በምሥራቅ ወለጋ ዞን የታጠቁ ቡድኖች ባደረሱት ጥቃት የንጹሃን ህይወት አለፈ

244960737 1653185624856425 6605859502819524826 n

በምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ሀሮ ቀበሌ የታጠቁ ቡድኖች በአማራዎች ላይ በከፈቱት ጥቃት የንጹሃን ህይወት ማለፉን እና ንብረት መውደሙን የጥቃቱ ሰለባ ቤተሰቦች ለአሚኮ ገልጸዋል፡፡ በአካባቢው በተደጋጋሚ እየደረሰ ባለው ጥቃት ሸሽተው እንደመጡ የገለጹት የተጠቂ ቤተሰቦች ከትናንት እኩለ ቀን ጀምሮ ደግሞ በቤተሰቦቻቸው ላይ የታጠቁ ቡድኖች ጥቃት መፈጸማቸውን ነግረውናል፡፡

ከዚህ በፊት ታጣቂዎች በዞኑ ውስጥ በሚኖሩ አማራዎች ላይ በከፈቱት ጥቃት የንጹሃን ዜጎች ሕይወት ማለፉንና በርካታ ንብረት መውደሙን አስታውሰው ትናንት ደግሞ ከዚህ በፊት ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በአንድ ላይ በሚኖሩባት የሀሮ ቀበሌ በተከፈተ ጥቃት ንብረት መውደሙን እና የንጹን ህይወት ማለፉን ነው የገለጹልን፡፡

ከዚህ በፊት ወደ አካባቢው የጸጥታ ኀይል እንዲገባ ተደርጎ ችግሩ ቆሞ እንደነበር ነግረውናል፡፡ ይሁን እንጅ የገባው የጸጥታ ኀይል በመውጣቱ ጥቃት ተፈጽሟል ብለዋል፡፡ በዚህም የንጹሃን ህይወት አልፏል፣ ንብረት ወድሟል፤ ቤት ተቃጥሏል፤ የተረፈውም በተደራጁ ቡድኖች መዘረፉን ተናግረዋል፡፡

ችግሩ እንዲፈታ ከዚህ በፊት በየደረጃው ለሚገኙ የመንግሥት አካላት ጥያቄውን ማቅረባቸውን አንስተዋል፡፡

መንግሥት የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ወደ አካባቢው በማስገባት ከጥቃት የተረፉ ቤተሰቦቻቸውን እንዲታደጋቸውም ጠይቀዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጡን ለምሥራቅ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ፣ ለዞኑ ፖሊስ መምሪያና ለጸጥታ ዘርፍ ኀላፊዎች ደውለን ስልካቸው መነሳት አልቻለም፡፡ በጉዳዩ ላይ የዞኑን የሥራ የኀላፊዎችና የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንን ምላሽ ይዘን ለመቅረብ ጥረታችን እንቀጥላለን።

ባሕርዳር፡ ጥቅምት 01/2014 ዓ.ም (አሚኮ)

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.