June 7, 2014
19 mins read

የጎዳና ተዳዳሪዎቹ ፍቅረኛሞች በአዲስ አበባ – [አሪፍ የፍቅር ታሪክ)

በአዜብ ታምሩ

ወጣቶች ናቸው፡፡ ዓለምፀሀይ ዘላለምና አበራ ተካ ይባላሉ፡፡ ኑሮን በጎዳና የሚገፉ፤ ተቃቅፈው ውለው ተቃቅፈው የሚያድሩ፤ ማንንም ለመስማት ጊዜ የሌላቸው፤ ከጥቂት ቡቱቶዎቻቸውና ከትንሿ ውሻቸው ውጪ ምሳ ካገኙ ስለራት የማያስቡ ከፍቅር ሌላ ምንም የሌላቸው ወጣቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ወጣቶች በአዲስ አበባ ከተማ መሀል አውቶቡስ ተራ አዲስ ከተማ መሰናዶ ት/ት ቤት ጀርባ ከሚገኘው መንደር የኢትዮጵያ ህፃናት መርጃ ድርጅትን አጥር ተገን አድርገው የሚኖሩ ፍቅረኛሞች ናቸው፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ነጋ ጠባ የሚገረሙባቸው፤ ቤት ውስጥ ያጡት አንዱ ላንዱ መስዋዕትነት የሚከፍልለት ፍቅር እዚህ መገኘቱ አጀብ የሚያሰኛቸው፡፡

በነዚህ ወጣቶች ፍቅር ከሚገረሙት ሰዎች መካከል አንዱ አቶ በላይ ይባላሉ፡፡ የኢትዮጵያ ህፃናት መርጃ ድርጅት የቴአትር ክፍል ሀላፊ የሆኑት እኒህ ሰው ናቸው ስለወጣቶቹ የነገሩኝ፡፡ ከእለት ጉርሳቸው ውጪ ሌላ የሌላቸውና ከማንም ምንም እንደማይፈልጉ የሚናገሩት ወጣቶቹ በቀላሉ ያዋሩኛል ብዬ
አልጠበኩም፡፡ እንዳሰብኩት ግን አልሆኑም፡፡ ከኔ ጋር ለማውራት ፍቃዳቸውን አልከለከሉኝም፡፡ ጥግ ይዘን ማውራት ጀመርን፡፡ እየሆነ ያለውን የሰሙ የአካባቢው ወጣቶች ተሰበሰቡ፡፡ ግርግሩን ፈራሁ፡፡ ወደ ድርጅቱ ግቢ ተያይዘን ገባን፡፡ የአካባቢው ልጆች ግን ‹‹ስለነሱ እኛን ጠይቂን፤ ነጋ ጠባ የምናያቸው የሚያስፈልጋቸውን የምናውቅ እኛ ነን›› አሉኝ፡፡ ያለ ምክንያት አይደለም እንዲህ ማለታቸው፤ እንደኔ ለአካባቢው እንግዳ የሆነ ሰው በመጣ ቁጥር ፍርሀታቸውን ያውቁታልና ሁሌም እንዲያ ይላሉ፡፡

“ፈራን መለያየት ፈራን” ይላል የሁለቱ ወጣቶች ልብ፡፡ የከበቡዋቸው የዚያ ሰፈር ልጆችም ‹‹እናንተን የሚለየው ሞት ብቻ ነው፡፡›› ይሏቸዋል፤ ግን ከዕለት ያለፈ ነገር ሊያደርጉላቸው አልቻሉም፡፡ እሱ ለሷ፤ እሷ ለሱ በሚሆኑት ነገር ተደንቀው የቀን ትዕይንት ካደረጓቸው ግን ከራረሙ፡፡ ዓለምፀሀይ ዘላለም ‹‹እድሜዬ 27 ነው›› አለችኝ፡፡ በደንብ ተመለከትኳት፤ ከዚህ አታልፍም፤ ጥቂት እውነት ብዙ መዘባረቅ የተቀላቀለበት ንግግሯ ከሚደጋገሙት መሀል እውነቶቹን እንድመርጥ አስገድዶኛል፡፡ በንግግሯ መሀል የእንግሊዝኛው ቃላት መደጋገም ሌላ ጥያቄ ያጭራል፡፡ አለምፀሀይ ጎበዝ ተማሪ ነበረች፤ ደብረ ማርቆስ ከተማ በሚገኘው ዋሸራ ብሮድቪው ኮሌጅ የሁለተኛ ዓመት የሴክሬተርያል ሳይንስ ተማሪ ሳለች የአእምሮ ህመም ስለገጠማት ትምህርቷን አቋርጣለች፡፡ (እሷ“ነቅዬ” ነው ትለኛለች ደጋግማ) አክስቶቿ ለማስታመም በሚል ወደ አዲስ አበባ ካመጧት በኋላ ረስተዋታል፡፡ ሄድ መለስ እያለች
ነገሮች እየተደበላለቁባት ስትነግረኝ አዲስ አበባ ከመጣች ሦስት ዓመት አልፏታል፡፡

ዝም ብለው ሲመለከቷት ከንግግር ቅልጥፍናዋና ጥንቅቅ ከማለቷ የአእምሮ ችግሯን ታስረሳለች፡፡ በቀላል ህክምና ለውጤት የምትበቃ ትመስላለች፡፡ ነገሩን የሚያውቅላት ይኑር አይኑር እንጃ እንጂ ብዙ ያነበበችም ለመሆኗ በንግግሯ የምታነሳሳቸው የዓለማችን ፀሀፍትና ፈላስፋዎች ምስክር ናቸው፡፡ እነሶቅራጥስ፣ አርስቶትልና ሌሎችም በአንደበቷ ሲጠቃቀሱ ይቺ ልጅ የሆነ ከአቅሟ በላይ የሆነባት፤ ሰው አልረዳ ያላት ነገር ቢኖርስ ብዬ ገመትኩ፡፡ ደግሞም ጠየኳት “በልጅነትሽ ምን መሆን ትፈልጊ ነበር?” ስል፡፡ ‹‹ሳይንቲስት መሆን፣ የፊዚክስ ሊቅ መሆን ፣ጠፈር ላይ መውጣት…” ለምጠይቃት
የምትሰጠኝ መልስ መጨረሻው ብቻ ነው ፈሩን የሚለቀው፡፡ በአብዛኛው በትክክል እየነገረችኝ ቆይታችን ቀጠለ፡፡

በወጣትነት እድሜ በተለይ በሃያዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የውስጥ ፍላጎቶቻችን የሚጋጩ ይመስለኛል፡፡ የሚያደምጥ የሚረዳ ሲጠፋ የሚፈልጉት ሳይገኝ ሲቀር ደግሞም የሚናገሩት ከማህበረሰቡ ለየት ሲል ‹‹ለየላት›› መባል ከዚያም ቤተሰብ መፍትሄ የሚለውን ሲያደርግ የአእምሮ ውጥረት ሲባባስ ጭንቀት ሲበረታ የባጥ የቆጡን መቀባጠሩ ቢያይል አይገርምም፡፡ በአለም ፀሀይ ህይወት ውስጥ ተመሳሳይ ነገር እንደተከሰተ ለመገመት አይከብድም፡፡ እሷንና ተወልጄ አድጌበታለሁ ያለችኝን ደብረ ማርቆስ ከተማ ቀበሌ ሰባት ሸዋ በር ተብሎ የሚጠራው ሰፈር ከፖሊስ ጣቢያው ወረድ ብሎ ያለውን መንደር አስተያየኋቸው፡፡ የእሷ ፍላጎት ከማህበረሰቡ አመለካከት ጋር ሲጋጭና የምታነሳቸው የተለዩ ሃሳቦች ‹አበደች. እያስባላት በድግግሞሹ ተገፍታ ለአዕምሮ ህመም እንደተዳረገች ያስታውቃል፡፡

አበራ አጠገባችን ተቀምጧል፡፡

የምናወራውን እየሰማ ነው፡፡ አንዳንዴ በወሬያችን መሃል ሳቅ ይላል፡፡ ቀይ ረዥም ቆንጆ ወጣት ነው፡፡ “አበራ ተካ እባላለሁ፡፡ ተወልጄ ያደኩት አዲስ አበባ መነን አካባቢ ነው፡፡ እድሜዬ አስርን ሳይዘል ከቤተሰቦቼ ጋር ጥሩ ኑሮ ስንኖር ከሌሎች ዘመዶቻችን ጋር ተቀላቅለን መኖር ጀመርን፤ ያኔ ወላጆቼ ለዘመዶቻችን ጥለውኝ ሲሄዱ እኔም ከቤት ወጣሁ፤ የጎዳና ተዳዳሪ ሆንኩ፡፡ ዛሬ እድሜዬ ሰላሳዎቹ መጀመሪያ ላይ ይገኛል፡፡ አብዛኛውን እድሜዬን ያሳለፍኩት ጎዳና ላይ ነው፡፡” እያለ ስለራሱ አጫወተኝ፡፡ በአዲስ አበባ የተለያዩ ሰፈሮች፣ በባህርዳር፣ ምዕራብ ሸዋ ጎዳናዎች ብዙ ክረምትና በጋዎች ዝናብና ፀሀዩ ተፈራርቆበታል፡፡ የሌት ቁሩ የቀን ወበቁ ገርፎታል፡፡ እናም ዛሬ ከተላመደው የጎዳና ህይወት ከመውጣት ሞት የሚሻል የሚመስለው አበራ ቀለል አድርጎ ‹‹ቀን ያገኘሁትን እሰራለሁ፤ ማታ ማታ እዚህ አድራለሁ›› በማለት የየዕለት ኑሮውን በአጭር ዓረፍተነገር ገለጸልኝ፡፡ በነአበራ ህይወት ውስጥ ማንም አብሮ ከሚኖረው የተለየ ብዙዎች ያጡትን የማፍቀርና የመፈቀር ህይወት በፍቅር ውስጥ ቢታመሙ አስታማሚ፣ ቢራቡም ቢጠግቡም የሚያወሩት የማያልቅ፣ ደስታ የማይለየው ለሌሎች ቦታ የሌለው መሆን ብዙዎች ያልታደሉት እንዲህ ባዶቤት እንዳንለው ጎዳናላይ ሲገኝ ለየት ያለ ስሜት መፍጠሩ አይቀርም፡፡ሁለቱ ወጣቶች ስለተገናኙበት አጋጣሚ አበራ ያስታውሳል፡፡ “ አውቶቡስ ተራ ጀርባ ሰላም ጂም አካባቢ ቁጭ ብዬ መጣችና አጠገቤ ቁጭ አለች፡፡ ከዚያ ካንተ ጋ መሆን እፈልጋለሁ፤ አለችኝ ተግባባን፤ አብረን መኖር ጀመርን” ይላል፡፡ እሷም “በቃ ስለወደድኩት አብረን መኖር ጀመርን” ትላለች፡፡ የዚያ መንደር ወጣቶችም “እዚህ አካባቢ የመጡ ሰሞን ማንም ትኩረት አይሰጣቸውም ነበር፤ እየቆየ ግን እንደሌሎቹ የጎዳና ልጆች አለመሆናቸውን ስናይ በነሱ ተሳብን” ይላሉ፡፡

እሱ ማንም እንዳይነካት ጠባቂዋ ነው፡፡ የመንፈስ ጭንቀቷ አይሎ መረበሽ ስትጀምር ወደ ደረቱ አስጠግቶ ወደ ራሷ ይመልሳታል፤ አብረው ያገኙትን ተቃምሰው ተቃቅፈው ውለው ያድራሉ፡፡ ‹አንድም ቀን ከዚህ የተለየ ነገር አላየንባቸውም› ሲሉ ይናገራሉ ነጋ ጠባ የሚያዩዋቸው፡፡ እሱም “ ታሳዝነኛለች፤ ታውቂያለሽ ይቺ ልጅ ትረበሻለች፡፡ እኔ ሳባብላት ነው ዝም የምትለው፡፡ ደግሞ እወዳታለሁ” ይላል፡፡ ይህንን የተመለከቱ እውነተኛ ፍቅር ማለት ይሄ ነው አሉኝ፡፡ ከነሱ ውጭ የሆኑ የትዳርና የፍቅር ሕይወቶችን እያነሳሱ፡፡

እንደ ምሳሌ ከጠቀሱልኝ መሀል የሰሞኑን ሰርጎች ከውጥን እስከመጨረሻቸው ለተመለከተ የትዳር መሰረት የሆነውን ፍቅራቸውንም ለመዘነ በየፍርድ ቤቱም ሳይጋቡ ተፋቱ አይነት የፍቺ ጥያቄዎችን መብዛት ላየ ደግሞም የፍቺ ጥያቄ የሚቀርብባቸው ምክንያቶች ግልፅ የማይሆኑና ስስ መሆናቸውን ለሰማ
የጋብቻ ትርጉም ቢደናገረው አይገርምም፡፡ ሲዘፈን እንደምንሰማው ተፅፎም እንደምናነበው የትዳር መሰረቱ ፍቅር ነው፡፡ ፍቅር ደግሞ ብዙውን ጊዜ ሳይታሰብ አንዳንዴም በመላመድ ይፈጠራል፡፡ የቱ ከልብ የሆነ የትኛው እውነተኛ ነው የሚለው በእያንዳንዱ ሰው ልብ የሚመዘን ነው፡፡ ፍቅር ሲታሰብ ምን አላት? ምን አለው? ከሚሉት ጀምሮ ከአቋም እስከ ዘሩ ከእውቀት እስከ አስተሳሰቡ ለክተው እስከሚጠብቁት ብዙዎችን አይተናል፡፡ ኑሮን ሀ ብለው ሲጀምሩም እንዲህ መሆኑን ባውቅ መች እገባበት ነበር? የሚሉት ብዙዎች ናችው፤ የሰው ባህሪ የጎደለውን መፈለግ ስለሆነ ሲይዙት ባዶ ቢመስል አይገርምም፡፡ ኑሮ ካሉት ሁለቱ ይስማሙ እንጂ የትም ቦታ በማንኛውም ሁኔታ ለመመስረቱ ብዙዎችን ስንሰማ ኖረናልና የእውነተኛ ፍቅር ምሳሌዎች ይኸው እነዚህ ተገኝተዋል፡፡ ለመገናኘትም አብሮ ለመኖርም ምክንያታቸው ፍቅራቸው ነውና ፡፡

“አንድ ቀን” አለኝ አብዲ የተባለ ወጣቶቹን የሚያውቅ የዚያ ሰፈር ወጣት፡፡ ‹‹ሀይለኛ ዝናብ እየዘነበ ወደቤት ለመግባት እየሮጥኩ ስመጣ እነሱ ግን ድንጋይ ላይ ተቃቅፈው ቁጭ ብለው ዝናቡ በላያቸው ላይ ይወርዳል፡፡ በጣም ደነገጥኩ፤ እነሱ ጋ የማይዘንብ ሁሉ መሰለኝ፡፡ ቀስ እያልኩ መራመድ ስጀምር ተመስጠው እያወሩ መሆናቸውን ልብ አልኩ፡፡ በፍቅራቸው እንደሁልጊዜው ቀናሁ፡፡ ፅናታቸውም አስገረመኝና ምነው በሞቁት ቤቶች መሀልም ይህን መሰሉ ፍቅር በሞላ አልኩ፡፡” ሌላዋ ወይዘሮ ደግሞ በትዳር መሀል ሳይቀር የሚያጋጠሙትን እያነሳን ሁሌም እንገረምባቸዋለን አለች፡፡ ”ዛሬ ማነው የአእምሮ ህመምተኛ የሆነችኝ ሴት እንዲህ በትዕግስት ተንከባክቦ ከችግር፣ ከረሀብና ከጥማት ጋር ድንጋይ ላይ ቁጭ ብሎ እየኖረ የሚያስታምም? ከሞቀ ቤታቸው እንኳ ብዙዎች የጎደለባቸውን ፍለጋ ሲሄዱ ነው የምናየው፡፡ እነዚህ ወጣቶች ግን ሲያማት እዚሁ እያስታመመ አብረው እየኖሩ ነው፡፡ነገረ ስራቸው ሁሉ እውነት ነው፡፡ እሱም መስራት የሚችል ቆንጆ ወጣት ነው፡፡ እሷም የተማረች ቀልጣፋ ወጣት ናት፡፡ ትንሽ ህክምናና ምክር ድጋፍ ቢያገኙ ተቆርቋሪ ሀላፊነት የሚሰማው ሰው ቢያግዛቸው በቀላሉ ራሳቸውን ችለው የሚያስመሰግኑ ወጣቶች ይሆኑ ነበር” አሉኝ፡፡

እነዚህ ወጣቶች በተለይ እሷ አዲስ አበባ ጉለሌ አካባቢ አክሰቶች እንዳሏት ትናገራለች፡፡ በየጊዜው መንገድ ላይ እንደምታገኛቸው ስትነግረኝ በአካባቢው ያሉ ወጣቶች ደግሞ በአንድ ወቅት ዘመዶችዋ መጥተው የተፈጠረውን አወጉኝ ፡፡ “አንድ ቀን ሁለት አክስቶችዋ መጡ፡፡ ከዚያ ልጃችንን ይዘን መሄድ እንፈልጋለን አሉ፡፡ እና ምን እናድርግላችሁ ስንላቸው ከሱ ነጥሉልን አሉን፤ መጀመሪያ ደብቆ ያመጣት መስሎን ውሰዷት ብለን ነበር፡፡ በፍፁም እሱንና ውሻዬን ትቼ አልሄድም፡፡ ስትል የሆነ ብር ወርውረውላት ሄዱ፡፡ ከዚያ በኋላ ለበዓል እንኳን መጥተው አላዩዋትም፡፡ ስለዚህ ቢወስዷትም የሱን ያህል ስለማያስታምሟት እሱ ይሻላታል›› ይላሉ፡፡

በነበረን ጥቂት ቆይታ ስለጎዳና ህይወት አስከፊነት አበክሬ ለመናገር ብሞክርም ሀሳቤ መፍትሄ መፈለግ መሆኑ ያልገባቸው ሁለቱ ወጣቶች በጥላቻ የተመለከቱኝ መሰለኝ፡፡ እሱን ወደ ስራ እሷን ወደ ህክምና የሚወስዳቸው ቢገኝ የሚለውን የልቤን ሀሳብ ካወቁ ቢታዘቡኝ አይገርምም፡፡ እነሱ የዘወትር ፍርሀታቸው መለያየት ነውና፡፡ እናም የዛሬው ፀሀይ የመጪው ክረምት ዝናብና ጎርፍ ቢያሰጋቸውም ይኸው አሉ፡፡ ለኛ ብዙ ነገር የጎደላቸው ቢመስለንም ፍቅር ህይወታቸውን ሙሉ አድርጎላቸዋል፡፡ የአብሮነት ኑሮአቸውን ይቀጥላሉ፤ መለያየትን ብቻ እንደፈሩ፡፡

(በአዲስ አበባ የሚታተመው ቁምነገር መጽሔት ላይ ታትሞ የወጣ)

Go toTop