መንግስት ባለፈው ሳምንት ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ቦታዎች በሚንቀሳቀሰውና የተለያዩ ሽብር ተግባራትን በማከናወኑ በኢፌዴሪ ሕ/ተ/ም/ቤት አሸባሪ ተብሎ ከተፈረጀው መንግስት ኦነግ ሸኔ ብሎ ከሚለው እራሱን የኦሮም ነፃነት ሰራዊት ብሎ ከሚጠራው ታጣቂ ቡድን ጋር ችግሮችን በውይይት ለመፍታት በታንዛኒያ መቀመጡን አሳውቋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ጥቅምት 24 /2015 ዓ.ም. የፕሪቶሪያው ስምምነት ሊደረግ መሆኑን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ‹‹በሌሎች የሀገሪቷ ክፍሎች ያሉ የታጠቁ ኃይሎችም ጋር በሰላማዊ ንግግር መፍትሔ የሚያገኝበት መንገድ ላይ በአፅንኦት መስራት ያስፈልጋል›› ሲል ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡
አሁንም ሰላም የሰፈነባት እና ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን ለማየት ከፈለግን የትኛውም ዓይነት የሃሳብ ልዩነቶች ከአፈሙዝ ተላቀው ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ መቅረብ እንዳለባቸው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እናምናለን፡፡
በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል በተደጋጋሚ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ክቡር የሆነው ሕይወታቸውን ሲያጡ ንብረታቸውም ሲወድምና ከቀያቸው ሲፈናቀሉ በገሀድ ተመልክተናል፤ መንግስትም በተደጋጋሚ የተፈፀሙትን በደሎች ይህ ታጣቂ ቡድን ሲፈፅማቸው እንደነበር ከማሳወቁ አንፃር ይህን መሰል የዜጎች ሰቆቃ የሚያስቆም ድርድር ውስጥ መግባቱን የምናበረታታው ነው።
ገዢው ፓርቲ ብልጽግና ሀገራችንን መምራት የጀመረበትን ጊዜ ጨምሮ ባለፉት አምስት ዓመታት በተለያየ ጊዜ የሚፈጸሙ እንዲህ አይነት ድርድሮች ግልጽነት ሲጎድላቸው እና አፈፃፀማቸው በተገቢ ሁኔታ ሳይከናወን ቀርቶ ብዥታዎችን ሲፈጥር ተመልክተናል፡፡
በቅርብ ጊዜ እንኳ መንግስት ከሕወሓት ጋር ድርድር አድርጌ ሰላም አውርጃለሁ ባለበት የፕሪቶሪያው ስምምነት እንደ ስምምነቱ ያልተፈጸሙ ጉዳዮችን አስተውለናል፡፡ ሂደቱም ምን ላይ እንደሆነ አሁንም ድረስ በግልፅ አይታወቅም፡፡ በዚህ ምክንያትም ኢዜማን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ላይ አሁንም ድረስ ከፍተኛ ቅሬታን እያስነሳ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡
ስለሆነም መንግስት ከዚህ ቀደም በለውጡ ሰሞን ኦነግ ከኤርትራ ወደ ሀገር ቤት ከገባ በኋላ በስምምነቱ መሠረት አልተፈጸመልኝም ሲል አንደነበረው ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር በተለይም ከሕወሓት ጋር ከተደረገው ስምምነት ልምዶች መነሻ በማድረግ፣ የድርድሩን ሂደትና ስምምነቱን በተመለከተ ህዝቡ ሊኖረው የሚገባውን ግልፅ መረጃ ፤ እነማን እየተሳተፉ እንደሆነ፣ የስምምነቱን ይዘት፣ እንዴት እንደሚፈጸም እና በአፈፃፀሙም ጊዜ ተግባራዊነቱን ለዜጎች ተገቢና በቂ መረጃን በማስተላለፍ ከተጨማሪ ውዥንብርና ትርምስ ማኅበረሰቡን እንዲጠበቅ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡