በጭምቷ ሀገረ ሲዊዝ መዲና በበርን ከተማ ረ/ አውሮፕላን አብራሪ ኃይለመድህን አበራ – ያበራል ሲሉ ወገኖቹ ዛሬ ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ።

February 28, 2014

ከሥርጉተ ሥላሴ (ሲዊዘርላንድ ዙሪክ)

„ታሪክ ሠራ ጀግና ሲዊዝ ላይ ገባና“

„ታሪክ ሠራ ጀግና ሲዊዝ ላይ ገባና
ዓለም አነጋግሮ ትኩረት ስቧልና፤

ተልኮ የመጣ ተብሎ ኃይለመድህን
መልእክቱን ለማድረስ ኢትዮጵያን ለማዳን፤
አጀብም አሰኜ ዓለም ተደመመ
ጣሊያንን ቆልፎ ታሪኩን ደገመ!

ታሪክ ሠራ ጀግና ጄኔብ ላይ ገበና
አለም አነጋግሮ ትኩረት ስቧልና!

እዚች ሲዊዝ ላይ ለአመታት ጩኸናል
በብርድም ተገርፈን፣ ጸሐይ አቃጥሎናል፤
ሰሚም አልነበረም ችላ ብለውናል።
የወያኔ ሴራ ተጋለጠ ለኣለም
ኢትዮጵያ ሽፍታ እንጂ መሪ መንግሥት የለም።
ገለጠው ጉዱነን የወያኔን ሥራ
ደቀቀ ወያኔ በአንድ ቀን በራራ።

ታሪክ ሠራ ጀግና ሲዊዝ ላይ ገባና
ዓለም አነጋግሮ ትኩረት ስቧልና።

ዬድርሻን መወጣት፤ ሁላችን እንልመድ
ከፍቶልናል ጀግናው፤ የነጻነት መንገድ።
ወደርም የለውም የዚህ ፍጹም ጀግና
ሲያበራ ይኖራል ብልሁ ገናና!
አበጀህ ብለናል ከጎኑ እንቆማለን
ሲነኩን የማንወድ የበላይ ዘሮች ነን።
ብሶት በደላችን የኖረው ታምቆ
ነገረ ለዓለም ግዜውን ጠብቆ።

ታሪክ ሠራ ጀግና ሲዊዝ ላይ ገባና
ዓለም አነጋግሮ ትኩረት ስቧልና።“

የጣሊያን አከርካሪ የሰበረው የኣድዋ ደማቅ የጥቁሮች ድልና የጄኔባ ዳግማዊ ድል የመንፈስ ሐሤታዊ ቅብብል የታዬበት የረዳት አብራሪ ኃይለመድህን አበራ ተገኘ ገድልን በመደገፍ ዛሬ የካቲት 28.02.2014 ለእናት ሀገራቸው ክብርና ነፃነት እንዲሁም ብሩህ ተስፋና የህግ የበላይነት ቀናዕይ የሆኑ ከመላ ሲዊዘርላንድ ችለው የመጡ ኢትዮጵውያን ወጣት የነፃነት ኮከባችን የወሰደው እርምጃ አድምቆናል፤ ኮርተንበታልም፤ ከጎኑ እንቆማለን፤ ተስፋችንና ነፃነታችን ነው ሲሉ የሲዊዝን ዋና ከተማን ይልቁንም በማዕከላዊ ምክር ቤቱን ግዛታዊ ደንበር በወልዮሽ በመሆነው በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ድምጻቸውን በልበ ሙሉነትና በድፍረት ለሲዊዝ መንግሥታዊ አስተዳደር አቅርበዋል።

ሲወዝ ልክን አውቀ መኖርን፣ እንደ ወጣትንት የሚጫን ጎረምሳዊ መንፈስንና ስሜትን አርግቦ ርጋታን ይሸልማል፣ የመብትና የግዴታ ጣሪያና ግድግዳን በአግግባቡ ተርጉሞ ከህግ ጥሰት ይታደጋል፣ „ይበቃኛልን“ አስተምሮ ኑሮን ያስጥማል፣ መሬት በያዘ ጉዳይ ላይ አቅምን ማፈሰስን ይሰብካል፣ ልታይ ልታይ አለማለትን ያውጃል፣ በልክ መኖርን ሆኖ ያሳያል፣ ውስጥን ሆኖ መዝለቅን ያትምበታል፣ ለህግ መገዛትን ያስነብባል፣ ማድመጥን ይሰጣል፣ መጠበቅን ያጠጣል፣ መክደነን በገፍ ያቀናል። ለዚህም ነው ጀግናው ረዳት /አውሮፕላን አብራሪ ኃይለመድህን አበራ ዓለምን በግራሞት በአስደመመው ትዕይንት በኋላ እንኳን አንድም ፎቶ ማግኘት ያልተቻለው እንኳንስ እራፊ ዜና። ሚስጥርነቱንም፤ ልቅናውንም ሆነ ብቃቱንም ሳስበው እኔ በግሌ ሲዊዘርላንድ በልኩ የተዘጋጀት የሥደት ጊዜውን ሱባኤ በጽናት የሚከውናባት ገዳማዊ ሀገሩ ናት እላለሁ። መንፈሳዊ ህይወት ዳር ድንበር የለውምና። ልኩ ናት ሲዊዝ።

የዛሬው ሰላማዊ ሰልፍ ታዳሚዎች ውስጥ እንዲህ ይነበባል። ሃይለመድህን ነፃነት ታሪካችን መጸሐፍ ነው፤ አርማችን ለነፃነት ፍለጋ የወሰደው እርምጃ ለአንባገነን አልገዛም በማለት የእንቢተኝነት ሰላማዊ እርምጃ አግባብ ነው፤ ድምጹ ድምጻችን ነው። የሲዊዝ መንግሥት እስካሁን ላደረገለት እንክብካቤ እያመሰገነን ለነፃነት አረበኛችን የመኖሪያ ፈቃድ ዕውቅና ይስጥልን፤ ድህንነቱንም ይጠብቅልን። የፖለቲካ ጥገኝነት ጥያቄው አግባብ ያለው መልስ ይሰጠው በማለት አቅም ባለው ድምጽ በፈረንሳይኛ፤ በጀርመንኛና በእንግሊዘኛ ወለዊ ስሜታቸውን እጅግ በሚመስጥ ወገናዊ ስሜት የእድሜ የፆታ፤ የሃይማኖት ልዮነት ሳይገድባቸው በጸደቀው ማንታቸው አብነት ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሲያሰሙ ነበር የዋሉት።

ሰልፈኞቹ በሀገራችን በኢትዮጵያ ያለውን ኢፍትኃዊ የሽፍታ አመራር፤ የጥቂት ብሄርተኛ ቡድን መሪ የሆነው የወያኔ አስተዳደር የሚያደርሰውን ሰባዕዊ ጭቆናና አንባገነናዊ አገዛዝንም ስለመሆኑ በመስማማት በአኃታዊ ስሜት ገልጸዋል። ሲዊዝ የሚኖሩ ኢትጵውያን ጀግናቸው የነፃነት መሪያቸው ከመሆን ባሻገር ከምንም ዓይነት የወንጀል ተግባር ጋር የተያያዘ ታሪክ አለመኖሩን በመግለጽ አሸባሪው የወያኔ ኃርነት ትግራይ አስተዳደር ነው ሲሉ ሥልጣን ላይ ያለውን የቲፒኤልኤፍን አስተዳደር አጥብቀው አውግዘውታል። በተጨማሪም ወያኔ ገዳይ ነው! ወያኔ ፋሽስት ነው! ወያኔ አፋኝ ነው! በማለትም በጉልበታም ድምጽ በወያኔ አስተዳደር ያላቸውን ግልጽ አቋምና ጥላቻ በአንድ ድምጽ አሰምተዋል። ከዚህም ሌላ በኢትዮጵያ የአኩልነት፤ የነፃነት የህግ የበላይነት ምክነት በማውሳት ከቶውንም ምልክት የማይታይበት መሆኑን አበክረው ገልጸዋል። ነፃ ጋዜጦኞች፤ የስብዕዊ መብት ተሟጋቾችና የፖለቲካ መሪዎች በእስር ላይ እንደሚገኙም በመግለጽ ኢትዮጵያም እስረኛ ስለመሆኗም አክለው በወላዊ ድምጽ አሰምተዋል። በሌላ በኩል ቀደም ሲል ሀገራችን የሥልጣኔ ምንጭና የታሪክ እንብርት ስለመሆኗም በውስት ገልጸዋል።

እኔም እንደማምንበት ለዘመኑ ለዛሬ ለነገም የተስፋ ብሩኽ ጮራ ረዳት አውሮፕላን አብራሪው ኃለይለመድህን አበራ ለነፃነት ፈላጊ ቤተሰቦች ሁሉ የመንፈስ ቋንቋችን ነው። ብልሁ ወጣት ዓለም ያጸደቀውንና የደነገገውን የታህሳስ 10 ቀን 1948 የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ሰብዕዊ መብት አከባበር 30 አንቀፆች መርሆ አባል ሀገሮች ምን ያህል ተፈጻሚ እንደ አደረጉት እንደገና ይከልሱት – ይፈትሹት ዘንድ በዝምታ ተግባር የቤት ሥራ ሰጥቷቸዋል። በስክነት በድርጊት ፍሬዎቹ አስገነዝቧል። የድንቅ ቁንጮ ገድለኛ ወጣት መንፈስ ስለ ሰብዕዊ መብት የተደነገጉት ባለ 30 አንቀጻት በአንባገነናት ምን ያህል ጫና እንዳለበቻውና እንደሚጠቀጠቁም በማሳሰብ በትህትና እንደገና ለመመርምር ጉባኤ እንዲቀመጡ ለሊቃነቱ መከሯል ።

ከዚህ በተጨማሪም ረዳት አውሮፕላን አብራሪ ኃይለመድህን አበራ ለሲዊዝ መንግሥት የአዬር ጥበቃውን ሥርዓት አስምልከቶም ትኩረት እንዲሰጠው ነግሯል። በሌላ በኩል እንደነዚህ ያሉ ያልተለመዱ ክስተቶችን እንዴት ሲዊዞች ሊያስተናግዱ እንደሚችሉም ሰፊ የማስተዋል መስክ ከፍቶላቸዋል። ከዚህ ሌላ ኢትዮጵውያን መከራችን አላለቀምና፤ እነ ከልታሜ በሀገራችን ተሰደን፤ በስደትም ተሰደን ባላቤት አጥተን መንከራተታችን እውቅና እንዲያገኝም ሰፊ የዋቢነት አኩሪ ተግባርም ፈጽሟል። ከሀገር ሀገር ለምንከራተተው ወገኖቹ እንደ አናንያን እንደ ሚሳኤል እንደ አዛርእያን ለነፃነታችን እራሱን ሰጠ። ብዙ ነገር እንደሚያጣ ቢውቀውም ፍቅርን እንደ እናት በተግባር ተረጎመ። እግዚአብሄር ይስጥልን። የተባረኩና የተቀደሱ ምስጉን ቤተሰቦችህንም እንዲህ ያለ ጠበቃ ወልደው ተንከባክበው አሳድገው ስለ ሰጡን እናመስግናለን።

ታላቅ ማሳሰቢያ።

ጀግናችን! ነፃነትን የተራቡ ህዝቦች በዬትኛውም መስክ፤ በዬትኛውም ሁኔታ ብሶታቸውን፤ እንቢተንነታቸውን ሊገልጹበት የሚችሉበት መንገድ ህግና ሥርዓት ሊደነገግለት እንደማይችልም ኮሽ ሳያደርግ ካለምንም ግድፍት ለሰው ልጆች ህይወት ያለውን ጠንቃቃ ተፈጥሮም አሳይቷል። ይህ ድርጊትና አፈጻጻም እያንዳንዱ የዐለም ህዝብ ሊታደምበት የሚገባ ይመስለኛል። ወያኔም እራሱ ለፍትህ አሰጣጡ በአዎንታዊ ረድፍ መሰለፍ አለበት ህሊና ካለው።

ዓለም ጉዞ ላይ ናት። እኔ ባልጓዝ ቤተሰቤ ይጓዛል። ቤተሰቤ ባይጓዝ እኔ እጓዛለሁ። ወይንም ሁለታችንም። ስለዚህ ለባለመክሊቱ ረዳት አብራሪ የሚሰጠው የርትህ መልስ ዓለምን ለነገ የሚያድን ወይንም የሚገድል ይሆናል። ልድገመው ለባለመክሊቱ አውሮፕላን ኢትዮጵያዊ ረዳት አብራሪ የሚሰጠው የርትህ መልስ ዐለምን ነገ የሚያድን ወይንም የሚገድል ይሆናል። ስለምን? ነገ በዬትኛውም ጊዜና ሁኔታ ዬትም ሀገር መሰሉ ተግባር መፈጸሙ አይቀሬ ነው።

የአስተዋዩ ረዳት አብራሪ ኃይለመድህን አበራ ሁለት ግልጽና ጥያቄ አሉታዊ ምላሽ ከተሰጠው፤ ተጓጓዥን ሆነ አውሮፕላኑን ለመታደግ እጅግ ዓለም ይከብዳታል። በስጋትም ትወረራለች – ። ከጉዞ ውጪ አለም አትታሰብምና። ትርፉ አዬር ላይ አመድ ማፈስ ብቻ ይሆናል ተስፋውም። ህይወትም ንብረትም አይተርፍም። ስለዚህ እያንዳንዱ ዬዐለም ዜጋ፤ ዓለም አቅፍ ድርጅቶች፤ አህጉር አቀፍ ድርጅቶች፤ የዬሀገሮች አስተዳደሮች ሁሉ በተደሞና በአንክሮ ሆነው በባለቤትነት ስሜት ለጥያቄው ተገቢውን አዎንታዊ ምላሽ ለመስጠት መሰናዳት የግድ ይኖርባቸዋል።

በመጨረሻ ከሐሤቴ በላይ ሐሤቱ ብርኃን ኃይለመድህን አበራ በህይወት መኖሩ። ከዚህ አንፃር መላመቶችን ሁሉ መልክ ሊየስዝ የሚችልበትን ቀንና ሰዓት መጠበቅ ሁላችንም ግድ ይለናል። እንኳንስ እኛ የወለዱት ወላጆቹ ይህ ቅብዕ ጸጋ መክሊት ዕንቡጣቸው ስለመኖሩ ሆነ ውስጡን ስለማወቃቸው የሚያውቀው መዳህኒዓለም አባታችን ብቻ ስለሆነ የተከደነ ሲሳይን እራሱን እራሱ እስኪተረጉምልን ድረስ አደቡን ይስጠን ለሁላችንም። አሜን!

ጀግናችን አጀንዳችን!
ጀግናችን ረዳት አውሮፕላን አብራሪው ኃለመድህን የነፃነት ሐዋራያችን ነው!
ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ነው።
ሲከር ይበጠሳል ሲሞላም ይፈሳል!

ሥነ ግጥም — ከሰላማዊ ሰልፉ ላይ በገጣሚ ነጂብ አሊ የቀረበ ነው። ለዚህም ነው በትምህርተ – ጥቅስ ውስጥ የገባው የእኔ አይደለምና። አመሰግንለሁ የኔ ውድ ሸበላ ወጣት – እመቤቴ!

የሰላማዊ ሰልፉ – ፎቶ በአቶ ሚሊዎን።

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

1 Comment

Comments are closed.

Previous Story

የ 91 ሚሊዮን ህዝብን ድምፅ ያፈነው መንግስት! (ከገብርሃልሁ ተሰፋዬ)

1959213 10203351622850970 1144408807 n
Next Story

በኖርዌይ የሚገኙ ኢትዮጵያኖች በዛሬው እለት ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ (ከገዛኸኝ አበበ ኖርዌይ)

Latest from Blog

አዲስአበባ ተኩስ ተከፈተ “ለመደራደር ዝግጁ ነን” አረጋ ከበደ | አብይ አደገኛውን ካርድ መዘዙ | አዲሱ አዋጅና የቀረበበት ተቃውሞ “የሞተም ሰው ንብረት ይጣራል | ጌታቸው ያጋለጠው ጸብ

አዲስአበባ ተኩስ ተከፈተ “ለመደራደር ዝግጁ ነን” አረጋ ከበደ\  አዲሱ አዋጅና የቀረበበት ተቃውሞ “የሞተም ሰው ንብረት ይጣራል አብይ አደገኛውን ካርድ መዘዙ ጌታቸው ያጋለጠው ጸብ

ከመጠምጠም መማርን እናስቀድም!

;በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com) አብዛኛው አንባቢ ተገንዝቧል ብዬ እንደምገምተው ሕዝብ ለቡና ቲራቲም፣ ለግብዣ፣ ለበዓል፣ ለሰረግ፣ ለሐዘን፣ ለእድር፣ ለእቁብ ለውይይትና ለሌሎችም ማህበረሰባዊ ጉዳዮች ሲገናኝ የሚበዛው አድማጭ ሳይሆን ተናጋሪ  ወይም ደግሞ ለመናገር  መቀመጫውን ከወንበር ወይም
Go toTop