Sport: አሁን ጊዜው የሲቲ ነው!

ጊዜው የሲቲ ነው!!

(ልዩ ትንታኔ)

ዕለቱ የፌሽታ ነው፡፡ ማንቸስተር ከተማ በዋንጫ አሸናፊነት ብዙ የዘፈነችው በዩናይትድ ድል አድራጊነት ነበር፡፡ ለዓመታት፡፡ የአቡ ዳቢዎቹ የአልናህያን ቤተሰቦች መጡና ትንሹን ሲቲ ግዙፍ አደረጉትት፡ ወደ 1 ቢሊዮን የሚጠጋ ፓውንድ ካፈሰሱ በኋላ የእሁድ ከሰዓት በኋላው አይነቱን የተደላደለና ለእነርሱ ያደላ ድል ተጎናፀፉ፡፡ ለሁለት አስርት ዓመታት የማንቸስተር ዩናይትድ ጥላ ሆኖ የነበረው ማንቸስተር ሲቲ የ2013/14 የውድድር ዘመን የእንግሊዝ ሻምፒዮን ሆነ፡፡

ሲቲ በ1960ዎቹ መጨረሻ ላይ የእንግሊሊ ሻምፒዮን ነበር፡፡ ከዚያ ወዲህ በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ አልፏል፡፡ እስከ ሶስተኛ ዲቪዚዮን ወርዶ ተጫውቷል፡፡ በዩናይትድ የስነ ልቦና የበላይነት የተጎዱት የሲቲ ደጋፊዎች ግን ሳያስቡት የነዳጅ ገንዘብ ከቤታቸው ደረሰና የኃያልነት ዘመን በድጋሚ ወደ መንደራቸው መጣ፡፡ በእርግጥ በ2011/12 ሲቲ የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን ሆኗል፡፡ ግን እንደዘንድሮው በግልፅ ጥንካሬና በተዋበ የጨዋታ እንቅስቃሴ አይደለም፡፡ የሮቤርቶ ማንቺኒ ቡድን እስከ መጨረሻው ጨዋታ የመጨረሻ ደቂቃዎች ተጠግቶ በምጥና በጩኸት ሻምፒዮን ሆኗል፡፡ የማኑኤል ፔሌግሪኒ ቡድን ግን የመከላከል ሚዛኑን ጠብቆ በተደራራ ማጥቃት ላይ በተመሰረተ የጨዋታ ስልት 102 ጎሎችን በማስቆጠር ሪከርድን ሁሉ ሰባብሯል፡፡ የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች አንገት ለአንገት የተያያዙበት የዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ ሰንጠረዥ ላይ የሲቲ ተፅዕኖ ያን ያህል የተጋነነ አልነበረም፡፡ በኖቬምበር 10 በስታዲየም ኦፍ ላይት በሰንደርላንድ ከተሸነፈ በኋላ 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀመጡ፡፡ በቀጣዩ ወር ዲሴምበር 28 ግን የሊጉ ሰንጠረዥ መሪ ሆኑ፡፡ ሊጉን ለረዥም ጊዜ የመራው አርሰናል ሲሆን ለ128 ቀናት በሰንጠረዡ አናት ላይ ቆይቷል፡፡ ቼልሲ በ64 እንዲሁም ሊቨርፑል ለ59 ቀናት በመሪነት ቆይተዋል፡፡ ሲቲ ከሂደቱ ይልቅ አጨራረሱ እንደሚጠቅም የተረዳ ይመስላል፡፡ በመሪነት ቆየ ቢባል ለ15 ቀናት ብቻ ነበር፡፡ የሲቲ ልጆች ፕሮፌሽናሊዝም፣ ትጋትና የማሸነፍ ስሜት በመጨረሻ እጅ የሚሰጡ አልሆኑም፡፡

ጥርሳጥርሱ ሁሉ በሚገባ ዘይት የጠጣው የማኑኤል ፔሌግሪኒ ማሽን በመጨረሻ የሚያቆመው አላገኘም፡፡ ከአምናው በ36 የበለጡ ጎሎችን አስቆጥሯል፡፡ በደጋፊዎቹ የክለቡ ታሪክ ምርጥ ቡድን መባሉ አስማምቷል፡፡ የኳስ ቁጥጥርን የበላይነት፣ በጎል ዕድሎች ፈጠራ እና በጎል ማግባት በማጀብ መጫወት መርሃቸው ያደረጉት የቺሊው አሰልጣኝ በአውሮፓ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ የሊግ ሻምፒዮን ሆነዋል፡፡

የዋንጫውን አሸናፊነት በሚያስረግጠው የዌስትሃም ጨዋታ ተአምር ተፈጥሮ መዶሻዎቹሲቲን ቀጥቅጠው በመጣል ሊቨርፑል የሊጉ ሻምፒዮን ይሆናል የሚል ምኞት የቀላቀለ ስሜት ነበር፡፡ የፔሌግሪኒ ልጆች ግን ገፍተው የመጡበትን የማሸነፍ ፍላጎትና ትጋት ደግመው አሳዩ፡፡ ጨዋታው እረፍት ሲሆን የዌስትሃም ተጨዋቾች በድምሩ የተቀባበሏቸው ኳሶች ብዛት 74 ብቻ ነበርር፡ ያያ ቱሬ ለብቻ ካቀበላቸው ኳሶች ጋር እኩል ነበር፡፡

ፔሌግሪኒ በማንቸስተር ሲቲ አምስት ዓመታት አምስት ዋንጫዎችን የማግኘት ዕቅድ አውጥተው ነበር፡፡ በመጀመሪያው የውድድር ዘመን የመጀመሪያውን አግኝተዋል፡፡ በስምንት ወራት የኃላፊነት ቆይታቸው ከወዲሁ ሁለቱን ዋንጫ አስገብተዋል፡፡

ዝምተኛው ሰው

ስታዲየም በደጋፊዎች ጩኸት ቢናወጥ፣ ተጨዋቾች በምንም አይነት ስሜት ቢጫወቱ የፔሌግሪኒን እርጋታ ሊነቀንቀው አይችልም፡፡ በእሁዱ ጨዋታ በኢቲሃድ ስታዲየም የፔሌግሪኒን የተረጋጋ ባህርይ የሚያወድሱ ጨርቆች በደጋፊዎች ይታዩ ነበር፡፡ ‹‹ዝምተኛው››፣ ‹‹ፈገግታ የማያጣው›› ወዘተ የሚሉ ፅሑፎች ተነበዋል፡፡ ፔሌግሪኒ እንደ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን አይቆጡም፡፡ እንደ ጆዜ ሞውሪንሆ የሌሎችን መብት የሚነኩ ቃላትን አይሰነዝሩም፣ እንደ አርሰን ቬንገር ለሽንፈት ሰበብ አይደረድሩም፡፡ በማንቸስተር ሲቲ የቡድን መንፈስና የእርስ በርስ መከባበርን በስብስቡ ውስጥ ፈጥረዋል፡፡ ፔሌግሪኒ ከተሾሙ ወዲህ ተጨዋቾች እርስ በርሳቸው የመጣላታቸውን ዜና አልሰማንም፡፡ ይልቁኑ በተጨዋቾች መካከል ፍቅርና መተሳሰርን አስፍነዋል፡፡ በሲቲ አዳዲስ ተጨዋቾች ሲመጡ የሚያላምዱ አምስት ተጨዋቾች አሉ፡፡ ‹‹የተጫዋቾች ተንከባካቢ›› የሚል ስያ የተሰተው ይኸው ቡድን የተጫዋቾችን ጉዳይ ይከታተላል፡፡ ተጨዋች ተመችቶትና የቤቱን ያህል ተላምዶ እንዲጫወት ይረዳሉ፡፡ ከፔሌግሪኒ መምጣት በኋላ ቀድሞ በካርሎስ ቴቬዝና ማሪዮ ባሎቴሊ ዙሪያ የሚነሱትን አይነት ውዝግቦች ተወግደዋል፡፡ በአሁኑ ሲቲ ውስጥ የኤላኖ እና ሮቢንሆ አይነት ‹‹ንዑስ ቡድን›› የለም፡፡ የባልካን ተወላጆቹ ኤዲን ዜኮ፣ አሌክሳንደር ኮላሮቭ እና ስቴፋን ዩቬቲች አብረው ይውላሉ፡፡ ነገር ግን ከሌሎች የቡድኑ አባላት ጋር ያላቸው መግባባትና ወዳጅነት እንከን አይወጣለትም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከውስጥ አዋቂ የተላከ - “የኮማንድ ፖስቱ የስራ ውጤቶች እየታየ ነው”

‹‹ፔሌግሪኒ ወደ ቡድናችን ሳቅና ደስታን አምጥተዋል›› ይላል የአጥቂ አማካዩ ዴቪድ ሲልቫ፡፡ ለቡድኑ ውጤታማነት የአሰልጣኙ አቀራረብ ዋና ምክንያት መሆኑን ሲልቫ አይጠራጠርም፡፡ ‹‹ክለባችንን የደስታ ቦታ አድርጎታል፡፡ በሜዳ ላይ እንኳን የጨዋታ ዘይቤያችን በማጥቃት ላይ ያተኮረና ብዙ ጎሎችን የሚያስቆጥር ነው፡፡ በየውድድሩ ቀንደኛ ተፎካካሪ አድርጎናል፡፡ ተጨማሪ ጉልበት ሰጥቶናል፡፡ ወደበለጠው ደረጃ አውጥቶናል›› ይላል፡፡

ሲልቫ የፔሌግሪኒ አብይ ጥንካሬ መረጋጋት መሆኑን ይመሰክራል፡፡ ማንቸስተር ሲቲ ከአሰልጣኙ እርጋታን ማግኘቱን ስፔናዊው ይሞግታል፡፡ ‹‹ኳስ እንድንቆጣጠር ይፈልጋል፣ የጎል ዕድሎችን እንድንፈጥርና በርካታ ጎሎችን እንድናገባ አድርጎናል›› ሲልቫ ተመስጋኝነቱን ለቺሊያዊው ይሰጣል፡፡ የ28 ዓመቱ ሲልቫ ‹‹በፔሌግሪኒ ስር በመስራቴ በግል በርካታ እመርታዎችን እንዳጎለብት ረድቶኛል›› ይላል፡፡

በተጠባባቂ ወንበር ላይ ሁለጊዜም በእርጋታ ተቀምጠው የምንመለከታቸው ፔሌግሪኒ በተጨዋችነት ህይወታቸው ‹‹ተናካሽ ውሻ›› እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ ተጨዋችነትና አሰልጣኝነት የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡ ቁንጥንጡን ሮቤርቶ ማንቺኒን ተክተው ፔሌግሪኒ ከመጡ በኋላ ነገር ሁሉ ሰላማዊ ሆኖላቸዋል፡፡ የ60 ዓመቱ አዛውንት በዩኒቨርሲዳድ ደ ቺሊ ክለብ ከተጫወቱባቸው ጊዜያት ይልቅ ብዙ ተቀይረዋል፡፡ ‹‹አሰልጣኝ ስትሆን መቀየር ያለበት የህይወትህን አካላት ትቀይራለህ›› ይላሉ ፔሌግሪኒ፡፡

በቪያሪያል፣ ሪያል ማድሪድና በማላጋ የሰሩት እና ‹‹ትልልቅ ቡድኖች በአንድ ዋንጫ ብቻ ተገድበው መቅረት የለባቸውም›› የሚሉት ፔሌግሪኒ ማንቸስተር ሲቲን የሚያክል ቡድን በአንድ ዋንጫ ይረካል የሚል እምነት የላቸውም፡፡ ‹‹እነዚህ ተጨዋቾች ከአንድ በላይ ዋንጫ ይገባቸዋል›› በማለት በተከታታይ ዓመታት ዋንጫዎችን ለማሸነፍና የማይገረሰስ ኃያል ቡድን የመስራት ዕቅዳቸውን ከእሁዱ ድል አድራጊነታቸው በኋላ ይፋ አድርገዋል፡፡ የፔሌግሪኒን ሃሳብ አምበሉ ቨንሳ ካምፓኒም ያስተጋባዋል፡፡ ‹‹ደጋግመን ዋንጫ የምናሸንፍ ቡድን አይደለንም፡፡ ትልቅ ክለብ መሆን ከፈለግክ ግን ይህ ሊሆን ግድ ይላል›› በማለት መጪዎቹም ዓመታት እንዲሁ በሊጉ ሻምፒዮንነት መቀጠል እንደሚገባቸው አስታውቋል፡፡

የማርች ወር ሲጀመር ማንቸስተር ሲቲ ካፒታ ዋን ካፕ አሸንፏል፡፡ ለአራት ዋንጫ ይወዳደር ነበር፡፡ ከዚያ በቻምፒዮንስ ሊጉ 16 ቡድኖች ዙር ላይ በባርሴሎና ተሸነፈ፡፡ በኤፍኤ ካፕ ሩብ ፍፃሜ ዊጋን ድል አድርጎ በመንገድ አስቀረው፡፡ ፔሌግሪኒ በአራቱ ዋንጫዎች የመወዳደርን ፈተና ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹ከየትኛውም የእንግሊዝ ክለብ ለበለጠ ጊዜ የተበራቱ ውድድሮች ላይ ቆይተናል፡፡ ከአራቱ ሁለቱን በማሸነፋችን ደስተኛ ነኝ›› ብለዋል፡፡

በእርግጥ ማንቸስተር ሲቲ ለዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊነት ከሚፎካከረው ሊቨርል በ14 ወይም በ15 ጨዋታዎች ይበልጣል፡፡ ሊቨርፑል በፕሪሚየር ሊጉ ብቻ እንደ ዘንድሮ የተወዳደረበት ሌላ ውድድር የለም፡፡

ለዘንድሮው ሲቲ ስኬት የያያ ቱሬ ሚና ሳይነሳ አያልፍም፡፡ ከአማካይ ክፍል ተነስቶ በዓመት 20 ጎሎችን ማስቆጠር ድንቅ ነው፡፡ ነገር ግን የጆ ሃርት ወደ ብቃቱ መመለስ፣ የኤዴን ዜኮ ጎሎችና የተከላካዩ ማርቲን ዴሚቼሊስ ድምር ውጤቶች ናቸው፡፡ የሲቲ ስኬት ከስብስቡ ጥልቀት ይጀምራል፡፡ ስለዚህ ፔሌግሪኒ በፈለጉት ዘዴ በማጥቃት ላይ የተመረኮዘ እግርኳስን መጫወት አስችሏቸዋል፡፡

የዴሚቼሊስ መመለስ

የውድድር ዘመኑ የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሳምንታት ለማንቸስተር ሲቲ ፈታኝ ነበሩ፡፡ ፔሌግሪኒ ወደማያውቁት ሀገር መጥተው በአዲሱ ሊግ ህይወት ምን እንደምትመስል በመለማመድ ላይ በነበሩበት በዚያ ሰዓት ቡናቸው ሲያጠቃ ድንቅ ነበር፡፡ የኋላ መስመሩ ግን ህፀፅ ነበረበት፡፡ የመጀመሪያዎቹን 12 (የሜዳና የውጭ) ጨዋታዎችን ብንመለከት ቡድኑ በወቅቱ የነበረበትን ሁኔታ የበለጠ ግልፅ ያደርግልናል፡፡ በኤቲሃድ ስታዲየም የኳስ ቁትጥሩን በበላይነት ይይዛሉ፡፡ በመጀመሪያዎቹ ስድስት የኤቲሃድ ጨዋታዎች 26 ጎሎችን አስቆጥረው ሁለት ብቻ ገባባቸው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የህወሓት የጦር ጄነራሎች የኮንትሮባንድ እቃዎችን በወታደራዊ መኪኖች ጭነው ይሸጡ እንደነበር ተገለፀ

ከሜዳቸው ውጭ ግን ተጋጣሚዎች ያጠቋቸዋልና ውጤቱ ተመሳሳይ ሊሆን አልቻለም፡፡ ከስድስት ጨዋታዎች አራቱን ተሸነፉ፡፡ ስምንት ጎሎችን ሲያስቆጥሩ 10 ተቆጠረባቸው፡፡ ከአስቶን ቪላ እና ቼልሲ ጋር ሲጫወቱ በተለይ የተጨዋቾች የግል ስህተት ዋጋ አስከፍሏቸዋል፡፡ በሴፕቴምበር ወር ዴሚቼሊስ በመፍትሄነት ቢቀርብም ሊሳካለት አልቻለም፡፡ የደጋፊዎችን ልብ ለማሸነፍም ጊዜ ወሰደበት፡፡

ፔሌግሪኒ ሰባት የተለያዩ የመሀል ተከላካይ ጥምረቶችን እያፈራረቁ ተጠቀሙ፡፡ የልብ የሚያደርስ አልተገኘም፡፡ ቨንሳ ኮምፓኒ ከጉዳቱ አገግሞ ሲመለስ ከዴሚቼሊስ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ አጣመሩት፡፡ ዕለቱ ዲሴምበር 4 ቀን ነበር፡፡ በ14ኛው ሳምንት ፕሪሚየር ሊግ ከዌስትብሮም ጋር ሲጫወቱ የመሀል ተከላካይ ጥምረት ብቅ አለ፡፡ ከዚያ በኋላ ሲቲ ተከላካይ መስመር መልክ ያዘ፡፡ ጠነከረ፡፡ በዘንድሮው ውድድር ዘመን ከቼልሲ በስተቀር እንደ ሲቲ ያነሰ ጎል የተቆጠረበት ቡድን የለም፡፡ በሊጉ ያነሱ የጎል ሙከራዎች የተመቱበት ቡድንም ማንቸስተር ሲቲ ነው፡፡ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ካምፓኒ እና ዴሚቼሊስ ተጣምረው ባደረጓቸው 20 የሊግ ግጥሚዎች መካከል ሲቲ የተሸነፈው በአንዱ (ከሊቨርፑል ጋር) ብቻ ነው፡፡

እንደዚም ሆኖ ዴሚቼሊስ የሚፈፅማቸው ጥፋቶች አልጠፉም፡፡ ከባርሴሎና ጋር ሲወቱ የተመለከተው ቀይ ካርድ ተጠቃሽ ምሳሌ ነው፡፡ ፈጣን ያለመሆኑ የተጋለጠበት አጋጣሚ ነበር፡፡ በፌብርዋሪ ከቼልሲ ጋር ሲጫወቱ ዴሚቼሊስን በአማካይነት መጠቀምም ስህተት እንደነበር ታይቷል፡፡ በትክክለኛ ቦታው ላይ ከሚያውቀው አጣማሪ ተጨዋች ጋር ሲሰለፍ ግን ጥሩ ተከላካይ ሊኖረው የሚገባ ብቃት ያሳያል፡፡ ከእንግሊዝ እግርኳስ ጋር ራሱን ምን ያህል ማመሳሰል እንደቻለ ማሳያ ጥሩ ምሳሌም አለ፡፡ በስምንቱ ወራት ያለ ኮምፓኒ የተጫወተው ማርች 15 ቀን ከሃል ሲቲ ጋር ቤልጂየማዊው በ10ኛው ደቂቃ ላይ ከቀይ ካርድ ከወጣ በኋላ ነበር፡፡ በዚያ ቀን ዴሚቼሊስ ድንቅ ነበር፡፡ ሲቲን ተከላካይ መስመር በአስገራሚ አመራር አዋህዷል፡፡ በመጨረሻም በ10 ተጨዋቾች 2-0 እንዲያሸንፉ ረድቷል፡፡ ወደ ኋላ መለስ ብለን ካየነው ያ ድል ወደ ዋንጫው ትልቁን እርምጃ ወደ ፊት ለመራመድ ያስቻለ ጨዋታ ነበር፡፡

የቁርጥ ቀኑ ዜኮ

ባለፉት ጥቂት ወራት የኤዲን ዜኮም ዕጣ እንዲህ ተቀይሯል፡፡ እንደ ሚቼሊስ ሁሉ በደጋፊዎች በትችት ከሚብጠለጠል ተጨዋችነት በዋንጫው ባለቤትነት ጉዞ ላይ ወሳኙን ስራ ወደ ፈፀመ ጀግናነት ተለውጧል፡፡ በውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ ሶስት ጨዋታዎች ከሰርጂዮ አጉዌሮ ጋር በፊት መስመር ተጣምሮ ነበር፡፡ ብዙ ሳይቆይ ግን ቦታውን ለአልቫሮ ኔግሬዶ ለቀቀ፡፡ ስፔናዊው ደግሞ ሳይውል ሳያድር ውጤታማነቱን ያሳይ ያዘ፡፡ ይህም ዜኮን የተጠባባቂ ወንበር ቁራኛ አደረገው፡፡

ሲቲ ቶተንሃምን 6-0 ባሸነፈበት የኖቬምበር 24ቱ ጨዋታ አጉዌሮና ኔግሬዶ የዓለም ምርጡ የአጥቂ ጥምረት ሆነው መወያያ ሆኑ፡፡ በዕለቱ ዜኮ ተጠባባቂ ሆኖ ዋለ፡፡ በሮቤርቶ ማንቺኒ ስር ከነበረበት ዘመን ይልቅ አሁን ቦታ የጠፋለት መሰለ፡፡ በማንቺኒ ስር ቦሲኒያዊው አጥቂ ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ መቀጠል ስለማይችል ተቀይሮ እየገባ ወሳኝ ጎሎችን ያስቆጥር ነበር፡፡ በዲሴምበር ወር መጨረሻ (ዘንድሮ) ከክሪስታል ፓላስ ጋር የማሸነፊያዋን ጎል አገባ፡፡ ከኦገስት መጨረሻ ወዲህ በ16 ጨዋታዎች ገና በቋሚነት የተጫወተበት አራተኛው ግጥሚያ መሆኑ ነበር፡፡ ጎሉም አራተኛዋ የሊጉ ጎል ነበረች፡፡

በ2014  ግን ታሪክ ሁሉ ተቀየረ፡፡ ከ19 የሊግ ጨዋታዎች መካከል በ16ቱ በቋሚነት ተጫወተባቸው፡፡ በዚህም 11 ጊዜ ኳስና መረብን አገናኘ፡፡ ዜኮ ለቡድኑ አስፈላጊ መሆኑን በተረዳ ቁጥር በራስ መተማመኑን የሚያዳብር አይነት ተጨዋች በመሆኑ ለውጡ አይገርምም፡፡ ለሲቲም በጣም አስፈላጊው አጥቂ ሆኗል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያውያንን በዘር ከፋፍለው የሚያፋጁንን ጎሰኞች በአንድነት ተነስተን “በቃችሁ” እንበላቸው!!! ከኢትዮጵያ አገር-አድን የቀውጢ-ጊዜ ግብረ-ኃይል የተሰጠ መግለጫ

ዜኮ እንደ አጉዌሮ አይነት ጨራሽ አጥቂ አይደለም፡፡ ወይም እንደ ኔግሬዶ ኳሱን በፊት መስመር ይዞ ሊቆይ የሚችል አይደለም፡፡ ሆኖም ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ የሚላኩትን የአየርና የመሬት ለመሬት ኳሶችን ሲያገኝ አይምርም፡፡ ከመረብ ጋር ያገናኛቸዋል፡፡ በተለይ ከፌብርዋሪ ወር ወዲህ ዜኮ ለሲቲ እጅግ አስፈላጊ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ አጉዌሮ በጉዳትት ኔግሮዶ ደግሞ በብቃት መውረድ ላይ ሳለ ዜኮ ዘጠኝ ጎሎችን አግብቷል፡፡ ዜኮ ከሶስተኛ ተመራጭ አጥቂነት ወደ ብቸኛ ቋሚ አጥቂነት መቀየር የቻለው ወሳኝ ጎሎችን በማስጠቆር ውጤታማ መሆኑን አስመስክሯል፡፡

ኤፕሪል በፓላስ፣ ኤቨርተንና አስቶንቪላ ላይ ያስቆጠራቸው ጎሎች ዋጋ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ በሜይ ወር ሲቲ ለፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫ የቅርብ ርቀት ላይ የተቀመጠው በዜኮ ቁልፍ ጎሎች ምክንያት መሆኑ አይካድም፡፡ በአስቶንቪላ ላይ የመክፈቻዋን ጎል ሲያስቆጥር በ2014 ለሲቲ ያስቆጠራት አምስተኛዋ የመክፈቻ ጎል ነበረች፡፡

ፔሌግሪኒ አሻሽለዋል

የውድድር ዘመኑ በገፋ ቁጥር ዴሚቼሊስ እና ኮምፓኒ ይበልጥ ተጣመሩ፡፡ ትውውቁ ውጤታማነታቸውን አጎለበተላቸው፡፡ በጠባብ የነጥብ ልዩነት ደረጃ ከፍ ዝቅ በሚልበት ሊግ ላይ ፔሌግሪኒ ከአስቸጋሪ ጨዋታ ላይ እንዴት ነጥብ ይዞ መውጣት እንደሚችል አውቀውበታል፡፡ አሰልጣኙ አብዛኛውን የውድድር ዘመኑን ጊዜ አራቱን ወሳኝ ተጨዋቾቻቸው (ቫንሳ ኮምፓኒ፣ ያያ ቱሬ፣ ዴቪድ ሲልቫ እና ሰርጂዮ አጉዌሮ) በጉዳት ምክንያት በአንድ ላይ ሊያጫውቷቸው ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ከ38ቱ ግጥሚያዎች እነዚህ የሲቲ ወሳኝ ተጨዋቾች በቋሚነት የተሰለፉት ለአምስት ጨዋታዎች ብቻ ነው፡፡ በስድስተኛው ጨዋታ ደግሞ ለጥቂት ደቂቃዎች ተሟልተው ተጫውተዋል፡፡ ከ3420 ደቂቃ ውስጥ አብረው የተለሰፉት በ285ቱ ብቻ ነው፡፡ ባለፈው እሁድ ከዌስትሃም ጋር አራቱም ተጨዋቾች ለ76 ደቂቃዎች አብረው ተጫውተዋል፡፡ ሳይነጣጠሉ ለረጅም ደቂቃ የተጫወቱበት አጋጣ መሆኑ ነው፡፡

የሃርት ነገር እንደህ ለማንቸስተር ሲቲ ውጤታማነት ሳይጠቀስ አያልፍም፡፡ ግብ ጠባቂው በውጣ ውረድ አልፎ በመጨረሻ ብቃቱን መልሶ አግኝቶታል፡፡ እነዚያ ተከታታይ ስህተቶቹ ወደ ተጠባባቂ ወንበር አውርደውት ነበር፡፡ ፔሌግሪኒ በኦክቶበር መጨረሻ ላይ ከጨዋታ ተገልሎ እንዲቆይ አደረጉት፡፡ ከገና በዓል ቀደም ብሎ ወደ ቋሚ ተሰላፊነት ከተመለሰ በኋላ ግን ወደ ምርጥ ብቃቱ መጥቷል፡፡ ሲቲ ከኤቨርተን ጋር ሲጫወት ሁለተኛው ግማሽ እንደተጀመረ በስቲቭን ኔይስማዝ የተመታችውን የጎል ሙከራ ያደነበት መንገድ ያስደንቃል፡፡ ኳሷ ከመረብ ተገናኝታ ቢሆን ኖሮ ጨዋታውን ብቻ ሳይሆን በውድድር ዘመኑም የሲቲ ዋንጫ ጉዞም በተበላሸ ነበር፡፡

በታክቲክ ረገድ ማኑኤወል ፔሌግሪኒ ተለዋዋጭ አይደሉም፡፡ እንደ አስፈላጊነቱ የመለዋወጥ ባህሪይም አይታይባቸውም፡፡ የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ ብሬንዳን ሮጀርስ እንደ አስፈላጊነቱ ሲስተማቸውን ይለዋውጣሉ፡፡ የተጋጣሚያቸው ሁኔታ አቀራረባቸውን ለመለወጣቸው አንድ ምክንያት ነው፡፡ ፔሌግሪኒ አመዛኙን የውድድር ዘመን በ4-2-3-1 ተጫውተዋል፡፡ በተለያዩ ጨዋታዎች የሚለዋውጡት የተጫዋቾቹ አይነት ብቻ ነው፡፡ በፈልባኮቻቸውም ማጥቃትን ይወዳሉ፡፡ ኮላሮቭ (ሰባት) እንዲሁም ዛባሌታ (ስድስት) ጎል የሆኑ ኳሶችን ያቀበሉበት ምክንያትም ይኀው ነው፡፡

ማንቸስተር ሲቲ ዘንድሮ በሁሉም ውድድሮች ከ150 ጎሎች በላይ ማስቆጠር የቻለ ብቻ ሳይሆን በአግባቡ የሚከላከል ቡድንም ነው፡፡ የማጥቃትና የመከላከሉ ሚዛን ደግሞ በመጨረሻ ለዋንጫው ባለቤትነት አድርሷቸዋል፡፡ ውጤት ብቻ ሳይበቃ የጨዋታቸው ውበትም ውሃ ሰማያዊዎቹ በመልካም እንዲታወሱ ይረዳቸዋል፡፡ አሁን ፔሌግሪኒ የሲቲን ‹‹ኢምፓየር›› መገንባት ይፈልጋሉ፡፡ ቡድኑ በ2011 12 ሻምፒዮን ሆኖ በተከታዩ ክረምት በአዳዲስ ተጨዋቾች በአግባቡ ሳይጠናከር የ2012 13 ዘመንን ዋንጫ ለማንቸስተር ዩናይትድ አስረክቧል፡፡ አሁን ግን ስህተቱን አይደግመውም፡፡ ይህ ቡድን ይበልጥ እንዲጠናከር የመሃል ተከላካይ፣ አማካይና ሌላ ፈጣሪ አማካይ ይፈልጋል፡፡ በክረምቱ ክለባቸው መገንባቱ እንደማይቀር ተማመኑ፡፡

 

Share