በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ምሁራን፣ የኢትዮጵያ የውይይትና መፍትሄ መድረክ (EDF) እና እምቢልታ ድርጅት በጋራ ያወጡት መግለጫ

የኢትዮጵያ፤የውዪዪትና፤መፍትሔ፤መድረክ
Ethiopian Dialogue Forum
9900 Greenbelt RD. E#343 – Lanham, MD 20706

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ የደረሰውን ፖለቲካዊ ጥቃት በጥብቅ እናወግዛለን!

ቀን ጥር 24፣2015 ዓመተ ምህረት

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፊደል ቀርጻ ያስተማረች፣ ዜጎች በበጎ ሥነ ምግባር ታንጸው እንዲያድጉ ብዙ የደከመች፣ የሃገር ልዕልና ሲነካ በግንባር ቀድማ ብዙ ዋጋ የከፈለች፣ በሃገረ መንግስት ግንባታው ላይ ደማቅ አሻራዋን የተወች፣ የኢትዮጵያ ባለውለታ የሃይማኖት ተቋም ከመሆኗም በላይ ዛሬ የሚሊዮኖች የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች መሰባሰቢያ ጥላ ናት።

ይህቺ ቤተክርስቲያን በተለይ በዚህ ክፉ ወቅት የሃገራችን ህዝብ ሳይከፋፈል አንድነቱንና ኢትዮጵያዊ ጨዋነቱን ጠብቆ የእርስበርስ መከባበርን ባህል አድርጎ እንዲኖር በየ እለቱ ደፋ ቀና የምትል ተቋም ናት። በዚህ ክፉ ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ ተቻችሎ የሚኖረው ከመንግስትና ከፖለቲካው አካባቢ ባለው ግፊት ሳይሆን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት መቻቻልን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን ከፍ አድርገው በማስተማራቸው ነው።

ይህቺ ቤተክርስቲያን በኢትዮጵያውያን የደስታ ጊዜም ሆነ የመከራ ጊዜ በሃገራችን ሕዝብ ዘንድ የማይዘነጋ በጎ ተግባር ከመፈጸሟም በላይ ከፍ ሲል እንደተገለጸው ሃገር በውጭ ወራሪ ሃይሎች ስትደፈር ሀገርህንና ነጻነትህን እንዲሁም ማንነትህን ጠብቅ፣ ለዚህም እግዚአብሔር ይርዳህ እያለች ስትቀሰቅስና ስታጀግን፣ በጾም በጸሎት አምላኳን ስትማጸን የቆየች ናት። በዚህም ምክንያት ትውልድ ሁሉ የማይረሳውን ውለታ የጣለች ቤተክርስቲያን ናት። የኢትዮጵያ ታሪክ ሲነሳ አስር ጊዜ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ስም እንዲነሳ የሚያደርገው በታሪካችን ውስጥ የዚህች ቤተክርስቲያን አስተዋጽዖ አያሌ በመሆኑ ነው። ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምእመናኖቿን ሁሉ በሰላም ጊዜ ልማት ላይ አንዲያተኩሩ፣ በወረራ ጊዜ ወታደር እንዲሆኑ፣ ዘወትር ሃይማኖታቸውን እንዲጠብቁ እየመከረች ልጆቿን ሁሉ አራሽ፣ቀዳሽ፣ተኳሽ እያደረገች ያሳደገች ግሩም እናት ናት እኮ ናት። የዛሬው ትውልድ ኢትዮጵያ ሃገሬ በቅኝ ግዛት ያልተገዛች ብቸኛ ሃገር ናት፣ የጀግና ህዝብ ልጅ ነኝ እንዲል፣ መላው አፍሪካውያንና ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የነጻነት ብርሃን እንዲያዩ በተሰራው ታሪክ ውስጥ ደማቁ ታሪክ የተጻፈው በዚህች ቤተክርስቲያን ቀጥተኛ ተሳትፎ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በአዲስ አበባ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ

ይሁን እንጂ ታዲያ በተለይ ባለፉት ሀምሳ አመታት ግድም በቅድሚያ በኢህአዴግ ሲቀጥል ደግሞ በኦህዴድ ብልጽግና መራሹ መንግስት አማካኝነት በሃገራችን ውስጥ በዘር በቋንቋ የከፋፈለ አደገኛ አገዛዝ ተዘርግቶ ሃገራችን በዚህ የከፋ አሳት ላይ ተጥዳ ባለችበት ወቅት እንደ ሃገር እንደ መልህቅ ሆኖ በዚህ ማእበል መሃል ያቆመን የሃይማኖት ተቋማት እሴቶቻችን በመሆናቸው የሃይማኖት ተቋማት ችግር ውስጥ ሲገቡ የሃገራችን መሰረት በከፍተኛ ሁኔታ መናጋቱ አይቀሬ ጉዳይ ነው።

እርግጥ ነው ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እንደ አንድ የሃይማኖት ተቋም በታሪካችን የገጠሟት አያሌ ፈተናዎች ነበሩ። ይሁን እንጂ የገጠሟትን ፈተናዎች ሁሉ እየበጣጠሰች ተሻግራ እዚህ ደርሳለች ፡፡ በአንድ በኩል የሃገርን ልዕልና ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት ግንባር ቀደም የነጻነት አርበኛ ሆና እንደኖረችው ሁሉ ሃይማኖቷን እና ትውፊቶቿን ሁሉ ከጥፋት የታደገች ቤተክርስቲያን ናት።

የሚያሳዝነው ነገር በዚህች ቤተ ክርስቲያን ላይ የተነሳው ክፉ ፍላጻ ዛሬም መልኩን ቀይሮ ይታያል። ምን አልባትም ይህቺ እናት ቤተ ክርስቲያን በዘመናት መካከል ከገጠሟት ፈተናዎች ሁሉ በላይ ዛሬ የከፋ አደጋ ገጥሟታል ብለን እናምናለን። በእኛ እምነት በመላው ሕዝባችን ትግልና በራሧ በቤተክርስቲያኒቱ አባላት ጠንካራ ትግልና ትምክህቷ በሆነው አምላኳ እርዳታ ይህንን ፈተና ትወጣለች ብለን እናምናለን። ይህንን ካልን በኋላ ግን የኢትዮጵያ መንግስት ይህቺን ህጋዊት ቤተክርስቲያን ሊበጠብጥ ብሎም የሀገራችንን ሰላም ሊያውክ የተነሳን ኃይል ሃይ ማለትና ጸጥታ ማስከበር ሃላፊነትና ግዴታ አለበት።

ማንም ሰው የፈለገውን ሃይማኖት መከተል መብቱ የተጠበቀ ነው። ይሁን እንጂ ሲኖዶስ ያወጣው ትእዛዝ በቤተክርስቲያኒቱ መዋቅሮች ውስጥ ስለሚሰራ ለዚህ አልታዘዝ ያለ ሰው የቤተክርስቲያኒቱን ሃብትም ሆነ የሃይማኖት ቦታዎች መጠቀም አይችልም። ምክንያቱም ስርዐተ ቤተክርስቲያንና ቀኖናው መከበር አለበትና።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአማራ ቅርስ ቦታዎችን ለድርድር ማቅርብ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስመልክቶ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ድርጅቶች የተሰጠ መግለጫ

ነገር ግን ከሰሞኑ የታዘብነው ነገር ከሲኖዶሱ እውቅና ውጭ የቤተክርስቲያኒቱን ንብረት ለመቀራመት የሚደረገው መሯሯጥና በተለይም የሃይማኖት አባቶችን ማዋከብና ማሰር ማንገላታት በቤተ ክርስቲያን ላይ ብቻ ሳይሆን በሃገሪቱ ሰላም ላይ የተቃጣ ህገ ወጥ የሆነ ድፍረት በጥብቅ እናወግዛለን።

በሌላ በኩል የቤተክርስቲያኒቱ አባላትና መሪዎች ችግሩን በሰከነ መንፈስ እያዩ ለመብታቸው በጥበብና በማስተዋል ታግለው ይህቺን የሃገር ባለውለታ ቤተክርስቲያን ከመከፋፈልና ከጥቃት እንዲታደጉ ጥሪ እናደርጋለን። ማናቸውም የሃይማኖት ተቋማትም ቢሆኑ ከሃይማኖታዊ ዶክትሪኖቻቸው ባሻገር እዚህች ቤተክርስቲያን ላይ የደረሰውን በደልና የገጠማትን ሲስተሚክ ፖለቲካዊ ጥቃት እንዲያወግዙ ጥሪ እናደርጋለን።

በመጨረሻም ሃገራቸን ውስጥ አንድ ጊዜ በብሔር፣ አንድ ጊዜ በነገድ፣ ሌላ ጊዜ በሃይማኖት፣ የሃገራችንን ህዝብ እያመሰ ያለው ከፋፋይ የሆነው የፖለቲካ አሰላለፍና ህገ መንግስት ለውጥና ለተሻለ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ኢትዮጵያውያን ሁሉ አምርራችሁ እንድትታገሉ እንጠይቃለን። ኢትዮጵያውያን ጌጣችን የሆነውን ህብረ ብሄራዊ ገጻችንን እየተንከባከብን የአብሮነት ባህላችን እንዳይሸረሸርና ጨርሶ እንዳይጠፋ ነቅተን

መጠበቅ ይኖርብናል። በሌላ በኩል ሀይማኖትን የፖለቲካ መጠቀሚያ በማድረግ መንግስት የሚጫወተውን እኩይ ሥራ በጥብቅ እያወገዝን ህበረተሰቡ የእምነት ቤቶቹንና ሃይማኖታዊ እሴቶቹን ነቅቶ እንዲጠብቅ ጥሪ እናደርጋለን።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚንስትሩ ለካቢኒያቸው የሰጡትን ማብራሪያ በጽሞና አዳምጠናል። በዚህ ንግግራቸው ላይ እንደወትሮው ሀገር አፍራሽና ነፃ ኀልውናን የሚፈታተኑ ቃላቶችን በመጠቀማቸው እጅግ አዝነናል። ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን እጅግ አሳንሰው ለዚህች ግዙፍ ቤተክርስቲያን ብጣቂ መሬት ሰጥተናታል እያሉ ሲመጻደቁ ማየት ብዙዎችን አስቆጥቷል። በመሰረቱ ኢትዮጵያ ሃገራችን ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ያገኘችው በረከት በእጅጉ ይልቃልና። ይህቺ ቤተክርስቲያን በልማት በኩል ያላት አስተዋጽዖ፣ በቱሪዝም የምታስገባው ገቢ እንደምን ሊዘነጋ ይችላል?። ያለ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ ተሳትፎ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባዶ ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሉዓላዊነትና እድገት ያደረገችው አስተዋጾ ጠቅላይ ሚንስትሩ በአደባባይ ካዱት እንጂ እጅግ እጅግ የላቀ ነው። ተሰጠ የሚባለው ቁራጭ መሬት ቀድሞውንም የቤተክርስቲያን የነበረ ይዞታ እንጂ የዚህ መንግስት መመጻደቂያ ችሮታ አይደለም። እንዲያውም ቤተክርስቲያኒቱ ገና ያልተከበረላት ይዞታ እንዳለ የአደባባይ ሚስጥር ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከአማራ ኢትዮዽያውያን ማህበር በስዊዘርላንድ የተሰጠ የአቋም መግለጫ

በሌላ በኩል እኚህ ሰው በሃገራችን ውስጥ የፖለቲካ ለውጥ እንዳይታሰብ በከፍተኛ ሁኔታ የሾሟቸውን ሚንስትሮች ሲያስፈራሩ፣ ሕዝብን ሊያሸማቅቁ ሲሞክሩ ተስተውለዋል። ምን አልባት የሾሟቸው ሚንስትሮች ለመብታቸው የማይታገሉ ከሆነ እነሱን ያስፈራሩ እንጂ የኢትዮጵያን ሕዝብ የመብት ጥያቄ ለማፈን የሚያደርጉት ማስፈራራት የሃላፊነት ጎደሎነትንና የትዕቢትን ጥግ ከማሳየት ያለፈ ፋይዳ

አይኖረውም። ስለሆነም የኢትዮጵያ ሕዝብ ከተቃጣብህ አንድነትህን፣ሰላምህን፣ ሃይማኖትህን ከሚያናጋ ሴራ ነቅተህ እንድትከላከል ከወዲሁ እናሳስባለን።

በመጨረሻም በሃገራችን ውስጥ በየጊዜው በምንሰማው እልቂትና መፈናቀል እጅግ ለተጎዱት ወገኖቻችን ሁሉ ቶሎ ማገገምን የሞቱትን ደግሞ እግዚአብሔር ነፍሳቸውን በአጸደ ገነት እንዲያኖርልን እንመኛለን።

ኢትዮጵያችን ለዘላለም ትኑር!

የኢትዮጵያ፤የውዪዪትና፤መፍትሔ፤መድረክ
Ethiopian Dialogue Forum

9900 Greenbelt RD. E#343 – Lanham, MD 20706

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share