May 1, 2014
24 mins read

አንድነት ሕዝቡን ለመድረስ የዘዉግ ድርጅቶች የግድ አያስፈልጉትም (አሰፋ ቤርሳሞ)

አሰፋ  ቤርሳሞ

(abersamo@gmail.com)
በመድረክ እና በአንድነት መካከል ስላለው ግንኙነት ሁለት ኢትዮጵያዊያን የጻፉትን አነበብኩ። ዶር መሳይ ከበደ፣ መድረክ ዉስጥ ባሉ የዘዉግ ደርጅቶች እና በአንድነት ፓርቲ መካከል ያሉት የፖለቲካ ፕሮግራም ልዩነቶች የማይታረቁ መሆናቸውን  በመገልጽ፣  አንድነት ጊዜዉን እና ጉልበቱን እነዚህ የዘዉግ ድርጅቶችን በማባበል ላይ ከማጥፋት፣ ከሌሎች አገር አቀፍ ድርጅቶች ጋር አብሮ እንዲሰራና እንዲዋሃድ ይመክራሉ።

አቶ ዳዊት ተሾመ በበኩላቸው፣ ለዶር መሳይ መልስ ይሆን ዘንድ ባቀረቡት ጽሁፍ ፣ የዶር መሳይን አቋም በኢትዮጵያ ያለዉ ፖለቲካ ወደ ጫፍና ጫፋን እንዲሄድ የሚያደርግ የማክረር ፖለቲካ ነው ሲሉ ጠንካራ ትችት ያቀርባሉ። በመድረክ እና በአንድነት መካከል ለተፈጠረዉ ችግር በዋናነት የአገር አቀፍ ድርጅቶችን (እነ አንድነትን) ተጠያቂ ያደርጋሉ።

«The main causes of conflict between UDJ and other ethnic-based Medrek members parties emanate from endogenous (i.e. UDJ elites’ political calculus and the modus operandi of Mederk) and exogenous (i.e. Semayawi party’s, diasporas’ and All Ethiopian Unity Party (AEUP)’s pressure) factors which, for the last few years, cause either the centrifugal or centripetal political trends.» ሲሉ ነበር አቶ ዳዊት፣  አንድነት፣ ሰማያዊ ፣ መኢአድና ዳያስፖራው ላይ ያነጣጠሩት።

አቶ ዳዊት፣ በመድረክ እና በአንድነት መካከል የነበሩትንና ያሉትን መሰረታዊ ችግሮች የተረዱ  አልመሰለኝም። የሰማያዊ ፓርቲ በቅርብ የተመሰረተ ድርጅት ነው። በመድርክ እና በአንድነት መካከል የነበሩት ችግሮች ከዚያ በፊት በርካታ አመታት ያስቆጠሩ ናቸው። መኢአድን ከወሰድን ደግሞ ፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የአመራር አባላቱ ለአመታት እርስ በርስ ሲናጡ የነበሩበት ሁኔታ ነው የነበረዉ። ወደ ዳያስፖራዉ ከተመለስን፣  መድረክ በተለይም በዉጭ ባሉ የአንድነት ድጋፍ ድርጅቶች ዘንድ ትልቅ ድጋፍና ተቀባይነት እንደነበረው የሚታወቅ ነው። ዶር መሳይ ከበደም እራሳቸው፣ የመድረክን ራእይና አላማ ይደግፉ እንደነበረም አስቀምጠዋል። መድረክ በጣም ተቀባይነት ነበረዉ።

ስለዚህ በአንድነት እና በመድርክ መካከል ያለው ችግር፣ በመኢአድ፣ ሰማያዊ ወይም ዳያስፖራዉ፣ በአንድነት ላይ ጫና ስላደረጉ ነው የሚለው መከራከሪያ ትንሽ ዉሃ የሚቋጥር አይመስለኝ።

መድረክ እንደተመሰረተ፣ ከምርጫ 2002 በፊት እና ከዚያ በኋላ የአንድነት ፓርቲና አረና፣  መድረክ እንዲዋሃድ ገና ከጅምሩ ግፊት ያደርጉ እንደነበረ በስፋት ተዘግቧል። መድረክ መዋሃድ እንዳለበት፣ አቶ ዳዊት እንዳሉት፣ የአንድነት ፓርቲ ለፖለቲካ ስሌት ሲል አሁን የያዘው አቋም ሳይሆን፣ ከጅምሮ ሲስራበት የነበረ ጉዳይ ነው። መድረክ ወደ አንድነት እንዲመጣ ወደ አምስት አመት ገደማ ፣ ብዙ ዉይይቶች ተደርገዋል። ነገር ግን የአረና እና የአንድነት ጥያቄ በሌሎች ድርጅቶች ዉድቅ በመደረጉ መድረክ ሊዋሃድ አልቻለም።

ለዚህም ዋናዉ ምክንያት፣ ዶር መሳይ ከበደ እንዳሉት፣  የፖለቲካ ፕሮግራም ልዩነቶችን ማጣበብ ስላልተቻለ ነው። በእንጥልጥል የቆዮ፣ እንደ መሬት ፖሊሲና የፌደራል አወቃቀር ያሉ ጥቂት፣ ግን ቁልፍ የፖለቲክ ፕሮግራም ልዩነቶች ላይ  ስምምነት ሊደረስ አልተቻለም። የዘዉግ ድርጅቶች አሁን ያለው በቋንቋ ላይ የተመሰረተው፣ በኃይል በሕዝቡ ላይ የተጫነው ፌደራል አወቃቀር እንዲቀጥል ይፈልጋሉ። በመሬት ፖሊሲ ዙሪያ አሁን ካለው የመሬት ፖሊሲ የተለየ አቋም የላቸውም፡፡ ዶር መሳይ ከበደ እንዳሉት መድረክ ዉስጥ ያሉ አንዳንድ የዘዉግ ድርጅቶች ከአንድነት ይልቅ በፖለቲክ ፕሮግራሞቻቸው ከኢሕአዴግ ጋር ነው በጣም የሚቀራረቡት። ይሄ ከድሮም ይታወቃል። ነገር ግን አንድነትዮች ሰጥቶ በመቀበል መርህ መሃከል የሆነ ቦታ መድረስ ይቻል ይሆናል የሚል እምነት ስለነበራቸው ነው።

«መድረክ መዋሃድ ካልቻለ፣ ያሉ ልዩነቶችን ይዞ ለምን በግንባርነት አይቀጥልም ? » የሚል መከራከሪያ ሊነሳ ይችላል። የተከበሩ ዶር ነጋሶ ጊዳ መድረክ ዉህደት ሊፍጠር እንደማይችል፣ ነገር ግን ፓርቲዎች በግንባርነት፣  በመለስተኛ ፕሮግራም ዙሪያ፣ መስራቱ እንደሚያዋጣቸው በመግለጽ፣ መድረኩ ጠንካራ የተቃዋሚዎች ስብስብ እንዲሆን ጠይቀው ነበር።

እርግጥ ነው እንደ ግንባር ለመቀጥል ሙሉ ለሙሉ የፖለቲካ ፕሮግራም መጣጠም መኖር የለበትም። ፓርቲዎች ያሏቸውን ልዩነቶች ይዘው፣ በሚስማሙበት ጉዳይ ላይ ግንባር ፈጥረው፣  አብረዉ መንቀሳቀስ ይችላሉ። ታዲያ «የአንድነት ፓርቲ ለምን በመድረክ ዉስጥ፣  ተዋህዶ ካልሆነ በቀር፣ እንደ ግንባርነት መቀጠል አልፈለገም ? » የሚለው ተከታዩ ጥያቄ ነው የሚሆነው።

በዋናነት አንድነት በመድረክ ዉስጥ እንደ ግንባር አብሮ የመስራት ችግር ያጋጠመው፣ ብዙዎች የሚዘነጉት፣ ምናልባትም አቶ ዳዊት ልብ ያላሉት፣  መድረክ ዴሞክራሲያዊ የሆነ አሰራር ስላልነበረው ነው። በመድረክ ዉስጥ ያለው ቢሮክራሲ ብዙ ስራዎች እንዳይሰሩ ትልቅ ማነቆ ፈጥሯል። መድረክ ዉስጥ በጉልህ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች በዋናነት የአንድነት ፓርቲ እና አረና ናቸው። ሌሎች የመድረክ አባል ድርጅቶች ምን ያህል አባላት እንኳን እንዳላቸው አይታወቅም። አንዱ ድርጅት በዶር መራራ ጉዲና የሚመራዉ ኦፌኮ ነው። ሌላው ደግሞ በነ ዶር በየነ ጴጥሮስ የሚመራዉ ቡድን ነው። እነዚህ ሁለት ምሁራን ምን ያህል በድርጅታቸው ዉስጥ ዴሞክራሲያዊ  አሰራር እንደሚፈቅዱ ለማወቅ ትንሽ ያስቸግራል። ምን ያህል በድርጅታቸው ዉስጥ ተጠያቂ እንደሆኑ አይታወቅም። ነገር ግን በመድረክ ዉስጥ፣ በድርጅቶቻቸው ስም፣ እነዚህ ሁለት ግለሰቦች ካልተስማሙ ምንም የሚሆን ነገር እንደሌለ፣ በአጭሩ፣  ዶር በየነ እና ዶር መራር በመድረክ ዉስጥ ቪቶ ፓወር እንዳላቸውና የምንሰማው።

ይህን አይነቱ አሰራር እንዲለወጥ፣ መድረክ ሪፎርምድ እንዲሆን፣ በአንድነት በኩል ጥረቶች ሲደረጉ አመታት አስቆጠሩ። በተለይም በዶር ነጋሶ ጊዳዳ የሚመራዉ፣  በመድረክ የአንድነት ተወክዮች ቡድን፣ መድረክ ዉጤታማ ሆኖ እንዲወጣ ብዙ፣ እጅግ በጠም ብዙ ደክሟል። ነገር እንደታሰበውና እንደተደከመበት አልሆነም።

በመድረክ ዉስጥ ያለ መዝረክረክ እና ጸረ-ዲሞክራስያዊ አሰራር፣ በርካታ የአንድነት አመራር አባላትና ደጋፊዎች በመድረክ ላይ ጥያቄዎችን እንዲያስነሱ አደረጋቸው። የሚነሱ ጥያቄዎች ከግዜ ወደ ጊዜ ፣ ከአመት ወደ አመት እየጨመሩ ሲመጡ፣ የአንድነት ፓርቲ የበላይ አካል የሆነው ብሄራዊ ምክር ቤቱ፣ ለሕዝቡ፣ ለአባላትና ለደጋፊዎቹ ተጠያቂ በመሆኑና በአባላቱ ዘንድ የሚነሱ ጥያቄዎችን የማስተናገድ ግዴታ ስላለበት፣ በመድረክ ዙሪያ መከረ። አንድነት ከመድረክ ጋር ያለዉን ግንኙነት በተመለከተ፣ መረጃ ላይ ያተኮረ ጥናት ተደርጎ ሪፖርት እንዲቀርብለት ኮሚቴ አቋቋመ። ኮሚቴዉ በታዘዘው መሰረት ሪፖርቱን አቀረበ። ምክር ቤቱ በመድረክ ዙሪያ ማሻሻያዎችን እንዲደረጉና ፣ ያሉ  የፖለቲካ ልዩነቶችን ማጣበብ ተችሎ፣ መድረክ ወደ ዉህደት እንዲመጣ ግፊት እንዲደረግ ወሰነ።

መድረክ በአገራችን ለዉጥ እንዲመጣ ሊረዳ የሚችል አማራጭ መንገድ እንጂ፣ በራሱ ፍጻሜ አይደለም። መድረክ የታሰበለትን ግብ ማስፈጸም ካልቻለ፣ መድረክ እንዲሻሻል ግፊት ማድረጉ ተገቢ ነበር። የአንድነት ፓርቲም ያደረገው ይሄንኑ ነው። ይሄ ሊያስወቅሰው በጭራሽ አይገባም።

የመድረክ አባል ድርጅቶች በመድረክ የአሰራር ለዉጥ እንዳይመጣ በር ዘጉ። የአንድነት ፓርቲ በፊቱ የሚቀረው አማራጭ፣ ከመድረክ ዉጭ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ሆነ። የሚሊዮኖች ድምጽ በሚል መርህ በመላው ኢትዮጵያ መንቀሳቀስ ጀመረ። የመድረክ ሌሎች አባል ድርጅቶች ደስተኛ አልሆኑም። አንድነትን ለስድስት ወራት አገዱ።

የአንድነት ፓርቲ፣ የፖለቲካ ፕሮግራሞችን ማጣጣም እስከተቻለ ድረስ፣  አገር ዉስጥ ከሚንቀሳቀስ የዘዉግ ይሁን አገር አቀፍ ደርጅቶች ጋር መዋሃድ በአምስት አመት እቅዱ ካስቀመጣቸው ፖሊሲዎቹ  አንዱ ነው። ከአምስት አመታት በላይ ከመድረክ ጋር በዉህደት ዙሪያ ሲሰራ ነበር። ብርሃን ለፍትህና ለዲሞክራሲ ከተባለ ድርጅት ጋር ዉህደትን መስርቷል። ከመኢአድ እና ከአረና ጋርም ለመዋህድ እየተነጋገረ ነው። (መሰናክሎች በሂደት ቢያጋጥሙም) ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር የሚደረግ የዉህደት ዉይይት እንዳለ እስከአሁን አልሰማንም። ሰማያዊ ለብቻው መጓዝ የሚፈልግ ፓርቲ እንደሆነ ነው የነበረን መረጃ የሚያሳየው። ያ ተለዉጦ ንግግሮች ከተጀመሩ፣ እሰየው ነው የምንለው።

አቶ ዳዊት ለማንጸባረቅ እንደሞከሩት፣ አንድነት ከሰማያዊ ወይንም ከመኢአድ ጋር ለመዋህድ ሲል ፊቱን ከመድረክ አላዞረም። መድረክ ነው አንድነትን እየገፋ ያለው። የመድረክ ድርጅቶች ናቸው ኢሕአዴጋዊ የሆነ የፖለቲካ አቋማቸዉን ለማቻቻል ፍቃደኛ ያልሆኑትና መድረክ የተኛ ስብስብ እንዲሆን ያደረጉት።

አቶ ዳዊት «The greater danger lies for Ethiopian unity, as a State, is not from any secessionist movements/parties but from how pro-unitary parties handle the case and portray ethnic-based parties.» ሲሉ እንደ አንድነት ፓርቲ ያሉ አገር አቀፍ ድርጅቶች፣  በዘዉግ የተደራጁ ድርጅቶችን እንዲለማመጡ የሚፈልጉ ይመስለኛል።

አቶ ዳዊት ተሾመ አንድ የዘነጉት ጉዳይ ቢኖር፣ በአገራችን እየገዙ ያሉት የዘዉግ ድርጅቶች እንደሆኑ ነው። ፖለቲካ በማስፋራርት አይሆንም። ብዙ የዘር ድርቶችና አክራሪዎች «ይህ ከሆነ ጦርነት ይመጣል፣ አገር ትገነጠላለች …» እያሉ በባዶ ማስፈራራቱ አንዱ ትልቁ መሳሪያቸው ነው። ፖለቲካችን በመርህ ላይ መመስረት አለበት። በዘር ተደራጅተናል የሚሉ፣ ሕዝቡን በምንም መስፈርትና ሚዛን የማይወክሉ መሆናቸውንም መገንዘብ አለብን። የአንድነት ፓርቲ ሕዝቡ ጋር ለመድረስ የዘር ድርጅቶች አያስፈልጉትም። በስለጠነ መልኩ፣ የሕዝቦች መቀራረብና መተሳሰር ላይ በማተኮር፣ የኢትዮጵያዉያን መሰረታዊ የዴሞክራሲ፣ የመብት፣ የኢኮኖሚ ጥያቄዎች እንዲፈቱ ከታገለ ፣ ኦሮሞዉ ከኦሮሞ ድርጅቶች ይልቅ አንድነትን፣ በደቡብ ያሉ ብሄረሰቦችም ከደቡብ ድርጅቶ በላይ አንድነት የማይደግፉበት ምንም ምክንያት የለም።

ለዚህም ነው፣  ኦሮሞው፣ ትግሬው፣ ጋሞዉ፣ ሃመሩ …ቅልቅሉ ከአንድነት ኋላ ተሰልፎ በየክልሉ የመብትን ጥያቄ የሚያነሳዉ። የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት በሚለው ዘመቻ፣ የአንድነት ፓርቲ በደቡብ ክልል በጂንካ፣ በአርባ ምንጭ፣ በወላይታ ሶዶ ሰላማዊ ሰልፎች ያደረገ ሲሆን፣ በሁለተኛው ዙር ዘመቻ ደግሞ፣  እንቅስቃሴዎችን በአዋሳ፣ እንደገና በጂንካ፣ በቁጫ ይደረጋሉ። (5 ከተሞች በደቡብ ክልል) ። እንደ አንድነት፣  ሌላ በደቡብ ያለ የዘዉግ ድርጅት የሕዝብን ጥያቄ ያጎላ አለን?

በኦሮሚያ ክልል ደግሞ በፍቼ፣ በባሌ/ሮቢ፣ በአዳማ እንቅስቃሴዎች የተደረጉ ሲሆን፣ በቅርቡ ደግሞ እንደገና በአዳማ፣ በነቀምቴ በአምቦና  በለገጣፎ አንድነት ሕዝቡን ያንቀሳቅሳል ( 6 ከተሞች በኦሮሚያ) ። እስቲ ኦሮሞዉን እንወክላለን ብለው ከሚያወሩት ቁጥራቸው ከማይታወቅ የየኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ኦሮሚያ ዉስጥ እንደ አንድነት ፓርቲ የሚንቀሳቀስ አለን ? «ኦሮሚያ የኦሮሞዎች ናት፣ አዲስ አበባ ኦሮሚያን ወረረች፣ የአኖሌ ሃዉልት መሰራቱ አኮርቶናል . ወዘተረፈ » እያሉ ለሕዝብ የማይጠቅም፣ ሕዝብን  ከሕዝብ የሚለያይ ጠባብ ፖለቲካ ያራምዳሉ እንጂ ምን የፈየዱት ቁም ነገር አለ?

በአማራው ክልል በደሴ፣ በጎንደር፣ በባህር ዳር ሰልፎ የተደረጉ ሲሆን፣ በደብረ ታቦርና በድብረ ማርቆስም ይቀጥላል። (6 ከተሞች በአማራዉ ክልል) ከትላልቆቹ ክልሎች በተጨማሪ በአዲስ አበባ፣ በድረደዋ፣ በመቀሌ፣ በአዋሳ እንቅስቃሴዎች ይኖራሉ።በተለያዩ ብሄረሰቦች ዘንድ በመዝለቅ ልዩነትን ሳይሆን አንድነትን ፣ ጥላቻን ሳይሆን ፍቅርን አንድነቶች እየሰበኩ ናቸዉ።በዚሁ ይቀጥሉ ባይ ነኝ።

የመድረክ ራእይ ጥሩ ነበር። ግን አልሰራም። መድረክ ዉስጥ ገብተው ለመስራት ያኔ መሞከራቸው ስህተት አልነበረም። ስህተት የሚሆነው ግን መድረክ እንደማይሰራ ታውቆ፣ ከአሁን በኋላ በመድረክ ዉስጥ መቀጠል የሚፈልጉ ወይም የሚያቅማሙ ከሆነ ነው።  የዶር መሳይ ከበደን ሃሳብ በመጋራት አንድነት ከመድረክ ጋር ያለውን የቀረ ጣጣ አስወግዶ፣ ትኩረቱን ከሚሰሩ ድርጅቶች ጋር ማድረጉ ያዋጣዋል ባይ ነኝ።

ዶር መሳይ ምናልባትም አንድነት ከመኢአድ ፣ ከሰማያዊ ከመሳሰሉት ጋር እንዲዋሃድ ነው የሚፈልጉት። እኔም ያ ፍላጎት አለኝ። ነገር ግን ፕራክቲካል መሆን ሊያስፈልገን ይችላል። ሰማያዊ ፓርቲ ለብቻቸው መስራት የሚፈልጉ ናቸው። የትብብር ትቅም ያልገባቸው ገና በስሜት የሚጋልቡ።  እነርሱን ካልፈለጉ መለማመጥ ተገቢ አይመስለኝም። መኢአድ ዴሞክራቲክ ድርጅት ነው ብዬ አላስብም። የመኢአድ የበላይ ጠባቂ የሚባል አለ፣ አቶ ኃይሉ ሻዉል የሚመሩት። (በኢራን እንዳሉት አያቶላ ማለት ነው)። አሁን ያሉት የመኢአድ ሊቀመንበር፣ ይመስለኛል፣ ለአቶ ኃይሉ ሻዉል እንጂ ለመኢአድ ላእላይ ምክር ቤት ተጠያቂ አይደሉም። ያ ቢሆን ኖሮማ፣ የላእላይ ምክር ቤቱ ዉህደቱን ተስማምቶ ሊቀመነበሩ፣ በሁለት ቀኑ የተለያዩ ምክንያት እያቀረቡ፣  በአቋራጭ የምክር ቤቱ ዉሳኔን ባልቀለበሱ ነበር። ከዚያም በተጨማሪ መኢአድ በሕዝብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት እዛ ማዶ ታች ወርዷል። ስለዚህ መኢአድ ላይም ብዙ ጊዜ ማጥፋት አያስፈልግም። አባላት አመራር አባላቶቹን ተጠይቂ አድርገው ፣ የአባላት ፍላጎት ተግባራዊ ቢሆንም ፣ አንድነት እና መኢአድ ገና ድሮ ይዋህዱ ነበር።

አንድነት ትኩረቱን አረና ላይ ቢያደርግ በጣም ጥሩ ሊሆን ይችላል። አረናዎች የመዋሃድ ትልቅ ፍላጎት አላቸው። ለምን ዉህደትን ከልብ የሚፈልግ፣ እንደገና የሚታዩ ተጨባጭ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ካለ ድርጅት ጋር ዉህደት እንዲፈጠር ቅድሚያ አይሰጠዉም ? የአረና አባሎችን አንድነቶች በትግራይ እጅና ጓንት ሆነው ነው የሚሰሩት። ያሉ ወይንም ሊኖሩ የሚችሉ ልዩነቶችን በማጣበብ በቶሎ ቢዋሃዱ ጥሩ ነው።

በአረና አንዳንድ አመራሮች ዘንድ አሁንም በመድረክ ላይ ተስፋ የማድረግ ነገር ያለባቸው ይመስለኛል። አንድነት በመድረክ ዉስጥ እንዲቀጥል ዉስጥ ዉስጡን ለማግባባት ይሞክሩ ይሆናል። ነገር ግን ጥረታቸው ዉጤት ያስገኛል ብዬ አላምንም። በዚህ ረግድ አቋሞቻቸውን ግልጽ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ወይም በመድረክ ይቀጥሉ፤ አሊያም ከአንድነት ጋር ይዋሃዱ።

 

Go toTop