ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ወንጀሎችን ለፍርድ ባለማቅረብ ተወቀሰች

በኢትዮጵያ ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ወንጀሎች በተደጋጋሚ ሪፖርት ቢደረጉም፣ ነገር ግን ተመርምረው ለፍትሕ የቀረቡ አለመኖራቸው ትልቅ ጉድለት መሆኑ ተነገረ፡፡ ስዊዘርላንድ ጄኔቭ ለሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የፀረ ማሰቃየት ኮሚቴ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሪፖርቷን በማቅረብ የተገመገመችው ኢትዮጵያ፣ የሰብዓዊ መብት ወንጀሎችን መርምሮ በማቅረብ ደካማ ተብላ ተወቅሳለች፡፡

የሰብዓዊ መብት ምክር ቤቱ የፀረ ማሰቃየት ኮሚቴ አሥር ገለልተኛ አባላት ያሉትና የአባል አገሮችን የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ በተናጠል የሚገመግም መሆኑ ይታወቃል፡፡ እ.ኤ.አ. ከሚያዝያ 17 እስከ ግንቦት 12 ባሉት ቀናት የስድስት አገሮችን የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ እየገመገመ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም ተራዋ ደርሶ ረቡዕ ሚያዝያ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ተገምግማለች፡፡

በፍትሕ ሚኒስትር ደኤታው አቶ ዓለምአንተ አግደው ወንድሜነህ የተመራ 11 አባላት ያሉት የኢትዮጵያ ልዑካንም ኮሚቴው ፊት ቀርቦ የአገሪቱን የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሪፖርት አቅርቧል፡፡

ሪፖርቱን በጽሑፍ ያቀረቡት ሚኒስትር ደኤታው አቶ ዓለምአንተ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ከለውጡ በኋላ ስለመሻሻሉ በሰፊው ዘርዝረዋል፡፡

በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ እጅግ ብዙ ሪፎርሞች መካሄዳቸውን የተናገሩት አቶ ዓለምአንተ፣ በርካታ ሕጎችንና አዋጆችን ከማሻሻል ጀምሮ፣ በተቋም፣ በቴክኖሎጂ፣ በአደረጃጀትና በአሠራር የሚገለጽ በርካታ ለውጥ ስለመመዝገቡም አንስተዋል፡፡

ከለውጡ በኋላ ሚዲያዎች ማበባቸውን፣ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማኅበራት በነፃነት መንቀሳቀሳቸውን ትልቅ ስኬት ሲሉም ጠቅሰዋል፡፡

በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች አያያዝም ቢሆን መሻሻሉንና በእስር ቤቶች ይፈጸም የነበረው ማሰቃየት መቆሙንም የለውጡ አንዱ ትሩፋት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ መንግሥታቸው ‹‹ገና በሽግግር ላይ ያለና ሽግግሩም ሙሉ ለሙሉ በተሳካ ሁኔታ ያለ እንቅፋት እየሄደ አለመሆኑን›› አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ለውጡ ተቃውሞ፣ የሚዲያ ዘመቻና ማጥላላት ሲገጥመው መቆየቱን አስረድተዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  አሰቃቂ እና ዘግናኝ የድሮን ጥቃት ዛሬ በሰሜን ሸዋ ዞን ብዙ የነፍስ እልቂትን አሰከትሏል| ለደመቀ ዘውዱ ከባድ ማስጠንቀቂያ ከፋኖ ተሰጠ |

ሚኒስትር ደኤታው ከዚህ በተጨማሪም ‹‹ለ30 ዓመታት የአንድ ወገን የበላይነትን አፅንቶ የኖረው ኃይል በሕዝብ ግፊት ከሥልጣን ሲወርድ መቀበል ባለመፈለግ፣ ሥልጣን አስመልሳለሁ በሚል ምኞት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጦርነት አወጀ›› በማለት ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ያም ቢሆን ሰብዓዊ መብቱ የተከበረና ከማሰቃየት አያያዝ ነፃ የሆነ ኅብረተሰብ አገር ያበለፅጋል በሚል መርሕ፣ በሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ላይ ብዙ ማሻሻያዎችን መሥራቱን ተናግረዋል፡፡ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ያለገደብ የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ መፈጠሩንም አቶ ዓለምአንተ አንስተዋል፡፡

የሚኒስትር ደኤታውን ሪፖርት ሲያደምጥ የዋለው የሰብዓዊ መብት ምክር ቤቱ የፀረ ማሰቃየት ኮሚቴው በሰጠው ሐሳብ ግን፣ አገሪቱ በሰብዓዊ መብት አያያዝ የሚያኩራራ ደረጃ ላይ አለመድረሷንና ገና ብዙ እንደሚቀራት በጉልህ አንስቷል፡፡

ከሁሉ በላይ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ወንጀሎች ትኩረት ሰጥተው የታዩት አስተያየት የሰጡ የኮሚቴው አባላት በጦርነቱ የሞቱ ሰዎች ቁጥርን ኢትዮጵያ ይፋ እንድታደርግ ጠይቀዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ኮንቬንሽን በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆን ለመገዛት ቃል የገባች አገር ናት፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ያ ሁሉ የሰብዓዊ መብት ወንጀል ሲፈጸም ማስቆም ለምን አልቻለችም›› የሚል ጠንካራ ጥያቄም ቀርቧል፡፡

ተመድ የመደበውን ገለልተኛ የሰብዓዊ መብት አጣሪ ቡድን ሥራ በማደናቀፍም ኢትዮጵያ በኮሚቴው ተከሳለች፡፡ አገሪቱ የሰብዓዊ መብት ወንጀሎች ሪፖርት ቢቀርብባትም፣ ነገር ግን ክትትትል በማድረግ አጣርቶ ለፍትሕ በማቅረብ ላይ የረባ ሥራ አልሠራችም በሚል ተወቅሳለች፡፡

አንዳንድ የኮሚቴው አባላት በትግራይ የተፈጸሙ ያሏቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ከዘር ማፅዳትና ጭፍጨፋ ጋር አዛምደው ሲያነሱ ተደምጠዋል፡፡ ይሁን እንጂ በኦሮሚያ ወለጋ የተከሰቱ ግድያዎችን ጨምሮ በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ያጋጠሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎች በቂ ትኩረት ሳይሰጣቸው መታለፉ አነጋጋሪ እየተባለ ይገኛል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዋልያዎቹ ወደ ሀገር ቤት እየተመለሱ ነው

ዮናስ አማረ

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share