አዲሱን አመት ከወለጋ ተፈናቃዮች ጋር – ገለታው ዘለቀ (ደብረ ብርሃን_ኢትዮጵያ)

ከአሜሪካን ሃገር ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ልቤ ሲያቀና ከገዛ ሃገራቸው የተፈናቀሉ ተፈናቃዮችን አይናቸውን ማየትና መጎብኘት እንደ ኢትዮጵያዊ ወግና ልማድ መጠየቅ ዋና እቅዴ ሆኖ ነበር የሰነበተው። እነሆ ዛሬ እግዚአብሔር ፈቃዱ ሆነና  ይሄውና በዚህ በአዲሱ አመት እንቁጣጣሽ ቀን እነዚህን ወገኖቼን ለመጎብኘት በቃሁ።
በመጀመሪያ ወደ መጠለያ ጣቢያው ሳቀና መታጠፊያዋ ላይ አንዲት በኢትዮጵያ ባንዲራ ያሸበረቀች ጊዚያዊ ቤተክርስቲያን አየሁ። ፀሎት አጠናቀው የሚሰናበቱ ሰዎች አያለሁ። እነዚህ ሰዎች የወለጋ ተፈናቃዮች መሆናቸውን ለማወቅ ጊዜ አልወሰደብኝም ነበር። ፈጠን እያልኩ ወደ ዋናው መጠለያ አቀናሁ። እዚህም እዚያም የ UNHCR ድንኳኖችን አያለሁ። ከድንኳኖቹ አካባቢ ተፈናቃዮቹ በቡድን ሆነው ስብሰባ ሲያደርጉ አያለሁ። ወዲያና ወዲህ እያማተርኩ ሳለ ከስብሰባው ወጣ ፈንጠር ብለው ከቆሙት ጋር እነሆ ሰላምታ መለዋወጥ ጀመርኩ…. ከነዚህ  ከወለጋ ተፈናቃይ አማሮች ጋር….
እንዴት ናችሁ? መልካም አዲስ አመት……አልኩ። እንደ ወግ ልማዱ።
ከዚህም ከዚያም፣ መልካም አዲስ አመት …መልካም አዱስ አመት …የሚሉ ብዙ ድምፆች ወደ እኔ በአፀፋው ሲወረወሩ አደመጥኩ….
እነዚህን ወገኖቼን ጠጋ ብዬ ማናገር ስጀምር መቼስ የተሰማኝን ስሜት አሁን ለእናንተ መግለፅ የለብኝም።  አርሶ አደሩ ገበሬ በዚህ ዘረኛና መርዘኛ ፓለቲካ ምክንያት ተጠቅቶ፣ ተገፍቶ፣ ሞፈር ቀንበሩን ተቀምቶ፣ ቤት ንብረቱን አጥቶ ዛሬ የሰው እጅ የሚመለከትና በድንኳን አዳሪ ሆኖ ስታዩት ምን እንደሚሰማ ታውቁታላችሁና። በተለይ ዛሬ ቀን ደግሞ በአል ነውና ልዩ ስሜትን ይፈጥራል። መቼስ ለአማሮች የአውዳመት በዓል ትልቅ ሀይማኖታዊም ባህላዊም ጉዳይ ነው። ያ ለብዙ የሚተርፍ ገበሬ ወግ ልማዱ ቀርቶ እንዲህ በስደተኞች ድንኳን ስር ሲተካክዝ ማየት ምን ስሜትና ቁጭት እንደሚፈጥር ታውቃላችሁ ብዬ ነው።
ከማናግራቸው ሰዎች መሃል ወጣቶቹ ከእኔ ጋር ብዙ ለማውጋት አዘንብለው አየሁ። ይገርማል። የሆድ የሆዳቸውን ሊያጫውቱኝ እንደፈለጉ ሁኔታቸው ይሰብቃል። አይኖቻቸው ግልፅ ቋንቋ አላቸው።  ሮጠው ያልጠገቡ ገና ብዙ አመታት ከፊታቸው ያሉ ወጣቶች ናቸውና። እነዚህ ወጣቶች የመፃኢ እድላቸው ጉዳይ፣ የቀጣዩ እድላቸው ጉዳይ ከባድ ሃሳብ ላይ ጥሏቸዋል። መጨረሻችን ምን እንደሆነ አናውቅም ሲሉ ደጋግመው በአንክሮ ነገሩኝ።
ለአሁኑስ እንዴት ናችሁ? ብዬ ስጠይቅ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ድርጅትንና ዩኒሴፍንና አንዳንድ ባለ ሃብቶችን ሲያመሰግኑ አየሁ። በእውነትም እነዚህ አካላት ለነዚህ ወገኖቻችን የእለት እርዳታ እያቀረቡ በመሆናቸው ሊመሰገኑ ይገባል።
ይሁን እንጂ የተፈናቀለ ሰው ጎደሎውና ቀዳዳው ብዙ ነውና በሃገርም ውስጥ በውጭም ያላችሁ ወገኖች እርዳታችሁን ለእነዚህ አማሮች እንድትዘረጉላቸው እማፀናለሁ።
ከሁሉ በላይ የእነዚህ ወገኖቻችን ችግር በዘላቂነት እንዲፈታና መዋቅራዊ ለውጦች እንዲመጡ ሁላችንም ዛሬስ አምርረን መታገል አለብን። የሰው ልጅ በገዛ ሃገሩ እየተፈናቀለ ሲሰቃይ እንደማየት ከቶ ምን የከፋ በደል አለ?  ከፀሀይ በታች ትልቁ ክፉ ነገር ይሄ ነው።
ስለሆነም ሁላችንም ዘረኛ የሆነ ህገ መንግስትና የፓለቲካ ትምህርት እንዲጠፋ የማንፈነቅለው ሰላማዊ ድንጋይ መኖር የለበትም። ሃገራችን ውስጥ በማንነት ላይ የሚደርስ መፈናቀል እያለ ትግል አይቆምም። መዋቅራዊ ለውጥ መምጣት አለበት። መዋቅራዊ ለውጥ እንዲመጣ ስንታገል ዛሬ የዜጎች ደህንነት መከበር አለበት የሚለው ድምፅ ጎልቶ መውጣት አለበት።
በመጨረሻም በዚህ አጋጣሚ እነዚህን ወገኖቼን ላሰባችሁልኝ ለወይዘሮ ሜጊል ዳየስና በመልካም ስራ ለተመሰገኑት ለወይዘሮ ሱዛን ማርቲኒ ምስጋናዬ ላቅ ያለ ነው። ለመላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ  መልካም አዲሱ አመት እንዲሆንላችሁ  እንደገና ምኞቴ ነው።
ገለታው ዘለቀ
ደብረ ብርሃን
#ኢትዮጵያ
ተጨማሪ ያንብቡ:  የሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች ተቃውሞ ቀጥሏል

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share