በአ.አ ጉድጓድ በሚቆፍሩ ሰዎች ላይ በደረሰ አፈር መደርመስ የ3 ወጣቶች ሕይወት አለፈ፤ አንድ ሰው ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል

(ዘ-ሐበሻ) ለባቡር ግንባታ በሚል ተቆፍሮ የነበረ አፈር ተደርምሶ በቁፋሮ ሥራ ላይ የነበሩ 3 ዕድሜያቸው ከ20 እስከ 23 የሚገመቱ ወጣቶች ሕይወታቸው ማለፉን ከአዲስ አበባ የመጣው መረጃ አመለከተ።
የአዲስ አበባ ከተማ ገጽታ (ፎቶ ከፋይል)
በአዲስ አበባ በዚህ ቁፋሮ ሳቢያ በየቀኑ ሰዎች እየወደቁ አካላቸውን ለጉዳት እያጋለጡ መሆናቸው በተደጋጋሚ የተዘገበ ቢሆንም ለእግረኞችም ሆነ ለሠራተኞች አመቺ ባልሆነ መንገድ የተከመረው አፈርና ድንጋይ አሁንም በሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን ቀጥሏል።

በዛሬው ዕለት በቁፋሮ ላይ እያሉ ህይወታቸው ያለፈው 3 ሰዎች በአቃቂ ክፍለ ከተማ ጉምሩክ ግቢ በተባለ ስፍራ ለቀላል ባቡር መስመር ግንባታ የሚሆን ጉድጓድ በመቆፈር ላይ የነበሩ ሲሆኑ ሰራተኞቹ ቆፍረው የከመሩት አፈር ተደርምሶ ሕይወታቸውን ሊያሳጣቸው ችሏል ከ3ቱ ቆፋሪዎች በተጨማሪም ሌሎች 4 ሰዎች ቀላልና ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ከአዲስ አበባ ለዘ-ሐበሻ የደረሰው መረጃ ሲያመለክት የሚመለከተው አካል በነዚህ ክምር አፈሮችና ድንጋዮች እንዲሁም በተቆፈሩ ቦታዎች አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ክትትል ካላደረገ በስተቀር እንዲህ ያለው አደጋ ሊቀጥል እንደሚችል ታዛቢዎች ይናገራሉ። ጉዳት ከደረሰባቸው ወገኖች መካከል አንዱ በከፍተኛ ጉዳት እየተሰቃየ መሆኑንም ጨምሮ የደረሰን መረጃ ይሳያል።

አዲስ አበባ ከተማ ላይ በተለያዩ ቦታዎች የተቆፈሩ ቦታዎች ላይ ሰዎች እንደሚራመዱበት ያስታወቁት የዘ-ሐበሻ ዘጋቢዎች እንደሚወድቁና አንዳንድ ጊዜም ለአካል ጉዳት እንደሚዳረጉ ጠቅሰው አስፈላጊው የጥንቃቄ ምልክቶች ሊቀመጡ እንደሚገባ ጥቆማቸውን ይሰጣሉ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በምሥራቅ ወለጋ ዞን የታጠቁ ቡድኖች ባደረሱት ጥቃት የንጹሃን ህይወት አለፈ

1 Comment

Comments are closed.

Share