ለቸኮለ! ሰኞ ታኅሳስ 25/2014 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የዕጩ ኮሚሽነሮች ጥቆማ ለመቀበል ያቋቋመው ሦስት አባላት ያሉት ኮሚቴ የዕጩዎችን ጥቆማ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጥር 6 ድረስ እንደሚቀበል አፈ ጉባዔ ታገሠ ጫፎ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ማስታወቃቸውን ምክር ቤቱ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል። የዕጩዎች ጥቆማ እና ምርጫ ሂደቱ በ1 ወር ከ15 ቀናት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ አፈ ጉባዔው ገልጠዋል። ለኮሚቴው አፈ ጉባዔው የሚመሩት አማካሪ ቡድን የተቋቋመለት ሲሆን፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት፣ የሐይማኖት ተቋማት እና ሲቪል ማኅበራት ተወካዮች የአማካሪ ቡድኑ አባላት እንደሆኑ ተገልጧል።

2፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግጭት ካለባቸው አካባቢዎች የመጡ ተመራቂዎች ግቢውን በታኅሳስ ወር መጨረሻ እንዲለቁ ማሳሰቡን ሪፖርተር አስነብቧል። ማሳሰቢያው የተሰጣቸው 41 ተመራቂዎች ከኦሮሚያ ክልል ከወለጋ ዞኖች፣ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን እና ከትግራይ ክልል የመጡ ናቸው። ተመራቂዎቹ የመጡባቸው አካባቢዎች የግጭት ቀጠና በመሆናቸው፣ ዩኒቨርስቲው ለተመራቂዎች የምግብ ምኝታ አገልግሎት የመስጠት ሥልጣን ሳይኖረው በጀቱን በማሸጋሸግ ብቻ እንዳቆያቸው የገለጸው ዩኒቨርሲቲው፣ አንዳንዶቹ ሥራ አግኝተውም ግቢውን ባለመልቀቃቸው እና ሌሎቹ ደሞ የመጡበትን አካባቢ በትክክል ለመግለጽ ባለመፍቀዳቸው ግቢውን እንዲለቁ ነግሬያቸዋለሁ ብሏል። አብዛኞቹ ከትግራይ ክልል የመጡ ተመራቂዎች ግን ቀደም ሲል ሥራ አግኝተው እንደወጡ ወይም ወደ ክልላቸው እንደተመለሱ ተገልጧል።

3፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ላሊበላ ከተማ እንደገና በየቀኑ በረራ መጀመሩን በድረገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። ቱሪዝም ሚንስቴር ዘንድሮ በላሊበላ ከተማ የሚከበረውን የክርስቲያኖች ገና በዓል ምክንያት በማድረግ የላሊበላን የቱሪዝም መዳረሻነት እንደገና ለማስተዋወቅ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል። አየር መንገዱ ወደ የላሊበላ በረራውን ያቋረጠው፣ የትግራዩ ሕወሃት በአካባቢው ጦርነት መክፈቱን ተከትሎ ሲሆን፣ የሕወሃት ታጣቂዎች ላሊበላ ከተማን በተቆጣጠሩባቸው ወራት በአውሮፕላን ማረፊያው ላይ ከባድ ውድመት ማድረሳቸው ይታወሳል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በሪያድ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ኮሚኒቲ ት/ቤት በገንዘብ እጥረት 3000 ህጻናትን በትኖ ሊዘጋ ነው * ወላጆች ለልጆቻቸው መበተን ዲፕሎማቱን ተጠያቂ ያደርጋሉ

4፤ በኦሮሚያ ክልል የምሥራቅ ወለጋ ዞን ለቀጠለው የጸጥታ ችግር የዞኑ አስተዳደር “አማርኛ ተናጋሪ ጽንፈኛ ኃይሎች” ሲል የገለጻቸው ታጣቂዎች፣ የቤንሻንጉል ሕዝቦች ነጻ አውጭ ንቅናቄ እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ወይም ኦነግ ሸኔ መሆናቸውን እንደገለጸ አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል። የተጠቀሱት ቡድኖች ከዞኑ በተለይም ከጊቶ ጊዳ ወረዳ ከ128 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን እንዳፈናቀሉ እና 54 ሺህ ያህሉ በኋላ ወደ ቀያቸው እንደተመለሱ የዞኑ አስተዳዳሪ አለማየሁ ተስፋዬ ለክልሉ ቴሌቪዥን መናገራቸውን ዘገባው ገልጧል። የክልሉ ጸጥታ ኃይል የተጠቀሱትን ታጣቂዎች ከዞኑ ለማጽዳት ጥረት እያደረገ ስለመሆኑ የገለጠው ዘገባው፣ “አማርኛ ተናጋሪ ጽንፈኞች” የተባሉት ታጣቂዎች ማንነት ግን በግልጽ እንዳልተብራራ ገልጧል።

5፤ የኬንያ ፖሊስ ወደ አውሮፓ ሕጻናትን እና ሴቶችን ጨምሮ በርካታ ሕገወጥ ፍልሰተኞችን ሲያዘዋውር የነበረውን ትውልደ ኤርትራዊ በቁጥጥር ስር እንዳዋለ ኢንተርፖል በድረገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። ጆን ሐብቴ የተባለው በዜግነቱ ሆላንዳዊ የሆነው ሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪ ለዓመታት በኢንተርፖል እና በሆላንድ መንግሥት ሲፈለግ የቆየ ሲሆን፣ የኬንያ ፖሊስ ከኢንተርፖል በደረሰው ጥቆማ በቁጥጥር ስር አውሎ ከሳምንት በፊት ለሆላንድ አሳልፎ ሰጥቶታል። ሐብቴ በዓለማቀፍ ደረጃ በዘረጋው የሕገወጥ ሰዎች ዝውውር መረብ አማካኝነት በትንሹ አራት ጊዜ ኤርትራዊያን ፍልሰተኞችን በሕገወጥ መንገድ በቡድን ወደ ሆላንድ አስገብቷል ተብሏል።

6፤ በአፍሪካ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የ1.2 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት በማፍሰስ ከመካከለኛው ምሥራቅ ቀዳሚ የሆነችው የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች አሁን ደሞ አፍሪካዊያን ቱጃሮች በግዛቷ ሙዓለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ መጋበዟን ዘ ኢስት አፍሪካን አስነብቧል። በኢምሬቶች ሙዓለ ንዋይ ለሚያፈሱ አፍሪካዊያን እና ሌሎች ቱጃሮች የሀገሪቱ መንግሥት እስከ 10 ዓመት የሚቆይ የቀረጥ እና የገቢ ግብር ምኅረት እንደሚያደርግ፣ የኢምግሬሽን ሕጎቹን በማላላት የ10 ዓመት ቪዛ እንደሚሰጥ እና የውጭ ባለሃብቶች በሀገሪቱ ሙሉ የኩባንያ ባለቤት እንዲሆኑ እንደሚፈቅድ አስታውቋል። ኢምሬቶች ከአፍሪካ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ጥሪ ያደረገችው፣ በመጋቢት ወር የምታካሂደውን ዓመታዊ ዓለማቀፍ የኢንቨስትመንት ጉባዔ አስመልክታ ባወጣችው ሰነድ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አትሰቀል ይቅር! (አሥራደው ከፈረንሳይ)

7፤ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክ ሥልጣናቸውን በፍቃዳቸው እንደለቀቁ በሀገሪቱ ቴሌቪዥን አስታውቀዋል። ሐምዶክ ሱዳን አደገኛ መስቀለኛ መንገድ ላይ ናት በማለት በመሰናበቻ ንግግራቸው አስጠንቅቀዋል። የሱዳን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጀኔራል አል ቡርሃን የቀድሞውን ገንዘብ ሚንስትር ኢብራሂም ኤል-ባዳዊን ጠቅላይ ሚንስትር አድርገው ሊሾሙ እንደሆነ ተሰምቷል። ሐምዶክ ከሥልጣን የለቀቁት፣ ከጦር ሠራዊቱ መሪዎች ጋር በደረሱበት አዲስ የሽግግር ስምምነት መሠረት የሲቪሎች የሽግግር ካቢኔ ማቋቋም አለመቻላቸውን እና ሱዳናዊያንም በአዲሱ የሽግግር ስምምነት እና በጦር ሠራዊቱ ሚና ላይ ተቃውሟቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን ተከትሎ ነው። [ዋዜማ ራዲዮ]

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share