የአድዋ ድል የጋራ ስኬታችን፤ የአንድነታችን ተምሳሌት ነው!

“ኢትዮጵያ ባለ ብዙ ባህል፣ ታሪክና ቅርስ ባለቤት ናት። ጥሩዎቹን እንንከባከባቸዋለን፤ መጥፎዎቹን እንማርባቸዋለን”  የኢዜማ ፕሮግራም

ኢትዮጵያ በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች የተጋረጡባትን ፈተናዎች አክሽፋ ህልውናዋን ያስጠበቀችው በልጆቿ ጠንካራ አንድነት ነው፡፡ በተለያየ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአራቱም አቅጣጫ በኢትዮጵያዊነቱ ተሰባስቦ የጋራ ቤቱ የሆነችውን ኢትዮጵያን ከህልውና አደጋ አትርፏል፡፡ የመጣውን ሀገራዊ አደጋ በአንድነት ኾኖ መክቷል፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ ህልውና በጋራ ጥረት እንጂ ለእኔና የእኔ ብቻ በሚል ከፋፋይ አስተሳሰብ እንደማይጠበቅ በተደጋጋሚ ትምህርት ሰጥቶ አልፏል፡፡

በተለይ ዛሬ የምናከብረውን የአድዋ ድል ዞር ብለን ስናይ በጉልህ የምናየው የአፄ ምኒልክ አመራር ጥበብን፣ የእትጌ ጣይቱ ወኔና አስተዋይነትን፣ የመሳፍንት እና መኳንንቱ ሀገርን ከምንም በፊት የማስቀደም መርህን፣ የመላው ህዝብ በኩራት በጋራ መቆምን እና ዛሬ በስም የማናውቃቸው አያሌ ጀግኖችን አኩሪ ተጋድሎ ነው፡፡

በአጠቃላይ በአልደፈርም ባይነት የተከፈለ መስዋትነትን፣ በሕብረት በመቆም የተከበረ ማንነትን፣ ልዩነትና አለመግባባትን ለሚገባው ቦታና ሰዓት አቆይቶ ከሀገር ሉዓላዊነት ጎን መቆምን፣ ከምንም በላይ ደግሞ የሰው ልጅ ሁሉ እኩል መሆንን በተጨባጭ ያሳየ አፍሪካን ያነቃቃ የቀደምት አባቶቻችን አኩሪ ገድል መኾኑን ነው፡፡

የድል በዓሉን ስናከብር ቀደምት አባቶቻችን የተዋደቁለትን ሀሳብ በሚገባ ልንገነዘበው ያስፈልጋል፡፡ አባቶቻችን መስዋዕትነት የከፈሉት ለኢትዮጵያዊነት፤ ለሀገራዊ አንድነት፤ ለጋራ ቤታችን ህልውና፤ ለክብርና ማንነታችን መጠበቅ፤ እንዲሁም ለነፃነታችን ነው፡፡ የአድዋ ድል ወራሾች መኾን የምንችለው የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት፤ ሉዓላዊነት፤ ክብር፤ ህልውና እና ነፃነት ማስጠበቅ ስንችል ብቻ ነው፡፡

የአድዋ ድል አንድምታ መንፈሳችንን ሊያነቃው፤ አንድነታችንን ሊያጠብቀው፤ ክብራችንንም ሊያስጠብቀው ይገባል፡፡ የአድዋ ድል የአንድ ቀን ክብረ በዓል ብቻ መኾኑ ቀርቶ፤ ድሉ ያጎነፀፈንን ትሩፋቶች በአግባቡ ልንጠብቃቸው ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነቱ ከተሸረሸረ፤ ነፃነቱ ከተገፈፈ፤ ዴሞክራሲ ከራበው፤ ልማት ከናፈቀው እና ሰላምና ደህንነቱ ካልተጠበቀለት የአድዋ ድል ትርጉም ያጣል፡፡ አያት ቅድመ አያቶቻችን አጥንታቸውን ከስክሰው ያስረከቡንን ሀገር አጥንት ቆጠራ ላይ መሠረት ባደረገ የዘውግ ፖለቲካ አንድነቷን እየሸረሸሩ የአድዋ ድልን በዓመት አንድ ጊዜ ማክበር ይህ የተከፈለውን መስዋዕትንት ገደል መክተት ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ደሴ የብሐራዊ መረጃዉ ሚስጥራዊ ስብሰባ ላይ ተኩስ ተከፈተ

ፓርቲያችን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የአድዋ ድል ያስገኘለትን ትሩፋቶች ይጠቀምባቸው ዘንድ የዜግነት ፖለቲካ፤ ማኅበራዊ ፍትህ እና ዴሞክራሲያዊ ፌደራሊዝም እውን መኾን እንዳለባቸው ያምናል፡፡ የዘር ፖለቲካ ባለበት፤ የሀብት ክፍፍል ሚዛን ባልተጠበቀበት እንዲሁም ሕዝብ በትክክል ዴሞክራሲን ተጎናፅፎ ራሱን በራሱ ማስተዳደር በማይችልበት ኹኔታ በአድዋ ድል የተገኘው ነፃነት፤ ክብር፤ ሉዓላዊነት እና አንድነት ለዛሬው ትውልድ የማይጨበጥ ተስፋ ኾኖ እንደሚቀር ማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

ዘላለማዊ ክብር ለአድዋ ጀግኖች!

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)

የካቲት 23፣2015 ዓ.ም

#የዜግነት_ፖለቲካ

#ማኅበራዊ_ፍትህ

#ኢዜማ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share