ለቸኮለ! ሰኞ ኅዳር 20/2014 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራዩ ጦርነት የተፈጸሙ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማጣራት እና ተጠያቂነትን ለማስፈን ያቋቋመው የሚንስትሮች ግብረ ኃይል ዛሬ በይፋ ሥራውን መጀመሩን ፍትህ ሚንስቴር በትዊተር ገጹ ባሰራጨው መግለጫ አስታውቋል። ግብረ ኃይሉ በጦርነቱ በተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር በጋራ አጥንተው ያቀረቧቸውን ምክረ ሃሳቦች ለመተግበር የሚያስችለውን ስትራቴጂ እና የድርጊት መርሃ ግብር ዛሬ አጽድቋል። ግብረ ኃይሉ ምርመራና ክስን፣ ስደተኞችንና ተፈናቃዮችን፣ የጾታ ጥቃቶችን እና ሃብት ማፈላለግን የሚመለከቱ 4 ኮሚቴዎች ያዋቀረ ሲሆን፣ ሥራውን የሚከታተል ማዕከላዊ ጽሕፈት ቤትም ያቋቁማል ተብሏል። የግብረ ኃይሉ ሥራ በአማራ እና አፋር ክልል የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንም ያካትታል።

2. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማዕከላዊ ዕዝ ዛሬ ባወጣው የተሻሻለ መመሪያ ባንዳንድ አካባቢዎች የተጣለው የሰዓት እላፊ ገደብ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲነሳላቸው መወሰኑን በመንግሥት ዜና አውታሮች በኩል ማምሻውን አስታውቋል። ማዕከላዊ ዕዙ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የሰዓት እላፊ ገደቡን ያነሳው፣ ገደቡ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና ስለሚያሳድር እና ኢንዱስትሪዎችን ለኪሳራ ስለሚዳርግ እንደሆነ ገልጧል። በተሻሻለው መመሪያ መሠረት፣ ከዛሬ ጀምሮ እያንዳንዱ አምራች ኢንዱስትሪ የራሱን የጥበቃ ሥርዓት አዘጋጅቶ ያለ ገደብ መደበኛ ሥራውን እንዲቀጥል ተፈቅዷል።

3፤ ብሄራዊ ባንክ ንግድ ባንኮች ቋሚ ንብረቶችን በመያዥነት ይዘው ብድር እንዳይሰጡ ከ4 ወራት በፊት የጣለውን የብድር እገዳ ሙሉ በሙሉ እንዳነሳ ለንግድ ባንኮች በጻፈው ደብዳቤ ማስታወቁን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል። ባንኩ የብድር ክልከላ መመሪያ ያወጣው በሀገሪቱ የሚፈጸሙ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አሻጥሮችን ለመከላከል በሚል ነበር። ባንኩ የብድር እገዳውን በባንኮች ላይ ከጣለ በኋላ ግን፣ በተለያዩ ጊዜያት ላንዳንድ የኢኮኖሚ ዘርፎች ብድር እንዲፈቀድላቸው መመሪያውን ማሻሻሉ ይታወሳል።

4፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የአፋር ክልል ልዩ ኃይሎች በአፋር ክልል የምትገኘውን ስትራቴጂካዊቷን ጭፍራ ከተማን ከአማጺው ሕወሃት ታጣቂዎች ነጻ እንዳወጡ የአልጀዚራው የኢትዮጵያ ዘጋቢ ሞሐመድ ጠሃ ተወከል ከሥፍራው ዘግቧል። በጦርነቱ የከተማዋ ሱቆች እና መስጊዶች እንደወደሙ እና ነዋሪዎች በሙሉ ከተማዋ ለቀው እንደወጡ ዘገባው ገልጧል። መከላከያ ሠራዊት እና የአፋር ተዋጊ ኃይሎች ጭፍራን ከተቆጣጠሩ በኋላ፣ በአማራ ክልል ወደሚገኙት ባቲ እና ኮምቦልቻ ከተሞች እየገሰገሱ መሆኑን ዘገባው ገልጧል። የመንግሥት ዜና አውታሮች ትናንት የመከላከያ ሠራዊት አባላት በከተማዋ የሀገሪቱን እና የክልሉን ባንዲራ ሲሰቅሉ በምስል አሳይተዋል።

5፤ ሱዳን የኢትዮጵያ ጸጥታ ኃይሎች በፈጸሙብኝ ጥቃት በርካታ ወታደሮቼ ተገድለውብኛል በማለት ያሰማችውን ስሞታ የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ ሐሰት ነው ሲል አስተባብሏል። ሱዳን አምና በኃይል በያዘችው አልፋሽጋ በተባለው አወዛጋቢ አካባቢ የኢትዮጵያ ታጣቂ ኃይሎች እና ሚሊሻዎች 6 የሱዳን ወታደሮችን እንደገደሉ ባለፈው ቅዳሜ የሱዳን ዜና ምንጮች የሀገሪቱን ጦር ኃይል ጠቅሰው ዘግበው ነበር። ሆኖም የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ከሱዳን የሚነሱ የሕወሃት ሰርጎ ገብ ታጣቂዎችን ጥቃት ሲቀለብስ እንደቆየ ረዳት ቃል አቀባይ ሰላማዊት ካሳ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

6፤ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሳቢያ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ እንደሆኑ ትምህርት ሚንስቴር በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። ከ1ኛ ደረጃ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ያስተምሩ የነበሩ ከ1 ሺህ 600 በላይ ትምህርት ቤቶችም በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 300ዎቹ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ እንደወደሙ ሚንስትር ደዔታ ሳሙዔል ክፍሌ ተናግረዋል። ጦርነቱ ባጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ መደበኛ የትምህርት መርሃ ግብር ሊጀመር እንደሚገባው የጠቆሙት ሳሙዔል፣ መስሪያ ቤታቸው የተጎዱ ትምህርት ቤቶችን ወደቀድሞ ይዞታቸው ለመመለስ ጥረት እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል።

7፤ የፈረንሳይ መንግሥት ከትናንት ሌሊት ጀምሮ በኢትዮጵያ የሚገኙ ፈረንሳዊያን ዜጎችን ከአዲሳባ የማስወጣት እንቅስቃሴ እንደጀመረ ሮይተርስ ዘግቧል። የሀገሪቱ መንግሥት ዜጎቹን ከኢትዮጵያ የሚያስወጣው በራሱ ወጭ ባዘጋጀላቸው የልዩ አውሮፕላን በረራ እንደሆነ ዘገባው ገልጧል። ፈረንሳይ በኢትዮጵያ የጸጥታ ሁኔታው እያሽቆለቆለ ሂዷል በማለት ዜጎቿ በራሳቸው አማራጭ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ባለፈው ሳምንት አሳስባ ነበር።

8፤ ቻይና ለታዳጊ ሀገሮች የሰጠችውን የቀረጥ ነጻ እድል እንደምታሰፋ በቻይና ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር ው ፔንግ በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል። ቻይና የቀረጥ ነጻ እድል ተጠቃሚ የምትፈቅድላቸውን የታዳጊ ሀገራት ምርቶች ብዛት ለመጨመር ያሰበችው፣ በቀጣዮቹ 3 ዓመታት ከታዳጊ ሀገራት ወደ ቻይና የሚገቡ ሸቀጦች ዋጋ በቀጣዮቹ 3 ዓመታት ወደ 300 ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ በያዘችው ዕቅድ መሠረት ነው።

9፤ የዓለም ጤና ድርጅት ኦሚኮርንየተባለው አዲሱ ልውጥ የኮሮና ቫይረስ በዓለም ላይ በፍጥነት የመሰራጨት አቅም አለው ሲል ዛሬ ማስጠንቀቁን ዓለማቀፍ ዜና ወኪሎች ዘግበዋል። ባለፈው ሳምንት በደቡብ አፍሪካ የተገኘው ልውጡ ተዋሲ ከባድ የጤና ስጋት ሊፈጥር እንደሚችል የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኻኖም ያስጠነቀቁ ሲሆን፣ በርካታ ሀገራትም ድንበራቸውን እንደገና መዝጋት ጀምረዋል። አሁን ያሉት ክትባቶች ልውጡን ተዋሲ ይቋቋሙት እንደሆነ ገና እንዳልተረጋገጠ የገለጹት ቴዎድሮስ፣ ሆኖም ሀገራት ለበሽታው ከፍተኛ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን በቶሎ እንዲከትቡና የጤና ተቋሞቻቸውን እንዲያጠናክሩ መክረዋል። ዶ/ር ቴዎድሮስ ይህን የተናገሩት፣ ለወደፊት ወረርሽኞችን ለመከላከል የሚያስችል አሳሪ ዓለማቀፍ ስምምነት ለማርቀቅ በተጠራ የአባል ሀገራት ጤና ሚንስትሮች ጉባዔ ላይ ነው።[ዋዜማ ራዲዮ]

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.