March 19, 2022
10 mins read

ለትልቁ ሰው፤ መድኃኔዓለም አቤት ብያለሁና፣ መልሴን እጠብቃለሁ!! – በዲ/ን ተረፈ ወርቁ

በ‘‘ዘመነ መሳፍንት’’ ከሚታወቁት መኳንንት የጎጃሙ ደጃች ብሩ ጎሹ ይጠቀሳሉ፡፡ እኚህ ሰው እንደማንኛውም የዘመነ መሳፍንት የጦር አበጋዞች ጀብደኝነትና ጭካኔ የሚያጠቃቸው መሪ ነበሩ፡፡  በአንድ በኩል ንጉሠ ነገሥት የመኾን ሕልመኛ መስፍን እንደመሆናቸው አባታቸውን ደጃች ጎሹን ሳይቀር ጦርነት ገጥመው በማሸነፍ ከግዛታቸው የተወሰነውን ቆርሰው በጉልበት የወሰዱ ጦረኛ ሰው ናቸው፡፡

በዚሁ በዘመነ መሳፍንት ወቅት- ከአብሮ አደጋቸው፣ ከቋራው ካሣ/ከዐፄ ቴዎድሮስ ጋር ውጊያ የገጠሙት እኚሁ ጦረኛ መስፍን፤ ደጃች ብሩ ጎሹ በጦርነቱ ተሸንፈው በምርኮኝነት ጭልጋ ውስጥ ተግዘው ሳሉ፤ ሚስታቸው ከገዛ አሽከራቸው ጋር መኮብለሏን ይሰማሉ፡፡ ንዴት ውስጣቸውን እየናጠው፣ በገናቸውን እየደረደሩ፣ ብሶታቸውን እንዲህ ሲሉ አሰሙ፤

የካሣስ እስራት ቀላል ነው አይጎዳም፣
ያንቺ ባል መሻር ነው የገረመኝ በጣም፡፡

አይተኻል ወይ ጎጃም ተዛሬ በፊት፣
ቀን ሲከዳ ስታይ የምትከዳ ምሽት/ሚስት?!

 

ደጃች ብሩ፤ ‘‘ጊዜ እንጂ እንዲህ ያዋረደኝ መች እንዲህ እሆን ነበር?!’’ ሲሉ ዳግመኛ በኀዘን ውስጥ ሆነው በገናቸውን አንስተው እንዲህ ተቀኙ፤

ድንበሬን ማን ገፍቶት አይሉም፤ አይሉም፣
አጥሬን ማን ደፍሮት አይሉም፤ አይሉም፣
ከእልፍኜ ሰው ገባ አይሉም፤ አይሉም፣
ሚስቴንስ ማን አይቷት አይሉም፤ አይሉም፣
ቀን የጣለ ለታ ይደረጋል ሁሉም፡፡

 

በወቅቱ ጎንደር የነበሩት እንግሊዛዊው መልእክተኛ ፕላውዲን እንደጻፈው፤ በደጃች ብሩ ላይ የደረሰውን ይህንን በደል የሰሙት ዐፄ ቴዎድሮስ፤ ‘‘ሚስትዎን የቀማውን ሎሌ/አሽከር አስይዤ አምጥቼ ልቅጣልዎት ወይ?!’’ ብለው ጭልጋ ውስጥ በግዞት/በእስር ላይ ለሚገኙት፣ የጦር ምርኮኛቸው፣ ለዳጃች ብሩ ጎሹ ጦማር/ደብዳቤ ላኩባቸው፡፡ ደብዳቤው የደረሳቸው ደጃች ብሩ፤ ‘‘ጃንሆይ፣ እርስዎ አይደከሙ፣ እኔ ለትልቁ ሰው፣ መድኃኔዓለም አቤት ብያለሁ፣ አመልክቻለሁና መልሴን እጠብቃለሁ!!’’ የሚል ምላሻቸውን ደብዳቤውን ይዞ በመጣው አሽከር በኩል ለዐጤ ቴዎድሮስ ላኩባቸው፤

ታዲያ የዐጤ ቴዎድሮስ አሽከር ገና ደጃች ብሩ ከተጋዙበት ከጭልጋ ወደ ጎንደር ሳይመለስ፤ የደጃች ብሩን ሚስት ያስኮበለለውን አሽከራቸውን በጠራራ ፀሀይ መብረቅ ወርዶ ገደለው፡፡  የቴዎድሮስ መልእክተኛም ይህን አስደንጋጭ ዜና ይዞ ወደ ጎንደር ተመለሰ፡፡

ይህን ዜና የሰሙት ዐጤ ቴዎድሮስ፤ ‘‘እኚህ ሰው፣ እኔንም ለትልቁ ሰው፣ መድኃኔዓለም አቤት እያሉ እንዳያስፈርዱብኝ በማለት ከእስራት እንዲወጡ ቆረጡ፡፡ ከተጋዙበት ጭልጋ ወደ ጎንደር የመጡት ብሩ- ዐጤ ቴዎድሮስ ፊት ቀረቡ፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ዘመኑ ባህል፣ ደጃች ብሩ ድንጋይ በጫንቃቸው ተሸክመው ይቅርታ መጠየቅ ሲገባቸው ሎሚ የምታክል ድንጋይ በእጃቸው ይዘው፣ ክንብንባቸውን ከራሳቸው ሳያወልቁ ጃንሆይ ፊት ቀረቡ፡፡

በደጃች ብሩ ሁኔታ የተናደዱት ዐጤ ቴዎድሮስም፤ ‘‘እግዜር አትፈታ ቢልህ ነው እንዲህ ያለ ትእቢት የምታሳየው፤’’ ብለው ዳግመኛ ወደ መቅደላ አምባ እስር ቤት፤ በግዞት እንዲቀመጡ ላኳቸው፡፡ ደጃች ብሩ የሕይወታቸው ፍፃሜም መቅደላ እስር ቤት ኾነ፡፡

ለመውጫ ያህልም፤ እንግዲህ ወራቱ ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እና ለካቶሊካውያን ክርስትያን አማኞች የጾም ወራትም አይደል… እናም እስቲ ደጃች ብሩ ‘‘ትልቁ ሰው’’ ሲሉ አቤቱታቸውን ስላቀረቡለት መድኃኔዓለም፣ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥቂት መንፈሳዊ ሐሳቦችን/አስተምህሮችን ላንሳ፡፡

የሥነ-መለኮት/የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን አስተምህሮ እንደሚገልጸው፤ ጌታችንና አምላካችን፣ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠራባቸው ስሞች አንዱ ‘‘የሰው ልጅ’’ የሚለው ይጠቀሳል፡፡ ለሰው ልጆች ሁሉ ኃጢአት ቤዛ ሊሆን ከሰማይ ሰማያት ወርዶ፣ ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍስዋ ነፍስ ነስቶ የተወለደው፣ ሰው የሆነው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ- ‘‘የሰው ልጅ’’ ተብሎ ተጠርቷል፡፡ እርሱ ፍጹም ሰው፣ ፍጹም አምላክ ነውና፡፡

የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ የሆነው ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ፤ ‘‘… የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም፤ ስለዚህ ሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ፣ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፣ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው፡፡ … እግዚአብሔር የሰጠኝንም ልጆች ሲል ወንድሞች ብሎ ሊጠራቸው አያፍርም፡፡’’ ሲል እግዚአብሔር ወልድ ከቅድስት ድንግል ማርያም በነሳው ሥጋ ለእኛ፣ ለሰው ልጆች ዘመድ፣ ወገን እንደሆነን አመስጥሯል፡፡

የቤተክርስቲያናችን ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫም፤ ‘‘አስተርእየ ገሀደ፤ በለቢሰ ሥጋ ኮነነ ዘመደ/ በለበሰው ሥጋ ዘመድ/ወገን ሆነን፡፡’’ ሲል ተቀኝቷል፡፡

የሀገራችን ባለመሲንቆ/አዝማሪ በዘለሰኛ ዜማውም፤

አብን ተወውና ንገረው ለወልድ፣
ጥሎ አይጥልምና የሥጋ ዘመድ፡፡

 

እናቶቻችንም ወደ ቅዱሳን መካናት/ወደ ገዳማት ለመሳለምና ለክብረ በዓላት ሲሔዱ፣ በአንድነት ሆነው ባማረ ዜማ፤

‘‘አብን ተወውና ንገረው ለወልድ፣

ተገርፏል፣ ተሰቅሏል፣

እርሱ ያውቃል ፍርድ፡፡’’ ሲሉ ማዜማቸው እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ከእመቤታችን፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም፣ በነሳው ሥጋ ከእኛ ጋር መዛመዱን፣ እርሱ ፍርድ አዋቂ፣ ለድሃ ደጎች አባት፣ ለመበለቶች ደግሞ እውነተኛ ዳኛ መሆኑን ሲያመሰጠሩልን ነው፡፡

የጌታውን፣ የደጃች ብሩን ሚስት ያስኮበለለውን ግፈኛ፣ ወንጀለኛ ፍርዱን ሳይውል ሳይድር የሰጠው ወልድ እግዚአብሐር፣ ወልድ ማርያም- ‘‘ትልቁ ሰው፤ መድኃኔዓለም’’ ዛሬም በዙፋኑ ላይ አለና እናስተውል፡፡ በአምሳሉና በምሳሌው በፈጠረው ሰው ላይ ግፍን፣ ዓመፃንና ክፋትን የምትፈጽሙ- ከታሪክ ለመማር የማትሹ ግፈኞች፣ አምባ ገነኖች ሁሉ እግዚአብሔርን ፍሩ፣ ሰውንም እፈሩ፡፡ እግዚአብሔር በእውነት፣ በጽድቅ ይፈርዳልና!!

‘‘እግዚአብሔር ይቅርታ እድራጊ ነው፤ ለተበደሉ ሁሉ ይፈርዳል፡፡ እግዚአብሔር ለድሆች፣ ለግፉአን በጽድቅ ይፈርዳል፣ ለምድርም የዋሆች በቅንነት ይበይናል፤ በአፉም በትር ምድርን ይመታል፣ በከንፈሩ እስትንፋስም ክፉዎችን ይገድላል፡፡’’ እንዲል ልብ አምላክ ዳዊት በመዝመሩ፡፡

ለሕዝበ ክርስትያን ሁሉ መልካም የጾም ወራት!!

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

የእናት አገር ጥሪ – ፀረ-ሸኔ – ዘመቻ ግብዓተ ኢትዮጵያ – ከአባዊርቱ

275976388 2276521065837705 2031677047501494837 n 1
Next Story

የትግራይ ክልል ተፈናቃዮች በቆቦ

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop