በአሸባሪው የትህነግ ቡድን የወደሙ የትምህርት ግብዓቶችን በማሟላት የመማር ማስተማር ሂደቱን ማስጀመሩን የሁመራ ከተማ ትምህርት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ

ሁመራ: መስከረም 28 /2014 (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በአስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በአሸባሪው የትህነግ ቡድን የወደሙ የትምህርት ግብዓቶችን በማሟላት ከመስከረም 24 ጀምሮ የመማር ማስተማር ተግባሩን ማስጀመሩን የሁመራ ከተማ ትምህርት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

humera, amhara, ethiopia
Humera, Amhara, Ethiopia
አሸባሪው የትህነግ ቡድን ሀገርን ለማፈራረስ በከፈተው ጦርነት መንግሥት በወሰደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ አካባቢውን ጥሎ ሲወጣ በሁመራ ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን እና የትምህርት መስጫ ግብዓቶችን ሙሉ በሙሉ አውድሟል።
ከሕግ ማስከበር ዘመቻው ማግስት የአካባቢው ኅብረተሰብ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ባደረጉት ጥረት ተማሪዎች ትምህርት እንዲጀምሩ ማድረግ ተችሏል።
የሁመራ ከተማ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ታሪኩ ዘውዱ በአሸባሪው ትህነግ ጦርነት በትምህርት ቤቱ ውስጥ የሚገኙ ኮምፒውተሮች፣ ፕላዝማዎች፣ ፕሪንተሮች፣ መጽሐፍቶች እና የተለያዩ የትምህርት ማስረጃዎች እንደወደሙ ገልጸዋል።
ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ጋር በመነጋገር የወደሙ የትምህርት ግብዓቶችን እና አጋዥ መጽሐፍቶችን በማሟላት የ2014 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሥራው መጀመሩን አቶ ታሪኩ ተናግረዋል።
በሁመራ ከተማ አራት አንደኛ ደረጃ እና አንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዳለ የገለጹት ኀላፊው በአራቱ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን በመመዝገብ የትምህርት ሂደቱን ሙሉ ለሙሉ ማስጀመራቸውን አብራርተዋል።
ተማሪዎች በቋንቋቸው ተምረው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ እንደሆነም ለአሚኮ አስረድተዋል።
ዘጋቢ፡-ያየህ ፈንቴ-ከሁመራ
ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢትዮጵያን አየር መንገድ ካለበት መጠነ ሰፊ ችግሮች መሃካል ዳያስፖራዎችን መቀበል እንዳቃተው ተሰማ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share