የግጭትና የጦርነት ሁሉ መነሻ ስግብግብነትና እራስ ወዳድነት ነው! (አገሬ አዲስ )

ጥር 2 ቀን 2015 ዓም(10-01-2022)

  በዚህ እርእስ ላይ ለመጻፍ ያነሳሳኝ የዓለማችን በተለይም የአገራችን የኢትዮጵያ ህዝብ ለአለፉት አያሌ ዘመናት ለተከታታይ ጦርነቶችና እልቂቶች ብሎም ሰላም አልባ ኑሮ፣ፍርሃት፣ጭንቀት፣መፈናቀል በሽታና ድህነት የተጋለጠበትን ምክንያት ለማሰስ በተነሳሁበት ጊዜ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ስፈልግ እንደ ምሳሌና ማስረጃ አድርጌ  ከወሰድኳቸው መካከል በህጻናትና በዳክዬ ዙሪያ ያዬሁት እራስ ወዳድነት፣የእኔ ባይነትና አለመርካት ለጽሁፌ መንደርደሪያ ሆኗል።

ታሪኩ እንዲህ ነው

በአንድ ዓመት ዕድሜ ላይ ያሉ ሁለት መንታ ህጻናት በአንድ ምንጣፍ ላይ ተቀምጠው እንዲጫወቱ ተመሳሳይ መጫወቻ ተሰጥቷቸው ሳለ አንደኛው ህጻን የራሱን መጫወቻ  በአንድ እጁ ይዞ  የሌላውን የወንድሙን መጫወቻ  መንጠቁ ሳያንሰው መልስልኝ የሚለውን ወንድሙን  በያዘው መጫወቻ ፊቱን መደብደቡ በተጎዳው ህጻን ለቅሶና ጩኸት ቤቱ ቀውጢ ሲሆን ያዬሁት ግራሞት ወደ ሌላ ሃሳብ ወስዶኝ እንዳስብበት አድርጎኝ  የሰው ልጅ ስግብግብነቱን የጀመረው ገና ከህጻንነቱ ጀምሮ ነው ለሚለው ድምዳሜ አንድ ማስረጃ ሆኖኛል፣በእንስሳቱም  ዙሪያ በዳክዬ ቤተሰቦች ያዬሁት የዚሁ ተመሳሳይ ነው።ከቤቴ ጀርባ ባለው ሰፊ የቦይ ውሃ ውስጥ የሚንጎራደዱ ዳክዬዎችን ማዬት ከምዝናናባቸው አንዱ ሲሆን ማዬት ብቻም ሳይሆን ለዳክዬዎቹ የዳቦ ፍርፋሪ መበተን ደስታ ይሰጠኛል።ታዲያ በዚህ የጋራ መዝናኛ ውሃ ላይ ያዬሁት ነገር እንደ መንታ ወንድማማቾቹ የአንድ ዳክዬ ልጆች  እርስ በርሳቸው በተወረወረላቸው ፍርፋሪ ሲተናነቁ፣አንዱ ሌላውን ሲያባርር፣እናት ሳትቀር ልጆቿን እያባረረች ለራሷ ስትሰበስብ ስመለከት ስግብግብነትና እራስ ወዳድነት በሁሉም ፍጥረት ላይ ያለ ድክመትና በሽታ መሆኑን ለመቀበል ተገደድኩ።ይህንን እንደመነሻ አድርጌ  ከፍ ወዳለው የዓለማችን ቀውስና ግጭት ሳመራ ምክንያቱ ከዚያ ከህጻናቱና ከአእዋፋቱ ያልተለዬ እራስ ወዳድነትና ስግብግብነት የተነሳ የተፈጥሮ ድክመት መሆኑን እንድረዳ እረድቶኛል።በዚህ ብቻም አላቆምኩም በጥናት የተደገፈ ማብራሪያ  ቢኖር ብዬ መጽሃፍት ማገላበጥና በጎጉል በኩል ስስት ወይም ስግብግብነት ምንድን ነው? ከምንስ መጣ?፣በምንስ ይገለጻል የሚል ጥያቄ  አንስቼ ፍለጋዬን ቀጠልኩ።

በሁሉም በኩል የተሰጠው ትንተና ሲጨመቅ ያገኘሁት ገላጭ ሃረግ በእንግሊዝኛው እንዲህ ይላል። “Greed means always wanting more,and never being satisfied” በአማርኛችን ስስት ሁልጊዜ ብዙ መፈለግና ባለው አለመርካት ነው ብሎ ይገልጸዋል።ይህንን ይዤ ስጓዝ ጥልቀት ወዳለው ማብራሪያ ገባሁ።ሁሉንም በዚህ ጽሁፍ ላይ ማቅረብ ስለማይቻል፣እርዕሱም የስነአዕምሮና የህብረተሰብ ምሁራንን  ትኩረትና  ጥናት ስለሚሻ  በበኩሌ ቀንጨብ ያደረኳትን ግንዛቤ ከማዬውና ከማውቀው ጋር አጣምሬ ይህንን አጭር ጽሁፍ ለውይይት ይረዳ ዘንድ ለማቅረብ ወሰንኩ።በርእሱ ላይ ሌሎች በተሻለ መልክ ሃሳብ አላቀረቡበትም ማለቴ ሳይሆን እኔ የተረዳሁትን ያህል ለማካፈል ነው።ሁሉም በሚመስለው መንገድ በርዕሱ  ላይ ትኩረት  ሰጥቶ ሃሳቡን ቢሰነዝር ለተሻለና ለጠለቀ እውቀትና ግንዛቤ ፣ ጎጂ ጎድን ካለውም  ለማረምና ለማሶገድ ይረዳል እላለሁ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  መማር እንችላለን ወይ? -አንዱዓለም ተፈራ

ስስት ወይም ስግብግብነት እንዲሁም ለእኔ ብቻ የሚለው እራስ ወዳድነት በሰዎች ህሊና ውስጥ ተወልዶ የሚያድግ ፣ለሰላምና ለአንድነት ጸር የሆነ ገጸ ባህሪ ነው።በዚህ ገጸ ባህሪ ላይ የተመራመሩ ምሑራን ሁለት መልክ እንዳለው  ይገልጹታል።አልፈው ተርፈውም በሁለት በኩል ስለት ያለው ሰይፍ ነው ይሉታል።ያንንም ሲሉ ጠቃሚና ጎጂ ገጽ አለው ማለታቸው ነው።በመልካምና ጠቃሚ ጎኑ ሲታይ ለበጎ ሥራ፣ለሰው ልጆች የጋራ ጥቅም፣ፍቅር፣ መተሳሰብና አንድነት፣ለዓለም ሰላም እንዲሰፍን  በመሻት በቃኝ ሳይሉ፣ሳይደክሙና ሳይታክቱ የመፍትሔ ሃሳብ መሰብሰብና በዚያ መስክ መወዳደር አንዱ ሲሆን ሌላው የዚያ ተጻራሪ የሆነው ለግል ጥቅምና ደስታ ሲሉ ግለኝነትን የሚያጎላ፣እኔ ብቻ ይኑረኝ፣ያሻኝን ልዝረፍ፣በሌላው ጉዳትና ኪሳራ እኔ ልበልጽግ፣እኔ የሥልጣኑና የሃብቱ ብቸኛ ባለቤት ልሁን፣እኔ ልብላ፣ሌላው ግን ይራብ፣እኔ ልደግ ሌላው ይቀጭጭ—ወዘተ በሚል  ዓላማ የሚገለጽ እኩይ ባህሪ የሚንጸባረቅበት  ነው።የዚህ አስተሳሰብ በዓለም ላይ የተካሄዱትን ጦርነቶችና ወረራዎች አስተናግዷል።

በፈላስፋዎችና  በሃይማኖት መሪዎች ስግብግብነት ወይም አልጠግብ ባይነት ኢሞራላዊና ሰይጣናዊ መንፈስ ነው ሲሉ በዚያው መስክ የተሰማሩ ሌሎቹ ምሁራን የዚያ ተቃራኒ ሆነው የህብረተሰብ የእገት ደረጃ የሚያመጣው የሥልጣኔ  ተግዳሮት ስለሆነ መቀበል ይገባል ይላሉ።በዚህ ተቃራኒ ደግሞ ወል ስትሪት(wall Street)በተባለው የፊልም ትዋኔ ላይ ስስትና መሰብገብን የእድገትን መንፈስ የጠለፈ እኩይ ተግባር ነው ሲል ይገልጸዋል።ወል ስትሪት የዓለም የገንዘብና ንግድ ዝውውር መዲና ወይም መደብር መሆኑ ይታወቃል፤የገንዘብ ዝውውር ብቻም ሳይሆን ስግብግቦችና ዘራፊዎች የሚወዳደሩበት የንዋይ ጦር ሜዳ ነው።አንዱ ሲወጣ ሌላው እንዲወርድ የሚፈረድበት የደላሎች ፍርድ ቤት ነው።ያንንም ማእከል በማድረግ ነው ፊልሙ የተሰናዳውና የቀረበው።በከበርቴው ወጭና አገር የተዘጋጀ ፊልም ቢሆንም የብዙሃኑን ቀልብ የሚስብ በመሆኑ ከሚያስገባው ገቢ አንጻር ታይቶ እንጂ ሥርዓቱን ለማሶገድ ይረዳል ተብሎ እንዳልሆነ ይታወቃል።ስርዓቱን የሚያጋልጡና የሚቃወሙ ብዙ ፊልሞችና  መጽሃፎች፣የፖለቲካ ድርጅቶች እንደሚታገዱ አይካድም።የሚዲያ ጦርነት አንዱ የትግል ሜዳ ስለሆነ ምናልባትም ባለችው የዴሞክራሲ ጭላንጭል ተጠቅመው የብዙሃኑን ስሜት የሚያንጸባርቁ ሊኖሩ ይችላሉ።

የስስትና የስግብግብነት  አፈቀላጤ የሆኑ ምሑራን በበኩላቸው የአልጠግብ ባዮችን ፍትጊያ፣ ለዕድገት የሚረዳ ውድድር አድርገው ይቆጥሩታል።መወዳደር ሁለት ገጽ እንዳለው ይክዳሉ።በበጎ ሥራ፣ለሰው ልጆች በሚጠቅም መስክ  ላይ ተሰማርቶ  መወዳደርንና መታወቅን ከስግብግብነት ጋር ከሚደረገው ውድድር እኩል ያዩታል።

በሰው ልጆች ኪሳራና ጉዳት ለመጠቀምና ከፍ ብሎ ለመታዬት መሞከር ከሃጢያትም በላይ ሃጥያት ነው። በመናጢነት፣በጨካኝነት፣በሌብነት፣በስግብግብነት፣በዘረኝነት፣በገዳይና አስገዳይነት የአሳፋሪ ተግባር  ትልቅ ምሳሌ ሆኖ በከፍታ ላይ ጎልቶ መታዬት እንዳለ ሁሉ በመልካም ሥራም ከፍ ብሎ መታዬት ይኖራል።ይህ ማለት በሁለቱም አቅጣጫዎች ከፍታ ይኖራል ማለት ነው። ለዬትኛው ከፍታ መወዳደርና መብቃት እንዳለብን አውቀን መምረጡ የያንዳንዳችን ውሳኔ ነው።በውሳኔያችንም ደረጃ ይዋል ይደር እንጂ የምንቀበለው ዋጋ ሊኖር ስለሚችል ከአሁኑ  ማሰቡና ምርጫችንን ማስተካከል ይጠቅማል።ስህተትን አምኖ ና ታርሞ ለመመለስ  መንገዱ አልተዘጋም።ሌላው ቢቀር ከታሪክ ተወቃሽነት እራስን ማዳን ሌላው ከፍታ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አሎሎ ቢንከባልል ያው አሎሎ ፣የሚደፈጠጠው ግን ሳሩ! - አገሬ አዲስ

ብዙሃኑ የሚያስፈልጋቸውን ሳያገኙ ጥቂት ስግብግቦች ሁሉንም ነገር ተቆጣጥረው ፣ባላቸው ሳይረኩ ለተጨማሪ ሃብት፣ሥልጣንና ደረጃ ሲሻኮቱ ሌላውን ሕዝብና አገራቸውን በነሱ ጦስ ለተከፈተ ጦርነት በግዳጅ እዬማገዱ ሲያስጨርሱና ሲያወድሙ ብዙ ወንጀል ተፈጽሟል።በዓለም ላይ የተደረጉ ጦርነቶችና ግጭቶች ሁሉ በስግብግብና በራስ ወዳዶች የተነሳ ነው።ይህንን የስግብግቦች የጥቅም ግጭት መልኩንና ይዘቱን የጎሳና የሃይማኖት በማስመሰል ተራውን  ሕዝብ በማሳሳት ተከትሏቸው እርስ በርሱ እንዲጨራረስ አድርገዋል፤አሁንም በማድረግ ላይ ናቸው።የሱ ጎሳ የበላይና የተሻለ ወይም በሌላው ጎሳ የተበደለ አድርገው በማቅረብ በበላይነት ወይም በዝቅተኝነት መንፈስ እንዲነሳሳ አድርገው ያፋጁታል።ለዚያም ነው ከላይ በወል ስትሪት ፊልም ላይ ስግብግብነት የእድገትንና የአብሮነትን መንፈስ የጠለፈ ወይም የበከለ እኩይ ተግባር ነው የተባለው።በአገራችንም ላለፉት 49 ዓመታት በተለይም ላለፉት 32 ዓመታት የሰፈነው በመደብና በጎሳ ፖለቲካ አንዱን ከሌላው ጋር እያጋጨ በሥልጣን ላይ ለመቆዬት የቻለው።

ከጥንት ጀምሮ ይህንን ጸረ ሕዝብ፣ጸረ ሰላምና ጸረ ፍትሕ የሆነ የስግብግብነትና የስስት ምግባር ፈላስፋዎችና የሃይማኖት መሪዎች ሲታገሉት ኖረዋል።ነብያቶችን ያስነሳቸው ዋናው ምክንያትም በሰው ልጆች መካከል የሰፈነው አለእኩልነትና ኢፍትሐዊ ግንኙነት፣የስግብግቦች መኖርና ያረመኔዎች በሥልጣን ላይ መቀመጥን ለማውገዝና ለማጋለጥ ነበር።እዬሱስ ክርስቶስም ሆነ ነብዩ ሞሃመድ የተነሱበት ዘመን የሰው ልጅ በባርነት ቀንበር ስር ወድቆ እንደ እቃ በሚሸጥ በሚለወጥበት፣ከአራዊት ጋር ታግሎ ደሙ ሲፈስ ማዬት እርካታ የሚሰጣቸው ጨካኝ ቄሳራውያንና መሰሎቻቸው መዳፍ ስር ዓለም በወደቀችበት ወቅት ነበር።ትግልና አስተምሯቸው ያንን አስከፊ ስርዓት በመቃወምና በማጋለጥ ሁሉም የሰው ልጅ በአንድ አምላክ የተፈጠረ እኩል የሆነ ፍጡር መሆኑን የሚያረጋግጥ  ነበር።ክርስቶስና  ተከታዮቹ፣ለነብዩ ሞሃመድና ለተከታዮቹም  ከስግብግብ አረማውያን የተሰጣቸው ምላሽ መሰደድ፣ መታሰርና መገደል ብቻ ነበር፣ያ ግን ለሥርዓቱ ባለቤቶች የመጥፊያ መንገድ ሆነ እንጂ አልጠቀማቸውም።ከአረማውያኑ ጎን የተሰለፉም ያይሁድ እምነት መሪዎች ነበሩ።ከዚያም ወዲህ ለመጡ ለሄዱ ጨካኝ መንግሥታት ያገለገሉና የቆሙ ዬዬሃይማኖቱ አባቶችና ምሑራን ነበሩ፤አሁንም አሉ።እስከ ዛሬ ድረስ ለእውነት የቆሙና መከራ የተቀበሉ የእምነት አባቶችና ምሑራኖች ነበሩ አሁንም አሉ።የነሱን አስተምሮ በመበከልና የተሳሳተ ትርጉም ሰጥተው የሚያሳስቱ ነበሩ አሁንም አሉ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አሜሪካንን ጠላሁዋት + አሜሪካንን ወደድኩዋት = _

ከጥንታዊት ግሪክ ስልጣኔ ጀምሮ እስከ መካከለኛው ክፍለዘመን፣ከዚያም የስግብግቦች በስርዓት  እስካደገበት የከበርቴ ሥርዓት የ16ኛው ክፍለዘመን ድረስ ብዙ ፈላስፋዎች ተነስተዋል፣የዓለምን መልክና መፍትሔም በማቅረብ የሰውንም ግንዛቤ ለማሳደግ ጥረዋል።አዲስ ግኝቶችን ፈልስፈው አበርክተዋል።ያ የነሱ መልካም አስተዋጽኦ ለስግብግቦቹ ግብአት ቢሆንም ህብረተሰብ በጥቂቱም ቢሆን ተጠቃሚ ሆኗል። በማህበረሰብ ግንኙነትና፣በኤኮኖሚ ዙሪያም ያለውን ኢፍትሃዊነት እያነሱ ያጋለጡና የተሟገቱ ብዙዎች ናቸው።የነሱን የፍልስፍና ትንታኔ የሥልጣን መወጣጫ አድርገው በተሳሳተ መንገድ ተርጉመው ዓለምን ለበለጠ ቀውስና የሰው ልጆችን ለከፋ እልቂት፣የአንድ አገር ዜጎችን ለእርስ በርስ  ጦርነት የዳረጉ አሁን በዘመናችን ጎልተው ይታያሉ።ከስግብግብነት ጋር የተቆራኘውን ፣በጦር ሃይል የታገዘ የዘረፋ ውድድር ለመልካም ነገር ከሚደረግ ውድድር ጋር የሚያመሳስሉ ምሑራን አልጠፉም።ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም የሚደረግ ትግል በማስመሰል የራሳቸውን ጥቅምና ሥልጣን ለማስከበር ጠንክረው ይሠራሉ።

ለማህበረሰብአዊ ፍትህ ሲሉ ብዙ መከራ የተቀበሉ ምሑራንና የሃይማኖት መሪዎች እንደነበሩ፣አሁንም እንዳሉ አይካድም።የነሱ ህብረተሰብአዊ ፍትህ ተጠልፎ ለገዢዎች መሳሪያ እንዲሆን ከተደረገ ዓመታት አልፈዋል።በአገራችንም ፍትህ መጫወቻ ከሆነ ውሎ አድሯል።

ወደ ተነሳሁበት እርእስ ስመለስ  ስስትና ስግብግብነት የግል ቁሳቁስ፣ንብረትና ገንዘብ በማካበቱ ዙሪያ ብቻ ተወስኖ አይቀርም።በእምነት ፣በጎሳ ማንነት፣በሰፈርና መንደር ደረጃ ወርዶ ሌላውን ማጥቃትና ማግለል የስስትና የስግብግብነት መገለጫዎች ናቸው። ምሑራን ስለስግብግብነት ሲገልጹ ሌላውን የማጥመድና የመበከል አዝማሚያ ተጠቅሞ ብዙሃኑን የማስከዳት ስልት ነው ይላሉ። ዘርዘር አድርገውም ስግብግብነት ከጥቅማ ጥቅም ጋር የተሳሰረ ስለሆነ የሚታለሉትን ጥቂቶቹን አታሎ በብዙሃኑ ላይ እንዲዘምቱ ወይም ለስግብግብ ስርዓቱ መከለያ (ካባ)  እንዲሆኑ ማድረግ ነው ይላሉ።ይህንን ሁኔታ በአገራችን በኢትዮጵያ በገሃድ እያዬን ነው።አንዱን በመጥቀም ሌላውን በመጉዳት፣ለአንዱ ሰጥቶ ሌላውን በመንሳት ጎረቤት ከጎረቤቱ፣ዘመድ ከዘመዱ ተራርቆ በጠላትነት  ለመጋደል ሲወጣ የዓይን ምስክሮች ሆነናል።በዚህ ከይሲ ምግባር ላይ በጥቅም የተገዙ የኪነት ሰዎች፣ምሑራን፣ነጋዴዎች፣የእምነት አባቶች ሳይቀሩ የጥፋት ሠራዊት ሆነዋል።ካለው የጥፋት አገዛዝ ጋር ተሰልፈዋል።በንጹሃን እልቂት ላይ ፈርደዋል።በጣሊያን ወረራ ጊዜ ለቪክቶር አማኑኤልና ለግራዚያኒ አገዛዝ የጸለዩና የባረኩ ጳጳሳት ነበሩ፤ከዚያም ወዲህ በአገራችን እስከአሁን ድረስ ለሰፈኑት ጨካኝ አገዛዞች ዕድሜ የለመኑ ቡራኬና ምርቃን የሰጡ ነበሩ፤ አሁንም አሉ።ንጹሃን ሲታረዱ ድምጻቸውን ያጠፉ ነበሩ፤አሁንም አሉ።ይህ ሁሉ ጭካኔና ክህደት በምድራዊ ህይወታቸው የስግብግብነትና የይኑረኝ ልክፍት በመበከላቸው ነው።ከዚህ እኩይ ምግባር የጸዱ ነበሩ፤አሁንም አሉ።ስማቸው በምድርም በሰማይም የተባረከ ይሁን!

ትግሉ የሁለት ዓለም ትግል ነው።የስግብግቦችና ስግብግብነትን በሚጠዬፉ ፣በፍትሃዊና ኢፍትሃዊ  በሆኑ መካከል የሚደረግ ትግል ነው።ድሉ ስግብግብነትን ለሚጠዬፉትና ለማህበራዊ ፍትህ ለቆሙት እንደሚሆን አያጠራጥርም።

ስግብግብነትና እራስ ወዳድነት ይወገድ!ኢትዮጵያዊነታችን ይመለስ፤ ሰውነታችን  ይታደስ!!

አገሬ አዲስ

2 Comments

  1. ሀገሬ አድስ
    እዉነት ላይ የተመሠረተ ነዉ ሰሚ ከተገኘ ትዝብት ለምን ቆመ ?

  2. ጎበዝ የኢትዮጵያን የመከላከያ ሃይል አርደው ትግሬዎች ነጻ ሲወጡ አቶ ታዲዮስ ታንቱ በዚህ እድሜያቸው በእስር ሲጉላሉ ዜጋ ለምን ዝም ብሎ ያያል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share