በአዲስ አበባ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ መጨመርና ተከራይን ከቤት ማስወጣት ተከለከለ

addis ababa zehabesha
addis ababa zehabesha

የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ መጨመርም ሆነ ተከራይን ከቤት ማስወጣት ቢያንስ ለቀጣይ 90 ቀናት የተከለከለ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

ለነዋሪው ቅሬታ ምላሽ በመስጠት አሁን እየታየ ያለውን አላግባብ የሆነ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ጭማሪ ለመገደብ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ከትናንት በስቲያ ባደረገው መደበኛ ስብሰባው የቤት ኪራይ ጭማሪን ለ90 ቀናት ለማገድ በቀረበ ደንብ ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል፡፡

በዚሁ መሠረት ደንቡ ከፀደቀበት ነሐሴ 18 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ መጨመርም ሆነ ተከራይን ከቤት ማስወጣት ለ90 ቀናት የተከለከለ ሲሆን በቀጣይም ታይቶ ክልከላው ለተጨማሪ ቀናት ሊራዘም እንደሚችል ተገልጿል፡፡

ደንቡን በመተላለፍ ጭማሪ የተደረገበት ተከራይ አቤቱታውን በፅሑፍ ለወረዳው ሥራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት በማቅረብ መፍትሄ ማግኘት የሚችልበት ሥርዓት በደንቡ መደንገጉም ተመልክቷል፡፡

በዚህ መሰረት በሚቀርቡ አቤቱታዎች ላይ ማጣራት ተደርጎ ጭማሪ ያደረገ አካል በደንቡ ተዘርዝሮ በተቀመጠው መሰረት ተጠያቂ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡

ይህንኑ አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዛሬው ዕለት መግለጫ አውጥቷል፤ የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

የመኖሪያ ቤት ኪራይ ጭማሪን ለመገደብ በወጣ ደንብ ላይ የተሰጠ መግለጫ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማችን የኑሮ ውድነት እየተባባሰ እንደመጣ የሚታወቅ ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱ በአብዛኛው አሳማኝ እና ምንም አይነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌለው በሰውሰራሽ ምክንያቶች የተፈጠረ ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱም የከተማችንን ነዋሪ ለከፍተኛ ችግር ዳርጓል፡፡

በሰሜን የሃገራችን ክፍል ሃገር በማፍረስ ተግባር ላይ የሚገኘውን የአሸባሪው ህወሃት እንቅስቃሴ ለማክሸፍ እየተደረገ ካለው ዘመቻ ጋር ተያይዞ የከተማችን ነዋሪ በገንዘብ መዋጮ፤ ለሠራዊት የሚሆን ስንቅ በማዘጋጀት፤ ከደም ልገሳ እስከ ህይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ባለበት በዚህ ወቅት ጥቂት ስግብግብ ግለሰቦች በተቃራኒው ቆመው ከኢትዮጵያዊነት ጨዋነት ፍፁም ባፈነገጠ መልኩ አሁን ካለው ችግር ላይ አላግባብ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ የተለያዩ ተግባራት ውስጥ ገብተው ይገኛሉ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  አብርሃም አለኸኝ ጥሩነህ/ህወሃትን እንደዚህ ተረዳ

መንግሥት እያጋጠመ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ከውጭና ከውስጥ ያሉ ጫናዎችን ተቋቁሞ ሀገር የማፍረስ ተግባር እንዲከሽፍና የዜጎች የኑሮ ጫና እንዲቀንስ የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል፡፡

በዚህም መሠረት እስከታችኛው የማኅበረሰብ ክፍልን የሚያሳትፍ የኢኮኖሚ አሻጥሩን ለመቀልበስ የተቋቋመው ግብረይል በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡

በአጭር ጊዜ ውስጥም ግብረሃይሉ ባካናወናቸው ተግባራት ተጨባጭ ለውጦች በመታየት ላይ ይገኛል፡፡

ከመሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ባሻገር አላግባብና የወቅቱን ሁኔታ ያላገናዘበ የቤት ኪራይ ጭማሪ የነዋሪውን ሕይወት በእጅጉ እየፈተነው ይገኛል፡፡

ይህም ወቅታዊ ሁኔታን በመጠቀም አላግብ ለመክበር የሚደረግ ከኢትዮጵያዊ ጨዋነትና መተሳሰብ ጋር በፍፁም የሚቃረን ተግባር ነው፡፡

በ2012 ዓ.ም የኮቪድ 19 ወረርሽ በሀገራችን መገኘቱ ተከትሎ በርካቶች ችግር ውስጥ በገቡበት ወቅት የከተማችን ነዋሪዎች እርስ በእርስ ከመረዳዳትና ማዕድ ከመጋራት አልፎ በርካታ ቤት አከራዮች የወራት የቤት ኪራይ ዋጋ ለተከራይ በራሳቸው ተነሳሽነት ቀንሰው ችግሩን በጋራ ለመፍታት ኢትዮጵያዊ የመረዳዳት እሴታችን የታየበት እንደነበር ይታወሳል፡፡

ይህም በወቅቱ በሕግ ተቀምጦ የነበረውን የቤት ኪራይ ዋጋ መጨመር የሚከለክለውን ድንጋጌ ሳይጨምር ነው፡፡

አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት በቤት ክራይ ላይ ዋጋ ጭማሪ መታየቱን ነዋሪዎች ቅሬታቸውን እያሰሙ ነው፡፡

ስለሆነም አሁን እየታየ ያለውን አላግባብ የሆነ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ጭማሪ ለመገደብ የነዋሪውን ቅሬታ ምላሽ ለመስጠት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በቀን 18/12/13 ባደረገው መደበኛ ስብሰባው የቤት ኪራይ ጭማሪን ለ90 ቀናት ለማገድ በቀረበ ደንብ ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል፡፡

በዚህም መሠረት ደንቡ ከፀደቀበት 18/12/13 ዓ.ም ጀምሮ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ መጨመርም ሆነ ተከራይን ከቤት ማስወጣት ለ90 ቀናት የተከለከለ ሲሆን በቀጣይም ታይቶ ለተጨማሪ ቀናት ክልከላው ሊራዘም ይችላል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በመተከል ዞን ለውክልና ጦርነት የተሰለፉ ፀረ-ሰላም ሃይሎች ላይ የተጠናከረ እርምጃ ይወሰዳል

ደንቡን በመተላለፍ ጭማሪ የተደረገበት ተከራይ አቤቱታውን በፅሑፍ ለወረዳው ሥራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት በማቅረብ መፍትሄ እንዲያገኝ የሚቻልበት ሥርዓት በደንቡ ተደንግጓል፡፡

በዚሀ መሰረት በሚቀርቡ አቤቱታዎች ላይ ማጣራት ተደርጎ ጭማሪ ባደረገ አካል ላይ በደንቡ ተዘርዝሮ በተቀመጠው መሰረት ተጠያቂ የሚደረግ ይሆናል፡፡

ምንም እንኳን ይህ ደንብ የወጣው ዜጎችን ካላስፈላጊ ጫና ለመከላከልና ጥፋተኞችን ተጠያቂ ለማድረግ ቢሆንም ህብረተሰባችን በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ችግሮችን በመተሳሰብና በመደጋገፍ ለማለፍ ያሳየውን ኢትዮጵያዊ የጨዋነትና አብሮነት እሴቶቹን በማዳበር ይህን ወሳኝና አስቸጋሪ ጊዜ በጋራ ማለፍን ማዕከል በማድረግ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ የከተማ አስተዳደሩ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

ነሐሴ 22 ቀን 2013

አዲስ አበባ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share