ምክር  –  ራሳችንን አናቁስል አንዱ ዓለም ተፈራ

June 3, 2022

ቅዳሜ፤ ግንቦት ፳ ፯ ቀን፤ ፳ ፻ ፲ ፬ ዓ. ም.

 

ለየኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ መንግሥት

ለየኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር አብር አሕመድ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ፓርላማ

ለየኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ የመከላከያ ጦር ሠራዊት

ለኦሮሚያ ክልል መንግሥት

ለአማራ ክልል መንግሥት

ለአማራ ክልል መግሥት ልዩ ኃይል

ለኦሮሚያ ክልል መግሥት ልዩ ኃይል

Abiy 90

ውድ የመንግሥት ተቋማትና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ፤

አሁን አገራችን ያለችበት የፖለቲካ ሀቅ የሚያሳየው፤ ከመንግሥት ችሎታ በላይ የሆነ ችግር እንዳለ ነው። እናም፤ መፍትሔውን ለማምጣት፤ የመንግሥት አካላት፣ የተደራጀው የሕዝብ ክፍልና ግለሰብ አገር ወዳዶች በሙሉ ሊረባረቡበት ይገባል። በቅርቡ በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርና በኦነግ ሸኔ የታጠቀ ኃይል፤ ፍጹም አረመኔና ስብዓዊ ያልሆኑ ተግባራት ተተግብረዋል። ብስጭት፣ ጭንቀትና የበቀል ስሜት ጉዳቱ በደረሰባቸው ወገኖች አይሏል። አገራችን ኢትዮጵያ፤ አንድም አዳክመውና መዳከሟን ዓይተው መቃብር ለመክተት፤ ሳጥኗ ላይ የመጨረሻውን ሚስማር ለመቸከል በሚሯሯጡ ጠላቶቿ፤ ሌላም የሥልጣን ጥማቸውን ለማርካት ጠባብ አጀንዳ መዘው በሚሯሯጡ የራሷ ልጆች እንዲህ እየተተራመሰች ብዙ ልትቀጥል አትችልም። የሶማሊያ፣ የዩጎዝላቪያ፣ የሲሪያና የሊቢያ እውነታ ይሄንን በግልጥ አሳይቶናል። ከሶማሊያ በላይ አንድ ሕዝብና አንድ አገር በዓለም ዙሪያ ብዙም የሉም። የተባበረ እጅ፣ የረጉ አእምሮዎችና የበሰሉ አስተዋዮች በሌሉበት ቦታ፤ በጥባጮች ይፈንድቃሉ። ይሄን ለመጻፍ ያስገደደኝ ይሄው እውነታ ነው።

የአገር ፖለቲካ፤ መሬት ላይ ባለው ተጨባጩ እውነታ እንጂ፤ በምናባችን ወይንም አንድም አስርም ሆነን በጭንቅላታችን ባረቀቅነው ምኞት አይመራም። በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያለ አካል፤ የአገሪቱን ፖለቲካ፤ “እኔ ጥቁር ወይንም ነጭ በምለው ነው የሚሄደው! ማንንም አልሰማም!” ብሎ የሚጓዝ ከሆነ፤ በሕዝብ ተወክሎ አገርን የሚያስተዳድር መሆኑ ይቀርና፤ የሕዝብ የበላይ ሆኖ የሚገዛ፤ አምባገነን ፈላጭ ቆራጭ ኃይል ነው። በሥልጣን ላይ ላለ አካል ትልቁ ችግር፤ “እኔ ብቻ ትክክለኛውን መፍትሔ አውቃለሁና፤ ሌሎች ዝም ብለው ይተውኝ!” የሚለው እብሪት ነው። መቶ በመቶ ትክክለኛ የሆነ መንግሥት በዓለም ላይ የለም! አገርን ማስተዳደር በጣም ከባድና አድካሚ ተልዕኮ ነው። ይህ ተልዕኮ፤ ከባድ አስተዋይነትን፣ ፅሞናንና የራስን ሕይወት ለሌሎች አሳልፎ መሥጠትን ይጠይቃል።

አገራችንን አንቆ የያዛት ጥያቄ፤ የዚህ ወይንም የዚያ ቡድን፤ እከሌ ወይንም እከሊት በሥልጣን ላይ መሆን አይደለም። ጥያቄው፤ ኢትዮጵያዊ የስብስብ አንድነቱ ዕሴት እየተሸረሸረ፤ ኢትዮጵያ እንደ አገር ልትቀጥል ነው ወይንስ አይደለም? የሚለው ነው። ምንም እንኳን ብዙዎች ሃይማኖተኛና በጎ ተመኚ ቢሆኑም፤ ኢትዮጵያን ተዓምር አይጠብቃትም። ኢትዮጵያ የተለየች መሬት፣ ኢትዮጵያዊያን የተለዬን ሕዝብ አይደለንም። እኛም አገራችንም የሶስተኛው ዓለም አካል ነን። የሶስተኛ ዓለም ፖለቲካ ደግሞ የኛምን ሀቅ አቅፎ ይዟል። እንደ ሌሎቹ የሶስተኛው ዓለም አገራት ሁሉ፤ ትርምስና አምባገነንነት ከጎናችን ሩቅ አይደሉም። በተጨማሪ፤ ቡድነኝነትና ሙስና፣ የግለሰብ ጥቅምን ማሳደድና ሌሎችን መወጣጫ አድርጎ ራስን ከአገር በላይ ማስቀመጥ የኒህ አገራት መለያ ምልክት ናቸው። የውጪ አገራት ጥቅም ፍለጋ ሩጫ፤ በአገር በቀል ሆድ አደሮች በመታገዝ፤ ሰላም በአገር እንዳይሰፍን ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደርጋል። ወደኛ አገር ስናተኩር፤ አገራችን ያፈጠጠባትን ችግር ዘርዛሪው ብዙ ነው! እጆቹን ቀስሮ፤ “እኒያ ናቸው ጥፋተኞቹ!” ባዩ ብዙ ነው። ይሄን ተረድቶ መደረግ የሚኖርበትን ሃሳብ አቅርቦና ለዚህ ሃሳብ ቁርጠኛ ሆኖ የተነሳ ማየቱ አዳግቶኛል። እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ፤ ይሄ ችግር የኔ ችግር ነው! ብሎ ተነስቶ፤ ከራስ ጥቅምና ከቡድን ፍላጎት ርቆ የተነሳ ማየቱ ቸግሮኛል። ከተወለድኩበት ቀን ይልቅ የምስናበትበት ቀን በጣም ቅርብ በሆነበት እውነታ፤ አገራችንን እንዲህ ሆና ጥያት መሄዱ እንቅልፍ ነስቶኛል። የምችለውን በማድረግ ወደተስተካከለ መንገድ እንድትገባ ጥረቴ ይቀጥላል። ምክሬም ይሄው ነው።

እስኪ አሁን በአገራችን ውስጥ ያለውን ተጨባጭ እውነታ እንመልከት!

በአሁኑ ሰዓት ለአገራችን ሕልውና የሚያሰጉትና የሕዝቡ ጠላቶች፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፣ ኦነግ ሸኔና የውጪ አገር ደጋፊዎቻቸው ናቸው። እኒህ ድርጅቶች፤ ሶስተኛ አካል ከሆነው በውጪ ካሉ የአገራችን ጠላቶች ቡድን ጋር በማበር፤ ሕዝቡን እያስጨነቁና እየገደሉ ናቸው። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ አሁንም በውጪ የአገራችን ጠላቶች እየታገዘ ሁለተኛ ወረራ ለማካሄድ ተዘጋጅቷል። አሁንም ቁጥራቸው እጅግ የላቀ ኢትዮጵያዊያን በገፍ ካገራቸው እየወጡ ለአስቃቂ ስደት እየተዳረጉ ነው። የፖለቲካ ዕርጋታ ባገራችን ባለመኖሩ፤ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆኑ፤ ገዢው ፓርቲም እየታመሰ ነው። በሚገርም መልኩ በፋኖ ላይ እየተፈጸመ ያለው ለቀማ፤ እየጦፈ ነው። የታወቀ ነገር ቢኖር፤ የፌዴራል መንግሥቱ፤ የፋኖም መንግሥት ነው። ፋኖ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርን እና የኦነግ ሸኔ ኃይልን ተቃርኖ፤ የፌዴራል መንግሥቱን ያወቀና የተቀበለ ነው። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር በአፋርና በአማራ ክልል ወረራውን ባካሄደ ጊዜ፤ ከየቦታው ተጠራርቶና ተሰባስቦ፤ ፋኖ ከመከላከያና ከአማራ ልዩ ኃይል ጎን በመሰለፍ አገሩን የታደገ ኃይል ነው። ፋኖ ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይል አይደለም። ፋኖ ራሱን የቻለ፤ የመንግሥት ሥልጣን ለመያዝ የተዋቀረ ኃይል አይደለም። ፋኖ ለአገር አድን ጥሪ ብቻ ከሕዝቡ መካከል ቆራጥና ብቁ የሆኑ አገር ወዳዶች፤ ሕይወታቸውን ለመስዋዕትነት ያቀረቡበት ስብስብ ነው። መንግሥት ፋኖን በጠላትነት የሚያይበት ምንም ምክንያት የለውም።

በርግጥ በመንግሥት ቀጥተኛ መዋቅር ሥር አለመግባቱና መንግሥት የማያዘው በመምስሉ፤ ውዥንብር አለ። ይህ ግን፤ በመግባባት መልስ የሚገኝበት ጉዳይ ነው። ያገር ሽማግሌዎችና የፖለቲካ ሊቆች ሚና፤ የሕዝብ ጠላት የሆኑትን የትግሬዎችን ነፃ አውጪ ግንባርን ወይንም የታጠቀውን የኦነግ ሸኔ ጦርን ከመንግሥት ጋር ማስታረቅ ሳይሆን፤ ፋኖ ከመንግሥት ጋር የሚተባበርበትንና ርዳታም የሚያገኝበትን ሁኔታ ማመቻቸትና መምከር ነው። ትክክል! ከመንግሥት ውጪ የታጠቀና የተደራጀ ኃይል በአገራችን ውስጥ መኖር የለበትም። ለዚህ ነው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርና የኦነግ ሸኔ ቡድን መደምሰስ ያለባቸው። ፋኖ ወቅታዊ የሕዝብ ታጣቂ ኃይል ነው። በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ አደጋ የሆኑት የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርና የኦነግ ሸኔ ሲደመሰሱ ፋኖ ይበታናል። አሁን ግን እኒህ የሕዝብ ጠላቶችና አገር አፍራሾች ከፍተኛ ያገር አደጋ በሆኑበት ሰዓት፤ ፋኖን ለመበተን መነሳት አደጋ አለው። ፋኖ ባሁኑ ሰዓት ከፍተኛ ሚና አለው። የፋኖ ክስተት በኛ አገር ብቻ ያለና የታየ አይደለም። አሜሪካ ስትመሠረት፤ ገና በእንጭጯ እቀጫታለሁ ብላ ቅኝ ገዥዋ እንግሊዝ በዘመተችባት ጊዜ፤ ለጋው መንግሥትን ያዳኑት ፋኖዎች ናቸው። እኒህ ናቸው ለአሜሪካ መደበኛ ጦር መቋቋምም መሠረት የሆኑት። አሁንም በዩክሬን፤ ሕዝቡ በያለበት ፋኖ ሆኖ በመደራጀት ነው የሩስያን ወረራ እየተቋቋመ ያለው። ፋኖ አጋዥ ኃይል ነው። አሁን ኢትዮጵያ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ባላችሁት እጅ ናት። ኢትዮጵያ በፋኖ እጅ አይደለችም። በመንግሥት ሥልጣን ላይ በመቀመጣችሁ፤ ይሄን የመሰለውን ያገር ድጋፍ ስታገኙ፤ በትክክል ልትይዙት ይገባል።

በሌላ በኩል ደግሞ፤ እንኳንስ ደመወዝ የማይከፈለው፣ ቀለብ የማይሰፈርለት፣ በየዱሩ እያደረ የራሱን ንብረትና ሕይወት ላገሩ የሚለግሰው ቀርቶ፤ መደበኛው ጦር እንኳን ስንት ስህተት ሠርቷል። ስንቶች ጀኔራሎች ናቸው በወረራው ሂደት ሊጠየቁበት የሚገባ ስህተት የፈጸሙት? አንድ ወይንም አስር የፋኖ አባላት ይሄንን ወይንም ያንን ሠሩ ብሎ ፋኖን ለማጥቃት መነሳት፤ የበጎ ሳይሆን የፖለቲካ አጀንዳን ለማሟላት መነሳት ነው። ፋኖ ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የማረከውን ከባድ መሣሪያ ለመከላከያ አስረክቧል! ፋኖ አሁን እንዲጠመድ የሆነበት ምክንያት፤ የአማራ የተደራጀ ክፍል በመሆኑና የአማራ ተቆርቋሪ ይሆናል ተብሎ ስለተፈራ ነው። አማራነት ወንጀል ሆኖ፤ ከፌዴራል መንግሥቱ ባለሥልጣናት እስከ አማራ ክልል አስተዳዳሪዎች፣ ከኦሮሞ ክልል አስተዳዳሪዎች እስከ ታጠቁ የኦነግ ሸኔ ባለጉልበተኞችና ማንኛውም የተደራጀ ኃይል፤ ልክ እንደ ትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርና ሕገ-መንግሥቱ፤ በአማራዎች ላይ ዘምቷል። ይህ የማይታበል የዕለት ተዕለት ሀቅ ነው።

ለኢትዮጵያ፤ እንቅልፋቸውን አጥተው ሌት ተቀን የሚዶሉቱላት ጠላቶቿ የሚያውጠነጥኑት ሴራ ብዙ ነው። ተጨማሪ ራሳችን የምንፈጥረው ሴራ አላስፈላጊ ነው። ራሳችንን አናቁስል። ሁላችንም እንቅልፍ አግኝተን እንድንተኛ፤ አገር እንድትለማና እንድታድግ፣ በግልም በሥልጣን ላይ ያላችሁት የበለጠ እንድትበለጽጉ፣ ትልቅ አገር መኖሯና ሰላም መስፈኑ ጠቃሚ ነው። “እኔ ለመጠቀም፤ ሌሎች መጎዳት አለባቸው!” የሚለው የትግሬዎች ነፃ አውጪ እምነት መወገድ አለበት። ከዚሁ ጋር፤ “አማራን ማጥቃት ዋና ተግባሬ ነው!” የሚለውም ለኢትዮጵያ አይጠቅምም። የኢትዮጵያ መሠረትና የወደፊት ሂደት፤ አብሮነትና አንድነት ነው። እንደገና! ራሳችንን አናቁስል!

ኢትዮጵያዊያን እንበርታ

2 Comments

  1. Release Meskerem Abera,Radios Tantu and journalists they don’t have weapons to block you to give Amharas region for tegreas.

Leave a Reply

Your email address will not be published.

photo5821312649554672610.jpg
Previous Story

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በፓሊስ ተደበደበ!! – ታሪኩ ደሳለኝ (የተመስገን ወንድም)

284594142 4980035762125997 4332042263139855699 n
Next Story

የ3ት ፎቶዎች ወግ – ተወልደ በየነ

Latest from Blog

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ የውጪ ግንኙነት የቤተክርስቲያኒቱን የሺሕ ዘመናት ታሪክ እና እሤቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርባታል!!

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) (ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደጻፈው) እንደመንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው ጽሑፌ መነሻ የሆነኝ- ባሳለፍነው ሳምንት በአፍሪካ ኅብረት ኔልሰን ማንዴላ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለአንድ ቀን የተካሄደው፤ ‹‹የአፍሪካ  መንፈሳዊ ቀን/The African Spiritual

የአበባው ታደሰ እና የአረጋ ከበደ ፍርጠጣ | ስለአማራ ክልል ከነዋሪዎች የተሰማው | አበባው ጉ’ድ ሆነ – “አበባውን ሳትይዙ እንዳትመጡ”|“በባህርዳር ተከበናል፣ ከፍተኛ አዛዦች ተመተዋል” | “ፋኖ መንግ’ስት ሆኗል” ጄ/ሉ |

የአበባው ታደሰ እና የአረጋ ከበደ ፍርጠጣ አበባው ጉ’ድ ሆነ – “አበባውን ሳትይዙ እንዳትመጡ”|“በባህርዳር ተከበናል፣ ከፍተኛ አዛዦች ተመተዋል”| “እጅ ከመስጠት ውጭ አማራጭ አይኖረንም” ፊ/ማ “ፋኖ መንግ’ስት ሆኗል” ጄ/ሉ |
Go toTop