የሩሲያ ወታደሮች ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ዩክሬን መግባታቸውን የአገሪቱ የድንበር ጥበቃ ኃይል አስታወቀ።

February 24, 2022

60894179 303ታንኮችን ጨምሮ በርካታ የሩሲያ ከባድ መሣሪዎች በክሬሚያ እና ሌሎች የሰሜን ዩክሬን ግዛቶች ድንበር ማቋረጣቸውን የዩክሬን የድንበር ጥበቃ ኃይል ዛሬ ሐሙስ ይፋ አድርጓል። ሩሲያ ክሬሚያን በኃይል ከዩክሬን የገነጠለችው ከስምንት አመታት ገደማ በፊት ነበር። የዩክሬን የድንበር ጥበቃ ኃይል አገሪቱ ከክሬሚያ በምትዋሰንበት አካባቢ አንድ አባሉ መገደሉን አረጋግጧል።

የጸጥታ ጥበቃ ካሜራዎች ከክሬሚያ የሩሲያ ጦር ተሽከርካሪዎች ወደ ዩክሬን በሰልፍ ሲሻገሩ አሳይተዋል። የሩሲያ ወታደሮች ዛሬ ሐሙስ በዩክሬን ላይ ሰፊ ጥቃት መጀመራቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።

ኪየቭ፣ ኻርኪይ እና ኦዴሳን በመሳሰሉ የዩክሬን ከተሞች ከባድ ፍንዳታዎች የተሰሙ ሲሆን የዓለም መሪዎች “የከፋ ጉዳት ያስከትላል” ያሉት ወረራ መጀመሩን እየተቃወሙ ነው። የዩክሬን ዜጎች ከአንዳንድ ከተሞች መሸሽ እንደጀመሩ አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል። በዘገባው መሠረት የሩሲያ ጦር የዩክሬን የአየር መቃወሚያዎች እና አየር ኃይል በሰዓታት ውስጥ ከጥቅም ውጪ አድርጊያለሁ ብሏል።

ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለገጠማቸው ውግዘት፣ ማዕቀብ እና ዛቻ ቁብ ያልሰጡት የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ሌሎች አገሮችን ጣልቃ ለመግባት የሚደረግ ሙከራ “አይታችሁት የማታውቁትን ዳፋ ያስከትላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ሩሲያ የዩክሬን ወታደራዊ የጦር ሰፈሮች ላይ እንዳነጣጠረች የገለጹት የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ በአገሪቱ ወታደራዊ ሕግ ደንግገዋል። መቼ እንደሆነ በግልጽ ባይነገራቸውም ሩሲያ ጥቃት ልትሰነዝር እንደምትችል ከዚህ ቀደም ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው የዩክሬን ዜጎች በመኖሪያ ቤታቸው እንዲቆዩ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል።

የጀርመኑ መራሔ-መንግሥት ኦላፍ ሾልስ “ሩሲያ በዩክሬን ላይ የሰነዘረችው ጥቃት በግልጽ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን የሚጥስ ነው። ምንም አሳማኝ ምክንያት የለውም” ብለዋል። የፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን መንግሥት የወሰደውን እርምጃ “ግድ የለሽ” በማለት የነቀፉት ሾልስ ከዩክሬን እና ከሕዝቦቿ ጎን እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል።

የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ኡርሱላ ፎን ደር ላየን የሩሲያን እርምጃ አውግዘው የፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲንን መንግሥት ተጠያቂ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል። የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በበኩላቸው ፑቲን “የደም መፋሰስን መንገድ መርጠዋል” ብለዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በሩሲያ ላይ አዲስ ማዕቀብ እንደሚጥሉ ቃል ገብተዋል። የሩሲያው ፕሬዝደንት በአገራቸው የቴሌቭዥን ጣቢያ ባደረጉት ንግግር ጥቃቱ በምሥራቃዊ ዩክሬን የሚገኙ ሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት ለመጠበቅ አስፈላጊ ነው የሚል ማመካኛ አቅርበዋል። አሜሪካ የሩሲያው ፕሬዝደንት ዩክሬንን ለመውረር እንዲህ አይነት ምክንያት እንደሚያቀርቡ አስቀድማ አስጠንቅቃ ነበር።

ፑቲን ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን በእንግሊዝኛ ምህጻሩ ኔቶ አባል እንዳትሆን እንዲሁም የጸጥታ ማረጋገጫ እንዲሰጡ ሩሲያ ያቀረበችውን ጥያቄ አሜሪካ እና አጋሮቿ ቸል ብለዋል ሲሉ ከሰዋል።

DW

Leave a Reply

Your email address will not be published.

127724
Previous Story

ዳያስፖራ ምሁራን በኢትዮጵያ ጉዳይ አፍቸው ለምን ለጎሙ? ዶክተር አክሎግ ቢራራና ዶክተር ወንድሙ የዝምታችንን ምክንያቶች እንናገራለን ይላሉ

274693661 5037843199615243 12591156626060572 n
Next Story

ሽኔ እና መንግስት ያፈናቀሏቸው እናቶች፤ የጸለዩላችሁ እናቶች እያለቀሱባችሁ ነው – ያሬድ ሃይለማሪያም

Go toTop