ሁልጊዜ ወገንተኝነታችን ከኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ጋር ይሁን!

ኢትዮጵያችን በየትኛውም የታሪክ እጥፋቶቿ ላይ ሕዝቧ በሚከፍለው መስዋዕትነት ደግማ ደጋግማ ስትፀና እና ስትበረታ እዚህ ደርሳለች፡፡ የሚዋደቁላት እና የሚሰዉላት ልጆች ስላሏት እንጂ መበርታቷ የአጥፊዎቿ ዕቅድ ቀላል ስለነበረ አይደለም፡፡ ሀገራችን ባለሩህሩህ እጅ ደግ፣ ባለብርቱ ክንድ ጀግና እናት ናት፡፡ ጠላቶቿን ማንበርከክ እንዲሁም ምርኮኞቿን መደገፍ ታውቅበታለች፡፡ እንኳን ከአብራኳ ለወጡ ልጆቿ፣ በስደት ደጅ ለጠኗት ከድህነቷ ላይ ቆርሳ ከልጆቿ ጉሮሮ ነጥቃ መስጠትን ትችልበታለች፡፡ ለሀገሬው ሕዝብ ደግነት እና ምህረት አዲስ የሚሰበኩለት እሴቶች ሳይሆኑ ወግ እና ልማዶቹ ናቸው፡፡ ተገዶ ጭንቅ ሆኖበት፣ ልጆቹ ታርደው፣ ተደፍረው እና ተገለውበት፣ ንብረቱ ወድሞበት፣ ቀና እንዳይል ዳዋ ጭነውበት እንጂ ሰላም ጠል ስለሆነም አይደለም ጠብ መንጃ ማንሳቱ፡፡ ሁላችንም ላይ የመጣን ስጋት ለሕይወቱ ሳይሳሳ የመከተው የኢትዮጵያ ኃይሎች ጥምረት ሰላምን ለማምጣት የመጨረሻውን አማራጭ ጦርነትን መጠቀም ግድ ሆኖበት መንግሥትም አሰማርቶት ነው እስከ ሕይወት መስዋዕትነት የተዋደቀው፡፡ ጭንቅ ውስጥ ሳለን የተዋደቁልን የኢትዮጵያ ልጆች ዘመን የማይሽረው ውለታቸው እያበራ ይኖራል፡፡ ሀገራችን በግድ ከገባችበት ጦርነት ወጥታ ሕዝቧ በሰላም የሚኖርባት እንድትሆን ከሁላችንም የሚጠበቅ ሆደ ሰፊነት እና ጥረትን ይጠይቃል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ታህሳስ 29 ቀን 2014 ዓ.ም በሕግ ጥላ ስር የነበሩ ሰዎች በክስ ማቋረጥ የተለቀቁት በእነሱ አነሳሽነት የተቀጠፉ ሕይወቶች ቁስል ባልሻረበት እና የወደሙ አካባቢዎች እስካሁን ባላገገሙበት ሁኔታ ነው፡፡ ወደዚህ ጦርነት ከመግባታችንም በፊት ሕዝባችን በሀገሩ እና በምድሩ ባይተዋር እና የተገፋ ሆኖ እንዲኖር ያደረጉት ብዙ ኃይሎች መኖራቸውን ለአፍታም አንዘነጋም፡፡ ኢትዮጵያ እኔ የምፈልገውን ካልሆነች ትጥፋ በሚሉ ኃይሎች ምስኪኖች መከራቸውን ሲበሉ ኖረዋል፡፡ ሕይወት ተቀጥፏል፣ ሕዝብ ተፈናቅሏል፣ ብዙም ሰቆቃ በምድራችን ታይቷል፡፡ ፀፀት ይቅርታን ትቀድማለች፤ ፍትህ ደግሞ የሁላችን ተስፋ የአብሮ መኖራችንም ማስተማመኛ ውል ነች፡፡ ተበዳይ ፍትህ ሳያገኝ እንዲሁም ሳይካስ በዳይን ነፃ ማውጣት በፍትህ ስርዓቱ መቀለድ፣ የሕዝባችንን ጉዳትም ማቃለል ነው፡፡ እንደዚህ በጥድፊያ የሚደረጉ ውሳኔዎች ፍትህን በመጨፍለቅ በተቋማቱ ላይ ያለንን እምነት በሂደት የሚሸረሽሩ ናቸው፡፡

እንዲህ ያለ ከሕዝብ ጋር ምክክር የጎደለው ግብታዊ እርምጃ የሀገር ባለቤትነት እና መብትን ለአመፀኛው፣ የፈለገው ነገር እስካልተፈፀመ ድረስ ሀገር ብትጠፋ ከቁብ ለማይቆጥረው እና የሕዝቧ ስቃይ ግድ ለማይሰጠው ኃይል አሳልፎ ይሰጣል፡፡ የፈለጉትን ለማስፈፀም እና ለመከወን አመፅ ትልቁ መሳሪያ እንደሆነ አሁንም አስረግጦ ያልፋል፡፡ በዚህ ውስጥ ሰፊውና በሀገሩ ክብር መነካት ጨርቄን ማቄን ሳይል የተመመውን ሕዝብ ሀገር አልባ እና መብት የሌለው ያደርገዋል፡፡ አመፀኝነትን የሚያበረታ እና መከፋፈልን የሚያጠነክር እጅጉን አሳሳቢ ተግባር ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ብዙ ንፁሀን “ከሽብር ቡድኑ” ጋር ንክኪ አላቸው ተብሎ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ታስረው በሚገኙበት እንደ ፓርቲም በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ አባላቶቻችን ላይ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተገን በማድረግ እስር እና ማንገላታት እየተፈጸመ ባለበት እኛም ከሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር በትዕግስት ምርመራ ተደርጎ ዜጎች እንዲፈቱ ጥረት እያደረግን ባለበት ወቅት ነው፡፡ አሁንም ንፁሃን ተጣርቶ በአስቸኳይ እንዲለቀቁ እናሳስባለን፡፡ የፍትህ ስርዓቱም በደመነፍስ ከመሰራት ተሻግሮ ለዜጎች ፍትህን የሚያሰፍን ሆኖ ሊደራጅ ይገባዋል እንላለን፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ረቡዕ፡-ከምሽቱ ሦስት ሰዓት የአማርኛ ዜና

በሰሜኑ ሀገራችን ክፍል ላለፈው አንድ ዓመት በተካሄደው ጦርነት ብዙ ጥፋቶች እና ውድመቶች መከወናቸው እሙን ነው፡፡ ቁጥራቸው ብዙ የሆነ ሰላማዊ ዜጎች ይሄ ነው የማይባል መከራን አሳልፈዋል፤ እያሳለፉም ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ታህሳስ 15 ቀን 2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ከጦርነቱ ጋር የተያያዘ ድርድርን እና ሀገራዊ ምክክር ተደበላልቀው እንዳይሄዱ ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡ አሁን በግልፅ እየታየ እንደመጣው ሁለቱን ጉዳዮች አጣብቆ ማምጣት መንግሥት ሆን ብሎ እየተከተለው ያለ መንገድ መሆኑን ነው፡፡ ሃገራዊ ምክክሩ ለዘመናት የቆዩ ችግሮቻችንንም ጭምር የምንፈታበት በመሆኑ ይህ በዘመናት አንዴ የሚገኝን ዕድል ወቅታዊ ችግሮችን ብቻ እንዲፈታ አድርጎ መጠምዘዝ ከትርፉ ኪሳራው ያመዝናል። አሁን መንግስት እየሄደበት ያለው መንገድም ሀገራችን ውስጥ በተደጋጋሚ መጥተው የከሸፉ የለውጥ ጭላንጭሎችን ዕጣ ፈንታ መልሶ ከመድገም ውጪ የሚያመጣው ዘላቂ ጥቅም አይኖርም፡፡ መንግሥትም እንደ ሀገር የገባንበትን ችግር እንዲፈታ ድጋፍ አደርጋለሁ ብሎ በአንድ የተሰለፈውን ኃይል ባይተዋር ባደረገ መልኩ በሂደቶች ላይ ካድሬዎቹን ብቻ እያወያየ ሕዝብ እንደመከረባቸው የሚደረጉ ቅጥፈቶች በፍጥነት መታረም አለባቸው፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት ከገባችበት ክፉ ድግግሞሽ እና አዙሪት መውጣት አለባት በሚለው ከተስማማን ብዙ ላያስደስቱን እና ሊያሙን የሚችሉ ውሳኔዎች ከፊታችን በብዛት እንዳሉ ማወቅ እጅጉን ወሳኝ እና አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህም ልንከፍል የሚገባንን ሁሉ ለዘላቂ ሰላም እና የሀገር አንድነት ስንል ለመክፈል ዝግጁ መሆን ከሁላችንም የሚጠበቅ ለሀገራችን የሚሰጥ ስጦታ ነው፡፡ ነገር ግን መንግሥት እጅግ የማይገመቱ እና ሀገሪቷን እና የሕዝቧን የትኩረት አቅጣጫ በእጅጉ የሚያስቅይሩ ኃላፊነት የጎደላቸው እና ከማን አለብኝነት የሚነሱ ተግባራትን ከመፈፀም በፍጥነት እንዲቆጠብ እናሳስባን፡፡ ሀገራችን ላይ የተከፈተባት ጦርነት ሕዝቧም የሚከፍለው መስዕዋትነት ገና ባልተቋጨበት ጦርነቱ አንዳለቀ ተደርጎ መቅረቡ ዜጎችን በማዘናጋት ከቀድሞው የከፋ መስዋዕትነት እንዳይጠይቀን ይህ አካሄድ ስህተት በመሆኑ ታርሞ አሁንም ስጋት ያለባቸውን አካባቢዎች በንቃት መጠበቅ ላይ ሊተኮር ይገባል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአቢይ አህመድ አገዛዝ በአማራ አራቱም አቅጣጫዎች አዲስ ዙር ጥቃት ከፈተ

የኢትዮጵያውያንን አብሮ መኖር ለማረጋገጥ በዚህ ጦርነት የመጀመሪያው ገፈት ቀማሽ የሆኑትን የሀገራችን አካባቢዎች ማቀራረብ እና ብሔራዊ እርቅን መፈፀም እጅጉን ወሳኝ ቢሆንም በየአካባቢው ያለው ሕዝብ ትኩስ ሬሳን ተሸክሞ ባለበት፣ የሚፈሰው ደሙ ባልረጋበት፣ የተደፈሩ እናቶች፣ እህቶች እና ልጆች ከስቃያቸው ባላገገሙበትና የተፈናቀሉ ወገኖች ወደቀያቸው ባልተመለሱበት በአጥፊነት ተጠርጥረው እና በጦር ግንባር ተይዘው በሕግ ጥላ ስር ያሉ ሰዎችን ክስ ማቋረጥ እና ምህረት ብሎ በዳይን መካስ እጅግ የሚያስቆጭ እና የሚያንገበግብ እውነት ነው፡፡ መንግሥት ከዚህ ድርጊቱ መቆጠብ ብቻ ሳይሆን በይፋም ይቅርታ መጠየቅ ይኖርበታል፡፡

በአሁን ሰዓት ትልቁ የሀገራችን አጀንዳ ከገባንበት ቅርቃር መውጫችን ሃገራዊ ምክክር ነው፡፡ ስለዚህም መንግሥት እና የመንግሥት ሚዲያዎች ለጉዳዩ እጅግ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው አለመሥራታቸው ለታይታ ከሚደረጉ ነገሮች በዘለለ መላውን ሕዝብ ያሳተፈ እውነተኛ ምክክር እንዲደረግ ቆራጥነት እንደሚጎድል ማሳያ ነው፡፡ ይልቁንም መንግሥት ሂደቱን ለመጥቀም ነው እያለ የሚፈፅማቸው አንዳንድ ተግባራት ሂደቱ ላይ ትልቅ ጠባሳ ሊጥሉ እናም ወደ ኃላ ሊጎትቱት የሚችሉ ተገማች ያልሆኑ ውሳኔዎች ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነት አካሄዶች ሂደቱ በከፍተኛ ሁኔታ በመንግሥት ተፅዕኖ ስር እንዲገባ ስለሚያደርገው በፍጥነት እንዲታረም መንግሥትን እናሳስባለን፡፡ መላው ኢትዮጵያውያንም ከዚህ ሂደት ሀገር እንድታተርፍ ከመጓተት ወጥተን ለተግባራዊ ስራ መዘጋጀት እና በየምዕራፎቹ ንቁ ተሳትፎን ማድረግ ይኖርብናል፡፡

በሀገራዊ ምክክር ሂደት በዝግጅት ምዕራፍ ወቅት ሊደረጉ ይገባቸዋል ከሚባሉ ተግባራት መካከል አንዱ በተሳታፊዎች መካከል እና በማኅበረሰቡም ውስጥ መተማመን እንዲኖር ማድረግ አንዱ ነው (trust-building)። ይህንን መተማመን ሊጎዳ እና ቅሬታ ሊጭር በሚችል መልኩ በሀገራዊ ምክከሩ ላይ ተሳታፊዎችን እና አጀንዳዎችን የሚወስነው ተብሎ ሥልጣን የተሰጠው ሊቋቋም ያለው ኮሚሽን ሆኖ ሳለ መንግሥት በቅርቡ ከእስር የፈታዋቸውን ሰዎች የፈታዋቸው በሀገራው ምክክር ሂደቱ እንዲሳተፉ ነው በማለት ከወዲሁ ተሳታፊዎቹን እየመለመለ ይገኛል፡፡ በሀገራችን ያሉ ድምፆች ሁሉ መደመጥ እንዳለባቸው ብንገነዘብም ይህ አይነት የመንግስት ድርጊት በአጠቃላይ በሂደቱ ላይ ሊያሳድር እየፈለገ ያለውን ተፅዕኖ በግልፅ የሚያሳይ ሲሆን ከመሰል ተግባራት እንዲቆጠብ በጥብቅ እናሳስባለን፡፡ ይህ የሃገራዊ ምክክር ሂደት ሁላችንንም የሚወክል እንዲሆን በዚህ ሂደት መንግሥት ከሚኖረው ሥልጣን እና ኃላፊነት ውጪ እየወጣ ሂደቱ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን በፍጥነት ማቆም ይኖርበታል፡፡

የተወደዳችሁ የኢትዮጵያ ዜጎች፣ ሀገሬ ተነካች ብላችሁ ቤት ንብረት ቤተሰባችሁን ጥላችሁ «ሆ!» ብላችሁ የተመማችሁ ኢትዮጵያውያን፣ የመስዋዕትነታችሁ ፀዳል እያበራ ቆመን እየሄድን ያለን እኛ ኢትዮጵያውያን የመስዋዕትነታችሁ መሰረት የሆነውን የሕዝብን በአንድነት እና በነፃነት መኖር ለአፍታም ሳንዘነጋ በደም እና አጥንታችሁ ላይ ቆመን የሀገራችንን ቀጣይነት እና የሕዝቧን ነፃነት ለማረጋገጥ ቃልኪዳናችንን እናድሳልን፡፡ መዋደቃችሁ ባመጣልን ዕድል አንቀልድም፡፡ ያለ እናንተ መስዋዕትነት በዚህ ሰዓት ሀገር አልባ ምስኪን ሕዝቦች ሆነን የብዙዎች ፈራሽ ሀገራት ዜጎች የደረሳቸው እጣ ፈንታ በደረሰን ነበር፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከሕወሓት ባለስልጣናት ጋር ባለው ትስስር የከበሩ ማዕድናትን ከዱባይ ወደ አዲስ አበባ ሲያዘዋውር የተያዘው ግለሰብ ተፈረደበት

በእናታችሁ ባንዲራ ስር የተሰባሰባችሁ ውድ ኢትዮጵያውያን፣ መቼም ቢሆን በእናት ተስፋ እንደማይቆረጥ መዘንጋት የለብንም፡፡ ሀገራችሁን ከማበርታት፤ የተጎዳውን ሕዝቧን ከመደገፍ አትቆጠቡ፡፡ በተለያዩ የተሳሳቱ የፖለቲካ ውሳኔዎች አሁን ያለንበት ቅርቃር ውስጥ አለን፡፡ ተደጋጋሚ የማያባራ መከራ ምስኪኑ ሕዝባችን ሲሸከም መኖሩ ሳያንስ አሁንም መከራውን የሚያረዝሙ ውሳኔዎች እዚህም እዛም ይወሰናሉ፡፡ ትግሉ መራር ጉዞውም አድካሚ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ መዓት ለመውጣት ስር ነቀል ለውጥን ማምጣት ይጠበቅብናል፡፡ ጥሪያችንም በአንድ በኩል ከሊቅ እስከ ደቂቅ ትክክል ያልሆኑ ውሳኔዎችን በንቃት እየተከታተልን እና እንዲታረሙ እየጠየቅን በሌላ በኩል ደግሞ የሀገራዊ ምክክሩ ሂደት በጥቂት ኃይሎች እንዳይዘወር እና አሁን እንደገባንበት ዓይነት የፖለቲካ ምስቅልቅል ውስጥ የሚከተን ውጤት ይዞ እንዳይመጣ የበኩላችንን እንድንወጣ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ ባነሰ መስዋዕትነት እጅግ የገዘፈ ድልን ማስመዝገብ እንችላለን እና አይናችንን ከኳሷ ላይ ሳናነሳ እንጓዝ፡፡

ውድ ኢትዮጵያውያን፣ አሁን መሰባሰባችንን የምናጠናክርበት እና ኃይላችንን የምናድስበት እንጂ የምንዝልበት እና የምንደክምበት ጊዜ አይደለም፡፡ የችግሩ መሀል ላይ ነን፡፡ ብዙ ሥራ ይጠብቀናል፡፡ ብዙ ሰጥቶ መቀበሎች ከፊታችን አሉ፡፡ ዳግም የማንገዳደልባት ሀገር ለመሥራት ዛሬ በሀሳብ ልንሸናነፍባት ግዴታ ነው፡፡ ሀገሪቷ ላይ ያሉ ሀሳቦች በሙሉ ወደጠረጴዛ መምጣት አለባቸው፡፡ ማንም ከዚህ ሂደት መቅረት የለበትም፡፡ ሙግታችን እና ትግላችን መጪው ትውልድ እኛ እንደኖርነው እና እንዳሳለፍነው ዓይነት ኑሮ እንዳናስረክበው ነው፡፡ ይህ ሀገራዊ ምክክር ከቅርቃራችን የምንውጣበት ሁነኛ መሣሪያ እንዲሆን እንሥራ፡፡ ጠላቶቻችን ሀገር ላይ ያሴሩትን ሴራ ላንዴ እና ለመጨረሻ በሕዝቧ ውሳኔ እንቅበረው፡፡

ውድ የሀገራችን ሕዝብ ሆይ፣ አሁንም ወገናችን እየተራበ የፈረሱት መሰረተ ልማቶቹ እንደወደሙ ነው፡፡ አሁንም በተደራጀ መልክ ወገናችንን መደገፍ እና መልሰን ማልማት የውዴታ ግዴታችን እንደሆነ ሳንረሳ ተሰባስበን እና ተጠናክረን ወገናችንን መደገፍ እንቀጥል፡፡ ሁልጊዜ ወገንተኝነታችን ከኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ጋር ይሁን፡፡

ጥር 1 ቀን 2014 ዓ.ም

የኢዜማ ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

አዲስ አበባ

ኢትዮጵያ

2 Comments

  1. ኢዜማ ግምቦቶች ኢሳቶች ምን አለ ለጊዜው ዝም ብትሉ እዚህ ፖለቲካ ውስጥ በጣም የናጠጣችሁ አልመሰላችሁም? እኛ ነገር ተምታቶብናል የመርጋጊያ ጊዜ ስጡን። ለብርሀኑም ልደቱ ሊመጣልህ ነው እቃህን ሸክፍ

  2. It is terribly painful to witness this kind of political stupidity and moral bankruptcy in this 21st century Ethiopian politics!
    What does to stand with Ethiopia and Ethiopiawinet mean in the real sense of the terms? Do these guys of the so-called EZEMA have any credible and sensible political gut and moral capacity?
    Who betrayed and abandoned the very principle and objective of bringing about fundamental democratic change three years ago and became very ugly speaking tools of the very dishonest, disgraceful, cynical, hypocritical, conspiratorial, cowardice and brutal ruling elites of the very backward and deadly politics of ethnocentrism who renamed themselves as Prosperity which is of course an insult to the people of Ethiopia who hoped for the better after paying huge and bitter sacrifices but had to face a huge and horrifying betrayal ?
    Was it not and is it not self-evidently true that these guys of so-called EZEMA who became parts and parcels of the very devastating betrayal being committed by the EPRDF faction that took over the palace politics led by an extremely deceptive, cynical, mischievous, politically infantile, chronically narcissist and above all brutal (no regret for what he horribly did and does) prime minister?
    Can these guys of so-called EZEMA tell us why and how it is and will be possible to stand with Ethiopia and Ethiopiawinet in a political arena (environment) terribly poisoned or polluted by the very unholy and deadly toxic political alliance of Abyi Ahmed’s ruling circle and themselves?
    Is this not an extremely disturbing insult to the very basic knowledge of the people?
    Is this not an attempt of dehumanization of the innocent people of Ethiopia?
    I hate to say but I have to say that these guys of so-called EZEMA are one those political groupings which have made themselves terribly if not deadly nonsensical as far as the very hard reality of Ethiopian politics on the ground is concerned!
    They have made the very political struggle of the Ethiopian people for the realization of genuine democratic system extremely difficult as they allowed themselves to be puppets of the ruling merchants of the very ugly and mutually destructive political system of ethnocentrism! Sad and sad!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share