ሥጋታችን “አክራሪ” ሃይማኖተኝነት ሳይሆን አክራሪ “አይማኖተኝነት” ነው

አዲስ ጉዳይ መጽሔት
adebabayblog@gmail.com;

ይህንን ጽሑፍ ለመጀመር ትርጓሜ የሚያስፈልጋቸውን ሐሳቦች ብያኔ በመስጠት እነሣለኹ። ሃይማኖት እና አይማኖት። በጥሬ ትርጉሙ ከወሰድነው ሃይማኖት “አሚን፣ ማመን፣ እምነት፣ አምልኮ” ማለት እንደሆነ የግእዝ እና የአማርኛ ቀዳማውያት መዝገበ ቃላት ደራስያን ደስታ ተ/ወልድ እና ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ይነግሩናል። ከዚያም አልፎ በዕለት ተዕለት ቋንቋችንና አነጋገራችን ካየነው ደግሞ እያንዳንዳችን የምንከተለውን እምነት እና ሃይማኖት በየስሙ እየጠራን “እገሌ የተሰኘው ሃይማኖት ተከታይ ነን” እንላለን።

“አይ” ደግሞ “የአሉታና የነቀፌታ ቃል ንኡስ አገባብ ሲኾን በቦታ፣ በኀላፊ፣ በትንቢት፣ ይገባል። ለምሳሌ “አይ ወዲያ፤ አይ በሉ” እንደሚባለው ነቀፌታን የሚያሳይ አገባብ ነው። “አይባልም፣ አይገባም፣ አይደለም፣ አይኾንም” የምንለውን ማስታወስ ነው።

ያዲሳባ ሰው አይጦም አይበላ፤

አያርፍ አይሠራ” እንዲሉ አለቃ ደስታ ተ/ወልድ።

ከ“ሃይማኖት” አሉታን የሚያሳይ “አይማኖት” የሚል ቃል መፍጠሬን ይመለከቷል። ሃይማኖተኛ እንደሚለው እምነት አልባ፣ እግዜር የለሽ (Atheist) መሆን ብቻ ሳይሆን ለሃይማኖት ጥላቻ ያለውን ሰው “አይማኖተኛ” (Antitheist) ብንል ያስኬደናል። ቃሉ ለምን እንዳስፈለገን ወደ ጽሑፉ ገባ ስንል እንገነዘባለን። በፈጣሪ መኖር የማያምኑ (Atheist የሆኑ) ብዙ ሰዎች አሉ። ግን ሃይማኖትና አማኒውን ላይጠሉ ይችላሉ። ሃይማኖትን እና አማኙን ለሚጠሉ ግን አይማኖተኛ (አንቲቴይስት Antitheist) የሚለው ይህ ቅጽል ገላጭ ይሆናል። እናብዛው ካልን “አይማኖተኛ፣ አይማኖተኝነት” ልንለው እንችላለን።

++++

ሃይማኖት ሥር እንደ ሰደደባቸው እንደማንኛቸውም አገሮች ሁሉ ኢትዮጵያም ስለ ሃይማኖት፣ ሃይማኖት በሕብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ስላለውና ሊኖረው ስለሚገባው ድርሻ እና ከፖለቲካ ጋር ስላለው ግንኙነት ሰፊ ውይይት ይደረግበታል። ውይይቱ አዲስ የተጀመረ ባይሆንም በዚህ ዘመን ያለው የጉዳዩ አያያዝ ከሌሎቹ ዘመናት በተለየ ሰፋና ጠለቀ ያለ ትርጉም እየተሰጠው ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያዊነት ምንድን ነው? - አንዱ ዓለም ተፈራ

አገራችን አዲስ መንግሥት እና አዲስ ሕገ መንግሥት ከተመሠረተባት ካለፈው 20 ዓመት ወዲህ በአገሪቱ ስላሉት እምነቶች፣ ከፖለቲካው ጋር ስላላቸውና ሊኖራቸው ስለሚገባው ግንኙነት ሰፊ መንግሥታዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው። ይኸው መንግሥታዊ እንቅስቃሴ በሁሉም ዘንድ ያለው መረዳት አንድ ዓይነት ነው ማለት አይቻልም።

በሕገ መንግሥቱ ላይ መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፤ መንግሥታዊ ሃይማኖት አይኖርም፤ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፤ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም” ይላል። (ሕገ መንግሥት አንቀጽ 11)።

አንዱ በአንዱ ተግባር ውስጥ “ጣልቃ አለመግባት” ማለት ምን ማለት ለመሆኑ በራሱ መፍታታት ይኖርበታል። መንግሥት በሃይማኖት ላይ የተመሠረተ፣ አንድን እምነት የመንግሥት እምነት አድርጎ የሚቀበል አይሆንም፤ ሃይማኖትም በራሱ ተነሳሽነት “ሃይማኖታዊ መንግሥት ለመመስረት አይንቀሳቀስም”። በሳዑዲ አረቢያ ወይም በሌሎች የእስልምና አገሮች “የአገሪቱ ብሄራዊ እምነት እስልምና” ሆኖ እንደታወጀው በኢትዮጵያም “ብሔራዊ እምነት የሚባል” አይኖርም ብለን እንውሰድ። በተጨማሪም እምነቶች እንደ ፖለቲካ ፓርቲዎች የራሳቸውን መንግሥት ለማቋቋም አይሞክሩም። በእምነት ስም ለፖለቲካ ማራመጃነት ማንኛውንም ፓርቲ (ሃይማኖታዊ ፓርቲ) ማቋቋም  አይፈቀድም።

ሕገ መንግሥቱ “የሃይማኖት፣ እምነትና አመለካከት ነጻነት” ባለው ክፍል ውስጥ ደግሞ ተጨማሪ እምነት ነክ መብቶች ዘርዝሯል (አንቀጽ 27)። ሲጠቃለል፦ መንግሥት በዜጎች እምነት ነክ ጉዳይ ጥልቃ የማይገባ፣ ከሃይማኖት የራቀ፣ “ሴኩላር” መሆኑን ያስረግጣል።

የመንግሥት ሴኩላርነት፣ ሃይማኖትን እና መንግሥትን የመለየት ፍልስፍና ከራሳችን ያነቃነው ሳይሆን ከሌሎቹ አገራት የቀዳነው እንደመሆኑ ፍልስፍናው እና አስተምህሮው በሌሎቹም ዘንድ ለረዥም ጊዜ ሲሰለቅ የኖረ ነው። አልፍሬድ ስቴፓን የተባሉ ፀሐፊ ዲሞክራሲ በፖለቲካ፣ በመንግሥታትና በሃይማኖቶች መካከል ስላለው ግንኙነት ሲናገሩ በአራት ከፍለው ያስቀምጣሉ።

1ኛ. ሴኩላር የሆነ ይሁን እንጂ ለሃይማኖት ጥላቻ የሌለው መንግሥት አለ፤

2ኛ. ሴኩላር ያልሆነ (እምነት ነክ የሆነ) ይሁን እንጂ ለዲሞክራሲ ጥላቻ የሌለው መንግሥት አለ፤

ተጨማሪ ያንብቡ:  የታመመው መንግስት (ጥሩነህ)

3ኛ. ሴኩላሪዝም ያቆጠቆጠበት እና ሃይማኖት ምንም ተጽዕኖ የሌለበት ፖለቲካ አለ፤

4ኛ. ሴኩላር የሆነ ነገር ግን ለሃይማኖት ጥላቻ ያለውና በሃይማኖቶች እና በመንግሥት መካከል ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት እንዲመሠረት የሚያደርግ አስተዳደርና ፖለቲካ አለ። (RAY TARAS. “POLAND’S TRANSITION TO A DEMOCRATIC REPUBLIC: The Taming of the Sacred?”. THE SECULAR and THE SACRED NATION, RELIGION AND POLITICS. (2005: p. 143)።

+++

ፈረንሳይ “ሴኩላር” የመንግሥት አስተዳደር የምትከተል ብትሆንምና ባለ ብዙ እምነት አገር ብትሆንም ለብዙ ዘመናት በአገሪቱ የቆየውን የካቶሊክ እምነት እና ባህል ግን ከአገሪቱ ማንነት ላይ ቀርፋ መጣል አትችልም። የሌሎችን እምነቶች ባህል ለማክበር የፈረንሳይ-ካቶሊክ እምነትና ባህል መጥፋት የለበትም። በታሪክ አጋጣሚ ካቶሊካዊነት ያገኘው ሥፍራ አሁን ባለው የእምነት-እኩልነት ምክንያት ሊኮስስ አይችልም።

ብዙ እምነት ካላቸው እና “ሴኩላር” አስተዳደር እንከተላለን ከሚሉት መካከል ሕንድን በተጨማሪ ብናነሣ አገሪቱ የተለያዩ እምነቶች አገር ብትሆንም ሁሉንም አስማምታ በአንድነት ማኖር የቻለችው ግን ገና ከ50 ዓመት ወዲህ ነው። ፓኪስታንን እና ሕንድና ያለያያቸው የርስበርስ ጦርነት የተደረገውና አንዷ ሀገር ሁለት ለመሆን የበቃችው በእምነት ልዩነት መስመር ነው። ፓኪስታን እስልምናን፣ ሕንድ ደግሞ ሒንዱ እምነትን በዋናነት በመያዝ። ሒንዱ ዋነኛው እምነት ቢሆንም አሁን ሕንድ ባላት ለእምነቶች ሁሉ እኩል ዕይታ ምክንያት ባለ ብዙ እምነት አገር ተብላ ትወሰዳለች። ሕገ መንግሥታቸውም ይህንን ያሳያል።

ሕንድ ሌሎች እምነቶችን ትቀበላለች ማለት የሒንዱ እምነት በአገሪቱ ላይ የነበረውን የቆየ አሻራ ታራክሳለች ማለት አይደለም። የአገሪቱ ባህላዊ ማንነት በሒንዱነት ቢበየን የታሪክ አጋጣሚ መሆኑ እሙን ነው። የቆየ እምነት ነውና ታሪካዊ ድርሻው ከፍ ማለቱ የማይጠረጠር ነው። ማንኛውም ሕንዳዊ የፈቀደውን እምነት መከተል ይችላል። ሁሉም እምነት ግን በሕንድ ታሪክ ላይ እኩል ድርሻ የለውም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የመከላከያ ሠራዊቱ-ድምበር አስከባሪ ወይስ አሳሪና አስተዳዳሪ ?

ከስፔን እስከ ቱርክ፣ ከፖላንድ እስከ አሜሪካ፣ ሃይማኖት ትልቅ ሥፍራ በሚይዝባቸው ነገር ግን መንግሥታቱ “ሴኩላር” ናቸው በሚባሉባቸው አገሮች በመንግሥታት እና በሃይማኖቶች መካከል እኩያነት፣ መከባበር፣ መተጋገስ እና ሕጋዊነት አለ። መጠናቸው ግን አንዱ ከአንዱ ይለያል።

+++

ባለፉት አርባ ዓመታት በአገራችን ያለው የፖለቲካ እና የሃይማኖት ግንኙነት ብንመለከት “ሴኩላር” መሆኑን ሁለቱም መንግሥ ቢገልጹም “ምን ዓይነት ሴኩላር መንግሥት?” የሚለውን ግን የምንገነዘበው ከድርጊታቸውና ከተግባራቸው ብቻ ነው። አልፍሬድ ስቴፓን  ሐሳቦች መነሻነት ከተመለከትናቸው መንግሥቶቻችን ሴኩላር ብቻ ሳይሆኑ ለሃይማኖት በጎ አመለካከት በሌለው ሴኩላር አስተሳሰብ ላይ የተገነባ ፍልስፍና  የሚከተሉ “አይማኖተኞች” መሆናቸውን መረዳት እንችላለን።

ይህ 40 ዓመት በትክክል ያሳየን አንድ ሐቅ ደግሞ አገራችንን ያጠፋው ይኸው አይማኖታዊ አመለካከት እንጂ ሃይማኖት አለመሆኑን ነው። በቀይ እና ነጭ ሽብር፣ በግራና በቀኝ አስተሳሰብ፣ በቋንቋና በዘር ፖለቲካ ወዘተ ተቆራቁሰን አገራችንን ከማጥፋታችን በስተቀር በሃይማኖት ሰበብ ድሆችና ኋላቀሮች አልሆንም። የእርበርስ ጦርነቶች ሕዝባችንን ያጎሳቆሉት ለአገራችን ችግር ዋነኛ ምክንያት ተደርጋ በምትፈረጀው በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰበብ አይደለም።

መንግሥት ሴኩላር መሆኑ ተገቢ ሊሆን ይችላል። ሃይማኖትን “ሴኩላር” ማድረግ ግን አይማኖተኝነትን በሃይማኖት ላይ መጫን ነው። ሰዎች በምርጫቸው እምነት አልባ መሆን መብታቸው ነው። በግድ እምነታቸውን ማስጣል እና ሃይማኖት ያላቸውን ሰዎች በጎ ባልሆነ አመለካከት መመዘን አይማኖተኝነት ነው። አክራሪነትን እቃወማለሁ። አይማኖታዊ አክራሪነትን ደግሞ የበለጠ እቃወማለሁ። አገራችንን ሲያጠፋ በደንብ አይቼዋለሁና። በተግባር የተገለጸ ሥጋታችን “አክራሪ ኦርቶዶክስ” ሃይማኖተኝነት ሳይሆን አክራሪ “አይማኖተኝነት” ነው።

ይቆየን – ያቆየን

 ህ ጽሑፍ አዲስ አበባ ለሚታተመው የአዲስ ጌዳይ መጽሔት የተጻፈና በዚያም ላይ ለሕትመት የበቃ ነው።

Share