በምዕራብ ጎንደር ዞን የአማራና ቅማንት ወንድም ሕዝቦች መልካም ግንኙነታቸውን ለማስቀጠል መከሩ

kimanet

ገንዳውኃ፡ ጥቅምት 15/2014 .(አሚኮ) በጠገዴ አርማጭሆና አካባቢው በጎ አድራጎት ማኅበር አዘጋጅነት በምዕራብ ጎንደር ዞን የአማራና ቅማንት ሕዝቦች የአካባቢውን ሰላምና ደኅንነት በጋራ ለመጠበቅና መልካም ግንኙነታቸውን በዘላቂነት ለማስቀጠል የሕዝብ ለሕዝብ ምክክር አካሂደዋል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን የተለያዩ አካባቢዎች በግል ጥቅመኞች የሰው እገታ፣ የሀብት ዘረፋ፣ የሰው ግድያ፣ የመንገድ መዘጋት፣ የጥይት ተኩስ እና መሰል የኅብረተሰቡን ሰላምና እረፍት የሚነሱ ወንጀሎች እየተበራከቱ መጥተዋል። በዚህም የኅብረተሰቡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዲላላ ከማድረግ ባሻገር ሥነ ልቦናዊ ጫና እያደረሰም ነው፡፡

የአማራና የቅማንት ወንድም ሕዝቦች ባካሄዱት ምክክር በአካባቢው እየተፈጸሙ ያሉ ኢሰባዊና አስነዋሪ ድርጊቶች ምንጫቸውን በዘላቂነት ለማድረቅ ሁለቱ ወንድም ሕዝቦች በጋራ መሥራት እንዳለባቸው አመላክተዋል፡፡ የአማራና የቅማንት ወንድም ሕዝቦች ወራሪውን የትህነግ ቡድን በመደምሰስ፣ ጽንፈኛውን ኮሚቴና ግብረ አበሮቹን በመዋጋት፣ ሌባና አጋቾችን በማውገዝ የአካባቢያቸውን ሰላም እንደሚያስጠብቁ እና ግንኙነታቸውን እንደሚያጠናክሩ ነው ያስረዱት።

በመድረኩ በአካባቢው በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት ልማታዊ እንቅስቃሴዎች ቁመዋል ያሉት የአካባቢው ባለሀብት አቶ ተመስገን ሰጣርገው ችግሩን ለመፍታት ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ከጠገዴ እና ከአርማጭሆ ኅብረተሰብ ተሞክሮ መውሰድ አስፈላጊ እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡

የሕዝብ ለሕዝብ ምክክሩ ዋና ዓላማ ችግር ፈጣሪውን በመለየት ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሔ በማስቀመጥ የአካባቢውን ሰላም እና ደኅንነት በዘለቄታ ማስጠበቅ ነው ያሉት ደግሞ የጠገዴ አርማጭሆና አካባቢው የበጎ አድራጎት ማኅበር አስተባባሪ አቶ አሰማረው መኮንን ናቸው።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህር እና የጠገዴ አርማጭሆና አካባቢው የበጎ አድራጎት ማኅበር አባል ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ጽሐዬ አብሮነት ለሰላምና ለዘላቂ እድገትበሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ በኢትዮጵያ ስለተፈጠረው አሁናዊ ችግር መነሻው ምዕራባዊያን እንደሆኑ አስገንዝበዋል፡፡ ረዳት ፕሮፌሰሩ የምዕራባዊያንን አጀንዳ ተሸክመው ለሚመጡ ባንዳዎች ፈጣንና ተገቢውን ግብረ መልስ መስጠት ጊዜው የሚጠይቅ ሆኗል ብለዋል። በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚፈጸመው ኢሰብዓዊ ድርጊት ዓላማው የትኛውንም ብሔር ነጻ ለማውጣት ሳይሆን ኢትዮጵያዊያንን እርስ በእርስ በማባላትና በማናከስ ለምዕራባዊያን ዕድል መፍጠር እንደሆነ አብራርተዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  “ፋኖ ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይልን እያርበደበደ ነው” የፋኖ ብርጌድ ምክትል አዛዥ ሻለቃ አራጋው እንዳለ

በምክክሩ የዞኑ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የወረዳ የሥራ ኀላፊዎች፣ ከሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ከላይ አርማጭሆ ወረዳ የተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ የጦር ጀነራሎች፣ መኮነኖች እና ባለሀብቶች ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ፡ቴዎድሮስ ደሴከገንዳውኃ

አሚኮ

1 Comment

  1. የማይተማመን ባልንጀራ በየወንዙ ይማማላል ይላሉ አበው። አሁን ማን ይሙት አማራና ቅማንት የሚያለያያቸው ነገር አለ? ግን የወያኔን የክፋት ጽዋ የተጎነጨ ሁሉ ራሱን በሰውነት ደረጃ ማየት ረስቱ በዘሩ፤ በቋንቋውና በሃይማኖቱ መሰለፉ የሴራው ፓለቲካ ምን ያህል በሃበሻው ምድር ሰርጾ እንደገባ ያሳያል። የደነቆሮ ጩኸት መልሶ መላልሶ እንዲሉ ከተግባር ይልቅ ሁልጊዜ ስብሰባ ማድረግ የተለመደ ባህል ሆኗል። ማን ነው በአይከል (ጭልጋ) ቤት የሚያቃጥለው፤ ሃገር የሚያተራምሰው፤ ለወያኔ አዳሪ ሆኖ ከውጭ ሃይሎች ጋር በማበር የመንግስት መ/ቤቶች እንዲዘጉና የሰው የእለት እለት ኑሮ እንዲቋረጥ ያደረገው? እነማን ናቸው የተከመረ እህል አቃጥለው ተራብን የሚሉት? የእብድ ፓለቲከኞች አይደሉም እንዴ?
    ዛሬ ወያኔ ከአማራ ህዝብ ጋር የማወራርደው ሂሳብ አለኝ በማለት ሰነድ ይዞ እያተራመሰ ባለበት በዚህ ወቅት ከወያኔ ጋር ተሰልፎ አብሮ ወገኑን የሚገድለው የቅማንት፤ የአማራና የአገው ሰው አይደለም? ግን ወያኔ ለራሱ እኩይ ተግባር ተጠቅሞ መልሶ እነርሱን አፈር እንደሚያለብሳቸው እንዴት ሰው መረዳት ይሳነዋል? አሁን በወሎና በአፋር ወያኔ የሚያደርገው የግፍ ሥራ ከወያኔ ጋር ሰው የሆነ ይሰለፋል? አንድ ገበሬ ጓደኞቹ ከፊቱ ላይ በጥይት ተደብድበው የሞቱበት የወሎ ገበሬ ፈጣሪ የአሁኑ እንኳን አተረፈኝ እንጂ እንደ አመት በዓለ ፍየል ተይዤ ከምታረድ እየተዋጋሁ እሞታለሁ በማለት ነበር ቁርጠኝነቱን የገለጠው። የወሊድ የምጥ ጭኾት ለመካን ሴት አይገባትም አይነት ነው ነገሩ።
    ባጭሩ የኢትዮጵያ ፓለቲካ ሰፈርና ጎጥን ተገን ያረገ ጠባብነት የተጠናወተው፤ እልፍ ተናግሮ አንድ መተግበር የማይችል ሰው የሚንጋጋበት ነው። ነገርን መዝኖ፤ ከመናገር በፊት ጉልበትንና አቅምን ሰፍሮ መናገር መልካም ሆኖ እያለ በየሜዳው እያቅራሩ የጠላትን ሃይልና አሰላለፍ ለይተው ሳያውቁ ወያኔ አንድ የማይሰራ ክላሽን ጥሎ ያኑ ለማንሳት ሲሻሙ በጥይት የጨረሳቸው ስንቶች ናቸው? ሽባ አስተሳሰብ ይዘው ጠ/ሚሩን የስንዴ ማሳ ጎበኘ፤ የስቴዲዪም ሥራን አየ፤ በምርጫው ማግስት ድግስ ደገሰ፤ ወታደራዊ መሪዎቹ አዲስ አበባ ተቀምጠው ሰው አለቀ የሚሉ የሾተል ፓለቲከኞች እንደ አሸን የፈሩበት ሃገር ነው። ጠ/ሚሩንም ሆነ ጄኔራሎችን የሚያስወቅስ አንድም ነገር የለም። ጦርነት እየተካሄደ ልማት አይልማ የሚል ሰው እብድ እንጂ ጤነኛ አይደለም። ግን የወሬ ምንዛሬው ከፍ ስላለ ሰው ሰውን እያጥላላና የውሸት ጡሩንባ እየነፋ ገቢ ሰብሳቢ ሆኗል። እንደዛሬው ሰው በዘሩና በቋንቋው በክልሉ ሳይሰለፍ አንዴ ከእነማን ጎን ተሰልፈሃል ቢለኝ ካድሬው ከማንም ስለው መሃል ሰፋሪ ነህ ማለት ነው ይለኛል። አዎን የሚመቸኝ መንገድ እሱ ነው በማለት ትንሽ ተከራክረን ተለያየንና ይህን ግጥም ቀምሬ በቁራጭ ወረቀት ላይ ጽፌ ሰጠሁት በሌላ ቀን ሰጠሁት። ካነበበው በህዋላ ከት ብሎ ስቆ። ትገርማለህ በማለት ያለስንብት ትቶኝ ሄደ። ያ ሰው አሁንም በህይወት አለ። ግጥሙ እንሆ።
    ምንንም ደግፌ ለማንም አልቆምም
    ይህ ይሻላል ብዬ ሌላውን አልጠላም
    እኔ የምመርጠው የሚመቸኝ መንገድ
    በማህል መሄድ ነው ማንም ባልቆመበት።

    መቼ ይሆን የሃበሻው ፓለቲካ ያዘው ጥለፈው የሚለውን የተንኮል ገመድ ጠቅሎ ሰውን በሰውነቱ መዝኖ አህጉራዊና አለም አቀፋዊ እይታው ሰፍቶ የሚኖረው? ጠብቀን እንይ። በቃኝ!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share