Sport: የውጭ ተጫቾች በኢትዮጵያ- ተጠቀምን ወይስ ተጠቀሙብን? – ከገነነ መኩሪያ (ሊብሮ)

(ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ)
አላን ኮል የተባለ ጃማይካዊ በ1969 ዓ.ም ለአየር መንገድ ሲጫወት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ፌዴሬሽን በሚያዘጋጀው ውድድር የተጫወተ የመጀመሪያው የውጭ ተጨዋች ነው፡፡አላን መልኩ ቀይ ሆኖ ቁመቱ ረጅም ሲሆን በኳስ ቴክኒክ ችሎታው የተደነቀ ኳስን እንደፈለገ የሚያደርግ ነበር፡፡ከምድር ጦር ጋር በተደረገ ጨዋታ ሪጎሬ እግሩን አቆላልፎ ሲመታ ተመልካቹ በጣም ተደንቆ ነበር፡፡አላን ኮል የታዋቂው የሬጌ አቀንቃኝ የቦብ ማርሊ ፕሮሞተር ነበር፡፡ከቦብ ጋር አብሮ አደግ ሲሆን ቦብ በ1971 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ያስመጣውም እርሱ ነበር፡፡ በእርግጥ በአዲስ አበባ ስታዲየም ለማቅረብ ያሰቡት ዝግጅት ባይሳካም(ይሄ ነገር እንዴት እንደከሸፈና ቦብ ሻሸመኔ መጥቶ የተከሰተውን ነገር ማወቅ ትፈልጋላችሁ?ልጻፍላችሁ?)አላን አሁን በእንግሊዝ ሀገር ይገኛል ፡፡በተጫዋችነት ዘመኑ ለአርጀንቲና ብራዚል ክለቦች ተጫውቷል ፡፡ናውቲካ፤ አጀኖቲካና ሳንቶስን የመሳሰሉ ክለቦች አዳርሷል፡፡አየርመንገድ አላንን ከውጭ አስመጥቶት እንደ ፕሮፌሽናል ተጫዋች ኮንትራት ተፈራርሞ ሰይሆን በሌላ ጉዳይ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለመጣ እንዲጫትላቸው ጠይቀውት ነው፡፡ ወደ ሀገሩ ለእረፍት ሲሄድ ትራንስፖርት በነጻ ነው፡፡ከአላን በኋላ የውጭ ተጨዋቾች መምጣት የጀመሩት ከ18 አመት በኋላ ነበር ፡፡በ1987 ዓ.ም ከኬንያ አንድ ናይጀሪያዊ አጥቂ ጊዮርጊስ አስመጣ፡፡አመት ቆይቶ ሄደ ፡፡ከዚያ በኋላ ለተወሰነ አመታት የመጣ ሰው አልነበረም፡፡ ካለፉት 12 አመታት ግን እየተበራከቱ ከበረኛ እስከ አጥቂ በመጉረፍ ላይ ይገኛሉ…………በእኔ እይታና ምደባ ከውጭ የሚመጡ ተጫዋቾች በአምስት ይከፈላሉ፡፡በተለይ ከናይጀሪያ፤ጋና፤ካሜሩን የመጡ ፡፡ለምሳሌ ከናይጀሪያ የሚመጡትን ስናይ

1ኛ ደረጃ፡- አውሮፓ በተለይ ትላልቅ ሊጎች እንግሊዝ፤ስፔይን ጣሊያን የሚጫወቱ
2ተኛ ደረጃ-፡ ምስራቅ አውሮፓ እንደ ሩማንያ፤ቡልጋሪያ የሚጫወቱ
3ተኛ ደረጃ-፡ በኤሽያ የሚጫወቱ
4ተኛ ደረጃ-፡በአፍሪካ ሰሜን አካባቢ ቱኒዝያ፤ግብጽ፤ሞሮኮ የሚጫወቱ
5ኛ ደረጃ-፡ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ናቸው፡፡እዚህ የሚጫወቱት ምራጭና አራቱ ጋር እድል ያላገኙ ሰሜን አፍሪካ ሞክረው ሳይሳካላቸው የሚመጡ ናቸው፡፡ስድስተኛ ደረጃ ስለሌለ የመጨረሻቸው እዚህ ነው፡፡በሀገራቸው ምናልባት ቀበሌ ካለ ከዚያ ወይም በዚያ አቻ ከሆነ ቦታ ወይም ሰፈር ከሚባለው ሜዳ የመጡ ሊሆኑ ይችላሉ ፡፡እዚህ የሚመጡት የናይጀሪያ ፤የካሜሩን ተጫዋቾች አንድም ቀን ለሀገራቸው ብሄራዊ ቡድን ያልተጫወቱ ፡፡መጫወት ብቻ ሳይሆን ለምርጫ የመጠራት እድል የማያገኙ ናቸው፡፡ፊፋ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን እነዚህን ተጫዋቾች የሀገራቸው ብሄራዊ ቡድን ሲጫወት የኢትዮጵያን ክለቦች ቶሎ እንዲለቋቸው አያስገድድም (ስለማይጠሩ)ክለባቸውም ለብሄራዊ ስለማይሄዱ የተጫዋች እጥረት ይገጥመኛል የሚል ሀሳብ የለበትም፡፡እስካሁን በብዛት ተጫዋች በግንባር ቀደም ያስመጣው ጊዮርጊስ ነው፡፡ካሜሩን ፤ኬንያ፤ሩዋንዳ፤ናይጀሪያ፤ታንዛንያ፤ኡጋንዳ፤ጋና……ጊዮርጊስ ከ1987 ጀምሮ ሲያስመጣ አስካሁን በውጭ ተጨዋች በመጠቀም 19 አመት ሆኗቸዋል፡፡ በእነዚህ አመታት ጊዮርጊስ ምን ተጠቀመ? ጊዮርጊስ እነዚህ የውጭ ተጫዋቾች ከማምጣቱ በፊት በርካታ ዋንጫዎች አግኝቷል፡፡እነርሱም ከመጡ በኋላ ሻምፒዮና ሆኗል፡፡ስለዚህ በእነርሱ የተለየ ነገር አላገኘም፡፡ጊዮርጊስ በኢንተርናሽናል ውድድር እነርሱ ከመምጣታቸው በፊት ደካማ ነው፡፡የውጭ ተጫዋቾች ይሄን ይቀርፋሉ እንዳይባል በፊትም የነበረውን ውጤት ነው አሁንም ያስመዘገበው፡፡በዚህ 12 አመታት በርካታ የውጭ ተጫዋቾች ወደ ክለቡ መጥተው የምስራቅ አፍሪካ(ሴካፋ)ዋንጫን እንኳን አላገኙም ፡፡ታዲያ የውጭ ተጫዋቾች በጊዮርጊስ ክለብ ውስጥ ምን የተለየ ነገር አሳዩ? በኢንተርናሽናል ለውጥ ከሌለው ለሀገር ውስጥ ዋንጫ ድሮም በኢትዮጵያውን ተጫዋቾች ውጤት ያመጣል፡፡ለውጥ ለሌላው ነገር ቢሳተፉ ዶላር ይወስዳሉ በተጨማሪም የአንድ ሀበሻ የመጫዋቻ ቦታ ይይዛሉ………….. መብራት ሀይል በሚያሳድጋቸው ተጫዋቾች ጥሩ ቡድን በተደጋጋሚ ሰርቷል፡፡ማሳደጉ የተጀመረው በ1958 ጀምሮ ነው(ከፍቃደ ሙለታ-እስከነ መስኡድ ድረስ)ከዚያን ጀምሮ በብዛት ከታችኛው ቡድን ያወጣል፡፡ በ1993 ዓ.ም ደብል ዊነር ሲሆን በአብዛኛው ባሳደጋቸው ተጨዋቾች ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ድል ዜና ከሸዋሮቢት! ህዝቡ በደስታ አበድ! | የአማራ ድምጽ ዜና

ካለፉት አራት አመታት ወዲህ ግን ከውጭ በግዢ በሚያስመጣቸው ተጫዋች እየተጠቀመ ነው፡፡ በቡድን ብቃት፤ በተጫዋች ጥራትና በውጤት ያሁኑ ቡድን ከበፊቱ ያነሰ ብቻ ሳይሆን የወረደ ነው፡፡ከጨዋታም ከውጤትም የለበትም፡፡በማሳደግ ጥሩ ተጫዋች እያገኙና ይሄን በቡድኑ ባህል የሆነውን አሰራር አፍርሶ ምንም ለውጥ ወዳላሳዩ የውጭ ተጫዋቾች መሄድ ለምን አስፈለገ?

1 ከገንዘብ አንጻር
2በብዛት ከማሳደግ አንጻር

የተሻለው የበፊቱ ነው፡፡በተለይ በ2004 ከበረኛ ጀምሮ እስከ አጥቂ በውጭ ተጫዋች ተደራጅቶ ነበር ፡፡አስታውሳለሁ ደጋፊው የናይጀሪያን ባንድራ ይዞ እስከማውለብለብ ደርሶ ነበር፡፡ቡድኑ የኢትዮጵያ መብራት ሳይሆን የናይጀሪያ መብራት ሀይል ይመስል ነበር፡እነዚህ ከውጭ ብዛት ተጫዋች የሚያስመጡ ለወደፊቱ ደጋፊ ከናይጀሪያ ካሜሩን ሊያስመጡ ይችላሉ የሚል ድምዳሜ ላይ እንድደርስ እየገፋፉኝ ነው፡፡

በሀገራችን እስካሁን የተጫወቱና በመጫውት ላይ ያሉ በሁሉም ክለቦች ሲታዩ ያን ያህል ወሳን ተጫዋቾች አይደለሙ(እንደ ናይጀሪያዊነታቸው)ለምሳሌ በረጅም አመት ቆይታቸው ኮከብ ተጨዋች የተባለ አጥቂ ወይም አማካይ ሰምቼ አላውቅም ፡፡እሺ!! ይሄ እንኳን መራጮቹ ለሀገራቸው አድልተው ነው ሊባል ይችላል፡፡ ኮከብ ግብ አግቢ ግን በምርጫ አይደለም ብቃት ነው፡፡ያገባው ጎል ነው የሚወስነው፡፡አንድ ጊዜ ኮከብ ግብ አግቢ ተብሎ ውድድሩን የጨረሰ የውጭ ተጨዋች አላየሁም፡፡መጨረስ ብቻ ሳይሆን ፉክክር ውስጥ ገብቶ ኮከብ ባይሆንም እስከመጨረሻው የዘለቀ ተጫዋች አይታይም፡፡
እነዚህ የውጭ ተጨዋቾች አዲስአበባ ብቻ ሳይሆን ክልል ድረስ እየሄዱ ነው፡፡በሀገራችን እግር ኳስ ላይ ምንም ጠቀሜታ ከሌላቸው ምን ያደርጉልናል፡፡ እነርሱን በክለባችን አካተንም ሆነ ሳናካትት በክለብ በኢንተናሽናል ውድር ወጤት ከሌለ የነርሱ መኖር ምን ጠቀሜታ አለው?፡፡ብርቃችን ነው እንዴ? ከአንድ አመት በፊት ድሬዳዋ ከነማ ሶሰት ያህል የውጭ ተጫዋች ነበሩ፡፡ ድሬዳዋ አሸዋ ሜዳ ባፈራቸው ድንቅ ተጫዋቾች ከራሱ አልፎ ለአዲስ አበባ ክለቦች በርካታ ተጨዋች አፍርቷል፡፡እነአሰግድ ፤ቡሉ፤አሸናፊ፤ኬኔዲ፤ሙቅቢል፤ጌቱ…..አስደናቂ ነገር በመስራት ተመልካቹን በማስደሰት የግል ደጋፊ የነበራቸውና እነርሱን ብቻ ለማየት ወደ የሚመጡ ብዙ ነበሩ፡፡ድሬዎች ያንን ትተው ከናይጀሪያ ተጫዋች አሰመጡ፡፡ ቡድኑም ያኔ(የዛሬ ሁለት አመት) ድሬዳዋ ከነማ ሳይሆን ናይጀሪያ ከነማ ሊያስብለው ምን ቀረ? ድሬዳዋን አነሳሁ እንጅ አዳማ ከነማም ገብተዋል፡፡ የሚገርመው ከከነማ አልፈው ክፍለ ከተማ ድረስ ሄደዋል፡፡ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አንድ የውጭ ተጫዋች አስፈርሞ ነበር፡፡ከነማዎች በስራቸው ብዙ ቀበሌ አለ ፡፡ከነማ አላማው በየቀበሌው ያሉ ተጫዋቾችን አወዳድሮ ጥሩ የተባሉትን ወደ ዋናው ቡድን ማሳደግ ነው፡፡ነገር ግን ይሄ ቀርቶ ከነማዎች ከውጭ ሲያስመጡ ከቆሙለት አላማና ከአሰራሩም ወጡ ማለት ነው፡፡ወደ ዋናው ቡድን እንገባለን ያሉ የቀበሌ ተስፈኞች ከነማ ፊቱን ወደ ናይጀሪያ ሲያዞር ከታች ያሰፈሰፉት የስራ ዘርፋቸውን ለመቀየር ይገደዳሉ፡፡በተለይ አሁን ከመቸውም ጊዜ የውጭ ተጨዋቾች በብዛት ወደ ሀገራችን በመጉረፍ ክለብ እያጠያየቁ በመሆናቸው አጥለቅልቀውንየኛን ወጣቶች ቦታ እንዳያሳጡን ያሰጋል፡፡……….ባለፈው ግዜ ፌዴሬሽን በጠራው ውይይት የተነሳው አንዱ ጉዳይ የበረኞቻችን ብቃት ማነስ ነው ችግር ተብሎ የቀረበው፡፡ በክለቦች አብዛኛው የመሰለፍ እድል የሚያገኙት ከውጭ የመጡት በመሆኑ የኛዎቹ በረኞች የመሰለፍ እድሉን ስለማያገኘ ብቃታቸው ወርዷል ተባለ፡፡ እንደውም ክለቦች ከውጭ በረኛ እንዳያስመጡ የሚል መመሪያ ለማወጣት እየተዘጋጁ እንዳለ አውቃለሁ፡፡በርግጥ ይሄ ሲታይ እውነት ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን የኛዎቹ ቦታቸው በውጭ በረኞች በመያዙ አልነበረም ብሄራዊ ቡድን ችግር የተፈጠረው፡፡ እነዚህ የውጭ በረኞች በብዛት የመጡት ከስምንት አመት ወዲህ ነው፡፡ከዚያ በፊትም ቡድናችን ላይ በብዛት ግብ እየተቆጠረ የነበረና ችግር አለ ሲባል ነበር፡፡አሁንም በበረኞቻችም ላይ ያለው ችግር ከአጨዋወት ጋር የሚያያዝ እንጅ የውጭ በረኞች ቦታ ስለያዙ አይደለም፡፡እንደ አጠቃላይ ሲታይ የውጭ በረኛ አሰለፍንም አላሰለፍም ምንም ለውጥ አላመጣንም ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ቀዳሚ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ሆነ

አሁን መነጋገር ያለብን የውጭ ተጫዋች በሀገራቸን እግር ኳስ ምን ለውጥ አመጣ የሚለው ነው…….በመንግስት በጀት የሚንቀሳቀሱ ክለቦች አላማቸው ስፖርቱን መደገፍና ቅድሚያ መስጥ ያለበት ለሀገሩ ዜጋ ነው፡፡ መንግስት ለሀገሬው ሰው ነው የፈቀደው፡፡በሀገራችን ገንዘብ የውጭ ሰው ቀጥረን የስራ አድል ለእነርሱ መስጠቱ ምን ይባላል፡፡ክለቦቻችን በኢንተርናሽናል ውጤት ቢኖራቸው የሀገርን ስም ስለሚያስጠራ ከውጭ አምጥቶ ማጫወቱ አይከፋም፡፡ ምንም ለውጥ ለሌለው ለምን ከውጭ እናስመጣለን? ያውም በዶላር ለምከፍል (አንዳንዶቹ በእኛ ብር ቢከፈላቸውም ብዙዎቹ በዶላር ነው)አሁኑኑ ይሄ ነገር በውይይት አንድ እልባት ማግኘት አለበት፡፡ደግሞም እኮ ዝውውሩ የአንድ ወገን ነው፡፡እኛ ሀገር በተለያየ ጊዜ ከ30 አስከ 40 የሚሆኑ ናይጀሪያውያን መጥተዋል፡፡ ነገር ግን አንድም ኢትዮጵያዊ ናይጀሪያ ክለብ የመጫወት ቀርቶ የሙከራ እድልም አላገኘም፡፡እኛ በእርግጥም ስለማንመጥን ወይም ለእግር ኳስ አስፈላጊ በሚባሉት ነገር ከናይጀሪያውያን ስለማንሻል ከእኛ አልወሰዱም ፡፡ሆኖም እኛም ስናመጣ እዚህ ካሉት የተሻሉ ሊሆኑ ይገባል፡፡ግን እስካሁን ወሳኝ አይደሉም፡፡እናም አሁን ቆም ብለን እናስብና እንወስን፡፡ስላልጠቀሙን ገንዘብና ከእኛ ልጆች የተወሰደውን የመሰለፍ ቦታ እናስመልስ፡፡ካለበለዚያ በየክለቡ በርካታ የውጭ ተጫዋች ይሰለፍና የኢትዮጵያ ፕሪመር ሊግ ሳይሆን‹‹የአፍሪካ ፕሪመር ሊግ››ወደሚያስብል ስያሜ ሊወስድ ይችላል፡

1 Comment

  1. Hi Genene,

    Thanks for your reasonable explanation. .By the way , I would like to read the story of BOB visit in Ethiopia? Please , when you have got time try to upload the story on the same web-site

    Regards
    Elias k/mariam

Comments are closed.

Share