኖር ዕድል ቢፈጥር ኖሮ ለሶማሌዎች፤ ለየመናዊያን፤ ለሶሪያዊያን፤ ለኢራቃዊያንና ለሊቢያዊያን በሰላም ማኖር በቻለ ነበር። በዓለማችን ላይ በከፋ መልኩ የሰላም ዕጦት ያለባቸው ሀገሮች አንድ ዓይነት ቋንቋ የሚናገሩ ህዝቦች የሚኖሩባቸው አካባቢዎች ናቸው። ስለዚህ ነገሮችን በዙሪያ ገብ (360 ዲግሪ) የዕይታ ስፋት ልትመለከታቸው ይገባል!

6ኛ. “የዘመናችን የትግራይ ገዢዎች የፈፀሙት የወልቃይት ፀገዴን ህዝብ ሰብአዊ ክብር የሚያዋርዱ ጥሰቶችን በዚህ መድረክ ላይ መግለፅ በህዝቦች መካከል አላስፈላጊ ቁርሾ ስለሚፈጥር እዛው ተከድኖ ይብሰል” እያልክ እንዳንተ አባባል የአማራ ገዢዎች በወልቃይት ፀገዴ ህዝብ ላይ አደረሱት የምትለውን ግፍ ግን አንድ ሳታስቀር ዝክዝክ አድርገህ ፅፈኸዋል። ታዲያ በወልቃይት ፀገዴና በአማራው ማህበረሰብ መካከልስ የሚፈጠረው አላስፈላጊ ቁርሾ አያሳስብህም? ያውም ተራ ነገር ከደምቢያ የሔዱ፤ ከወገራ የሔዱ በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ምግብ በሉ ጠላ ጠጡ እያልክ ትንንሿን ነገር እያጋነንክ ሁለት ቤተሰብ ማጋጨት ከንፁህ ህሊና የሚጠበቅ አይደለም። እርግጥ ነው ኢትዮጵያ በወቅቱ በበጀት የታገዘ ዘመናዊ የሆነ መንግሥታዊ መዋቅር ስላልዘረጋች ገዢዎች በሚሄዱበት አካባቢ ማረፊያና ቀለባቸው የሚያዘጋጅላቸው ህዝቡ ነበር – በመንግሥት የሚመደብላቸው በጀት ባለመኖሩ! የወልቃይት ፀገዴ የአካባቢ ገዢዎችም ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩ ማረፊያቸውና ቀለባቸውን የሚጎበኙት ህዝብ ነበር የሚችላቸው።
ታዲያ ደሞዝ የላቸው! ገንዘብ እንኳ ቢይዙ የሚስተናገዱበት ሆቴል የለ! የት ይሒዱ? እንኳን ይህ ቀላል የሚበላና የሚጠጣ ማቅረብ ይቅርና የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት መጣ በተባለ ቁጥር ከመንግሥት ምንም ውለታ ሳይጠብቅ በራሱ ስንቅና ትጥቅ ከጠላ ጋር ሲዋጋ የኖረ ህዝብ ነው። አፄ ዮሐንስ ኢትዮጵያን ለብዙ ዓመታት ሲያስተዳድሩ ሠራዊታቸውን እኮ የሚቀልብላቸው የአማራው ማህበረሰብ ነበር። ይህ ደግሞ እንድብዝበዛ ወይም እንደበደል የሚቆጠር ሳይሆን ጊዜው የሚጠይቀው ያ ስለነበር ነው። ስለዚህ ትናንትን በዛሬ ሚዛን፤ ዛሬን ደግሞ በትናንት ሚዛን መለካት ተገቢ አይደለም። ትናንትን በትናንት፤ ዛሬን በዛሬ እንጂ!

እንዲያውም ምን እንደታወሰኝ ታውቃለህ? ወያኔዎች የኦሮሞን ህዝብና የአማራ ህዝብ ለማጋጨት ከ150 ዓመት በፊት የተደረጉትን መጥፎ ትዝታዎች ብቻ እየቀሰቀሱ – አፄ ምኒልክ የኦሮሞ ሴቶች ጡት ቆርጠዋል – እያሉ በህዝቦች መካከል ቁርሾ ለመፍጠር የተቆረጡ ጡቶች የያዙ እጆች ሐውልት አሰርተዋል። ሴቶች ጡታቸውን ተቆርጠው እኮ በህይወት መኖር ይችላሉ – ይህን ስል ጡት መቁረጥ ወንጀል አይደለም ማለቴ እንዳመስልህ! ወያኔዎች በአንድ ጀምበር 150 ሰው እየገደሉ፤ ከ5000 ሰዎች በላይ እስር ቤት እያጎሩ፤ ከ150 ዓመት በፊት ለተቆረጡ ጡቶች ሐውልት ያሰራሉ – ያውም እኮ ወንጀሉ ተፈፅሞ ከሆነ ነው?
የድሮ ገዢዎች መጀመሪያ ሲገቡ የአካባቢ ህዝብ ፈርቶ እንዲገዛላቸው የጭካኔ ርምጃ ይወስዳሉ እንጂ አንዴ ወደ ህዝቡ ከቀረቡ በኋላ ሩህሩሆች ነበሩ። ወያኔዎች ግን ሲገቡ ጀምረው መግደል ማጋደል፤ ማሰርና መዝረፍ የጀመሩ 25 ዓመት ሙሉ ቀጥለውበውት እስካሁን አላቆሙም። ስለአፄ ምንሊክ ካነሳሁ አንድ ነገር ልበልና ላብቃ! የእምዬ ምንሊክን ስም ማጥፋት የሚፈልጉ ሰዎች “አፄ ምንሊክ ሰው እንዳይሞት ጋላም (ኦሮሞም)ቢሆን” ብለዋል። ስለዚህ ኦሮሞን እንደሰው አይቆጥሩም ነበር እየተባለ ይወራል። እውነታው ግን ይህ አልነበረም። አጼ ምንሊክ በጊዜው ከደቡብ ኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ኦሮሞች ነበሩ ጠንከር ብለው ይዋጓቸው የነበሩና ደቡብ አካባቢ በቁጥጥራቸው ስር እያዋሉ ሲሔዱ ህዝቡን እየሰበሰቡ “ሰው እንዳይሞት! እየተዋጉኝ ያሉ ኦሮሞዎችም ቢሆን በሰላም እጃቸውን ከሰጡ እንዳትገድሉዋቸው” ለማለት ነው! ሰዎች አይደሉም ለማለት አይደለም። ለምሳሌ ደርግ ወያኔዎችን አሸንፎ የትግራይ አካባቢ ቢቆጣጠር ከተማ ከያዘ በኋላ “አንድ ሰላማዊ ሰው እንዳይሞት! ወያኔም ቢሆን” ሊል እንደሚችል ማለት ነው። እንኳን ሰላማዊ ሰዎች እየተዋጉኝ ያሉ ወያኔዎች በሰላም እጃቸው ከሰጡ አትግደሉዋቸው ለማለት እንጂ ወያኔዎች ሰዎች አይደሉም ለማለት አይደለም። ወያኔዎችም በተራቸው ኢትዮጵያን ሲቆጣጠሩ – አንድ ሰው እንዳይሞት፤ ኢሠፓም ቢሆን – ሊሉ እንደሚችሉ ማለት ነው። እውነት ለመናገር አፄ ምንሊክ ኦሮሞን እንደሰው እማይቆጥሩ እሳቸው ምን ቢሆኑ ነው?
7ኛ. ሌላው የመጨረሻ አስተያየቴ “አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሥርዓት በበጎ ጎኑ የሚታወቀው በኢትዮጵያ ውስጥና ሰላም ባልሰፈነባቸው የአካባቢያችን ቀጠናዎች ሰላምንና መረጋጋትን በማምጣቱ ነው፤ ከዚያም በተጨማሪ የብሔረሰቦችን ጥያቄ ምላሽ ለማምጣት የተደረገው ሙከራ አዎንታዊ ይዘት አለው” የሚለው አባባልህ ላይ ነው። ይህ አባባል በውነቱ የወያኔ የከፋፍለህ ግዛና ዘረኛ ፖሊሲ ተልዕኮ ለማስፈፀም ራሳቸውን ለጥቅም በመሸጥ ህሊናቸው የማይፈቅደውን የሐሰት መልዕክት ከሚያስተላልፉ ግብዞች የሚተናነስ አይደለም። በምንም መመዘኛ ወያኔዎች ችግርን ከማባባስና የራሳቸውን ጥቅም ከማሳደድ በስተቀር አንድም ችግር አልፈቱም፤ ለወደፊቱም አይፈቱም። ይህን የምለው በጣም እርግጠኛ ሆኜ ነው። ንቦች ማር ለመሥራት አበባ መቅሰም እንዳለባቸው ሁሉ ወያኔዎችም ትርፍ የሚያገኙት ችግር በመፍጠርና ሌላውን ክፍል በመጉዳት ስለመሆኑ የታወቀ ነው። ስለዚህ ወያኔዎች ችግር ፈቱ ማለት ኪሣራ ላይ ወደቁ ማለት ነው።
እንደሚታወቀው እንደ እስስት መቀያየር የማይቸግራቸው ወያኔዎች የደርግ መውደቅ ተከትሎ ኢትዮጵያን ለመዝረፍ ኢትዮጵያዊ መልክ ተላብሰው ኢትዮጵያዊ ይምሰሉ እንጂ ሲጀመር ፀረ-ኢትዮጵያ አጀንዳ ቀርፀው የተንቀሳቀሱ ኃይሎች ናቸው። አንግበውት የተነሱ ዓላማ እኮ ትግራይ የራሷ ሪፐብሊክ ሊታወጅላት፤ ኤርትራ በቅኝ ግዛት የተያዘች እንጂ የኢትዮጵያ አካል አይደለችም፤ አማራ የትግራይ አዝብ ጠላት ነው፤ የኢትዮጵያ ህልውና የ አንድ መቶ ዓመት ታሪክ ነው፤ ባንዲራ ጨርቅ ነው እያሉ ለራሳቸው ተሳስተው ኩሩ ኢትዮጵያዊው የትግራይ ህዝብን ያሳሳቱ (በአሁኑ ሰዓት ያለው የትግራይ ህዝብ ወያኔዎች በፈርሃ እግዚአብሔርና በሃገር ፍቅር ስሜት የነደዱ ቀደምት የትግራይ አባቶችና እናቶች ገድለው ጨርሰው ብሬይን ዋሽ የተደረጉ በልጅነት አዕምሮዋቸው በአምሳላቸው ቀርፀው ያሳደጓቸው ነው ያሉት። ለዚህ ነው ተዉ የሚል ሰው የጠፋው። ሠርቀው ትግራይ ቢገነቡ እሰየው፤ የኢትዮጵያን ህዝብ ቢጨፈጭፉ እሰየው፤ የሰው መሬት ቀምተው ቢሰጡአቸው እሰየው፤ የኢትዮጵያ መሬት ለውጭ ባለሀብት ቢሰጥ መሬታቸው አይመስላቸው፤ የሀገር ድንበር ተቆርሶ ለጎረቤት አገር ቢሰጥ የሀገራቸው ድንበር አይመስላቸው፤ የትግራይን ወጣት አደንዝዘው የነሱ የጥፋት ተባባሪ አድርገውታል። እና ወገናችን የትግራይ ህዝብ ሳያውቀው በጠላት እጅ ወድቋል። ስለዚህ ነፃ መውጣት ካለ በቅድሚያ ነፃ መውጣት ያለበት የትግራይ ህዝብ ነው) እነዚህ ኢትዮጵያዊ ሥጋ ደም ተላብሰው ኢትዮጵያን ለማጥፋት የመጡ የውጭ ጠላት ተልዕኮ አስፈፃሚዎች በምን መልኩ ነው ከነዚህ ጥሩ ነገር ይመጣል ብለህ ምስክርነትህ የምትሰጠው? ዘርን መሰረት ካደረገው የወያኔ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ እንዴት በጎ ነግር ትጠብቃለህ? የብሔረሰቦች ችግር መፍታት ማለት ለዘመናት ተዋልዶና ተዛምዶ ለኖረ ህዝብ ብዙ መልካምና መጥፎ ትዝታዎች አብሮ ያሳለፈ ህዝብ በ18ኛው ክፍለ ዘመን የተሰሩ መጥፎ ትዝታዎች ብቻ እየመዘዙ ብሔር ከብሔር ማጋጨት ይህ ነው መፍትሔ? አገሪቷን በ10 የቋንቋ ክልል ከፋፍሎ፤ አስር ባንዲራ ሰጥቶ፤ አንቀፅ 39 ፈጥሮ መገነጣጠል ትችላላችሁ ማለት ነው የብሔረሰብ ችግርን መፍታት? ወይስ ህዝብ የማያወቃቸው፤ ፈቅዶ ያልመረጣቸው፤ ብሔሩን የማይወክሉ የወያኔ ተላላኪዎችና የተባሉትን ፈፃሚዎች የአሻንጉሊት ፌዴራሊዝም ፈጥሮ የ95 ሚሊዮን ህዝብ ድርሻ ለአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝብ ብቻ እየዘረፉ ማጋዝ ነው ፍትህ? ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ገንብተናል ብለው ምርጫውን መቶ በመቶ አሸነፍን የሚሉ?
በወያኔ ያልተሰቃየ ብሔረሰብ ማን ነው? ኦሮሞ፤ አማራ፤ አፋር፤ ጉራጌ፤ ሶማሌ፤ አኝዋክ ወዘተ ማን ነው የደም እንባ ያላነባ? በንጉሡ ዘመንና በወታደራዊው መንግሥት ይታይ የነበረው የየመሥሪያ ቤቱ የብሔር ተዋፅኦ ስብጥር እኮ ዛሬ ያለ ይሉኝታ በአንድ ብሔር መተካቱ ፍትህ ነው? መከላከያ፤ ፖሊስ ሠራዊት፤ ደህንነት፤ ቁልፍ ቁልፍ የሃገሪቷ የሥልጣን ተዋረድ በአንድ ብሔረሰብ መያዙ መፍትሔ ነው?
ይህ ነው የብሔረሰቦችን ችግር መፍታት ማለት? በኔ በኩል ይበልጥ አወሳሰቡት እንጂ ምንም መፍትሔ አላመጡም፤ እስከመጨረሻም አያመጡም። አስር የማይሞሉ ፊውዳሎች የደሃ ገበሬ መሬት ወሰዱ ብለን “መሬት ላራሹ” እያልን እንዳልሞትንና እንዳልቆሰልን ሁሉ ዛሬ ዓይናችን እያየ ለህንድ፤ ለአረብ፤ ለአውሮፓዊያንና ለመላው የዓለም ባለሀብቶች የድሀውን ገበሬ መሬት በውስጥ ለውስጥ ገበያ በገፍ እየተቸበቸበ ያለበት ዘመን እኮ ነው ያለነው! ለአጭር ጊዜ በሥልጣን ለመቆየት ሲባል ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን መስዋዕትነት ከፍለው ያቆዩልንን ዳር ድንበራችን እንደኬክ እየተቆረሰ ለአጎራባች አገሮች የሚታደልበት ዘመን ደርሰን መፍትሔ አመጡ ትለናለህ። ከትግራይ በስተቀር ሌላው ኢትዮጵያዊ እንደወገናቸው የማይቆጥሩ፤ አግዘው የማይደክሙ፤ ዘርፈው የማይጠግቡ ይሉኝታ ቢሶች! አንድ ህንፃ ሊገነቡ 1000 አባወራ፤ አንድ ኪሎ ሜትር መንገድ ሊሰሩ 10000 አባወራ የሚያፈናቅሉ ጨካኞች! ሥልጣን ላይ ከወጡ በ25 ዓመት ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ህዝብ ስም በዕርዳታ 45 ቢሊዮን ዶላር፤ በብድር 30 ቢሊዮን ዶላር በድምሩ 75 ቢሊዮን ዶላር ተረክበው 65 ቢሊዮኑን ወደኪሳቸው ከተው በ10 ቢሊዮን ዶላር ልማት አለማን እያሉ የሚመፃደቁ አጭበርባሪዎች! ደርግኮ በ17 ዓመቱ የሥልጣን ዘመኑ 3.7 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነበር በዕርዳታ ያገኘው። ይታይህ እንግዲህ!
በል ወዳጄ! የነዚህ ጉድ እንኳን በ9 ገፅ በ9 መጻህፍት ተፅፎ አያልቅምና በዚሁ ልሰናበት!

ተጨማሪ ያንብቡ:  በየፊናችን እየተማረርን መማራችን ለበጎ ነው - ከይነጋል በላቸው

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

ግዛት ተገኘ
ለማንኛውም አስተያየት gizat.tesfaye@gmail.com ይጠቀሙ

4 Comments

  1. Thank u

    What do u expect from that Banda he is tplf left over trash eko when the time comes he will pay the price

  2. እንግዲህ “አላርፍ ያለች እጣት ምን ነክታ ትመጣለች” አለ ዐማራ

    አቶ ሃይሉ የሺወንድም ጭንብልዎት አንዴ ተገልጦ የመሸጉበት ህወሃታዊ ማንነትዎ ፍንትው ብሎ መታየት ጀምረ መሰለኝ:: እንግዲህ ይቻሉት! ለአማራ ህዝብ ያለዎት የመረረ ጥላቻና የትግሬን ጫማ መላስዎና መጎብደድዎ እለት በእለት እየተጋለጠ እንደሚመጣ አልጠራጠርም::

    ይልቁንም በእነ ወ/ሪት አዘብ መስፍንና በህወሃቶች ታዘው አፍዎን በከፈቱና ወረቀት በሞነጫጨሩ ቁጥር ምን ያህል እየተጋለጡና በውስጥዎ የኖረው መርዛማውና በወጣትነትዎ ከጀብሃ የተቀበሉት ተልዕኮዎ አደባባይ እየወጣ ነውና ይበርቱ::

    እርግጠኛ ነኝ እንደ አቶ ግዛት ተገኝ አይነት እጄ-ወርቅ የወልቃይትን ህዝብ ከትግራይ-ትግሬያዊነት ወደ ኢርትራ-ትግሬያዊነት ለማጠጋጋት የሞከሩበትን ሴራና ከጀብሃ የተቀበሉትን ተልዕኮ ለአደባባይ እንደሚያበቃው አልጠራጠርም

    በመጨረሻ አቶ ግዛት ተገኝ ከእውነት ጎን በመቆምዎት ምስጋናየ ይድረስዎ

    ወልደአረጋዊ ነኝ ከኮሎራዶ

  3. ጉድ ነው ቛንቛም የአዘቦትና የክት አለዉ?አረ አገሬ ስንቱን አቅፈሽ ይዘሻል?ጥያቄ አለኝ የክቱ ቛንቛ እስኪነገር ድረስ የት ነው የሚቀመጠው ?ተናጋሪዉ ከቤቱ ሲወጣ ስንት የክት ቃላት ይዞ ይወጣል ?አረ ሌላም ሌላ ጥያቄ ማንሳት ይቻላል።ማፈሪያ ለዚህ ዘመን ትዉልድ የማይመጥን ፁሑፍ “…አማርኛ ለክትሲነገር … ትግርኛ ግን በዘወትር ብቻ ይነገራል … “አጃኢባ ማለት አሁነዉ።አጭር አገላለፅ ወልቃይት የትግራይ ክልል ማለት በቂነበር ቛንቛን የክት የዘወትር ከማለት።

  4. ሰላም ለወንድም ግዛት! የአንተን የመልስ ጽሁፍ ሳነበው ከግርምት ጋር ነበር። ቀልብህ የሳቡትን ሃረጎች ከአውዳቸው እንደመሰለህ እየመዘዝክ ለእያንዳንዷ ሃረግ ዘለግ ያሉ አስተያየቶችን ሰጥተሃል። የጽሁፍህ ይዘት ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ሆኖ ባገኘውም በአነሳሃቸው የመከራከሪያ ነጥቦች ግን መቶ በመቶ (100%) እስማማለሁ። ለምሳሌ ያህል ስለ ወልቃይት ስትጽፍ “ጸገዴን” አልጠቀስክምና ሁለቱን አለያይተሃል ከሚል የተሳሳተ መነሻ ብዙ ሃቆችን ጽፈሃል። ለእኔ ግን ወልቃይት ጠገዴ ነው ጠገዴም ወልቃይት ነው። አምሳል ምትኬም
    ጉምጉም ጉምጉብ በዛ፡
    ወልቃይት መጣ እያገሳ፡
    ብላ ዘፍናለችና ጠገዴን ያልጠቀስሽ ብለህ ክሰሳታ። ስለሆነም መነሻህ (premise) እንጂ በአቋም ደረጃ ልዩነት ስለሌለን ለአንተ መልስ መጻፉ ትርፍ የለውም። ይልቁንስ የጻፍከው ሃቅ አንባቢው እንዲማርበትና ህወሓት በወልቃይት ህዝብ ላይ ያደረሰውን ግፍ እንዲያውቅ ያደርጋልና በዚህ ትመሰገናለህ። የእኔ የአንድ ግለሰብ ስም መጥፋት ችግር የለውም። ጊዜው ሲደርስ እውነቱ ይለያል።

Comments are closed.

Share